Saturday, 12 November 2011 07:23

ያልተፈታች እንቆቅልሽ - ኢትዮጵያ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ ህዝቦችዋም እንቆቅልሽ የሆነች ሀገር ነች፡፡ ሰሞኑን በየሃ ተገኘ የተባለው እና ወደፊትም በአርኪዎሎጂ ምሁራን የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች የእኛን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ታሪክ የሚቀይር አመለካከት እንደሚፈጥር እጠረጥራለሁ፡፡ በኢትዮጵያ፤ የራሷንም ሆነ የቀሪውን ዓለም የታሪክ ክፍተቶች የሚሞሉ ቅርሶች ከመሬት በታች እንደሚገኙ እገምታለሁ፡፡ 
የእኛ ምሁራን ብዙ ትኩረት አይሰጡትም፡፡ ሆኖም በርካታ የውጭ ምሁራን እኛ እንደ አፈ ታሪክ የምናየውን የንግስት ሳባ እና ንጉስ ሰለሞንን ታሪክ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ያጠኑታል፡፡ ይህን “አፈ ታሪክ” የሚደግፉ በርካታ የአርኬዎሎጂ ውጤቶች እንዳሉ የሚናገሩ ምሁራን፤ በብሉይ መፃህፍት የተጠቀሱትን የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪኮች፤ ከአሁኑ ፍልስጤም እስራኤል/ እንዲሁም እና ከሶሪያ አካባቢ አውጥተው ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ይፈልጋሉ፡፡ የብሉይ ዘመን ታሪክን የሚመረምሩ የታሪክ ምሁራን፤ የመፅሃፍ ቅዱስ አርኪዎሎጂ መረጃዎችን በመያዝ “ማክሲማሊስት” እና “ሚኒማሊስት” በሚል ጎራ ለይተው ይከራከራሉ፡፡ አንደኛው ወገን፤ “የምንሰማው ታሪክ ሙሉ በሙሉ አፈ ታሪክ ወይም በእጅጉ የተጋነነ ነው” ይላል፡፡ ሌላኛው፤ “እስከ ዛሬም የታሪኩን እውነተኛነት በበቂ የሚያረጋግጡ መረጃዎች አሉ፡፡ ወደ ፊትም ተጨማሪ መረጃዎች ይገኛሉ” በማለት ይሟገታሉ፡፡

በተለይ “ሚኒማሊስት” በሚል የሚጠቀሰው ወገን ትንታኔ፤ የዛሬዋን እስራኤል የታሪክ መሠረት ወደ ሌላ አቅጣጫ ስለሚወስድ፤ አዲስ የታሪክ እና የፖለቲካ ጎዳና ስለሚከፈት ይፈራል፡፡ ከመፅሃፍ ቅዱስ ተከፍሎ የተቀነሰ የታሪክ ክፍል አለ የሚል ጥርጣሬም አላቸው፡፡ ቤተ-እስራኤላዊያን ከኢትዮጵያ ምድር እንዲወጡ የተደረገው የታሪክን ዱካ ለማጥፋት ነው ብለው የሚያስቡም አሉ፡፡ እንደ ዳቬንቺ ኮድ ላሉ በርካታ ሥራዎች መነሻ የሆነውም ይኸው ክፍተት እና ጥርጣሬ ነው፡፡ 
