Monday, 25 March 2013 14:56

በ40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ጥሩነሽ እና ኢማና ይጠበቃሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በፖላንዷ ከተማ ባይድጎስዝ ነገ በሚደረገው 40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ጠንካራ ቡድን በማሳተፍ ለተቃናቃኝ አገሮች ፈተና እንደምትሆን ተገለፀ፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ከ56 አገራት የተውጣጡ ከ432 በላይ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ለአዋቂ እና ለወጣት በተዘጋጁ አራት የውድድር መደቦች ይሳተፋሉ፡፡ በአዋቂ አትሌቶች ውድድሮች የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ እንደምትሆን የተጠበቀችው ኬንያ ብትሆንም ባለፉት የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ለሜዳልያ ፉክክር የበቁት ኤርትራ እና ኡጋንዳም ጠንካራ አትሌቶች ያሳትፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዓለም የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና ታሪክ ከ1980 ወዲህ በተደረጉ የአዋቂ አትሌቶች ውድድሮች በወንዶች 13 የወርቅ ሜዳልያ በመውሰድ ኬንያ ስትመራ ኢትዮጵያ 11 በማስመዝገብ ሁለተኛ ነች፡፡

በሴቶች ደግሞ 9 የወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ የምትመራ ሲሆን ኬንያ በ4 የወርቅ ሜዳልያዎች ትከተላለች፡፡ ለሻምፒዮናው አይኤኤኤፍ ለሽልማት ያዘጋጀው 280ሺ ዶላር ሲሆን በዋናዎቹ የወንዶች 12 ኪሎ ሜትር እና የሴቶች ስምንት ኪሎሜትር ውድድሮች በግልና በቡድን እስከ ስድስት በሚመዘገበው ደረጃ መሰረት ገንዘቡን ያከፋፍላል፡፡ ለግል አሸናፊዎች ለወርቅ ሜዳልያ 30ሺ ዶላር ለቡድን አሸናፊ ደግሞ 20ሺ ዶላር ተመድቧል፡፡ በ40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ቡድን ከሁለት አመት በፊት በስፔን ፑንታ ኡምቡራ የገጠመውን የውጤት መቀዛቀዝ እንደሚያሽል ተስፋ ተደርጓል፡፡

በአዋቂ ወንዶች ከተያዙት አትሌቶች ከ2 አመት በፊት በስፔን ፑንታ አምብራ በተካሄደው 39ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ12 ኪሎሜትር የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ ያስገኘው የ24 አመቱ ኢማና መርጋ እና በለንደን ኦሎምፒክ በ10ሺ የነሐስ ሜዳልያ ያገኘውና ከፍተኛ ልምድ ያለው ታሪኩ በቀለ በሜዳልያ ተቀናቃኝነት ትኩረት አግኝተዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ በአገር አቋራጭ ሩጫ ለአራት ጊዜያት የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው ጥሩነሽ ዲባባ እና ለሁለት ጊዜያት በታዳጊዎች ውድድር ያሸነፈችው ታናሽ እህቷን ገንዘቤ ዲባባ ውጤታማ እንደሚሆኑ ተዘግቧል፡፡ ኢማና መርጋ የዓለም አገር አቋራጭ የሻምፒዮናነት ክብሩን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን የገለፀው የአይኤኤኤፍ ዘገባ ጥሩነሽ ዲባባ በበኩሏ በአዋቂ ሴቶች የስምንት ኪሎሜትር ውድድር በኢትዮጵያዊ አትሌት ለመጨረሻ ጊዜ ከ5 ዓመት በፊት የተገኘውን የወርቅ ሜዳልያ ክብር ወደ ኢትዮጵያ ልትመልስ ትችላለች ብሏል፡፡

በባይድጎስዝ 40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በአዋቂ ሴቶች ህይወት አያሌው፤ ገነት ያለው ፤መሰለች መልካሙና በላይነሽ ኦልጅራ ተሳታፊ ሲሆኑ በወንዶች ደግሞ ከኢማና መርጋ ሌላ ማራቶኒስቱ እና የዘንድሮው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ አሸናፊ ፈይሳ ሌሊሳ ፤ ሞሰነት ገረመው፤ አበራ ጫኔ፤ ታሪኩ በቀለ እና መካሻው እሸቴ ተወዳዳሪ ናቸው፡፡ በወጣት አትሌት ውድድሮች ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች አዳዲስ አትሌቶችን በብዛት የምታሳትፍ ይሆናል፡፡ በወጣት ወንዶች የ8 ኪሎሜትር ውድድር የ18 አመቱ ሃጎስ ገብረህይወት የሚጠበቅ ነው፡፡ ባለፈው ወር በቦስተን አሜሪካ በቤት ውስጥ የ3ሺ ሜትር ውድድር አዲስ ሪከርድ ያስመዘገበው ሃጎስ ዘንድሮ በጃንሜዳ የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወጣቶች ውድድር አሸናፊ ነበር፡፡ ባለፈው አመት በዓለም የታዳጊዎች ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ሙክታር ኢድሪስም ለውጤታማነቱ ግምት ያገኘ ሲሆን አትሌቱ ከሁለት ወራት በፊት በጣሊያን የተደረጉ ሶስት ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን የአገር አቋራጭ ውድድሮች በማሸነፍ ጥሩ ብቃት መያዙ ተመስክሮለታል፡፡

በወጣት ሴቶች የ6 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ ኢትዮጵያ አዳዲስ አትሌቶችን እንደምታሳትፍ ተገልጿል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በስፔን ፑንታ ኡምብራ ተደርጎ በነበረው 39ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በውጤቱ በኬንያ በጣም ተበልጦ ነበር፡፡ በወቅቱ በአትሌቶችና በቡድን ደረጃ ለሽልማት ከቀረቡት 8 የወርቅ ሜዳልያዎች የኬንያ ቡድን 6ቱን ሲወስድ የኢትዮጵያ ቡድን 2 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ብቻ አግኝቷል፡፡ በአጠቃላይ የኬንያ ቡድን በሻምፒዮናው ከቀረቡ 24 ሜዳልያዎች 11 ሲወስድ በኢትዮጵያ የተመዘገበው 5 ሜዳልያዎች ብቻ ነበር፡፡ በሻምፒዮናው ለሽልማት ከቀረበው ገንዘብ የኬንያ ቡድን 127ሺ ዶላር በመረከብ ከፍተኛ የበላይነት ሲያሳይ ለኢትዮጵያ የደረሰው 72ሺ ዶላር ብቻ እንደነበርም ይታወሳል፡፡

Read 4000 times