Monday, 07 November 2011 13:30

ትህትና ወይም ክርስቶሳዊ ጅራፍ “ትዕቢተኛ ሆኖ ፊልም ሰሪ መሆን አይቻልም” ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ

Written by  ተስፋ አሰፋ (ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ) tedla.tesfaassefa@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

ቀኑንና ዕለቱን በትክክል ባላስታውስም 2001 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ፤ ስፍራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ነው፡፡ አላቲኖስ የፊልም ሰሪዎች ማህበር አንድ ዝግጅት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የዕለቱ ዝግጅት መታሰቢያነቱ ለታዋቂው የፊልም ባለሙያ ሚሼል ፓፓቲከስ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ የቀድሞው የባህል ቱሪዝም ሚኒስትር ክቡር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር ሲሆኑ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት ደግሞ ኢትዮጵያዊው ፊልም ሰሪና መምህር ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ናቸው፡፡ መድረኩን ይመራ የነበረው ወጣት የዕለቱን ፕሮግራም አስተዋውቆ ዝግጅቱ በይፋ ተጀመረ፡፡ በፕሮግራሙ መሰረት በቅድሚያ የቀረበው ለሲኒማ ዕድገት መደበኛ የሆነ ትምህርት ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም በሚል የተለያየ አቋም ያላቸው ግለሰቦችን አስተያየት በሚያሳይ አጭር ዶክመንተሪ ፊልም ነበር፡፡

ዶክመንተሪ ፊልሙ እንዳበቃ የመድረክ መሪው፤ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማን በተያዘላቸው ፕሮግራም መሰረት ለታዳሚው ንግግር ያደርጉ ዘንድ ወደ መድረክ ጋበዘ፡፡ አዳራሹን የሞላው ታዳሚ በከፍተኛ ሞራልና ጭብጨባ ተቀበላቸው፡ፕሮፌሰሩ ዋናው መድረክ ላይ አልወጡም፡ ከመድረኩ በታች ከታዳሚ ፊት ለፊት ካለው ክፍት ስፍራ ላይ ነው የቆሙት፡፡ ታዳሚው ንግግራቸውን ለመስማት በጉጉት እየጠበቀ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ሰዎችም ነበሩ፡፡ የሚያደርጉትን ንግግር ሊቀርፁ ካሜራ ከፊት ለፊታቸው ተደቅኗል፡ንግግራቸው በሙሉ በአባታዊ ወቀሳና ተግሳጽ የተሞላ ነበር ማለት ይቻላል፡በተመለከቱት ነገር አለመደሰታቸውን ያለምንም ይሉኝታ ነበር ሳይደብቁ አፍረጥርጠው የገለፁት፡፡ ከንግግራቸው ሁሉ ግን ያስደመመኝንና ሁልጊዜም ከአእምሮዬ የማይጠፋውን ልጥቀስ፡፡ 
“ትዕቢተኛ ሆኖ አገር መምራት ይቻላል፤ ትዕቢተኛ ሆኖ ፊልም ሰሪ መሆን ግን አይቻልም” ነበር ያሉት እኔ እንደማስታውሰው፡እንደተረዳሁት እሳቸው “ፊልም ሰሪ” ይበሉ እንጂ ንግግሩ በአጠቃላይ የኪነጥበብ ሰዎችን ሁሉ የሚመለከት ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ዛሬ ይህንን እንዳስታውስ ግድ ያለኝ ከዚሁ ከሲኒማ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አቶ በፍቃዱ ዓባይ ባለፈው ሳምንት በዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የተመለከቷቸው ትዝብቶች ናቸው፡፡ አቶ በፍቃዱ መፍትሔ ይሁናሉ ያሏቸውን ሃሳቦችም ሰንዝረዋል፡፡ እኔ ደግሞ ከእሳቸው ልቀጥልና የተሰማኝን ልበል፡፡
