Monday, 08 April 2013 08:54

ትኩረት የተነፈገው የርቀት ትምህርት ጉዳይ

Written by  ቦጋለ ንጋቱ (Bogale@gmailcom)
Rate this item
(2 votes)

የሀገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ስር ነቀል በሆነ መንገድ የተቀየረው ተግባር ተኮር በጥራትና ጠንካራ ምዘና ላይ የተመሰረተ ትምህርት በጥናትና ምርምር እንዲሁም ፈጠራ ላይ የተረባረበ ስልጠና በመጠናከሩ ነው” ቦጋለ ንጋቱ (Bogale@gmailcom) ለአንድ ሀገር ዕድገት መሠረታዊ ከሚባሉት ጉዳዮች አንዱ ትምህርት መሆኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬ በስልጣኔ የገሰገሱ የአለም ሀገራት የዕድገታቸው ዋነኛ መነሻ ትምህርት ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው፡፡ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ የአገልግሎት ፓኬጅም ሆነ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች በዘመናዊ አኳሃን እንዲመነደጉ ከተፈለገ በተግባር የታገዘ፣ ፈጠራና ክህሎትን የሚያዳብር ጥራት ያለው ትምህርት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ለብዙ የልማታዊ መንግስታት ሞዴል ከሚባሉት አንዷ የሆነችው ደቡብ ኮሪያ አራት አስርት አመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተአምራዊ ለውጥ ያመጣችው በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ጥንካሬ ነው፡፡

“Facts about Korea” (2011) የሚለው ዓመታዊ መጽሐፋቸው እንደሚያስረዳው፤ “የሀገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ስር ነቀል በሆነ መንገድ የተቀየረው ተግባር ተኮር በጥራትና ጠንካራ ምዘና ላይ የተመሰረተ ትምህርት በጥናትና ምርምር እንዲሁም ፈጠራ ላይ የተረባረበ ስልጠና በመጠናከሩ ነው” ኮሪያውያን ዛሬ በሞባይልና የICT ቴክኖሎጂዎች፣ በመርከብና መገጣጠሚያ ዕቃዎች፣ በአውቶሞቢልና መሠል ኢንዱስትሪ ዘርፎች የአለም ግንባር ቀደም አምራቾች ሆነዋል፡፡ የነብስ ወከፍ ገቢዋ 21ሺ ዶላር፤ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቷም 1 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ የደረሰው ከዚሁ ጠንካራ የትምህርትና ስልጠና ስርዓቷ ጋር በተያያዘ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የደቡብ ኮሪያን ስኬት ወይም የትምህርትና ስልጠና አፈፃፀም መዳሰስ አይደለም። ነገር ግን ኢህአዴግ ራሱ “አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ” እንደሚባለው “ሞዴላችን” የሚላት ሀገር ያለችበትን ገጽታ ለማሳየት ያህል ነው፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ለትምህርት ጥራትና ምዘና እንዲሁም ተግባራዊ ሂደት (Practical Senario) የምትሠጠው ትኩረት ከነኮሪያ በተቃራኒው መሆኑም ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት፤ 31 ዩኒቨርስቲ፣ 64 የግል ኮሌጆች፣ 183 የግልና የመንግስት ማሠልጠኛ ተቋማት እንዳሉ ይገልፃል፡፡ በርቀት ትምህርት ረገድም ከሰርተፍኬት እስከ ፒኤችዲ ድግሪ በሀገር ውስጥና በውጭ ተቋማት ደረጃም ይሰጣል፡፡ ማንም ግን ስለጥራቱና በተጨባጭ የትምህርት ስርዓቱ ስላመጣው ለውጥ ሲናገር አይደመጥም (በኢትዮጵያ ሁኔታ እየታየ ያለው ዕድገት ከትምህርትና ስልጠናው መለወጥ ጋር ተሳስሮ የሚነገር አለመሆኑን፣ አሁንም ከኋላቀር እርሻ አለመውጣታችንን፣ ለውጥ ቢኖርም ዛሬም መርፌ እንኳን ሀገር ቤት ያለመመረቱን ልብ ይሏል)፡፡ ከምንም በላይ አሳሳቢ እየሆነ ያለው “ማን እንደተማረ፣ ማን እንደተፈተነ” ሳይታወቅ ሰውን ሁሉ ድግሪ በድግሪ እያደረገ ያለው የርቀት ትምህርት ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት ለዘርፉ በቂ ትኩረት ያለመስጠቱ ማሳያ “የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጅን” በስድስት ጉልህ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ሲቀርጽ፣ የርቀት ትምህርት ጉዳይ ግምት ውስጥ አለመግባቱ ነው፡፡

