Saturday, 30 March 2013 13:34

መድረክ የብሄራዊ አንድነት መንግስት እንዲቋቋም ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(19 votes)

ኢህአዴግ “ህዝባዊ መሠረት” ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ተወያይቶ የአገሪቱን ችግሮች እንዲፈታ ተጠየቀ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የኢትዮጵያን ወቅታዊና መሠረታዊ ችግሮች የመፍቻ አቅጣጫዎች ያመላክታል ብሎ ይፋ ባደረገው ማኒፌስቶው፤ በአሁን ወቅት አገሪቱ በዘርፈ ብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እንደምትገኝ ጠቅሶ፤ ከነዚህ ችግሮች ለመውጣት ገዥው ፓርቲ ሃላፊነት በመውሠድ ከሁሉም ህዝባዊ መሠረት ካላቸው የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ተወያይቶ መፍትሄ መሻት እንዳለበት አሣሠበ፡፡ መድረክ ለጋዜጠኞች ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ማኒፌስቶው፤ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ መስክ፣ በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም በመልካም አስተዳደር ዘርፍ ውስጥ አሉ የሚላቸውን የሃገሪቱን ችግሮች ያላቸውን በዝርዝር አቅርቧል፡፡

ፓርቲው በፖለቲካው ዘርፍ ይስተዋላሉ ብሎ ካቀረባቸው ችግሮች መካከል በሃገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ መጨናገፉ፣ የህግ የበላይነት እና ገለልተኛነት እንይረጋገጥ በየደረጃው ተጠያቂነት አለመኖሩ፣ ሃሣብን በነፃ የመግለፅ መብት ከመደብዘዝ አልፎ ለመጥፋት መቃረቡ፣ የዲሞክራሲ ተቋማት አለመኖርና አሉ የሚባሉትም (ፓርላማ፣ ምርጫ ቦርድ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን) በኢህአዴግ ፍፁማዊ ተፅዕኖ ስር የሚንቀሣቀሡ መሆናቸው፣ ከምርጫ 97 ጀምሮ በሲቪክ ማህበረሠብና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች (መያዶች) ላይ አዲስ ህግ በማውጣት ጥቃት መክፈቱ፣ ህገመንግስቱ ለነፃ ፕሬስ የሠጠውን መብት በጠራራ ፀሃይ እየጣሠ መሆኑ፣ ሃቀኛ ተቃዋሚዎችን የሚደግፉ ዜጐችን ሠርቶ የመኖር መብት መንፈጉ፣ በሃቀኛ ተቃዋሚዎች ላይ ሠፊ የማጥላላት ዘመቻ ማካሄድ እና ከሠላማዊና ከህጋዊ ፓርቲዎች ጋር ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ ለመደራደር አሻፈረኝ ማለቱን በዝርዝር ገልጿል፡፡

በኢኮኖሚው ዘርፍ የተገኙ ጉድለቶች ተብለው በማኒፌስቶው ከተዘረዘሩት መካከልም መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ ከዜጎች የመግዛት አቅም በላይ ማሻቀቡ እና የህዝቡ የኑሮ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሄዱ፣ በህገወጥነት በትላልቅ የንግድ ተግባራት ውስጥ በመግባት ግዙፍ ፋብሪካዎችን፣ የፋይናንስ፣ የትራንስፖርት፣ የኮንስትራክሽን ወዘተ ኩባንያዎችን በማንቀሣቀስ የሃገሪቱን ነፃ የኢኮኖሚ ምህዳር ማዛነፋቸው፣ በየመስኩ “የመንግስት ሌቦች” እየተበራከቱ መሆናቸው፣ መንግስት ያለ አግባብ ከፍተኛ አስተዳደራዊ ወጪዎችን መመደቡ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሃብት የሆነውን መሬት ለውጭ ባለሃብቶች “ነፃ” በሚባል ዋጋ ማቅረቡ፣ ለ21 አመታት በቆየው የስልጣን ጊዜው የምግብ ዋስትና ጥያቄን አለማረጋገጡ እንዲሁም የኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት መቆራረጥ የሚሉት ተመልክተዋል፡፡ በተመሣሣይ በማህበራዊ ዘርፍ ከተገኙ ችግሮች መካከል የስራ አጥነት ችግር፣ እጅግ ጥቂት ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮች ሲፈጠሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሆች እየተፈለፈሉ መሆኑ እንዲሁም ብቃት ያለው የማህበራዊ ዋስትና ስርአት ባለመዘርጋቱ ዜጐች ለእለት ጉርሣቸው፣ ለመጠለያ፣ ለእርቃነ ስጋ መሸፈኛ ዋስትና አጥተው ከሠብአዊ ፍጡር በታች ተዋርደው የሚኖሩበት ሁኔታ መስፈኑ የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡ ትምህርትን በሚመለከት ያሉ ችግሮችን ሲዘረዝርም የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች የስራ እድል ለማግኘት የፓርቲ አባልነት መጠየቃቸው፣ የትምህርት እድሎች በዜጐች ብቃት ሣይሆን በፖለቲካ አመለካከት ላይ መመስረቱ፣ መምህራን በነፃነት የሙያ ማህበር ማቋቋም አለመቻላቸው የመሣሠሉት በማኒፌስቶው እንደ ችግር ተንፀባርቀዋል፡፡

