Monday, 15 April 2013 07:57

“ኢህአዴግ በርቱ ብሎናል…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“የመግባባት አንድነት ሠላም ማህበር” ከተቋቋመ ገና አራት ወሩ ቢሆንም፣ ኢህአዴግን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አነጋግሮ አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኘ ይናገራሉ፡፡ ህገመንግስቱ ለአገራችን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጅማሮ በቂ ነው የሚሉት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ብርሃኑ፤ የፍርድ ቤቶች ነፃነት፣ የፕሬስ ነፃነትና የማህበራት ነፃነት ስላልተከበረ የአገሪቱ ችግሮች እየተባባሱ መምጣታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በየጊዜው የሚከሰቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኙና በመንግስት እየተዳፈኑ፣ የኋላ ኋላ የሚፈነዱ ፈንጂዎች እየሆኑብን ነው የሚሉት አቶ ፋንታሁን፤ በቀልን በማስወገድና ችግሮችን በግልግል ዳኝነት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ይቻላል በሚል የተቋቋመ ማህበር መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ጋዜጠኛ ሠላም ገረመው “የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነትና የስልጣን ባለቤትነቱን እንዲጨብጥ እንሰራለን” ከሚሉት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ብርሃኑ ጋር ያደረገችው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ማህበሩ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያም ጭምር የሚሰራ ነው፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት የፀዳ ነው? ማህበራችን ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ነው፡፡ የአገራችንን ችግሮች ስንመለከት ከጊዜ ወደ ከጊዜ እየከፋ እጅግ በጣም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እየገባን ነው፡፡ ይህን ፈተና ለማሸነፍ ተገቢውን ያህል ሁነኛ ነገር አልተሠራም፤ ብዙም አልተጮኸም፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር በቀል ነው፡፡ በአገራችን የሚከሰቱ የመንግስት ለውጦች ላይ ሁሉ በቀል አለ፡፡ ሁሌም ደም መቃባት አለ፡፡ አሁን ላለው ገዢ ፓርቲም ይህንን ፍራቻችንን እንነግረዋለን፡፡ ሁላችንም የበቀል ስሜቱ ይብቃን ማለት አለብን፡፡ ሠላም እንምጣ እያልን ነው ወደ ተግባር ለመግባት የመጀመሪያ ስራዎቻችን የጀመርነው፡፡ የማህበሩ አላማ ምንድነው? ብዙ አሳሳቢ ነገሮችን እናያለን፡፡ የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ይሰዳዳሉ፡፡ የፍርድ ቤት ነፃነት ላይ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ጣል ገብነት አለ፡፡ የተለያዩ አይነት ግጭቶች በመንግስት ሃይል ይዳፈናሉ እንጂ መፍትሔ አያገኙም፡፡ ይሄ ያሳስበናል፡፡ እንዲህ አይነቱ አሳዛኝ ታሪክ እስከመቼ ይቀጥላል? ብለን እንሰጋለን፡፡

ሀገራችን በዓለም ህዝብ ፊት የምትታወቀው በእርስ በርስ ጦርነት፣ በረሃብ፣ በተመፅዋችነትና በስደት ነው፡፡ ከሶስተኛ ዓለም ሀገራት ከመጨረሻዎቹ ተርታ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ አሳዛኙ ታሪክ መቀየር አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በሶስት ሺህ አመታት ታሪክዋ ያጣችውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት ህዝቦች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተፈቃቅደውና ተዋደው፤ የፈቀዱትን የሀገር መሪ የመምረጥ፣ ካልፈቀዱም የማውረድ መብት የሚያገኙበት የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት እንዲረጋገጥ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያስፈልገናል፡፡ በአንድ ሀገር መልካም አስተዳደር እውን የሚሆነው፣ በግልፅነትና በተጠያቂነት መርህ ላይ የተመሰረተ የመንግስት አሰራር የሚሰፍነው፤ ሙስና፣ አድልዎና ወገንተኝነት በተጨባጭ መረጃና በህዝብ ነፃ ተሳትፎ እየተጋለጠ የሚወገደው፣ ለፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጠረው ዲሞክራሲያዊ መንግስት ሲኖር ነው፡፡ ለዚሁም ዲሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት ያስፈልጋል፡፡ የእኛ አገር ህገመንግስት፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጅማሮ በቂ ነው፡፡ ህግ አውጪው አካል ለምሳሌ ፓርላማው ህግ የማውጣት ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ህጎቹ ተግባራዊ የሚሆኑት በአስፈፃሚ አካል ነው - ለምሳሌ በጠቅላይ ሚኒስትርና ካቢኔ፡፡ ማንኛውም የመንግስት አካል ከህግ ውጭ እንዳይሰራ የመቆጣጠርና የህጎችን ትርጓሜ እየተነተነ የመዳኘት ስልጣን ደግሞ የፍርድ ቤቶች ነው፡፡