ለምሣሌ አንድ ታሪክ ላጫውታችሁ፡፡ ከማል ሳሊቢ የተባሉ ሊባኖሳዊ የታሪክ ምሁር እ.ኤ.አ በ1985 ዓ.ም “አረባዊ ይሁዳ” የሚል ታሪክ አምጥተው ነበር፡፡ እርሳቸው በፃፉት «The Bible Came from Arabia´ የተባለ መጽሃፍ፤ “ከስደት በፊት የመጀመሪያው የአይሁዶች ርስተ ምድር የነበረው ሰሜናዊው የመን ነው” ብለዋል፡፡ በእርሳቸው አመለካከት፤ በብሉይ ኪዳን የሚጠቀሱት ታሪኮች ግብጽን፣ ኢትዮጵያን እና አረቢያን የሚጠቅሱ እንጂ የአሁኖቹን ሶሪያ፣ ፍልስጤም እና እስራኤል የሚገኙበትን አካባቢ የሚመለከት ታሪክ አይደለም፡፡ ተመሳሳይ ሀሳብ ያላቸው የስዑዲ እና የምዕራብ ሀገራት ምሁራን አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ከሦስት ዓመታት በፊት በየሃ አካባቢ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር በርናንድ ሊማን ናቸው፡፡
እንደ ከማል ሳሊቢ ዓይነት ሀሳብ ያላቸው ምሁራን አመለካከት “የተስፋይቱን ምድር” አሁን ካለችበት ሥፍራ ወደ ሌላ አካባቢ ስለሚወስድ ይፈራል፡፡ ታዲያ የሳሊቢ ጥናታዊ ሥራ፤ በእስራኤል የማይወደደውን ያህል፤ በሶሪያ እና በስዑዲም አይፈለግም፡፡ ኃይለኞቹ “ፂዮናዊ መስፋፋትን” ይቀሰቅሳል በሚል ይፈሩታል፡፡ የሳሊቢ መጽሀፍ በሶርያና ስዑዲ አረብያ በእነዚህ ሀገሮች እንዳይነበብ የህግ ማዕቀብ ተጥሎበታል፡፡ እንዲያውም በስዑዲ፤ የብሉይ ኪዳን ዘመን ታሪካዊ ስፍራዎች ሊሆኑ ይችላሉ በሚል በሳሊቢ የተጠቀሱት አካባቢዎች በስዑዲ አረብያ መንግስት መልካቸው እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡
ስዑዲ አረቢያም ሆነች ሶሪያ፤ ከእስራኤል ጋር ንትርክ ይጎትትብናል በሚል ይሰጋሉ፡፡ እስራኤል ደግሞ የህጋዊነት ጥያቄን ያስከትልብኛል የሚል ስጋት አላት፡፡ እውነቱ፤ ሁሉም የሳሊቢን ነገር እንደ ጦር ይፈሩታል፡፡ በዚህ ሁሉ የታሪክ “ጦርነት”፤ ኢትዮጵያ ማጠንጠኛ የሚሆን ድርሻ ያዛለች፡፡ ታዲያ ከሰሞኑ በየሃ አዲስ የታሪክ ቅርስ የመገኘቱን ዜና ስሰማ የታሪክ ዶሴ ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሄሮደተስን አገኘሁ፡፡ ከዚህ የግሪክ የታሪክ ፀሃፊ ጋር በአጋጣሚ ተገናኝቼ፤ ያሰብኩትን ትቼ ወዳላሰብኩት ጎዳና ገባሁ፡፡ ዋናው ጨዋታ ነው ብዬ ከሄሮደተስ ጋር ቆየሁ፡፡ እናም ሄሮደተስ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ከፃፈልን በርካታ ነገሮች ለጨዋታ የሚመቸውን መርጬ ወደ ናንተ መጣሁ፡፡
ሄሮደተስ «The Histories of Herodotus of Halicarnassus´ የተሰኘ ርዕስ በተሰጠው ሦስተኛው መፅሃፍ፤ “አባይ ከሊቢያ ይነሳል” ይላል፡፡ ታዲያ በዚህ የተሳሳተ መረጃ ያልበረገገ ሰው በርካታ ትምህርታዊ እና አዝናኝ ታሪኮች ከመፅሃፉ ይገኛል፡፡ ጋሽ ስብሀት ገ/ እግዚአብሄር፤ ሌኒንን ጠቅሶ ልበል?፤ “መዝናናት፣ መዝናናት፣ አሁንም መዝናናት” እንዳለ አዝናኝ በሆኑልኝ ታሪኮች ተመስጬ ንባቤን ቀጠልኩ፡፡ ታዲያ ከእነዚህ መሳጭ ታሪኮች አንዱን ባጫውታችሁ ምን ይላችኋል?
