Saturday, 06 April 2013 14:13

“ነገም ሌላ ቀን ነው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በቀደም ቦሶቻችንና፣ ለቦስነት ‘መተካካትን በናፍቆት የሚጠብቁት’ ተስፈኞች ቂ…ቂ..ቂ… ችግራቸው “አብዛኛዎቹ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች አድር ባይ መሆናቸው…” እንደሆነ ሲጠቀስ ሰማን አይደል! ይቺን ታህል ማመንም አንድ ነገር ነው። እናማ… የቦተሊካ ታሪካችን በአብዛኛው የአድር ባይነት እንደሆነ ተመራምሮ ማረጋገጫ የሚሰጠን ተመራማሪ ይምጣልንማ!

እንዴት ሰነበታችሁሳ! “ማን ይሆን ትልቅ ሰው…” ተብሎ ተዘፍኗል፡፡ አዎ፣ አሁንም “ማን ይሆን ትልቅ ሰው…” እያልን እየጠየቅን ነው፡፡ ‘ትልቅነት’ በስልጣን፣ በገንዘብ፣ በዘር ምናምን ሳይሆን… ትልቅነት ‘ሰው በመሆን’ ማለታችን ነው፡፡ እናማ… የ‘ትልቅ ሰው’ ቁጥር እያነሰብን እየሄደ አሁንም እንደ ፈላስፋው በ‘ሰው’ በተሞላው መሀል ገበያ ውስጥ ፋኖሳችንን ይዘን ‘ትልቅ ሰው’ እያፈላለግን ነው፡፡ በሌላው ትከሻ ላይ ተረማማዶ ብርቱካኗን ከዛፉ ላይ ለመቀንጠስ የማይሞክር፣ ምንም ሳያውቅ “አውቃለሁ” ብሎ ‘ኤክስፓየር’ ባደረገ ካርድ (ቂ…ቂ…ቂ…) የማይታበይ፣ የገንዘብ መጨመር የአስተሳሰብ መጨመር የማይመስለው፣ ሀሳብን በሀሳብ መመለስ ሲያቅተው ሀሳብን በ“ወዮልህ! ብቻ አንተን አያድርገኝ!” ፉከራ ጭጭ ለማሰኘት የማይሞክር…‘ትልቅ ሰው’ እየናፈቀን ነው፡፡ ከዜግነት፣ ከጎጥ፣ ከጎሳ፣ ከአበልጅነት… ምናምን በፊት ‘ሰው መሆን’ እንደሚመጣ ያልጠፋውና ማህበራዊ ግንኙነቶቹን ቅጥያ ሳያበጅላቸው ‘ሰው በመሆን’ ብቻ የሚያራምድ ‘ትልቅ ሰው’ እያፈላለግን ነው፡፡