ህገ መንግስቱ በዚህ መልክ የህግ ተርጓሚነት ስልጣን የፍርድ ቤቶች እንደሆነ ቢገልፅም፤ የፍ/ቤቶች ነፃነት በአስፈፃሚው አካል ጣልቃ ገብተን ይጣሳል፡፡ ስለዚህ አስፈፃሚው ጣልቃ ገብነት ሊገታ ይገባዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አስፈፃሚው አካል፣ በፓርላማ (በህግ አውጪው) አካል እውነተኛ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፡፡ ፓርላማውም እንዲሁ በህዝብ ቁጥጥር ስር መሆን ይኖርበታል፡፡ በህዝብ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተወከለ መሆን አለበት፡፡ በየጊዜው የሚቀረፁ ህጎችና ፖሊሲዎች ህገ-መንግስቱን እንዳይሸራርፉ የህገ-መንግስቱ ገለልተኛ ጠባቂ አካል ያስፈልጋል፡፡ የእኛ አላማም ይህንን ለማስገንዘብ ነው፡፡ በሀገራችን መልካም አስተዳደር ሰፍኖና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ራዕያችን እውን ሆኖ ልማት እንዲስፋፋ፣ መሰረታዊ ችግሮች መቀረፍ አለባቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች ሙያዊ ብቃት፣ ተቋማዊ ጥንካሬ ተጎናፅፈው በነፃነትና በገለልተኛነት የሚሰሩበት ስርዓት መዘርጋት፣ ለዘላቂ ሰላምና ለአስተማማኝ ዲሞክራሲ ዋስትና ይሆናል፡፡ ገለልተኝነቱ የተረጋገጠ ጠንካራ የዳኝነት ስርዓት ካልተዘረጋ፣ ህገ መንግስትና ህግ በመውጣቱ ብቻ የሰላምና የዲሞክራሲ ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ የዳኝነት ስርዓት ፍትህን የማንገስ፣ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ ሰላምና መረጋጋትን የማስፈን ራዕይ ሊሰነቅ ይገባል፡፡ ይህን ለማስገንዘብ እንሰራለን፡፡ የሰላም የልማትና የዲሞክራሲ ግንባታ፣ በመንግስት የተናጠል ጥረት በተዓምር እውን ሊሆን አይችልም፡፡ ይቻላል ከተባለም የዴሞክራሲ ግንባታ ተዳፍኖ፣ በመቶ አመት ታሪክ ከድህነት ወደ መካከለኛ ገቢ ማሸጋገር ይቻል ይሆናል፡፡