ሄሮደተስ ከሚተርክልን በርካታ አስደናቂ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ንጉስ ካምቢሰስ
ግዛት በማስፋፋት ስራ የተጠመደው የፋርስ ንጉስ ካምቢሰስ፤ ከራሱ ጋር ብዙ ከመከረ በኋላ ሦስት ዘመቻዎችን ለማድረግ እቅድ ነደፈ ይላል፤ ሄሮደተስ፡፡ አንደኛው በካርቴዢያውያን፤ ሁለተኛው በአሞናውያን፤ ሦስተኛው ደግሞ ሄሮደተስ “የረጅም ዘመን ዕድሜ ባለቤቶች፤ በዓለም አቻ የሌላቸው መልከ መልካሞች” ወዘተ እያለ በሚጠቅሳቸው ኢትዮጵያውያን ላይ የታቀደ ዘመቻ ነበር፡፡
ሄሮደተስ እንዲህ ይላል፤ ኢትዮጵያውያን የደቡብ ባህር ድንበርተኛ በሆነ እና የሊቢያ ግዛት አካል በሆነ አካባቢ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ካምቢሰስ አውጥቶ አውርዶ ካርቴዢያውንን የሚወጋ ጦር ለመላክ ወሰነ፡፡ ግማሹን ጦሩን ደግሞ አሞናውያንን ሰደደ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ደግሞ ሰላዮቹን ላከ፡፡”
የላካቸው ሰላዮች “ከፋርስ ንጉስ ስጦታ ይዘን መጣን” በሚል ወደ ኢትዮጰያ ገብተው፤ በሀገሪቱ የሚያዩትን ነገር ሁሉ ልቅም አድርገው መዝግበው እንዲመጡ፤ በተለይም “የፀሐይ ገበታ” የሚባለው የመሰዊያ ስፍራ የት አካባቢ እንደሆነ አጥርተው እንዲመለሱ ሰላዮቹን ላከ፡፡
እንደሚባለው ከሆነ፤ “የፀሐይ ገበታ” በከተማዋ ዳርቻ ባለ አንድ መስክ የሚገኝና፤ ገንዳ ሙሉ የተቀቀለ ሥጋ ያለበት ሥፍራ ነው፡፡ ታዲያ የከተማው ሹም ዘወትር ማታ ማታ ገበታው ሙሉ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ እናም ቀኑን ሙሉ ሥጋ ያማረው ሰው ወደ “ፀሐይ ገበታ” እየሄደ እስኪበቃው ይበላል፡፡ ታዲያ የሀገሩ ሰዎች “ምግቡ የሚፈልቀው ከመሬት ነው” ይላሉ፡፡
ካምቢሰስ ሰላዮቹን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ከወሰነ በኋላ ኤሌፋንታይን በተባለ ሥፍራ ወዳሉት አይሲትዮፋጊዎች ሰው ላከ፡፡ እነርሱ የኢትዮጵያውያንን ቋንቋ መናገር የሚችሉ ናቸው፡፡ ወደነሱ ሰው ከላከ በኋላ ጦሩን ወደካርቴዢያ እንዲዘምት አዘዘ፡፡ ሆኖም ወደካርቴዢያ እንዲዘምቱ ያዘዛቸው ፊንቃውያን፤ “እኛ ግዝት ስላለብን ካርተዢያውያንን ለመውጋት አንዘምትም፡፡ በራሳችን ልጆች ላይ ጦርነት አንከፍትም” አሉት፡፡ ካንቢሰስ ፊንቃውያንን አስገድዶ ለማዝመት ወይም ለመውጋት አልፈለገም፡፡ ምክንያቱም እነሱ ወደው - ፈቅደው ለፋርስ የገበሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ ካምቢሰስ የሚያካሂደው የባህር ላይ ውጊያ በአብዛኛው በፊንቃውያን ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ፤ ካርቴዢያውያን፤ “ግዝት አለብን” በማለት ከጦርነትና በፋርስ ባርነት ከመውደቅ ዳኑ፡፡ ከፊንቃውያን ሌላ ሲፕራውያን ወደው ፈቅደው ከፋርስ ጦር ጋር ተቀላቅለዋል፡፡ ከፋርስ ወግነው በግብፅ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ወደ ኤሌፋንታይን የላካቸው ሰዎች መልዕክታቸውን አድርሰው አይሲቲዮፋጊዎችን ይዘው መጡ፡፡ ወዲያው ካምቢሰስ እቅዱን ነገራቸው፡፡ ከነገራቸውም በኋላ ሀምራዊ ካባ፣ የወርቅ የአንገት ሀብል እና አምባር፣ ሳጥን ከርቤ እና አንድ ደንበጃን ወይን ስጦታ ብሎ አስይዞ ወደ ኢትዮጵያ ላካቸው፡፡ ይህ የልዑካን ቡድን በተላከበት አገር የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ወንዶች ረጃጅምና በዓለም ላይ ወደር የሌላቸው መልከ መልካሞች መሆናቸው ይነገራል፡፡ በአድራጎታቸውም ከሌላው የሰው ዘር በሙሉ የተለዩ ናቸው፡፡ በእጅጉ ልዩ የሚያደርጋቸው ደግሞ ንጉሳቸውን የሚመርጡበት ሥርዓት ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ካሉት ሰዎች በጠቅላላ በጣም ረጅም እና የርዝመቱንም የሚያህል ጠንካራ የሆነውን ሰው መርጠው እንዲገዛቸው ያነግሳሉ፡፡ አይሲቲዮፋጊዎች ኢትዮጵያ እንደ ደረሱ ይዘውት የመጡትን ስጦታ ለንጉሱ አስረከቡ፡፡ ስጦታውን ሲያስረክቡም “የእርሶ ታማኝ ወዳጅ እና አጋር ለመሆን የሚጓጓው የፋርሱ ንጉስ ካምቢሰስ፤ በቤትዎ ተገኝተን እርሶን እንድናነጋግር ልኮናል፡፡ ይሄንም የሚያዩትን ስጦታ ልኳል፡፡ እነዚህ የተላኩ እጅ መንሻ ስጦታዎች እርሱ አብዝቶ የሚወዳቸው ነገሮች ናቸው” አሉት፡፡
በዚህ ጊዜ፤ ሰዎቹ ለስለላ መምጣታቸውን የተረዱት ኢትዮጵያውያን እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “የፋርሱ ንጉስ ይህንን ስጦታ አስይዞ ወደኔ የላካችሁ፤ የኔ የልብ ወዳጅ እና አጋር ለመሆን ፈልጎ አይደለም፡፡ እናንተም እንዲህ ነን ብላችሁ ስለራሳችሁ የተናገራችሁት ቃል እውነት አይደለም፡፡ እናንተ ግዛቴን ልትሰልሉ የመጣችሁ ሰላዮች ናችሁ፡፡ ንጉሳችሁም እውነተኛ ሰው አይደለም፡፡ እውነተኛ ሰው ቢሆን ኖሮ የእርሱ ያልሆነውን ግዛት የእርሱ ለማድረግ አይቋምጥም ነበር፡፡ አንዳች ባልበደለው ህዝብ ላይ ባርነትን ለመጫን አይከጅልም ነበር፡፡ እናም ለንጉሳችሁ ይህንን ቀስት ስጡትና እንዲህ በሉት፤ “የኢትዮጵያው ንጉስ እንዲህ ብሎሃል በሉት፡፡ ፋርሶች ይህን ጠንካራ ቀስት በቀላሉ መሳል፣ ከቻሉ፤ የፋርሱ ንጉስ ጠንካራ ሰራዊቱን ይዞ ረጅም ዕድሜ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ለመውጋት ይምጣ፡፡ እስከዚያው ግን፤ የራሳቸው ያልሆነ ግዛት መሻት ከኢትዮጵያውያን ልብ ያራቀ ፈጣሪን አመስግን በሉት” አለ፡፡ ይህንም ብሎ ቀስቱን ወጠረውና ለመልዕክተኞቹ ሰጣቸው፡፡ ከዚያም በስጦታ የተላከለትን ካባ አነሳ፡፡ “ይሄ ምንድን ነው?” አላቸው፡፡ “ከምንስ የተሰራ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም በእውነት መልስ ሰጡ፡፡ ወይንጠጅ ሐምራዊ ቀለም የያዘው ለምን እንደሆነ፤ የቀለም አነካከሩም እንዴት እንደሆነ አስረዱት፡፡ በዚያ ጊዜ፤ንጉሱ እነኝህ ፋርሶች እንደ ልብሳቸው አሳሳቾች ናቸው አለ፡፡ ቀጥሎም አምባርና ሐብሉን አንስቶ ጠየቃቸው፡፡ አይሲቲዮፋጊዎችም መለሱለት፡፡ “የሀገራችን ሰው ጌጣጌጦች ናቸው” አሉት፡፡ በዚያ ጊዜ ንጉሱ ሳቀ፡፡ የሰጡትንም ሀብል እንደ ሰንሰለት ስለቆጠረው “ኢትዮጵያውያን ከዚህ በእጅጉ የሚጠነክር ሰንሰለት አላቸው” አላቸው፡፡ ሦስተኛም ስለከርቤው ጠየቃቸው፡፡ ከርቤው እንዴት እንደ ተሰራ ከነገሩት በኋላ፣ ስለ ካባው እንደ ተናገረው ተመሳሳይ መልስ ሰጣቸው፡፡ በመጨረሻ ወደ ወይኑ ዞረ፡፡ እንዴት እንደሚሰራም ጠይቆ ከተረዳ በኋላ ከወይኑ ጎንጨት አደረገ፡፡ ወይኑም አመረቃው፡፡ ከዚያም የፋርሱ ንጉስ ምን መብላት እንደሚወድ ጠየቃቸው፡፡ የሀገራቸው ረጅም ዘመን ኖረ ሲባል ስንት ዘመን እንደሚኖር ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ንጉሱ የሚበላው ዳቦ እንደሆነ፣ ዳቦውም ከምን ዓይነት ስንዴ እንደሚጋገር ነገሩት፡፡ አክለውም ከፋርሳውያን መካከል ረጅም ዘመን ኖረ የሚባለው ሰው ዕድሜው 80 ዓመት መሆኑን ነገሩት፡፡ እርሱም፤ በዚህ ነገር አትደነቁ እንዲህ ያለ ቆሻሻ ነገር የሚበላ ሰው ዕድሜው - ማጠሩ አያስገርምም፡፡ እንዴውም ይሄንን የሚያመረቃ ወይን ባይቀምሱ ኖሮ ዕድሜያቸው 80ም ባልደረሰ ነበር፡፡ ሆኖም በወይን ጠመቃው ፋርሶች ኢትዮጵያውያንን ይልቃሉ አላቸው፡፡ አይሲቲዮፋጊዎችም የንጉሱን ቃል ከሰሙ በኋላ እነርሱም በፈንታቸው ንጉሱን ይጠይቁት ጀመር፡፡ የኢትዮጵያ ነገስታት ዕድሜያቸው ስንት ዘመን ይዘልቃል አሉት? ህዝቡስ የሚበላው ምንድን