“ብትውልም መልካም ውለታ ስለ ሰው ብትንገላታ ከሌለህ ማን አለ ደጅህ …ኪስህ ነው የልብ ወዳጅህ” ተብሎም ተዘፍኗል፡፡ አዎ፣ ውለታ መሥራት የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ጎጂ ባህል ነገር እየሆነ የመጣበት ዘመን ላይ እየደረስን ነው፡፡ ሁሉ ነገር ከኪስ እብጠት ጋር የተያያዘበትና ገንዘብ ያለውን ሰው ቤት እንደ ቤተ መቅደስ ትልቁም፣ ትንሹም ሲሳለመው፣ ያጣ የነጣውን ሰው ቤት ዝንቦች እንኳን እየተጠየፉት…አለ አይደል…“ከሌለህ ማን አለ ደጅህ…” እያልን ነው፡፡ አድርባይነት “በረሀብ ከመሞት ይሻላል…” ተብሎ ‘እሬት፣ እሬት…’ እያለ የሚያዝ ባህሪ የብዙዎቻችን የህይወት መመሪያ እየሆነ ነው፡፡ ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በቀደም ቦሶቻችንና፣ ለቦስነት ‘መተካካትን በናፍቆት የሚጠብቁት’ ተስፈኞች ቂ…ቂ..ቂ… ችግራቸው “አብዛኛዎቹ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች አድር ባይ መሆናቸው…” እንደሆነ ሲጠቀስ ሰማን አይደል! ይቺን ታህል ማመንም አንድ ነገር ነው። እናማ… የቦተሊካ ታሪካችን በአብዛኛው የአድር ባይነት እንደሆነ ተመራምሮ ማረጋገጫ የሚሰጠን ተመራማሪ ይምጣልንማ! (ሀሳብ አለን…በየመድረኩ ባቡሩ ከሄደ በኋላ ጣቢያው የደረሳችሁና ቅልጥ ያላችሁ ‘አገር ወዳዶች’ ‘ለመምስል’ የምትሞክሩ፣ የተለመዱትን ‘ትራንስፎርሜሽን’ ‘ህዳሴ’ ምናምን የሚሏቸውን የ‘ጆከር’ ካርታ ሚና የሚጫወቱን ቃላት ሁሉ ነገር ውስጥ እየወሸቃችሁ የእነ ሌኒን ህጋዊ ወራሽ ለመሆን የሚቃጣችሁ…በተናገራችሁ ቁጥር “በቀደም ስብሰባ ላይ እኮ አድርባይ የተባሉት እነኚህ ናቸው…” እንደምንል እወቁልንማ! አሀ…አይደለም እኛ ቦሶቹ እንኳን ነቅተውባችኋላ!) እናላችሁ…በዘፈን ዘመን የሚሻገሩ መልእክቶች ይተላለፉበት በነበረ ጊዜ የተባሉ ነገሮች ዘንድሮም በትኩስነታቸው እያገለገሉን ነው፡፡ “ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ እንግዲህ ታከተኝ የሆዷን ጠይቆ ማን ባሰናበተኝ” ተብሎ ተዘፍኖ ነበር፡፡

ዘንድሮም ደጅ እየጠናንባቸው ያሉ ብዙ ነገሮች መአት ናቸው፡፡ ውሀ ሁለትና ሦስት ሳምንት እየጠፋብን አይደለም ለመለቃለቂያ ጉሮሮ ማርጠቢያ እያጣን “ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ…” እያልን ነው፣ የመብራቱ መቆራረጥ ነገር ከምንችለው በላይ እየሆነብን በየጊዜው እየተቃጠሉ እንደምንተካቸው አምፖሎች የማንተካውን አእምሯችንን ‘ፊዩዞች’ ሊያፈነዳብን ሆኖ ስጋት ስለገባን “ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ…” እያልን ነው፣ በስልከ ከማውራት ይልቅ ደብዳቤ መጻጻፍ የተሻለ የሚሆንበት ዘመን ‘እየተመለስን’ ነው እያልን፣ አንድ አረፍተ ነገር ለመጨረስ ሦስትና አራት ጊዜ ደጋግመን ለመደወል እየተገደድን “ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ…” እያልን ነው፣ ለልማት ተብሎ ተፈናቅለን ኮንዶሚኒየም ከገባን ረጅም ጊዜ ሆኖንም ውሀ፣ መብራት፣ ስልክ የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን የሚያስገባልን አጥተን የሞቁ መንደሮቻችን ከእነችግሮቻቸው እየናፈቁን “ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ…” እያልን ነው፡፡

