Monday, 15 April 2013 09:20

ስትሮክን መከላከል ሳይከሰት በፊት ነው!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

በየዓመቱ 6 ሚሊዮን ሰዎች ለህልፈት ይዳረጋሉ መንስኤው ምንድነው?ህክምናውስ?

የቀድሞዋ የእንግሊዝ ጠ/ሚ ማርጋሬት ታቸር ህይወታቸውን ያጡት በስትሮክ ነው

ከሰውነታችን ወደ አንጐላችን ህዋሣት የሚሰራጨው ደም በተለያዩ ምክንያቶች ሲቀንስ ወይም ሲዛባ በተወሰነ የአንጐላችን ክፍል ተግባር ላይ መስተጓጐልን ያስከትላል፡፡ ይህ በድንገተኛ የአንጐል የደም ስርጭት መዛባት ሳቢያ የሚከሰተው ድንገተኛ በሽታ (celebeler vascular Accident) ወይም ስትሮክ በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡ የአለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በዓለማችን በየዓመቱ 20 ሚሊዮን ሰዎች በዚሁ በሽታ ይጠቃሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ስድስት ሚሊዮን የሚደርሱት በስትሮክ አማካኝነት ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ በስትሮክ የተጠቁ ሰዎች በአብዛኛው ህይወታቸው የሚያልፈው ችግሩ ካጋጠማቸው የመጀመሪያ ቀን አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ድረስ መሆኑንም መረጃው ይጠቁማል፡፡

“አይረን ሌዲ” በሚል ስያሜ የሚታወቁትና እ.ኤ.አ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው እስከለቀቁበት 1990 ዓ.ም ድረስ እንግሊዝን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ማርጋሬት ታቸር፤ ባለፈው ሰኞ በስትሮክ ሣቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የአንጐል የደም ስር በሽታ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ስትሮክ፤ በአደጉት አገራት ለሞት መንስኤነት ከሚጠቀሱት የልብ ህመምና የካንሰር በሽታዎች ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ቀደም ሲል በሽታው ዕድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ በብዛት ይታይ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሽታው ወጣቶችም ላይ መከሰቱንና ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ በብዛት እንደሚታይ ይገልፃል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በዘር ውስጥ ቀደም ሲል በስትሮክ የተጠቃ ሰው ካለ ለበሽታው መከሰት አስተዋጽኦ እንዳለውም መረጃው ያመለክታል፡፡

በዓለማችን በስፋት የሚታየው የስትሮክ አይነት፣ በአንጐል ውስጥ የሚገኘው የደም ስር ውስጣዊ ግድግዳ በመጥበቡ ምክንያት የሚከሰት ሲሆን ይሄ አይነቱ ስትሮክ በአገራችንም ሪራዥር እንደሚከሰትና ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በአገራችን በበሽታው ዙርያ የተደረጉ ጥናቶች ባይኖሩም፣ የበሽታው መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሄዱንና ለብዙዎች ህልፈት መንስኤ እየሆነ መምጣቱን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር አብርሃም ገዛኸኝ ይናገራሉ። በአንጐል ውስጥ የሚገኘው የደም ሥር በመጥበቡ ምክንያት ከሚከሰተው የስትሮክ በሽታ በተጨማሪ በአንጐል ደም ሥር መድማት ሳቢያ የሚመጣ የስትሮክ አይነት መኖሩንና ችግሩ በአገራችን በስፋት እንደሚታይ ሃኪሙ ገልፀዋል፡፡ ስትሮክ የሚከሰተው የተወሰነ የአንጐላችን ክፍል ደም ቅዳ (Arteries) የደም ሥር ውስጣዊ ስፋቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጠብ፣ አንጐላችን በበቂ ሁኔታ ኦክሲጅንም ሆነ ጉሉኮስ ለማግኘት ባለመቻሉ የተነሳ በአንጐል ሕዋሳት ላይ ጉዳት ሲደርስባቸው ነው።