የመምህራን ልማት መርሃግብር፣ የት/ቤት መሻሻል መርሃ ግብር፣ የስነዜጋና የስነምግባር መርሃግብር፣ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ መርሃ ግብር፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙንኬሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት የመስፋፋት መርሃ ግብር እንዲሁም፣ የአጠቃላይ ትምህርት አመራር፣ አሠራርና አደረጃጀት መርሃ ግብር መውጫ መግቢያቸው ሲታይ ስለ ርቀት ትምህርት ብዙም የተባለ ነገር የለም፡፡ ከዚህ አንፃር ፓኬጁ በተሟላ መንገዶች ተተግብሮ የረባ ውጤት ገና ባይመጣም የርቀት ትምህርት ጥራት ላይ ምንም አቅጣጫ ያለመቀመጡ የአደጋውን ከባድነት ያመለክታል፡፡ ዛሬ በአጭር ጊዜ ከመሬት ተነስተው ባለ ዶክትሬት የሆኑ ግለሰቦች እውን በተገቢው ተምረውና ተመዝነው ያመጡት ውጤት ነውን? ከፍ ያለ ገንዘብ በመክፈል፣ ፈተናንም ሆነ መመረቂያ ጽሑፍን በገንዘብ በማሰራት ባለድግሪ የሆነው ስንቱ ነው? (በራሳቸው ጥረት የተማሩትንና የሚማሩትን አይመለከትም)፡፡ ዘሪሁን በላይ (ስሙ የቀየረ) የተባለ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እንደሚገልፀው፣ “በውጭ ቋንቋ ሃሳባቸውን አሳክተው ሦስት ደቂቃ የማይናገሩ፣ አንድ ገጽ የተስተካከለ የእንግሊዝኛ ጽሑፍ የማይሰድሩ፣ አፍ በፈቱበት ቋንቋም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል ምሁራዊ የፈጠራ ስራ ሳያሳዩ ባለማስትሬትና ዶክትሬት ድግሪ የተባሉ በየደጃፋችን አሉ፡፡

በትክክለኛው መንገድ ፒኤችዲ ለማጠናቀቅ ከ18-22 ዓመታት በትምህርትና ምርምር ማሳለፍ እንደሚያስፈልግ እየታወቀ እነዚህን “የአቋራጭ ምሁራን” ለመቀበል አስቸጋሪ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡” ኢህአዴግ ወደስልጣን በመጠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት ከውጭ የተመለሱ ስደተኛ ምሁራን የትምህርት መረጃን “የአቻ ዕውቅና” የመስጠት ስራ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ያም ቀርቶ ግለሰቦች ብድግ ብለው “ፒኤችዲ ጨረስኩ” ወይም “ይሄው ማስትሬቴ” ሲሉ ያለምዘና መቀበል የዘርፉን ችግር ላይ መውደቅ አመላካች ነው፡፡ አንድ ሰሞን የርቀት ትምህርት መስጠት የሚችሉና የማይችሉ ተቋማት በሚል ስታንዳርድ ወጥቶ ፈቃድ መከልከልም ተጀምሮ ነበር፡፡ አሁን አሁን ይሄም የቀረ ይመስላል፡፡ የትምህርት ባለሙያዋ ወ/ሮ አወጣሽ ሃይሉ በሰጠችው አስተያየት፤ “የርቀት ትምህርትን ከሸቀጥ ንግድ እኩል ገንዘብ መሰብሰቢያ ማድረግ የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

