Saturday, 30 March 2013 14:37

በፓኪስታን የመጀመርያው ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይሳካ ይሆን?

Written by  ኤልሳቤጥ እቁባይ
Rate this item
(1 Vote)

ከ66 አመት በኋላ የስራ ዘመኑን በቅጡ ያጠናቀቀ ፓርላማ ፓኪስታን ነፃነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ መፈንቅለ መንግስት ተለይቷት አያውቅም፡፡ ከተካሄዱት መፈንቅለ መንግስቶቹ ጋር በተያያዘም አገሪቱ በተለያዩ ወታደራዊ አገዛዞች ስር ለመውደቅ ተገድዳለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1958 የጠቅላይ ሚኒስትር ፌሮዝ ካህን መንግስትን በሀይል በመገልበጥ የጦር አዛዡን አዩብ ካህንን ለስልጣን ያበቁት የአገሪቱ የመጀመሪያ ፕሬዚደንት ጀነራል ሚርዛ፤ ወደስልጣን ባመጧቸው አዩብ ካህን ነበር ከስልጣን የተወገዱት፡፡ ኦፕሬሽን ፌር ፕሌይ የሚል የኮድ ስም የተሰጠው የ1977ቱ መፈንቅለ መንግስት የተመራው በጀነራል ዚያ አልሀቅ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዙልፊካር አሊ ቡቶንና ሚኒስትሮቻቸውን በእኩለ ለሊት በቁጥጥር ስር በማዋል የፓኪስታን ብሄራዊ ጉባኤ መፍረሱንና የአገሪቱ ህገመንግስትም ተፈፃሚነት እንደሌለው በቴሌቪዥን አወጁ፡፡ ሌላው በፓኪስታን ታሪክ ከተሳኩ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች ተርታ የሚመደበው እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም በጀነራል ፐርቬዝ ሙሻራፍ ታማኝ የጦር መኮንኖች አማካኝነት በጠቅላይ ናዋዝ ሸሪፍ ላይ የተደረገው መፈንቅለ መንግስት ነው፡፡ ፓኪስታን ብዙ የከሸፉ መፈንቅለ መንግስታትም የተካሄዱባት አገር ናት፡፡

እ.ኤ.አ በ1949 በሜጀር ጀነራል አክባር ካህን የተመራው እና በአሊ ካህን መንግስት ላይ የተሞከረው መፈንቅለ መንግስት ከከሸፉት ውስጥ ተጠቃሽ ሲሆን በ1995 ደግሞ ሜጄር ጀነራል ዛሂሩል ኢስላም አባስ ፤ በቤናዝር ቡቶ ላይ የሞከሩት የከሸፈ መፈንቅለ መንግስት ይገኝበታል፡፡በ1980 ዓ.ም ሜጀር ጀነራል ታፕሙል ሁሴን የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ የግድያ ሙከራ ማድረጋቸውም ይታወቃል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች እና ወታደራዊ ጣልቃገብነት የተነሳም አገሪቱ ነፃነቷን አውጃ ፓርላማ ካቋቋመች ጊዜ ጀምሮ ፓርላማው የስራ ዘመኑን ሳይጨርስ እንዲበተን ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሰሞኑን የአምስት አመት የስራ ዘመኑን አጠናቆ የተበተነው የፓኪስታን ፓርላማ ፤ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ክስተት በመሆኑ ከተለያዩ ወገኖች አድናቆትን አግኝቷል ፤ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክትም እየጎረፈለት ይገኛል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜም የፓርላማ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ አገሪቱን በሞግዚትነት የሚያስተዳድር አካል ተመርጦ ቃለ መሀላ ፈፅሟል፡፡ በዳኝነት ለረጅም አመታት ያገለገሉት ጡረተኛው ሀዛር ካህን፤ የሞግዚት አስተዳደሩ ፕሬዚደንት እንዲሆኑ የተወሰነው ፖለቲከኞች በቀረቡ እጩዎች ላይ በመወዛገባቸውና ከቀረቡት እጩዎች ውስጥ ሀዛር ላይ ብዙ ጭቅጭቅ ባለመነሳቱ ነው፡፡ የአገሪቱ የፓርላማ ምርጫ በመጪው ግንቦት ተካሂዶ አሸናፊው ወገን ስልጣን እሰኪረከብ ድረስ ሀዛር ፓኪስታንን ያስተዳድራሉ ማለት ነው፡፡ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ራጃ ፐርቬዝ አሽራፍ፤ ፓርላማው የስራ ዘመኑን አጠናቆ መበተኑን ለፓርላማ ካወጁ በኋላ ለአገሪቱ ራዲዮ እና ቴሌቪዚን በሰጡት መግለጫ፤ ዲሞክራሲውን ለማጠንከርና እዚህ ደረጃ እንዲደርስ አስተዋፅኦ ያበረከቱትን ወገኖች እና ተቋማት በሙሉ እንደሚያመሰግኑ በመግለፅ ፤ ምንም እንኳን መንግስታቸው የተለያዩ አሉታዊ ፕሮፓጋንዳዎች ሰለባ ቢሆንም የስራ ዘመኑን መጨረሱ በራሱ ታሪካዊ እንደሚያሰኘው ተናግረዋል፡፡

