Saturday, 30 March 2013 15:15

የፍቅር ሃዲዶች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(19 votes)

“ምን ዓይነት ሰው ማግባት አለብኝ?”

ደረጀ በላይነህ ስለ ፍቅርም ስናወራ ኖረናል፤ግን ዛሬም የትረካው ገደል አልጠረቃም፤ አፉን ከፍቷል፤ፍቅር ዛሬም ጥያቄ ፣ዛሬም ተአምር ነው፡፡ትልቅ-ትንሹ-ደራሲው-ሰአሊው፤ፈላስፋው-ሳይንቲስቱ፤ሁሉም ተገርሞ፤ሁሉም ተደምሞ አልፎበታል፡፡ተረኛው ደግሞ ገና ይደመማል፡፡ ጃኩሊን ቢ ካር በዚህ ይስማማሉ፡፡ “Many books have been written on the subject of love,yet love remains a mystry that defies understanding.” ታዲያ እርሳቸው እንደሚሉት ፍቅር ብዙ ነው - ለምሳሌ ህፃን ልጅ እናቱን “እወድሻለሁ”ይላል፡፡ ይህ ማለቱ “ታስፈልጊኛለሽ” ነው፡፡ ብቻ ፍቅር በየመልኩ መፈላለግ ነው፡፡እኔ ዛሬ የምለው ፍቅር ግን ከመፈላለግ ያልፋል፡፡ ወፈፍ ያደርጋል የሚባለው፣ በተመስጦ እልም ብለው ኬላ የሚጥሱበትን የተቃራኒ ጾታ ፍቅር ነው፡፡ ምናልባትም ውስጡ ላሉት ሰዎች ካልሆነ በቀር ዳር ላሉት አጋፋሪዎች ትርጉም የማይሰጠው አይነት፡፡

ይህን ሃሳብ ለመግለጥ የታገል ሰይፉ “ፍቅር ለኔና አንቺ” የሚለው ግጥም በጣም ተስማሚ ነው፡- የለም ትንገራቸው-የጠየቋት ለታ ምን እንዳልኳት እቱ፣ ያው ዋሽቷል ቢሏት ነው-በቃላት ጋጋታ በውዳሴ ከንቱ፣ አውቃለሁ ውሸት ነው-ጨርሶ እማይመስል ዳር ቆሞ ለሰማኝ፣ አስር ጊዜ እየማልኩ-ውሃ አይጠማኝም ስል ፍቅርዋ እንደሚጠማኝ፣ አውቃለሁ ውሸት ነው-የሚያስቅ ሺህ አመት ላገር ለከተማው፣ ካለስዋ አይበራም ስል- የዘመኔ ጽልመት የቀኔ ጨለማው ፣ አውቃለሁ ውሸት ነው-ፍሬ ቢስ ገለባ ለሰማኝ በሩቁ፣ እስከ ዛሬ ድረስ - የሷ አይነት አበባ በቅሎ አለማወቁ፣ ግና ይሄ ውሸት-ይህ ውዳሴ ከንቱ አገር ያቀለለው፣ በኔ እና እሷ መሐል - ዕውነት መሆኑ ነው ፍቅር የሚባለው፡፡ የታገል ግጥም ፍቅር ላልመሰጠው ሰው፤ ዕብደትም ሊመስል የሚችል ትርጉም የለሽ ድራማ ነው፡፡ በአብዛኛው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዕንቁላሉን የሚጥለው ለጋ ፍቅር፤ በሶስተኛ ደረጃ ትምህርት ጊዜ ጥርስ ያወጣል፡፡

በሥራ አለም እሸት ይግጣል፤ብዬ አምናለሁ፡፡ በአንድ ድንኳን ወይም ጎጆ ገብቶ ይፈተናል፤ይፈተጋል፡፡ይህ ሁሉ ታዲያ ሲሳካ ነው፡፡ ፍቅር ትንሽ -ትንሽ ማበድ የሚመስለው ሰው የተፈጥሮ ጸባዩን አጥር ሲዘልል መገኘቱ ነው፡፡ አይናፋሩን አይናውጣ፤ቀርፋፋውን ፈጣን አድርጎ እንደገና መፍጠሩ ከሚደንቁት ባህርያቱ አንዱ ነው፡፡ አንዳንዴ እስቲ ደመና ላይ የምትራመዱ፤ጸሃይን የጨበጣችሁ፤ጨረርዋ ላይ ቅርጫት የደፋችሁ መስሏችሁ አያውቅም? የማትቆጣጠሩት ስሜትም ሆናል፡፡ “Some times we experience love as feeling ,…seeming uncontrollable emotion…..Some times we experience love as a body response with rocking,hugging,and kissing.” ሌላ ጊዜ ደግሞ ፍቅርን በቃላት “እወድሻለሁ” ወይም “እወድሃለሁ” በማለት እንገልጣለን፡፡ ከላይ ጸሃፊው እንዳሉት በመተቃቀፍና በመሳሳምም እንገልጣለን፡፡