መንግስትም ቢሆን አሁን ትኩረት የሚሰጠው ለሽፋን ስለሆነ በዝምታ ቢያልፈውም ወደፊት ሁሉም ነገር እንደሚጠብቅ እገምታለሁ” ብላለች፡፡ በዝምታ መታለፉን የማይቀበሉት ወገኖች ግን ሀብት ባክኖ፣ ሰዎች በጥራት ባልወሰዱት ትምህርት በሰርተፍኬት ተንበሽብሸው፣ ፈጠራና የተግባር ለውጥ ከተዳከመ በኋላ እንደ አዲስ ከመጀመር ለምን ከወዲሁ ትኩረት አይሰጥም ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ሁሉም የርቀት ትምህርት የሚሰጡ ተቋማት ችግር አለባቸው፡፡ ወይም የርቀት ትምህርት ከነአካቴው አያስፈልግም እያልኩ አይደለም፡፡ በቀጥታና በሙሉ ጊዜ ትምህርት ለመማር ዕድል ያላገኙ ዜጐችን ይጠቅማልና፡፡ ነገር ግን ለተማርኩ ባይ “ቀማኞች” በር ይከፍታልና ጥንቃቄም ያሻዋል፡፡ በሀገራችን “COC” የሚባለው የምዘና ስርዓት ከተጀመረ ወዲህ በሙሉ ቀን ትምህርት፣ ተግባር ተኮር በሆኑ የቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ከሰለጠኑ ዜጐች መካከል 32 በመቶው እንኳን ምዘናውን እንደማያልፉ ታዝበናል፡፡

(ይህ አሳሳቢ አፈፃፀም መሆኑን መንግስትም ገልጿል) እንግዲህ ይሄንኑ ስልጠና ከሙሉ ቀን ትምህርት አውጥቶ በርቀት ትምህርት ይሰጥ ቢባል የሚመጣውን ውጤት መገመት አያዳግትም፡፡ ሀገሪቱ በየአመቱ እስከ 300ሺ ዜጐችን ከዲፕሎማ በላይ ባሉ ደረጃዎች እያስመረቀች (በዚያው ልክ ስራ ባለመፈጠሩ ባልሠለጠኑበት ኮብልስቶንና ጥቃቅንና አነስተኛ አደረጃጀት መሰማራታቸውን ልብ ይሏል) ተጨማሪ 300ሺ ለማስመረቅ የርቀት ትምህርት የሚያስፈልጋት አይመስለኝም፡፡ ከዚያ ይልቅ በጐልማሶች ትምህርትና “ሁሉም ህፃናት ወደ ት/ቤት” የሚለውን መርህ ለማገዝ በታችኛው ደረጃ የርቀት ትምህርት ቢሰጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዲፕሎማ፣ ድግሪና ማስትሬት አልፎ ፒኤችዲ እንደአልባሳት ገዝቶ “ማጌጥ” ግን ሄዶ ሄዶ ይዞን ይጠፋል፡፡

ከወራት በፊት በሀገራችን በተካሄደው የዩኒስኮ የትምህርት ኮንፈረንስ ላይ፤ “የርቀት ትምህርት” ላይ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ተገልጿል፡፡ በትምህርት ጥራትም ሆነ በአጠቃላይ በሀገር ዕድገትና የስልጣኔ ሽግግር ላይ የሚፈጥረው አደጋም ተወስቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ሀገራት ዘርፉን ከጠንካራ ምዘና (በተለይም ፕላዝማና ስካይፒን ከመሰሉ የቀጥታ ውይይት ጋር በማስተላለፍ) እየተገበሩ ነው፡፡ በቴክኖሎጂ እያስተሳሰሩ ተግባር ተኮር እንዲሆንም ይሠራሉ፡፡ ወደዚህ ስርዓት ያልገቡት ደግሞ የርቀት ትምህርት እንዲቀንስና እንዳይበረታታ (ህንድ፣ ብራዚልና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት) ያደርጋሉ፡፡ ኢትዮጵያስ? ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

Read 3806 times