ገና ከአሁኑ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች በፓርላማው ፊትለፊት ሰልፍ በማድረግ ቀጣዩ ምርጫ ነፃ እና ፍትሀዊ እንዲሆን እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡ የፓኪስታን ፓርላማ የስራ ዘመኑን ማጠናቀቁን አስመልክቶ የፖለቲካ ተንታኞችም የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ነው፡፡ የነፃ እና ፍትሀዊ ምርጫ ኔትወርክ ዳይሬክተር ራሺድ እንደሚሉት፤ ፓኪስታን አገር ሆና ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ የወታደራዊ ጣልቃገብነት ትልቁን ሚና የሚይዝ ሲሆን የአሁኑ መንግስትም የተመሰረተው በመጨረሻው ወታደራዊ አምባገነን በጄነራል ፐርቬዝ ሙሻራፍ እግር ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የፓኪስታን የሲቪል መንግስት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች እየበሰሉ እንደመጡ ያሳያል፤ ለፖለቲካ ብስለቱ እንደ ዋና ተምሳሌት የሚወሰደው ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ዲሞክራሲው መቀጠል አለበት በሚለው ነጥብ ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ነው ተብሏል፡፡ ኔትወርኩ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የአምስት አመት የፓርላማው አፈፃፀም ሰነድ መሰረት፤ በፓርላማ የፀደቁ ህጎች በመቶ ሀምሳ ፐርሰንት እድገት አሳይተዋል፤ ይሁን እንጂ ህግ እና ስርአት በማስከበር ረገድ እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የመንግስት ስራ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አልቀረም፡፡ በላሆር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር የሆኑት ራሱል ባከሽ እንደሚሉት፤ በአምስት አመቱ የፓርላማ ዘመን ሙስና፤ ከህግ አውጭ አካል ጋር ፍጥጫ ፤ ስርአት አልበኝነት እና የመሳሰሉት ችግሮች በስፋት ቢስተዋሉም ቅሉ እንደከዚህ በፊቱ የወታደሩ ኃይል ጣልቃ መግባቱን አልፈለገም ፡፡