ነው? ሲሉ ጠየቁት፡፡ የህዝቡ ዕድሜው እስከ 100 እና 120 እንደሚዘልቅ፤ አንዳንድ ሰዎችም ከዚህ በላይ እንደሚኖሩ፤ የሚበሉትም የተቀቀለ ሥጋ እንደሆነ፤ ከወተት በቀር ሌላ ነገር እንደማይጠጡ ነገራቸው፡፡ አይሲቲዮፋጊዎች በኢትዮጵያውያን የዕድሜ ዘመን ርዝማኔ ተደነቁ፡፡ ከዚያም ወደ አንድ ምንጭ ወሰዳቸው፡፡ በዚያ ምንጭ ውሃ ገብተውም ሲታጠቡ ገላቸው ወዛም እና ለስላሳ ሆነ፡፡ ገላቸው በዘይት ገንዳ ውስጥ ተነክረው እንደ ወጡ ሆነ፡፡ መኣዛቸውም እንደ አበባ መኣዛ ሆነ፡፡ ኢትዮጵያውያን ውሃው የተለየ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ውሃ እንደ ላባ ክብደቱ የቀለለ ነገር ቢገባ በውሃው ላይ አይንሳፈፍም፡፡ እንጨት እና ላባ በአንድነት ቢጥሉበት ሁለቱም ቁልቁል ወርደው ከመሬት ያርፋሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስለ ውሃው ያሉት ይህ ነገር ትክክል ከሆነ፤ የኢትዮጵያውያን ዕድሜ መርዘም ምስጢሩ፤ በዚህ ውሃ መታጠባቸው መሆን አለበት፡፡ መልዕክተኞቹ ከውሃው እንደ ወጡ ንጉሱ ወደ እስር ቤት ወሰዳቸው፡፡ በእስር ቤቱም ያሉ እስረኞች በጠቅላላ በወርቅ ሰንሰለት የታሰሩ መሆናቸውን አዩ፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ ውድ ነገር የሚታየው መዳብ ነው - ብዙ ስለሌለ፡፡ መልዕክተኞቹ እስር ቤቱን ካዩ በኋላ “የፀሐይ ገበታ” ወደ ሚባለው ቦታ ሄዱ፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያውያንን የሬሳ ግንዘት ጥበብ አዩ፡፡ ኢትዮጵያውያን የሬሳ ሳጥን የሚሰሩት ከክሪስታል ነው፡፡ አስከሬኑን እንደ ግብፃውያን አድርገው ካደረቁት በኋላ በጂብሰም እንዲሸፈን ይደርጉታል፡፡ በዚያ ላይ በህይወት ያለ ሰው እስኪመስል ድረስ በስዕል ያስጌጡታል፡፡ ከዚያም በአስክሬኑ ልክ ከተቦረቦረ የክሪስታል አምድ ውስጥ አስገብተው እንዲቀመጥ ያደርጉታል፡፡ በኢትዮጵያ ክሪስታል በሰፊው እየተቆፈረ ይወጣል፡፡ አሰራሩም ቀላል ነው፡፡ አስክሬኑም በተቦረቦረ አምድ ውስጥ ተሰክቶ እንደ ተጋደመ ይታያል፡፡ መጥፎ ጠረን ግን የለውም፡፡ ለዓይንም የሚያስቀይም ነገር የለውም፡፡ የአስከሬኑ አካልም ራቁቱን እንደሆነ ይታያል፡፡ የሟቹ የቅርብ ዘመድ የሆነ ሰው በክሪስታል አምድ የገባውን የሟች አስክሬን ወስዶ ለአንድ ዓመት ያህል በቤቱ እንዲቀመጥ ያደርጋል፡፡ ሁሌም ከሚበሉት ፍራፍሬ የመጀመሪያውን ለሟቹ ይሰጣሉ፡፡ መስዋዕት በማድረግም ያከብሩታል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ አምዱን ከቤት በማውጣት በከተማዋ አቅራቢያ ካለ ሥፍራ ወስደው ያቆሙታል፡፡