ለኢትዮጵያ ሲኒማ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለኪነጥበቡ ዕድገት ሁለት መፍትሔዎች ይታዩኛል፡፡ ትህትና ወይም ክርስቶሳዊ ጅራፍ፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት ተረድተው “ትዕቢተኛ ሆኖ አገር መምራት ይቻላል፤ ትዕቢተኛ ሆኖ ፊልም ሰሪ መሆን ግን አይቻልም” ያሉት የኃይሌ ገሪማ ንግግር ሀቅ መሆኑን ለመረዳትና ምሳሌ ለመጥቀስ ብዙ መቸገር አያስፈልግም፡፡ ትዕቢተኛ ሆነው አገር የመሩ ብዙ የዓለማችንን አምባገነኖች አይተናል፤ ዛሬም እያየን ነውና፡፡ የእኛ አገር “ፊልም ሰሪዎች” ይህንን ንግግር ሲሰሙ ምን ይሉ ይሆን? ራሳቸውን ይጠይቁ፡፡ እንደ እኔ አመለካከት ግን ይህ ንግግር አብዛኞቹን የሚያስደነግጣቸውና ቆም ብለው ራሳቸውን እንዲጠይቁ የሚያደርጋቸው ይመስለኛል፡፡
አሁን ባለንበት ዘመን አንድ ኪነጥበባዊ ስራ ወደ ህዝቡ ደርሶ የሚያመጣው መንፈሳዊና አእምሮአዊ ትርፍ ሳይሆን እንደማንኛውም ሸቀጥ (ቅቤ፣ ማር፣ በርበሬ፣ ቅመማቅመም… ወዘተ) ተቸርችሮ የሚያስገኘው የገንዘብ ትርፍ ብቻ ነው ዋነኛ ግብ እየሆነ የመጣው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት የገበያ ግርግር ውስጥ ደግሞ ባለሙያ ነኝ ከሚለው ግለሰብ ትህትናን መጠበቅ ከባድ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ላይ የቆመ ኪነጥበባዊ ስራም ዓላማው ትውልድን ማወናበድ፣ ማጭበርበር ብሎም በድንዛዜ ሸብቦ ማስቀመጥ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን ጐልቶ እየወጣ ያለና የኪነጥበቡን መድረክ (ሲኒማን ጨምሮ) የተቆጣጠረ ከበርቴ ቡድን የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡ መድረኩን በሞኖፖል ይዞ በጥበብ ስም ሲሸቅጥና ሲያቅራራም ይታያል፡፡
ክርስቶስ፤ ትህትናን ሊያስተምር ወዶ ነበር እታች ወርዶ የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበው፡ተግባራዊ ትምህርት ይሏል ይሄ ነው፡፡ ይኸው የትህትና መምህር የሆነው ክርስቶስ ትህትና የማይገባቸውን የቤተመቅደስ ውስጥ ሸቃጮች ለመግራት ደግሞ በሌላ ቦታ ላይ ጅራፍ አንስቶ ሸቀጦቻቸውን እስከመገለባበጥ ደርሶ እንደነበርም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (ዮሐ 2፥13-17)፡ ለምን ቢሉ መቅደሱን መነገጃ ሲያደርጉት በመመልከቱ፡ትህትናን መማር የመጀመሪያው ተመራጭ መፍትሔ ነው፡፡ ሙያን አክብሮ ዘመን ተሻጋሪ ስራ ለመስራት ከትዕቢት መንጻት የግድ ነውና፡፡ ይህ ለማይገባው አወናባጅ ግን ክርስቶሳዊ ጅራፍ የሚያቀምስ ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ ከዚያ ልክ ይገባና ራሱን ይገራል፤ አለበለዚያም መቅደሱን ለቆ ይሸሻል፡፡ ኪነጥበብን እንደ ቤተ መቅደስ ብንቆጥር፤ ማንም በቆሻሻ ጫማው ዘው ብሎ የሚገባበት እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡
በጥበቡ ዓለምም ከእንደዚህ ዓይነት ድፍረት ለመዳን ትህትና የግድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ትህትና ሊገባው ያልቻለውን ግን አሁንም ሊገራው የሚችለው ክርስቶሳዊ ጅራፍ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
በሌላ አጋጣሚ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ፣ በ1996 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ይመስለኛል አ.አ.ዩ. ባህል ማዕከል ለተማሪዎች ንግግር ሲያደርጉ፣ ከታደሙት ተማሪዎች አንዱ ነበርኩ፡፡ ንግግራቸውን በሙሉ አላስታውስም፡፡ ነገር ግን ከንግግራቸው ሁሉ ከትውስታዬ የማይጠፋው “የኢትዮጵያ ሲኒማ የሚወለደው ምድጃ ውስጥ ነው” ያሉትን ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የስነቃልና የባህል ባለፀጋ በሆነ አገር ተረት የሚወራው ምሽት ላይ እሳት ዳር ሰብሰብ ተብሎ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተዋጣለት ኢትዮጵያዊ ሲኒማ ካማረን ተረቶቻችንን፣ ስነቃሎቻችንንና ባህላችንን እንቆፍር ማለታቸው ነው ኃይሌ ገሪማ - እኔ እስከገባኝ ድረስ፡፡ ከእኛነታችን ውስጥ ነው የኢትዮጵያ ሲኒማ የሚወለደው፡፡ ከዚያ ውጪ ከሆነ ግን ቅዠት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ በቅዠት ደግሞ ቤት መስራትም ሆነ እንጀራ መጋገር አይቻልም፡፡ እውነተኛ ማንነትን ፍለጋ ጉዞው መጀመር አለበት፡የችግራችን መፍትሔ እዚያው ውስጥ ይገኛልና፡፡ አቶ በፍቃዱ በጥቅምት 18ቱ ጽሑፋቸው “ፊልምን አስተምረው ብቁ የሚያደርጉ ተቋማት ያለመኖራቸው አንድ ችግር መሆኑን አውቃለሁ፡እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የትምህርት ተቋማት በዚህ በኩል ብዙ ቢጠበቅባቸውም ምንም እገዛ ያለማድረጋቸው የሚያሳስብ ስለመሆኑም እስማማለሁ” በማለት ለሲኒማ ዕድገት የትምህርት አስፈላጊነትን አንስተዋል፡፡ ትዝብታቸው ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲኒማ ት/ቤት እስኪከፍት ድረስ ምን እናድርግ? የትህትና አስፈላጊነት የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡ትህትና ከሌለ እኮ ት/ቤቱ ቢከፈትም የሚማር ሰው አይኖርም፡፡ ምክንያቱም ወደ ተማሪ ቤት ለመሄድ መጀመሪያ አለማወቅን መረዳትና መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ልክ መታመሙን የተረዳ ሰው ወደ ሀኪም ዘንድ እንደሚሄደው ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው መታመሙን አምኖ ሳይቀበል የሃኪም ምክር ሊጠይቅ አይሄድም፡፡ ትህትና ያለው ሰው ግን የሲኒማ ትምህርት ቤት እስኪከፈት ድረስ እጁን አጣምሮ አይጠብቅም፤ ራሱን በራሱ ያስተምራል፤ ቢያንስ ከታናናሾቹና ከታላላቆቹ ይማራል፡፡ ሁልጊዜም አዲስ ነገር ለመማር ራሱን ዝግጁ ያደርጋል፡፡
