Saturday, 30 March 2013 16:05

የእንግሊዝ ተዋናዮች በሆሊውድ ተመራጭ ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የብሪታኒያ ተዋናዮች በሆሊውድ ፊልም ሰሪዎች ተመራጭ እና ተፈላጊ እየሆኑ መምጣታቸውን ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር አስታወቀ፡፡ በማራኪ የእንግሊዘኛ ቋንቋ አነጋገር፤ በምርጥ የትወና ብቃታቸው፤እንዲሁም በሚጠይቁት ተመጣጣኝ ክፍያ የእንግሊዝ ተዋናዮች ተመራጭ ሆነዋል ተብሏል፡፡ በበርካታ የሆሊውድ ፊልሞች መሪ ተዋናይነት በመስራት እና በመልመል አሜሪካውያኑን ከገበያ እያስወጡ እንደሆነም ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

የእንግሊዝ ምርጥ የትወና ብቃት በሲኒማ ብቻ ሳይሆን በቲቪ ተከታታይ ፊልሞችም እየታየ ሲሆን በአሜሪካ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በአሜሪካውያን ህይወት ላይ የሚያጠነጥኑ ፊልሞች ላይ ሳይቀሩ እንግሊዛውያኑ በብዛት እየተወኑ ነው፡፡ የታላቋ ብሪታኒያ የፊልም ኢንዱስትሪ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል ከወር በኋላ ንግስት ኤልዛቤት በሚገኙበት እንደሚከበር የገለፀው ዘጋርድያን፤ በዚሁ ስነስርዓት ላይ በሆሊውድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙ የብሪታኒያ ምርጥ ተዋናዮች ይመሰገናሉ ብሏል፡፡

ድሮ ድሮ በሆሊውድ ፊልሞች የመጥፎ ገፀባህርያት ሚና ይሰጣቸው የነበሩ የብሪታኒያ ተዋናዮች፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን በከፍተኛ በጀት በተሰሩ፤ ታሪካዊ ይዘት ባላቸው እና በሱፐር ሂሮ ፊልሞች ላይ መተወን ይዘዋል፡፡ በሆሊውድ የእንግሊዞቹ ዋና ተፎካካሪዎቻቸው አውስትራሊያውያን ብቻ እንደሆኑም ታውቋል፡፡ አንቶኒ ሆፕኪንስ፤ ማይክል ኬን፤ ጋሪ ኦልድማን፤ ሲን ኮነሪ፤ሁውጅ ግራንት፤ራልፍ ፊነስ በሆሊውድ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ የእንግሊዝ ተዋናዮች ናቸው፡፡

በ“ሊንከለን” ፊልም ላይ የተወነው እንግሊዛዊው የፊልም ባለሙያ ዳንኤል ዴይ ሊውስ ለሶስተኛ ጊዜ በምርጥ ተዋናይነት የዘንድሮን ኦስካር በመውሰድ ሪከርድ ያስመዘገበ ሲሆን ባለፉት አምስት ዓመታት ከአምስት በላይ የብሪታኒያ ተዋናዮች የኦስካር ሽልማቶችን እንደወሰዱ ይታወቃል፡፡ 2013 ከገባ ወዲህ ክርስትያን ቤል፤ጃሬድ ሃሪስ፤ ዳንኤል ዴይ ሊውስ፤ ኢድሪስ ኤባ እና ሌሎች እንግሊዛውያን ተዋናዮች በምርጥ የሆሊውድ ፊልሞች ላይ በመሪ ተዋናይነት በመተወን ተወዳዳሪ አልተገኘላቸውም፡፡

Read 3080 times Last modified on Saturday, 30 March 2013 16:15