ዘለቅ ሲልም ወደ ጎጆ ገብተን አልጋ ውስጥ ድንኳን እንሰራለን፡፡ የዌስተርን ኢሊየን ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች ላይ ያደረገው ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ሮማንቲክ የሚባለው ፍቅር አንድ አይነት ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የስሜት መሳሳብን የሚጨምር ነው፡፡ ዶክተር ሙሬይ ባንክ እንደሚሉት፤ ብዙዎቻችን ፍቅርና የተንቀለቀለ የወረት ስሜት ይምታታብናል፡፡አልማዝን ከብልጭልጭ እኩል እንደ ማድረግ፡፡ዶክተር ባንክ፤ ፍቅር በሁለት ሰዎች መካከል ያለ የጋራ ነገር ሆኖ ለየብቻ ከመሆን ይልቅ በጋራ ሲሆኑ ጠንካራ ሊያደርጋቸው የሚችል ነገር ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙበት፤ ሮማንቲክ ፍቅር ከወረት ጋር ስለሚቀላቀል በጥቂት ጊዜ እልም ብሎ ጠፍቶ “ምን ሆኜ ነበር?”የሚል ፈተና ያመጣል፡፡

የሰው-ሰው ሜዳ ላይ መጣልም ለህሊና ዕዳ ነውና ብዙዎች ምጥ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ክፋቱ ደግሞ እኛ ሃበሾች ማፍቀርም ነውር ይመስለናል፡፡ ጨለማ ውስጥ እንደ ቡሄ ዳቦ የሚገማመጠው ሁሉ ጠዋት ጸሃይ ላይ ስለፍቅር ስታወራው “አትባልግ” ይልሃል! ብልግናው ግን ራስን ማታለሉ ነው፤ለመሆኑ እግዜር ፍቅርን መፍጠሩ ብልግና ይሆን? አንዳንድ ሀይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች፤ ፍቅርን እንደ ብልግና መቁጠራቸው እግዜርን መስደባቸው እንደሆነ ልብ ያሉት አይመስልም፡፡ ፍቅር በምን-በምን ይመጣል?የሚለውን ስንፈትሸው አንዳንዴ ለራሳችንም ግራ ይገባናል፡፡ ብዙ የምንስማማባቸው የጋራ ነጥቦች ቢኖሩም---ለምሳሌ አብዛኛው ሰው ውጫዊ ውበት ብቻ ማረከኝ ሲል፣አንዳንዱ ደግሞ ጸባዩ-ጸባይዋ ይላል፡፡

