Monday, 08 April 2013 08:44

አባይ - የቀድሞውን ትውልድ ህልም ከዛሬው ጋር ያጨባበጠ!

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(3 votes)

በተግባር የተሳካለት የአሁኑ መንግስት ቢሆንም የቀድሞዎቹ መንግስታትም ሃሳቡና ፍላጐቱ እንደነበረባቸው የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ፡፡ ስለዚህም ኢህአዴግ “በሁሉም ዘርፍ የለውጡ ጀማሪና ፈፃሚ እኔ ነኝ” የሚል አመለካከቱን ቢያስተካክል ለራሱም ይበጃዋል - ሃሳቡን የሚደግፉ ወገኖችን የበለጠ ለማበራከት፡ ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ የተጀመረበትን ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በብሔራዊ ቴአትር በተሰናዳ ዝግጅት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ባቀረቡት ንግግር “በተለያየ ዘመን የአባይን ወንዝ ገድቦ ለልማት ለማዋል ጥቂት የማይባሉ የአገር መሪዎችና ኢትዮጵያውያን ጥረት ማድረጋቸውን ከእኔ በተሻለ የታሪክ ባለሙያዎች የምታውቁት እውነት ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረ በኋላ ሥራው ለኢትዮጵያውያን ስድስተኛው የስሜት ህዋሳችን ሆኗል፡፡ ማንም እንዲነካብን አንፈልግም፡፡ በዚህም ምክንያት በአገር ውስጥና በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያውያንን አስተባብሮናል፡፡ ይህንን ወርቃማ ዕድል ለመጠቀም ከዚህም በላይ በአንድነት መንቀሳቀስ አለብን” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ መድረክ ላይ በተለያዩ ዘመናት የተፃፉና ጭብጣቸውን አባይ ላይ ያደረጉ አስራ ስምንት ያህል ግጥሞችና የተለያዩ ጥበባዊ ዝግጅቶች ቀርበዋል፡፡

የብሔራዊና የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች ዘመናዊ የሙዚቃ ባንዶች በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበረ ሙዚቃዎች ባቀረቡበት ዝግጅት፤ ገጣሚ አያልነህ ሙላቱንና ጌትነት እንየውን ጨምሮ በርካታ አንጋፋና ወጣት ገጣምያን ግጥሞቻቸውን ለታዳሚው አንብበዋል፡፡ በእለቱ የቀረቡት አባይ ተኮር - ግጥሞች በተፃፉበት ዘመን በሦስት ተከፍለው ነበር የቀረቡት፡፡ “ጥቁር አባይ” በሚል ርእስ በ1967 ዓ.ም የተፃፈውና 38 አመታት ያስቆጠረው ግጥም ፤ የመጀመሪያውን ምድብ ሲወክል፤ “ዛሬ ልስልህ ነው” የተሰኘው በ1995 ዓ.ም ተፅፎ በአፀደ ውድነህ የቀረበው ግጥም ከ10 አመት በላይ ያስቆጠሩትን መርቷል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ ከተጀመረ በኋላ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ንግግር መነሻ ሆኗት “እኛው ነን” በሚል ርዕስ ገጣሚ ውዳላት ገዳሙ የፃፈችው ግጥም ደግሞ በሦስተኛው ምድብ ቀርቧል፡፡ በእለቱ ከቀረቡት ንግግሮች መካከል በተለይ የኢንጂነር ስመኘው በቀለ አጭር፤ ነገር ግን ብዙ ቁምነገርና መልዕክቶችን ያዘለ ነበር፡፡ የኢንጂነሩ ንግግር፤ አባይ የቀድሞ ኢትዮጵያዊያንን ምኞትና ህልም ከዛሬው ዘመን ጋር ማጨባበጡን፤ በሥርዓት የተመራና የተያያዘ ባይሆንም፣ ለአገር መልካም የመሥራትና የመመኘት ፍላጐት ከትላንት ወደ ዛሬ መሸጋገሩን፤ የብዙዎች ምኞት የነበረውን “ወርቃማ ዕድል” ያገኘው የዛሬው ኢትዮጵያዊ፣ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ለአገሩ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለበት መረዳቱን… የሚያመለክቱ ሃሳቦች ተንፀባርቆበታል፡፡

ከኢትዮጵያ የሚሌኒየም በዓል ጋር በተያያዘ የለውጥ ዘመን መጀመሩ በተበሰረ ማግስት ሥራው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፤ ወደ ታላቅነታችን መመለስ መጀመራችንን ማረጋገጫ ነው በሚለው ብዙዎች ቢስማሙም ነገሩን በጥርጣሬ የሚያዩትም አልጠፉም፡፡ ለልዩነቱ መፈጠር ምክንያት ከሚመስሉኝ ነገሮች አንዱ “በሁሉም ዘርፍ የለውጡ ጀማሪና ፈፃሚ እኔ ነኝ” የሚል አመለካከት የሚንፀባረቅበት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ ለዛሬው ህዳሴ መሠረት ለሆኑት ወገኖች እውቅና መንፈጉ ነው፡፡ አዲስ ነገር በቀደመ መሰረት ላይ እንደሚፈጠር ለማሳየት “የኢትዮጵያ ህዳሴ” የሚለው ሥያሜ ጥሩ ምሳሌ ይመሥለኛል፡፡ በዘመን አቆጣጠር፣ የራሷ ፊደል ባለቤት በመሆኗና በሌሎች ነገሮች ከብዙዎቹ የዓለማችን አገራት እንደምትለይ የሚነገርላት ኢትዮጵያ፤ የህዳሴ ዘመን የልማት ሥራዎቿም ተጨማሪ ትኩረትን ስቦላታል፡፡ ህዳሴው ለኢትዮጵያ አዲስ ዘመን ቢሆንም፤ ከ500 ዓመታት በፊት በአውሮፓ አገራት ታላላቅ ተግባራትና ስኬቶች የተመዘገበበት ዘመን ሆኖ እንዳለፈ ታሪክ ይጠቁማል፡፡ የ”ህዳሴ”ን ፅንሰ ሀሳብ ከሌሎች መውሰዳችንን ከተማመንን በህዳሴው ዘመን ለመተግበር ያቀድናቸው ተግባራትም እስካሁን ፈፅሞ ያልታሰቡ አዲስ ፈጠራዎች ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡

ከኢህአዴግ በፊት ኢትዮጵያዊያን በአባይ ወንዝ የመጠቀም ፍላጐትና አዝማሚያ እንደነበራቸው በ1967 ዓ.ም የተፃፈውና በብሔራዊ ቴአትር የተነበበው “ጥቁር አባይ” የተሰኘ ግጥም ያመለክታል፡፡ በአያልነህ ሙላቱ የተፃፈው ይሄ ግጥም የሌሎች ገጣምያን የግጥም ሥራዎች በተሰባሰቡበት “ፅጌረዳ ብዕር” በሚል ርእስ የታተመ መፅሐፍ ውስጥ ተካትቷል፡፡ እንዲህ ይላል - ብልሃትን ሕዝብ አወቀው፣ በትብብር ገጥሟል ጫንቃ፡፡ አንዱ ዶማ፣ አንዱ አካፋ፣ አንዱ ማጭድ፣ ድጅኖ ስበው፣ ያ… መዶሻ፣ ያ… መጥረቢያው፣ ጐፋጭ… ቀያሽ… ሆነው ቀርበው፣ የአንተን ብልጠት ካንተ ወስደው፣ ሊገዙህ ነው ገነጣጥለው፡፡ ለመስኖ ውሃ ለፍል ውሃ…፣ ለመብራት ሃይል ቦይ ከፋፍለው፣ ጥቁር አባይ ምን ይውጥህ…፣ እንደመጣ ተቀበለው…፡፡ የአባይ ወንዝን ገድቦ ለልማት የማዋል ፍላጐትና ምኞቱ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ አይመስልም፡፡ የጥንቱ መንግስታት ከጐረቤት አገራት ጋር ግጭት ሲገጥማቸው “አባይን እገድባለሁ” እያሉ ወንዙን እንደ ማስፈራርያ ተጠቅመውበታል፡፡ በተግባር የተሳካለት የአሁኑ መንግስት ቢሆንም የቀድሞዎቹ መንግስታትም ሃሳቡና ፍላጐቱ እንደነበረባቸው የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ፡፡

ስለዚህም ኢህአዴግ “በሁሉም ዘርፍ የለውጡ ጀማሪና ፈፃሚ እኔ ነኝ” የሚል አመለካከቱን ቢያስተካክል ለራሱም ይበጃዋል - ሃሳቡን የሚደግፉ ወገኖችን የበለጠ ለማበራከት፡፡ የቀድሞ ዘመን ኢትዮጵያዊያንና ነገሥታት የአባይ ወንዝን ለመገደብ አስበው ተግባራዊ ማድረግ እንዳልቻሉት ሁሉ፣ አውሮፓውያን የህዳሴያችን ዘመን እያሉ በሚጠሩት አስራ አምስተኛው ክ/ዘመን ሊዎናርዶ ዳቪንቺም በንድፍ ደረጃ ያዘጋጃቸው ብዙ አዳዲስ ሀሳቦች ነበሩት፡፡ እ.ኤ.አ በ1972 የታተመው “The Wonderful Story of Man” መፅሐፍ ውስጥ በዝርዝር እንደቀረበው፣ ሊዎናርዶ ዳቪንቺ ከስዕል ሥራው ውጭ በተለያዩ ዘርፎች ብዙ ጥናት ማድረጉን ያመለክታል፡፡ የአውሮፕላን ንድፍ ከሥራዎቹ አንዱ ነበር፡፡

ሊዎናርዶ ዳቪንቺ የአውሮፕላን ንድፍ ከሰራ ከ500 ዓመታት በኋላ ነበር ራይት ብራዘርስ አውሮፕላን ሰርተው የበረራ ሙከራ ማድረግ የቻሉት፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኢህአዴግ በአባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት የሚያስችለውን “ወርቃማ ዕድል” ያገኘው የቀደመው ትውልድ ለብዙ ዘመናት ሲያስበውና ሲያልመው በነበረው መሰረት ላይ ቆሞ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ፤ በህዳሴው ዘመን የተገኘውን ወርቃማ እድል ከግብ ለማድረስ በአንድነት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል እንዳሉት ሁሉ፤ የዛሬ ተስፋ ሰጪ ጅማሬዎቻችን መሰረታቸው በትላንት ውስጥ እንደሆነ ተገንዝበን ለትላንቱ እውቅና በመስጠት ለዕድገትና ሥልጣኔ እንትጋ፡፡ ሌሎች ላደረጉት ሙከራና ጥረት እውቅና መስጠትም በራሱ ሥልጣኔ መሆኑን ማወቅ ብልህነት ነው፡፡

Read 4054 times