ግን እዚያም የትም አይደርስም፡፡ ስለዚህ በመንግስት ጥረት ብቻ እውን ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ የህዝብ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ በነፃነት የሚንቀሳቀሱ ህዝባዊ ማህበራት፣ የሙያ ማህበራት (ለምሳሌ የመምህራን ማህበር) የንግድ ማህበር፣ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲያብቡ በህገመንግስቱ የተዘረዘሩ መብቶችን በተግባር ማስከበር አለበት፡፡ ግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዞ ሊቀበላቸው ይገባል፡፡ በተለይ የማህበራት አደረጃጀት ላይ የሚስፋፋ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ተወግዶ ማህበራት በነፃነት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ጣልቃ ገብነቱ ካልተገታ ግን ስርዓት አልበኝነት ይነግሳል፡፡ ግጭቶች ሁሌም እየተራገቡ ከድጡ ወደ ማጡ እየዘቀጡ የሚጓዙበት ጉልበት ያገኛሉ፡፡ የሀገራችን ችግርም ይሄው ነው፡፡ የተሻለ ለውጥ የማግኘት ጭላንጭል ከአመት አመት እየተዳፈነ ግጭቶች መፍትሄ ሳያገኙ ይቀጥላሉ፡፡ የሚከሰቱ ግጭቶች ሁሌም የሚረግቡት በዘላቂ መፍትሄ ሳይሆን በመንግስት ሃይል ነው፡፡ በመንግስት የሃይል የበላይነት ለጊዜው ግጭቶች ቢዳፈኑም፤ ከአደጋ አያላቅቀንም፡፡ የተዳፈነ እሳት እንደማለት ነው፤ ወይም ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ ይሆናል፡፡ ማህበሩ መንግስትን የሚተችበት ጉዳይ ምንድነው? ዘላለማዊ ገዢ መሆን የለበትም ነው የምንለው፡፡

ማንኛውም መንግስት ስልጣን መያዝ ያለበት ህዝብ በምርጫ ለአምስት ዓመት በኮንትራት ሲሰጠው ብቻ ነው፡፡ በህግ የተገደበ የኮንትራት ውክልና እንጂ ዘላለማዊ ስልጣን አይደለም፡፡ ዘላለማዊ ገዢ ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ ለሰላምና ለመግባባት የሚሰራ ማህበራችን የፍቅር ማህበር ነው፡፡ የፍቅር ምንጭ ፈጣሪ በመሆኑ፤ ማህበራችን በውሸት ለመቀባትና ስም ለመለጠፍ አልተፈጠረም፡፡ ነጩን ነጭ፤ ጥቁሩን ጥቁር እንላለን፡፡ እውነትና ሰላም የናፈቃት አገር ነች፡፡ በኢትዮጵያችን በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭቶች ከመጥበብ ይልቅ እየሰፉ፣ እልቂት ማየትና ዋይታ ማዳመጥ እንደ ባህል እየቆጠርን እንገኛለን፡፡ ጆሮም እውነትን ማዳመጥ የናፈቀበት ዘመን ውስጥ ነን፡፡ የሃሳብ ልዩነትን በመከባበርና በመቻቻል ከማስተናገድ ይልቅ፣ የጎሪጥ በመተያየትና ተለያይቶ በመጠቋቆር የጥቁር ህዝብ የአንድነት ታሪክንና አሻራን መናድ ያብቃ፡፡ እያለ ስርዓት አልበኝነት ውስጥ እየተዘፈቅን እንገኛለን፡፡