እዚህ ላይ የኃይሌ ገሪማን “ጤዛ” ፊልም እንደምሳሌ ላንሳ፡፡ ለእኔ ይህ ፊልም ያነሳው ርዕሰ ጉዳይና ጭብጥ ሲጨመቅ ከሚለው በላይ የፊልሙ የስራ ሂደት (process) የሚናገረው ይበልጥብኛል፡፡ ለምሳሌ “ጤዛ” ፊልም ላይ የተሳተፉትን ተዋንያን ስንመለከት ዝነኞች አይደሉም፡፡
እንደውም አብዛኞቹ ማለት ይቻላል የማናውቃቸው ናቸው፡፡ የአንበርብር እናት ሆነው የተጫወቱት እታታ ታከለች (ስማቸውን በትክክል አላስታወስኩ እንደሆነ ታላቅ ይቅርታ እጠይቃለሁ) ለዚህ ዋና አብነት ይሆናሉ፡ፊልሙ በ2001 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር በተመረቀበት ዕለት ፕሬስ ኮንፍረንስም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ፕሬስ ኮንፍረንስ ላይ ኃይሌ ገሪማን ጨምሮ ፊልሙ ላይ የተሳተፉት ተዋንያን ከተመልካቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ኃይሌም ጐንደር ድረስ ሔደው እታታ ታከለችን ፊልሙ ላይ እንዲሳተፉ ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው፣ ከእኚህ እናት ያገኙት ምላሽ ስሜት የሚነካ ነበር፡፡ ምንድነው ያሉት? “አይ ልጄ እኔ ምኑን አውቄው ብለህ ነው፡፡ ተው ይቅርብኝ አበላሽብሃለሁ” ነበር ያሉት፡ ከዚህ በላይ የትህትናን ትክክለኛ ትርጉም የሚያሳይ ምሳሌ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም፡እኚህ እናት ለመማር ተዘጋጅተዋል፡፡ ትህትና ማለት ይሄ ነው፡፡ ኃይሌ መንገዱን አሳዩአቸው፤ በመጨረሻም እንደታየው ድንቅ ስራ ሰሩ፡፡
ምናልባት እዚህ ላይ ኃይሌ ገሪማ ፊልማቸው “የተዋጣለት” እንዲሆን አብዛኞቹ “ፊልም ሰሪዎች” እንደሚያደርጉት ለምን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ዝነኛ ተዋንያንን አልመለመሉም ብሎ የዋህ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ መልሱ ግን ቀላል ነው፡፡ በከንቱ ውዳሴና በዝና ሞራ ዓይናቸው ስለተጋረደ አብዛኞቹ አዲስ ነገር ለመማርም ሆነ ለመቀበል ዝግጁነቱ ስለሌላቸው ነው፡፡ ተጣሞ ያደገን ዛፍ ለማቃናት ሲታገሉ ራስንም ሌላንም ከመጉዳት፤ ራሱን ለመማር ያዘጋጀና አዲስ መንገድ ለማየትም የሚሻ እንዲሁም ትህትናን የተላበሰ (እንደ እታታ ታከለች ያለ) ባለሙያ መፈለግ ምርጫ የሌለው መሆኑን ስለተረዱ ይመስለኛል፡፡
በሌላ በኩል ኃይሌ ገሪማ “ትዕቢተኛ ሆኖ ፊልም ሰሪ መሆን አይቻልም” ያሉትን ንግግራቸውን ራሳቸው በተግባር ፈጽመውታል ብዬ አስባለሁ፡ “ተው ይቅርብኝ ልጄ አበላሽብሀለሁ” ሲሉ ትህትናን ያሳዩትን የእታታ ታከለችን ችሎታና እምቅ መመልከት ችለዋል፡፡ ከዚህ በላይ ትህትና አለ እንዴ? ደሞም ትህትና ፍሬው ምን እንደሚመስል “ጤዛ” ፊልም ያገኘውን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት መመልከት ብቻ ይበቃል፡ፊልም ሰሪ ነን የሚሉና ራሳቸውን ለመማር ያዘጋጁ ሁሉ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሲኒማ ት/ት ቤት እስኪከፍት ድረስ ኢትዮጵያዊ ሲኒማ እንደምን ያለ ነው የሚለውን ለመረዳት እንዲያስችላቸው ቢያንስ የኃይሌ ገሪማን “ጤዛ” ፊልም ይመልከቱ ስል በታላቅ ትህትና እጠቁማለሁ፡፡

 

Read 3750 times Last modified on Monday, 07 November 2011 13:32