አንድ የስነ ጋብቻ አዋቂ በጻፉት መጽሃፍ እንደሚጠቅሱት በአእምሮ ብስለት፣በጥሩ ጸባይ፣የሚማረኩ ብዙ ናቸው፡፡ ስለፍቅር ሳነሳ ትዝ ያለኝን የዕብደት ያህል የሆነ የፍቅር ደብዳቤ ልጥቀስና ትንሽ ልበል መሰለኝ፡፡ እንዲህ ይላል፡- “በአገርም በዓለምም የሌለሽ ሲመስለኝ የአዲስ አበባን ፎቆች በባህር ላይ እንደሚዋኙ ዳክዬዎች ፈራኋቸው፤የቆምኩበት የብስ ውሃ መሰለኝ፤ ባባሁ፡፡ ማዕበሉ ሲያንገላታኝ ባህሩ ዳር የቆምኩ ቄጤማ ነኝ ብዬ እስክጠራጠር ተዋከብኩ፡፡ይገርማል፣የደስታዬ ጧፍ ባንች እጅ ነውና፤የህይወቴ ብርሃን አዘል ተስፋ፣የነገው ውጋገን አድማስ አንቺ መሆንሽንና ቀኔን ልትደብቂብኝ እንደምትችዪ አሁን ገና ተከሰተልኝ፡፡ ጓደኞቼ…እህቶቼ…ቤተሰቦቼ የኔን ህይወት የሚያጣፍጡ ቅመሞች አይደሉምን?…ለካስ ጨው ከሌለው ቅመምም ከንቱ ነው፡፡…ባልፈጠርሽው ዓለም ማን ገዢ እንዳደረገሽ ባላውቅም መላውን ዓለም መልክ-የለሽ ስታደርጊብኝ ራሴን ታዘብኩት፡፡ እንደገና ደግሞ ሳስበው የኔንና ያንቺን ዓለም ውብ አድርገሽ የሰራሻት አንቺ ነሽና በዓለማችን ውስጥ እንደፈቀድሽ ማድረግ የምትችዪው አንቺ ነሽ፡፡ ፀሐዬን ማውጣት አሊያም ማግባት የምትችዬው…” ፍቅር ዕብደት ነው የሚያሰኘኝ ይሄኔ ነው፡፡

ፍቅረኛው ፀሐይን የምታወጣለት የሚመስለው ሰውዬ፤ለጊዜው ሾጥ አድርጎታል ቢባል ውሸት ይሆን?…ቀጣዩም ግጥም ተመሳሳይ ቃና አለው፡፡ የፍቅር ድንኳን ዕብደት ነው፡፡ እንዲህ ለመስከርም ሆነ ለማበድ ፍቅር እንኳን ኖረ!!.. ሰማይ ፍርክስ ይበል-ከነአድራሻው ይጥፋ፣ የፍጥረት ዘር ይፍሰስ-ቦሃቃው ይደፋ፤ ከምድር ስር መሰረት-ድንኳን ሁሉ ይነቀል፤ በየአድማሳቱ ላይ-ቢያሻው ነፋስ ይብቀል፤ ምድርን የሞላው ዉቅያኖስ ባህሩ ሽቅብ ዞሮ ይፍሰስ፣መሰረቱ ይታጣ፣ ጸሃይ ከዋክብትም - ጮራቸው ይራገፍ-ጽልመት እንደ ሌባ ከደጃቸው ይምጣ፤ ምንም በሌለበት ደረቅ ምድረ-በዳ የትኛውም ነገር በሌለበት ዓለም፣ ባንቺ በራስሽ ውሥጥ በማልጠግበው ቀለም፣ ሳልበላ ሳልጠጣ… ኖራለሁ ዘላለም፡፡ ጃኩሊን ቢ ካር፤ አሜሪካዊያን ፍቅርና ትዳርን እንደ ፈረስና ጋሪ አድርገው ተቀብለውታል ይላሉ፡፡ እንደኔ - እንደኔ ከእነርሱ ይልቅ ነገሩ እውነት የሚሆነው ለኛ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ወደ ትዳር የማይደርስ ፍቅር እንደ ሞራል ዝቅጠቶች ሊታይ ይችላል ማለት አይከብደኝም፡፡

ፍቅር ግቡ ጤናማ ትዳር ሊሆን ይገባል፡፡ አጀማመሩም ለዚሁ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ሲል ይህንኑ ጣፋጭ ፍቅር ለሰው ተመኝቶ ነው፡፡ ፀሐፊው እንደሚሉት፤ አሜሪካ ውስጥ የትዳር/ጋብቻ ትርጉም በየጊዜው የተለያየ ነበር፤ነውም፡፡ ለምሳሌ በ1950ዎቹ ፤96 በመቶ የሚሆኑት ልጅ መውለጃ ጊዜ ላይ ይጋቡ ነበር፤ያ ብቻም አይደለም፤ለዘላለም ነው ብለው ይቀበሉ ነበር፡፡ ትዳር መያዝን ወደ አዋቂነት ጎራ መቀላቀል አድርገውም ያዩት ነበር፡፡ የስነ ጋብቻ ምሁሩ አንድ ሰው ከማግባቱ በፊት ቀጣዮቹን ጥያቄዎች እንዲጠይቅ ይመክራሉ፡- -አመት በዐል ብቻዬን ሳከብር ይደብረኛል -ቴአትር ቤት ብቻዬን መሄድ ጥሩ ስሜት ይሰጠኝም -ለህይወቴ ግቦች የሚያግዘኝ ሰው ያስፈልገኝ ይሆን -ውሳኔዎችን ለመወሰን ሌላ ሊረዳኝ የሚችል አጋር ያሻኛል -ብቻዬን መተኛትና ምግብ መብላት ያስጠላኛል -ገንዘቤን ከሌላ ሰው ጋር መጋራት እፈልጋለሁ -ልጅ መውለድ እሻለሁ -ቀጣይ የሆነ ግንኙነት ካንድ ሰው ጋር እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ ሌላው ጥያቄ “ምን ዓይነት ሰው ማግባት አለብኝ?” የሚለው ነው፡