ይህ ደግሞ ጦር ሠራዊቱ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ያሳያል፡፡ ነገር ግን ይላሉ ራሱል “የጦር ሠራዊቱ ጥላ በሲቪል መንግስቱ ላይ እንደቀድሞው ጎልቶ ባይታይም አሁንም ጥላው እንዳለ ነው፡፡ ለዚህም ጥሩ ማስረጃ የሚሆነው በፓኪስታን የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር በወታደራዊ ጫና መባረራቸው ነው” ይላሉ፡፡ ፓኪስታን ቀጣዩን ምርጫ በግንቦት ወር የምታደርግ ሲሆን ትክክለኛው ቀን በአገሪቱ ፕሬዚደንት አሲፍ አሊ እንደሚወሰን ታውቋል፡፡ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜም በምርጫ የተመረጠ መንግስት ስልጣኑን በምርጫ ለሚመረጥ ባለተራ ያስረክባል፡፡ “የአገልግሎት ዘመኑን ያጠናቀቀው ፓርላማ በአገሪቱ ታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ሆኗል ፡፡ ፓርላማው የዲሞክራሲ ሂደቶችን በተግባር አሳይቷል፡፡ ለቀጣዩ ፓርላማም ስራችንን አቃሏል” ይላሉ- የገዢው ፓርቲ አባል ያስሜን ራሺድ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባሉ ሳርዳር መሀታብ አህመድ ከሀን በበኩላቸው፤ ፓርላማው የስራ ዘመኑን መጨረሱ ብቻውን መታየት የለበትም፡፡ እውነት ነው ከዚህ ቀደም የነበረው ወታደራዊ አገዛዝ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መሰረቶች አናግቷል፡፡ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ከተመረጠ መንግስት ዜጎች ብዙ ነገሮችን ይጠብቁ ነበር፤ ሆኖም ያገኙት ነገር ቢኖር ከፍተኛ ታክስ፤ የሀይል መቋረጥ፤የጋዝ እጥረት፤ የዋጋ ንረት እና ተስፋ ቢስነትን ነው ብለዋል፡፡

የፓኪስታን ኢኒስቲትዩት ኦፍ ሌጂስሌቲቭ ዴቨሎፕመንት ኤንድ ትራንስፓረንሲው አህመድ ቢላል በሰጡት አስተያየት፤ “ምንም እንኳን የስራ ዘመኑን ያጠናቀቀው ፓርላማ በመልካም አስተዳደር እጦት እና በሙስና የተዘፈቀ ቢሆንም ያደረጋቸው የፖለቲካ እና የምርጫ ማሻሻያዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ፓርላማውን ጠንካራ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፤ ለታችኛው የመንግስት መዋቅር ስልጣን መስጠት እና ተቃዋሚዎች በምርጫ ኮሚሽን ምርጫ ላይ ሀሳባቸውን እንዲያካትቱ ማድረጉም ታላላቅ ድሎች ናቸው” ብለዋል፡፡ በ66 አመት ታሪክ ውስጥ የስራ ዘመኑን አጠናቆ ለቀጣዩ ለማስረከብ መዘጋጀት ትልቅ የታሪክ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነው፤ ነገር ግን የፓኪስታን ውጤታማነት በብዙ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች ተተብትቦ የሚገኝ በመሆኑ በርካታ ትኩረት የሚፈልጉ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር የተያያዙ ችግሮች፤ ዜጎችን ወደ አደባባይ እንዲወጡ ያስገደደው ተደጋጋሚ የሃይል መቋረጥ፤ ከህንድ ጋር ያለው ያልተቋጨ የድንበር ውዝግብ፡ ከሀይማኖት ጋር የተያያዙ ግጭቶች ፤ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባቶችና ሌሎች መልስ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ለቀጣዩ ፓርላማ ይተላለፋሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አሽራፍ በርካታ ችግሮችን ከጄነራል ፐርቬዝ ሙሻራፍ የተረከብናቸው ናቸው በማለት ባለፈው መንግስት ላይ በማሳበብ ይታወቃሉ፡፡