በጤናው ረገድም ከህዝብ ብዛት አንፃር ተመጣጣኝ የህክምና አገልግሎት አለማግኘት እና የግል ህክምና ተቋማት ከህብረተሠቡ አቅም በላይ ዋጋ የሚጠይቁ መሆኑ ከችግሮቹ መካከል ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሚል የዘረዘረው ማኒፌስቶው፤ ሙስና፣ የልማት ሠራዊት በሚል የተጀመረው የ1ለ5 አደረጃጀት ለፖለቲካ አላማ መዋል እና በየመንግስት መስሪያ ቤቶች የሠፈኑ ዝርክርክ አሠራሮች ዜጐችን እያማረሩ መሆኑ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቅሷል፡፡ ፓርቲው ችግር ብሎ ለዘረዝራቸው ጉዳዮች የመፍትሄ ሃሳቦችን ያስቀመጠ ሲሆን የመድብለ ፓርቲን ስርአት እውን ማድረግ፣ የነፃ ሚዲያ ስርአትን ማስፈን፣ የዜጐችን መሠረታዊ ሠብአዊ መብቶችና የህግ የበላይነት እንዲሁም የዳኝነት ነፃነትን ማረጋገጥ፣ የምርጫ ስርአቱን ማስተካከል፣ በሃቀኛ ተቃዋሚዎች ላይ እየተደረገ ያለውን አፈናና የማቀጨጭ እርምጃዎች ማስቆም የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በኢኮኖሚ ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች ደግሞ ዜጐች ያለ አድልኦ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል፣ ለዜጐች ሠፊ የስራ እድል መፍጠር ሙስና የልማቱን ቀጣይነት እና ውጤታማነት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት ሠጥቶ ፈጣን መፍትሄ መሻት፣ በኢኮኖሚው ህይወት ውስጥ ከፍተኛ መዛነፍ ፈጥረው የሚገኙትን የኢህአዴግ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ወደ ገበያ ኢኮኖሚ አካልነት የሚሸጋገሩበትን ሁኔታ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በመደራደር መቀየስ የሚሉት ዋና ዋና የመፍትሄ ሃሣቦች ተብለው በማኒፌስቶው ቀርበዋል፡፡

የመድረክ አመራሮች በጋራ በሠጡት መግለጫ፤ ሃገሪቱ በአሁን ሠአት በዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ለመገኘቷ ኢህአዴግ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ አመልክተው፣ ይህን ማኒፌስቶ ማውጣት ያስፈለገውም ፓርቲው እነዚህን የሃገሪቱን ችግሮች ተረድቶ ከሌሎች የሃገሪቱ ፓርቲዎች ጋር በመግባባት መፍትሄ እንዲሻ ለማሣሠብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “የተዘረዘሩት ችግሮች በመሉ ከዚህ ቀደም ከምትሏቸው በምን ይለያሉ?” በሚል ጋዜጠኞች ላቀረቡት ጥያቄ የመድረክ አመራሮች ሲመልሱ፤ “ማኒፌስቶው በ21 አመታት ጊዜ ውስጥ የተፈጠሩና አሁንም ድረስ የቀጠሉ ችግሮችን ይዳስሣል፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም” ብለዋል፡፡ የአረና ሊቀመንበርና የመድረክ አመራር አባል አቶ ገብሩ አስራት በሠጡት ማብራሪያ፤ መድረክ ሃገሪቱ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች ብሎ በማኒፌስቶው የገለፀው፣ መንግስት ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ሣያንሡ በሃይማኖት ጉዳዮች ውስጥ እጁን አስገብቶ በመገኘቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም የመድረክ አመራር አባል የሆኑት የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ (ኦህኮ) ሊቀ መንበር ዶ/ር መራራ ጉዲና፤ ኢህአዴግ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመደራደር ብሄራዊ የአንድነት መንግስት በጥምረት ማቋቋም እንደሚገባው ባደረጉት ንግግር አመልክተዋል፡፡

Read 4267 times