ችግሩ የሚከሰተው ድንገትና ሳይታሰብ በመሆኑም የሚያስከትለው ጉዳት አስከፊ የሚሆንበት አጋጣሚ ከፍተኛ ነው፡፡ ድንገትና ሳይታሰብ ይከሰታል ሲባልም በሽታው የራሱ የተለዩ ግልፅ ምልክቶች (Symptoms) የሉትም ለማለት ነው፡፡ ስትሮክ ከመከሰታቸው በፊት የሚታዩት ምልክቶች በሌሎች በሽታዎች ላይ ሊታዩ ስለማችሉ አሳሳቾች ናቸው፡፡ በስትሮክ በተጠቁ ሰዎች ላይ በአብዛኛው ቀደም ብለው ከሚታዩ ምልክቶች መካከል፣ የእጅና የእግር መዛል፣ የሙቀት ስሜት ማጣት፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት መከሰት፣ ድንገተኛና ከባድ ራስ ምታት፣ የጡንቻ መዛል፣ ለመናገር መቸገር (መንተባተብ)፣ መንገዳገድ፣ የተወሰነ የአካል ክፍል መንቀጥቀጥ፣ የእይታ ብዥታ መፈጠር፣ ህሊናን መሣትና የሌላን ሰው ንግግር ለመረዳት አለመቻል የሚጠቀሱ እንደሆኑ ዶ/ር አብርሃም ይገልፃሉ፡፡ የስትሮክ መንስኤዎች የደም ቅዳ የደም ስሮች ግድግዳ መቀደድ (መድማት) የደም ዝውውር መዛባት በአንጐል ውስጥ የሚገኙ የደም ስሮች ስሜት መጥበብ የረጋ ደም ከደም ሥር ግድግዳ ላይ ተላቆ በአንጐል ውስጥ በሚገኙ የደም ስሮች ግድግዳ ላይ መጣበቅና የደም ስርጭቱ እንደቀነሰ ማድረግ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ለስትሮክ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ከፍተኛ የደም ግፈት፣ በቁጥጥር ሥር ያልዋለ የስኳር ህመምና የሰውነት የስብ ክምችት የልብ በሽታ፣ የነርቭ በሽታ፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ዕድሜ፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል ተጠቃሚነት፡፡

የቀይ ደም ሴል መብዛት ሲጋራ ማጨስ፣ የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚነት፣ የአልኮል ሱስኝነት፣ ለስትሮክ ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የአመጋገብ ባህል መቀየር፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የዘመናዊ ትራንስፖርት አመቺነትና ጉልበትን የሚጠይቁ ሥራዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየቀሩ መምጣታቸው የስትሮክ በሽታ እንዲከሰት ምክንያት እንደሚሆኑ ዶ/ር አብርሃም ይገልፃሉ፡፡ ስትሮክ በምን ዓይነት ምርመራ ይታወቃል? የደም ሴሎች ምርመራ የደም ኮሌስትሮል ምርመራ ሲቲ ስካን የጀርባ አከርካሪ ፈሳሽ ምርመራ ዶፕላር አልትራ ሳውንድና የደም ስሮች የደም ፍሰት መጠን ምርመራ… ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዘመናዊ ምርመራዎች አማካኝነት ጉዳቱ የደረሰበት ሰው፣ የደረሰው ጉዳት መጠንና ጉዳቱ የደረሰበትን ሁኔታና ትክክለኛ ቦታ በማወቅና በመለየት ምርመራ ማካሄድ ይቻላል፡፡ ለስትሮክ የሚደረገው ህክምና ሙሉ በሙሉ ውጤታማ ይሆናል ለማለት እንደማያስደፍር የሚገልፁት ዶ/ር አብርሃም፣ ችግሩ የተከሰተበትን ቦታ ለይቶ ህክምና በመስጠት የደረሰውን የጉዳት መጠን በተወሰነ ደረጃ እንዲሻሻል ከማድረግ ባለፈ ወደቀድሞ የጤንነት ሁኔታ እንዲመለስ ማድረግ እምብዛም እንደማይሳካ ይናገራሉ፡፡

ለስትሮክ የሚሰጡ ህክምናዎች በደም ግፊት ሳቢያ የሚከሰተውን ስትሮክ… የደም ግፊት መጠን ቁጥጥርና ክትትል ህክምና ማድረግ የረጋ ደምን የማስወገድ ህክምና የደም ጉሉኮስ መጠን ቁጥጥር ህክምና የሰውነት ሙቀትና ማቀዝቀዝ ህክምና በደም ስር የሚወሰዱ መድሃኒቶችን የመስጠት ህክምና የአንጐል እብጠትን ለመቀነስ የሚረዱ መድሃኒቶችን የመስጠት ህክምና የደም መርጋትን የሚከላከሉ መድሃኒቶችን የመስጠት ህክምና (ለምሳሌ አስፕሪን) ደምን ለማቅጠንና ሥርጭቱ እንዲስተካከል ለማድረግ የሚረዱ መድሃኒቶችን የመስጠት ህክምና ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ዘመናዊ ህክምናዎች ከላይ እንደተገለፀው ውጤታማነታቸው አስተማማኝ ባለመሆኑ፣ ስትሮክ እንዳይከሰት መከላከሉ ከተከሰተ በኋላ ከሚሰጠው ህክምና የበለጠ ዋጋ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ በስትሮክ ሳቢያ የሚከሰተውን የአካል እንደልብ አለመታዘዝ (ፓራላይዝድ) መሆን ማስቀረት የሚቻለውም በህክምናው ሳይሆን ችግሩ እንዳይከሰት በሚደረገው ጥንቃቄ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

Read 8600 times