ግንቦት ወር ላይ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ ላይ እንደሚሳተፉ ያሳወቁትና በራሳቸው ላይ ጥለውት የነበረውን አገር ውስጥ ያለመኖር ማእቀብ አንስተው ፓኪስታን የገቡት፤ በ1999 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ይዘው በ2008 በተደረገ ምርጫ ስልጣናቸውን ያጡት የቀድሞው ወታደራዊ መሪ ጀነራል ፐርቬዝ ሙሻራፍ፤ በቀጣዩ ምርጫ ብቻ ሳይሆን በወደፊቱ የአገሪቱ እጣፈንታ ላይም በአወንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ የሚጫወቱት ሚና እንዳለ ከወዲሁ እየተነገረ ነው፡፡ በምርጫው አገኛለሁ ብለው የሚያስቡትን ድምፅ በተመለከተ ሙሻራፍ ለህንድ የዜና ጣቢያ በሰጡት ቃለምልልስ፤ “ራሴን እጅግ አጋንኜ ማቅረብ ባልፈልግም ፈላጊ የሌለኝ በማድረግም ላጣጥለው አልሻም ፤ የኔ እምነት ሳይሞክሩ ቁጭ ከማለት ሞክሮ መውደቅ ይሻላል የሚል ነው፡፡ ፓኪስታን ወደ ልማት እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መመለስ አለባት” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሙሻራፍ ካራቺ፤ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ወደ 1500 የሚጠጉ ሰዎች የተቀበሏቸው ሲሆን ቁጥሩ ከፓኪስታን ፖለቲካ አንፃር እጅግ ትንሽ ነው የሚያስብል ሊሆን ይችላል፡፡ ደጋፊዎቻቸው ግን ብዙ ሰዎች ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እንዳይመጡ በፖሊስ መታገዳቸውን ተናግረዋል፤ ምንም እንኳን ክሱ ተጨባጭ ማስረጃ የለውም ቢባልም፡፡ ካራቺ አውሮፕላን ማረፊያ ሊቀበሏቸው ለመጡ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ፤ “ከአምስት አመት በፊት የተውኳት ፓኪስታን የታለች? አገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ሳይ ልቤ ደም አነባ፤ የተውኳትን ፓኪስታን ለመመለስ ተመልሼ መጣሁ” ብለዋል፡፡ ሙሻራፍ ወደ ፖለቲካው ከመመለስ ይልቅ ለፈፀሟቸው ወንጀሎች ፍርድ ቤት መቆም አለባቸው በሚል ፓርላማ አቅርቦት የነበረው ጥያቄ በወታደሩ ኃይል ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም፡፡ የፓኪስታን የመጨረሻው አምባገነን ወታደራዊ መሪ በመባል የሚታወቁት ሙሻራፍ፤ ከወታደሩም ሆነ ከሲቪሉ ህዝብ የሚገጥማቸው አንዱ ፈተና “ሲቪሉን ሙሻራፍ ተቀበሉ ማለታቸው ነው” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፤ በፖለቲካ ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ የሚወሰነው ግን በወታደሩ ውስጥ በሚያገኙት የድጋፍ መጠን እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ሙሻራፍ የመጡት ሲቪል ሆነው ሳይሆን የወታደሩን ድብቅ ፍላጎት ሰንቀው ነው የሚሉ ወገኖች በበኩላቸው፤ “የፓኪስታን ወታደራዊ ኃይል ለስልጣን ያለው ጥም አሁንም አልቆረጠለትም፡፡ ከፓኪስታን ታሪክ መማር እንደሚቻለው ወታደሩ እንኳን በስራ ላይ ያሉትን ቀርቶ ጡረታ የወጡትን ጀነራሎቹን እንኳን እንዲቦዝኑ አያደርግም፡፡

የሙሻራፍ ወደ ፖለቲካው መምጣትም ያንን የሚያረጋግጥ ነው” ይላሉ፡፡ በጡረታ ከመገለላቸው በፊት የአየር ሀይል መኮንን የነበሩት ፋሩቅ ዳውድ የሙሻራፍን ወደ ፓኪስታን መመለስ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ ሙሻራፍ ቅንጦት የተሞላውን ኑሮውን እዚያው መቀጠል ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን አገሩን ለማገልገል ተመልሶ መጥቷል ብለዋል፡፡በቀጣዩ ግንቦት ወር የሚካሄደው ምርጫ ያለምንም ደም መፋሰስ እና ጣልቃገብነት ከተከናወነ በፓኪስታን የመጀመሪያው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ይሆናል፡፡ የ24 አመቱ ፓኪስታናዊ የአካውንቲንግ ተማሪ ስለመጪው ምርጫ በሰጠው አስተያየት፤ “በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመራን በአምባገነን ብዙ ለውጥ የለውም ፡፡ ህዝቡ ደሀ ስለሆነ የሚፈልገው ሰላም፤ የኢኮኖሚ መረጋጋትና የስራ እድል ነው” ባይ ነው፡፡

Read 2858 times