እንግዲህ ሰላዮቹ ይሄን ሁሉ ነገር ካዩ በኋላ ወደ ግብፅ ተመለሱ፡፡ ለካምቢሰስም ያዩትን ሁሉ ነገሩት፡፡ ካምቢሰስም በተናገሩት ነገር በእጅጉ ተናደደ፡፡ በንዴት ጦፎም ለሰራዊቱ የሚበቃ ስንቅ እንኳን ሳይዝ፤ ዘመቻው የሩቅ አገር ዘመቻ መሆኑንም ፈፅሞ ሳያስብ፤ ለዘመቻ ተነሳ፡፡ ፈፅሞ አበደ፡፡ አይሲቲዮፋጊ የሚነግሩትን ነገር ሳይጨርሱ አቅሉን እንደሳተ እብድ ለዘመቻ ተነሳ፡፡ በሰራዊቱ ውስጥ የነበሩ ግሪካውያንን ባሉበት ጸንተው እንዲጠብቁ ትዕዛዝ ሰጥቶ ከሀገሩ እርሱን ተከትለው የወጡትን የሰራዊቱ አባላት ብቻ ይዞ ተነሳ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሲጓዝ ቴቤዝ የተባለች ሀገር ደረሰ፡፡ ቴቤዝ ሲደርስ ከያዘው ሰራዊት አብዛኛውን ከፍሎ አሞናውያንን እንዲወጉ፤ ህዝቡንም ምርኮ አድርገው እንዲያመጡ፤ ጁፒተር የተባለውንም ጣዖት እንዲያቃጥሉ አዘዘ፡፡ እርሱ ግን ቀሪውን ሰራዊት ይዞ ኢትዮጵያውያንን ለመውጋት ገሰገሰ፡፡ ሆኖም ከጉዞው አንድ አምስተኛ የሚሆን ርቀት እንኳን ሳይሸፍን፤ የሰራዊቱ ስንቅ አለቀ፡፡ በዚያ ጊዜ ወታደሩ አውሬ መብላት ጀመረ፡፡ ቆይቶም አውሬው ችግር ሆነ፡፡ ካምቢሰስ የሆነውን ሁሉ አይቶ፤ መሳሳቱን ተረድቶ፤ ሰራዊቱን ይዞ ቢመለስ ኖሮ ትልቅ ጥበብ በሆነለት ነበር፡፡ የመጀመሪያውን ስህተት ማረም በቻለም ነበር፡፡ ነገር ግን እርሱ አቅሉን ስለሳተ በዘመቻው ቀጠለ፡፡ ሰራዊቱም ምድር ያፈራችውን ነገር ሳይመርጡ ሳሩንም - ቅጠሉንም እየበሉ ህይወታቸውን ለማየት ሞከሩ፡፡ ሆኖም ወደ በረሃው ሲገቡ ብዙዎቹ በመምጣታቸው ተፀፀቱ፡፡ ቢቸግራቸው፤ አስሩ ሆነው ዕጣ እያወጡ፤ እጣ የወጣበትን ሰው አርደው በመብላት ህይወታቸውን ለማቆየት ተጣጣሩ፡፡ ካምቢሰስ ይህን ሲሰማ በሰራዊቱ ውስጥ ባየው የ”በላዔ ሰብእ” ተግባር ደንግጦ፤ በኢትዮጵያ ላይ ያቀደውን ዘመቻ በመተው፤ በመጣበት መንገድ ተመለሰ፡፡ እጅግ ብዙ ሰው በሞት አጥቶ ቴቤዝ ገባ፡፡ ከቴቤዝም ቁልቁል ወደ ሜንፊስ ወርዶ፤ በዚያ የነበሩትን ግሪኮች በሙሉ ወደ ሀገራቸው እንዲሄዱ አሰናበተ፡፡ የኢትዮጵያም ዘመቻ በዚሁ ቀረ፡፡” ይላል ሄሮደተስ፡፡ እሱ ይቀጥላል፡፡ እኛ ግን በዚሁ እናብቃ፡፡ መልካም ሣምንት፡፡

 

Read 5490 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 07:29