እናላችሁ… “ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ…” የምንልባቸው ነገሮች እየበረከቱ “የሆዳቸውን ነግሮ የሚያሰናብተን…” አጥተን ቸግሮናል፡፡ በቴሌቪዥን ካሜራ ፊት የሚቀርቡ ሪፖርቶችንማ…አለ አይደል…ምንም እንኳን ነገሩ ለቀባሪ ማርዳት አይነት ቢሆንም…በቀደም እኮ ለመድረክ የሚቀርቡ ሪፖርቶች በአብዛኛው “መድረኩን ለማስደሰት” መሆኑን በአደባባይ ሰማን፡፡ እናማ የይገባኛል ጥያቄ የማይቀርብባቸውን ቁጥሮች እየደረደሩ “መድረኩን ለማስደሰት…” መሞከር “የተበላ ዕቁብ…” እየሆነ ነው፡፡ (እኔ የምለው…ግራ ስለገባኝ ነው፣ ቦሶቻችን እነኛን ነገሮች ካሉ በኋላ… “የከርሞ ሰው ይበለን…” ተባብለው ...በቃ ወደ የሞቁ ቤቶቻቸው ገቡ ማለት ነው!) ህይወት እምሻው የተባለች አሪፍ፣ በዘመኑ ቋንቋ “ደጋግሞ ይመችሽ” የምትባል ጸሀፊ ፌስቡክ ገጿ ላይ ያሰፈረቻት ነገር ትዝ አለችኝማ፡፡ ምን አለች መሰላችሁ… “እዚያ ጋር፤ ፖለቲከኞች ለስልጣናቸው ሲፈሩ ለህዝቡ ይሰራሉ፡፡

እዚህ ጋር፤ ፖለቲከኞች ለስልጣናቸው ሲፈሩ ህዝቡን ይሰሩለታል፡፡” አሪፍ አይደለች!…ለስልጣን መፍራት ምልክቶችን በቀደም አይተናል፡፡ ምን እንደሚደረግ ለማየት ‘ወንበራችን ጫፍ ተቀምጠን’ እየጠበቅን ነው፡፡ እናላችሁ “…ይቅርታ እለምናለሁ፣ ጥፋቴን አውቄያለሁ…” ተብሎም ተዘፍኗል፡፡ ይኸው በዚህ ዘመን ጥፋታችንን ተገንዝበን “…ይቅርታ እለምናለሁ፣ ጥፋቴን አውቄያለሁ…” የምንል ሰዎች መመናመን ብቻ ሳይሆን ጭርሱን ‘ብርቅዬ እንሰሳ’ ነገር እየሆንን ነው፡፡ ከላይ እስከታች ከምናለማው ይልቅ የምናጠፋው በበዛበት ዘመን “…ይቅርታ እለምናለሁ፣ ጥፋቴን አውቄያለሁ…” ማለት የ‘ትልቅነት’ ሳይሆን የ‘ትንሽነት’ ምልክት እየተደረገ ነገራችን ሁሉ የ‘ጨረባ ተዝካር’ ሆኖላችኋል፡፡ ላጠፉት ጥፋት፣ ለተሳሳቱት ስህተት ይቅርታ መጠየቅ በራስ የመተማመን ምልክት በነበረበት ዘመን “ጥፋት እንዳለብኝ ይቅርታ….” ተብሎም ተዘፍኗል፡፡

“እባክሽ ፍቅሬ ሆይ ተመከሪ ከይሉኝታ ጋራ ጡርን ፍሪ…” ተብሎም ተዘፍኗል፡ ‘ጡር መፍራት’ የሚባለው ነገር ጭራሽ ኢሚግሬሽን በር ላይ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ሳይሰለፍ፣ ማህበራዊ ጉዳይ በር ላይ ሳይጋፋ በራሱ ዘዴ ተሰዶ ከሄደ ሰነበተ፡፡ እናማ ጡርንፍሩ እያልን ነው፡ እናማ…ከአሥር ቁና ስምንቱን አስገብቶ ሁለቱን ብቻ ለራሱ እንደሚያስቀር ጭሰኛ ሊያዩን የሚሞክሩ ፖለቲከኞችንን “ጡርን ፍሩ…” እያልን ነው፡ መብታችንን ለማስከበር ሳይሆን እርጥባን ልንጠይቅ እንደመጣን ምንዱባን ሊቆጥሩን የሚዳዳቸውን አገልግሎት ሰጪዎችን “ጡርን ፍሩ…” እያልናቸው ነው፡፡ አራተኛ ዲቪዚዮንም፣ አንደኛ ዲቪዚዮንም ያሉና “ፍርዴ ይገለበጣል እንጂ፣ እኔ አልገለበጥም…” አይነት ነገር የሚሉንን ባለወንበሮችን (“ባለ ጊዜዎች…” የሚለውም አስፈላጊ ከሆነ ሊተካ ይችላል…) “ጡርን ፍሩ…” እያልናቸው ነው፡፡ (‘እየተማረርን’ እንደሆነ በበቀደሙ ስብሰባ ላይ ተነገረ አይደል! መማረር ወደ ማምረር የተለወጠ ዕለት…“አድማጮቻችን እዚህ ላይ የምትሉት ነገር ካለ የጽሁፍ መልእክት ላኩልንማ!” ቂ…ቂ…ቂ…) “የኑሮ መጠንሽን ከእኔ ጋራ አትለኪ በዘመዶችሽ ሀብት ይቅር አትመኪ“ ተብሎም ተዘፍኗል፡፡ በዘመዶቻችን ሀብትና ስልጣን የምንመካ ሰዎች እየበዛን ነው፡፡

“የእንትና አበ ልጅ ነኝ…” “ከእንትና ጋር ትውልዳችን አንድ መንደር ነው…” እየተባለ በ‘ቦተሊካውም’ ሆነ በሀብት…እንደ መኪና እሽቅድድም ‘ፖል ፖዚሽን’ ላይ ባሉ ዘመዶች የምንመካ በዝተናል፡፡ “በአንድ የሞባይል ጥሪ ልክ እንዳላገባህ…” የምንል በዘመዶቻችን ሻኛ የእኛን ስስ ትከሻ ለማንጎማለል የምንሞክር በዝተናል፡፡ እናማ…“እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር…” ተብሎም ተዘፍኗል፡፡ “ወደ መጣሁባት ምድር እስክመለስባት በክብር ሰውን ከማስደሰት በቀር አይወጣኝም ክፉ ነገር” ተብሎም ተዘፍኖ ነበር፡፡ ዘንድሮ አይደለም “…አይወጣኝም ክፉ ነገር…” ሊባል ቀርቶ የሰዉ አንደበት ሁሉ “ደግ አያናግርህ…” የሚል ግዝት ያለበት መስሏል፡፡

በመጨረሻም… “ከአገሩ የወጣ አገሩ እስኪመለስ ቢጭኑት አህያ ቢቀመጡት ፈረስ” ተብሎም ተዘፍኖ ነበር፣ አገር ጥሎ የሄደ ሆድ ይብሰዋልና! ይኸው የወጡትም ወጥተው ያልውጣነውም ሆድ እየባሰንም እዚሁ ሆነን “ቢጭኑን አህያ ቢቀመጡን ፈረስ…” ሆነናል፡፡ “…ጌታዬ አንድ አድርገን…” ተብሎም ተዘፍኗል፡፡ የሁሉ ችግሮቻችን መነሻና መድረሻ፣ የኋላ ቀርነታችን ‘ምስጢር’፣ የመናከሳችን… የመቧጨቃችን ምክንያት…አንድ አለመሆናችን ብቻ ነው፡፡ ግድግዳ ሙሉ ባንዲራ ከጀርባ ሰቅሎ ከሚደሰኰር…አለ አይደል… ለሮማንቲክ ኮሜዲ እንኳን የማይሆን የተጠና ዲስኩር እውነታችንን አይሸፍንልንም፡፡ አሁንም አንድ ያድርገን! የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የማይደረስበት የተራራ ጫፍ አይኖርም። የቅርብ አስርት ዓመታት ምስቅልቅላችንን ታሪክ የሚያደርግ ‘የተሻለ ነገ’ ይምጣልንማ፡፡ ደራሲው እንዳለው በእርግጥም “ነገም ሌላ ቀን ነው፡፡” ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5387 times