፡ለዚህ ጥያቄ መልሱ የሚወሰነው በሰውየው ማንነት ነው፡፡ ሰውየው ማንነቱንና ቅድሚያ የሚሰጠውን ነገር ማሰብ አለበት፡፡ ምን እንደሚፈልግ፣ማወቅ አለበት፡፡ እነዚህ ደግሞ የሰውን ውጫዊ አካላዊ/ገጽታ፣ሰብዕና፣ገንዘብ፣ማህበራዊ ደረጃ፣ ወዘተን ይጨምራሉ፡፡ ለአካላዊ ገጽታ ቅድሚያ የሚሰጥ ሰው ገንዘብ ያለውን፣ወይም ጥሩ ማህበራዊ ተቀባይነት ያለውን ሰው ቢያገባ አይረካም፤ይሁንና የ20 አመት ጎረምሳና የ40 አመት ጎልማሳ የምርጫ ሚዛናቸው ተመሳሳይ አይሆንም፡፡ ብቻ በዚያም አለ በዚህ ሁለት ሰዎች በአንድ ቤት ህይወትን አንድ ላይ የሚገፉ ከሆነ የጋራ የሆኑ ምርጫዎች ሊኖሩዋቸው ይገባል፡፡ ልክ እንደ አካላዊ መስህብ ፈላጊዎች ተቃራኒ ጾታ ውስጥ የውስጥ ውበትን የሚፈልጉና ብስለትን የሚመርጡ አሉ፡፡ በነገራችን ላይ ተመሳሳይ ክንፍ ያላቸው ወፎች አንድ ላይ ይበርራሉ ፤እንደሚባለው በሳል ሰው አእምሮ ላይ ማተኮሩ የግድ ነው፡፡

የኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ሮበርት ዊንች ስለ ፍቅር ሲናገሩ፤ ማንም ሰው ሲያፈቅር በዋናነት ጥቅሙ ለራሱ ለአፍቃሪው ነው ይላሉ፡፡ ይሁንና ፍቅር ወደ መጨረሻ ድንኳኑ ከገባ በኋላም ጣጣው ብዙ ነው፡፡ በሩቅ - ለሩቅ ፍቅር ወቅት የተደበቁ ጸባዮች ሲገለጡ ጦርነቱ እንደ አዲስ ይጀመራል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት፤ በእጮኝነት ጊዜ መጠናናት የትዳርን ዉበት ሊጨምረው ይችላል፤ምክንያቱም ብዙዎቹን ነገሮች አውቆ መግባት ችግሩን ከስሩ ባያጠፋውም ይቀንሰዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የሰው ጸባይ በጥናት ያልቃል፤ወይም ይደረስበታል ማለት አይደለም፡፡

ብሩስና ካሮል ብሪተንን ጨምሮ ብዙ የስነ ጋብቻ አማካሪዎች፤“የትዳር አንዱ ጠንቅ ከቀድሞ የጥንዶቹ ህይወት ውስጥ የተሰነቀረ ችግር ነው፡፡ በተለይ ከቀድሞ የፍቅር ጓደኞቻቸው ጋር ተያይዞ የሚመጣው ጣጣ ትዳሩን እስከማፍረስ ይደርሳል፤ያለመተማመንና የፍቅር መቀዝቀዝን ያመጣል” ይላሉ፡፡ ፍቅር ሲጀምሩ ታጥቦ ታጥኖ ካልሆነ በሁለት ልብ ሁለት ዛፍ መውጣት አይመከርም፡፡ በራስም በሌላውም ህይወት መቀለድ ነውና፡፡

Read 10935 times