የቋንቋ፣ የብሄር፣ የሀይማኖት፣ የጎሳ ልዩነታችን የኢትዮጵያ ውበት መሆኑ በወረቀት ላይ ብቻ ሆነብን፡፡ ማህበራችን እነዚህን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በእውነት እንድንቆምና በአንድነት ለአንድነት እንድንነሳ፣ በመቻቻል ለመከባበር እንድንግባባ ይሰራል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምእራብ ለአንድነት ለእውነትና ለሰላም፣ ለፍቅርና ነፃነት እንስራ፤ ግጭትና ረሀብ፣ ፍርሃትና አድልዎ ከሀገራችን ይወገዱ፡፡ እውነት፤ ፍቅር እንደ ውሃ ጠማን፡፡ የእውነትና የፍቅር ፏፏቴዎች ይፍለቁ፡፡ በሰላምና በነፃነት እጦት ተራቆትን፡፡ የሠላምና እና የነፃነት ሸማ እንልበስ እያልን በአንድነት እናዚም፡፡ መጠቋቆርንና መጋጨትን ጥላቻንና በቀልን ከውስጣችን አስወግደን፣ እውነትንና ፍቅርን፣ ሰላምንና ነፃነትን በልባችን ለማሳደር የመግባባት አንድነት መድረክ እንፍጠር ስንል፣ መንግስት ህዝብ የጣለበትን አደራ ባለመወጣቱ እየተቸገርን ነው፡፡ በሃገሪቱ ውስጥ የታሰሩና በግዞት የሚገኙ የነፃው ፕሬስ ሰራተኞችና የፖለቲካ እስረኞች ምህረት ሊያገኙ እንዲቻል ከመንግስት አካላት ጋር እንዲሁም ከሽምግሌዎች ጋር በመወያየት እልባት ላይ ለመድረስ እንሰራለን፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ ስርዓት መፍጠር አለብን፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ መንግስት፣ በውጪ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሙያ ማህበራት፣ ምሑራንና ታዋቂ ግለሰቦች፣ በአጠቃላይ ሁሉንም ወገን የሚያሳትፍ፤ ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜም በቀል የሚያከትምበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት ብሔራዊ የምክክር እርቅ ጉባኤ እውን እንዲሆን እንሰራለን፡ ለዚህም በሮች እንዳይዘጉ፣ የተዘጉትም እንዲከፈቱ እናደርጋለን፡፡ የሠላም ሸንጎ ተመስርቶ የሰላም ጉባዔ እንዲካሄድ እናደርጋለን፡፡ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከአባት አርበኞች፣ ከጡረተኞች፣ ከምሁራን (ከመምህራን)፣ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከትራንስፖርት ሰራተኛው፣ ከገበሬው፣ ከሠራተኛው፤ ከጋዜጠኛው፤ ከአካል ጉዳተኞች፤ ከሴቶች፤ ከወጣቶች፣ ከተማሪዎች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች እና ከሌሎችም የተውጣጣ ሀገር አቀፍ ግጭት አስወጋጅ የሰላም ም/ቤት ሸንጎ እንመሰርታለን፡፡ “ሠላም ማህበር” ፍቅር፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር ለናፈቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመግባባት አንድነት መድረክ ይሆናል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተነጋግራችኋል? ከኢህአዴግስ? ጉዳዩን ስንጀምረው በማህበሩ አላማና ሃሳቦች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተነጋግረናል፡፡ ከገዢው ፓርቲና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተነጋግረናል፡፡ እኛ፣ “ተቃዋሚ ፓርቲ” ናቸው አልንም፡፡ ምክንያቱም “ተቃዋሚ” ሲባል ጠላትነት ይመስላል፡፡ ተፎካካሪ ናቸው፡፡ አነጋግረናቸዋል፡፡ የኢህአዴግ ፓርቲ አመራሮችንም አነጋግረናል፡፡ “መውጫ ቀዳዳ አጥተን አዘቅት ውስጥ ነበርን፤ እናንተ በመምጣታችሁ ደስ ብሎናል፤ በርቱ” ብለውናል፡፡ ሃሳባችንን ደግፈዋል፡፡

ምርጫ ቦርድም ተቀብሎን ጥሩ ምላሽ ሠጥቶናል፡፡ ኢህአዴግ … መንግስት አላማችሁን ደግፎታል? አላማችንን ተቀብሎት ነው ማህበሩን የመሠረትነው፡፡ ስለዚህ አሁንም በንግግራችን ወቅት ጥሩ ጅምሮች ነው እያየን ያለነው፡፡ በእርግጠኝነት ተቀብለውናል ማለት ይቻላል፡፡ የታሳሪ ጋዜጠኞች ጉዳይ እንዲሁም ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች ጉዳይ ላይ ሃሳባችሁ የሚሰምር ይመስላችኋል? መንግስትን እናውቀዋለን፡፡ ምንም እንኳ ማህበራችን ዕውቅና እንዲያገኝ ቢፈቅድም፣ ምንም እንኳ መንግስት ሃሳባችንን ቢጋራም፣ ለእሱ እስካልተመቸው ድረስ በተለያዩ ወገኖች ላይ የተለያየ ስያሜ እየለጠፈ፣ ሠዎችን በመወንጀል የማሰር ተግባሩን መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ይሄ ለእሱ ትክክል ነው፡፡ እኛ ደግሞ ይህንን እንቃወማለን፡፡ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል እንጂ ከአላማችን አንዱ፣ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ ከዳር ማድረስና በቀልና ቂምን ማስወገድ ነው፡፡

Read 2440 times