Saturday, 20 April 2013 11:14

ከሁለት ዓመት በፊት የወጣው የትራፊክ ደንብ ተግባራዊ ሆነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትራፊክ ጽ/ቤት ከሁለት ዓመት በፊት የወጣውንና እስካሁን ያልተተገበረውን የፌደራል የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ አሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ ማድረግ እንደጀመረ ተገለፀ፡፡ የእግረኞች እና “ሌሎች የደንብ መተላለፎች”ን የሚመለከተው የደንቡ ክፍል በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ከሚያዚያ 1 ቀን 2005 ጀምሮ አዲሱ የትራፊክ መቆጣጠርያ ደንብ በሥራ ላይ መዋሉን የገለጹት የትራፊክ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡ፤ ደንቡን ተከትሎ በተደረገው የተቀናጀ ቁጥጥር ምን ያህል ጥፋቶች እንደተመዘገቡ የተጠናቀረ መረጃ ባይቀኖርም ባለፈው እሁድ ብቻ በሞተረኛ ትራፊክ ፖሊስ በተደረገ ቁጥጥር ከ55 በላይ አዲሱን አዋጅ የሚጥሱ ጥፋቶች መመዝገባቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ ህግ ላይ በፊት በነበሩ የቅጣት መጠኖች ላይ በየእርከኑ የ20 ብር ጭማሪ ተደርጐባቸዋል የሚሉት ዋና ሳጅን አሰፋ፤ አጥፊዎች ሲቀጡ የጥፋት ሪኮርድ በነጥብ እንደሚያዝባቸውም ተናግረዋል፡፡ በእያንዳንዱ ጥፋት ከሁለት እስከ ሰባት ነጥብ የሚያዝ ሲሆን ነጥቦቹ ተደምረው 20 ወይም 21 ሲደርሱ መንጃ ፈቃድ እንደሚያስነጥቅ ሳጅኑ ገልፀው ፤ መንጃ ፈቃዱን ማግኘት የሚቻለው ከሁለት ዓመት በኋላ ነው ብለዋል- እንደ አዲስ በማውጣት፡፡ በአዲሱ ደንብ መሠረት፤ ተሣፋሪ ጭኖ ነዳጅ ማደያ በመግባት ነዳጅ የሚቀዳ እንዲሁም ያልተፈቀደ ጭነት ከህዝብ ጋር የጫነ የህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪ፣ 120 ብር ከመቀጣቱም በተጨማሪ 4 ነጥብ በጥፋትነት ይያዝበታል፡፡ የፌደራል የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ለማስፈፀም የወጣው አዋጅ፤ አሽከርካሪዎች ሲያጠፉ ከሚቀጡበት ዝርዝር የደንብ መተላለፎች በተጨማሪ እግረኞችና ልዩ ልዩ የመንገድ ተጠቃሚዎችን የሚመለከቱ ደንቦች የተካተቱበት ሲሆን የእግረኞች እና “ሌሎች የደንብ መተላለፎች” ተብለው የተመለከቱትን ለጊዜው ተግባራዊ ማድረግ አልተጀመረም ብለዋል - ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡ፡፡

ደንቡን ተግባራዊ ለማድረግ ያዝ ለቀቅ እንዳይሆን ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል የሚሉት ሃላፊው፤ እግረኞች ሲያጠፉ የሚቀጡባቸው ዝርዝር የአፈፃፀም ሂደቶች ሊኖሩ እንደሚገባና ይህንንም የትራፊክ ጽ/ቤት እና የትራንስፖርት ባለስልጣን በቅርቡ በጋራ እንደሚያስፈፅሙት አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል በተባሉት “ሌሎች የደንብ መተላለፎች”ን በተመለከቱ የጥፋት ዝርዝሮች ላይም በመንገድ ላይ አላግባብ እንስሳት የነዳ ወይም ይዞ የተገኘ 80 ብር፣ የተሽከርካሪ ወይም የእግረኛ መሄጃ መንገድ የቆፈረ፣ ያበላሸ ወይም ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችን ያከናወነ በ1ሺህ ብር እንዲሁም በተሽከርካሪ ወይም በእግረኛ መሄጃ ላይ የተሽከርካሪዎችን ወይም የእግረኞችና እንቅስቃሴ የሚያውክ ቁሳቁስ ወይም ሸቀጥ ያስቀመጠ፣ ወይም የነገደ፤ በሃዘን ምክንያት ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር ያለ ፍቃድ የተለያዩ ነገሮችን የተከለ ወይም ተመሳሳይ ነገሮችን ያከናወነ 300 ብር እንደሚቀጣ በደንቡ ላይ ተመልክቷል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ የደንቡ ክፍል የተመለከቱትን ሌሎች ተጨማሪ የጥፋት አይነቶችን የፈፀመ ከ40 ብር እስከ 1000 ብር መቀጮ ይቀጣል፡፡ እግረኞችን በተመለከተ ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርግ መንገድ ያቋረጠ፣ ለተሽከርካሪ በተፈቀደለት መንገድ ላይ ያለበቂ ምክንያት የቆመ ወይም የተጓዘ፣ የእግረኛ መንገድ በሌለበት መንገድ ላይ ቀኝ ጠርዙን ይዞ የተጓዘ፣ ለእግረኛ መንገድ ተብሎ ከተከለከለ መንገድ ውጭ የተጓዘ እንዲሁም በብረትም ሆነ በግንብ ተለይተው የታጠሩ መንገዶችን ዘሎ መንገዱን ያቋረጠ 40 ብር እንደሚቀጣ ተመልክቷል፡፡ በሌሎች የሃገሪቱ ክልሎች የሚሰራበት ደንብ በአዲስ አበባ ለምን እንደዘገየ ሳጅን አሰፋ ሲያስረዱ፤ ከተማዋ በርካታ ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱባት በመሆኗ እንዲሁም በደንቡ ዙሪያ ለአስፈፃሚ እና ፈፃሚ አካላት ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ በመቆየታቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በትራፊክ ጽ/ቤቱ እና በትራንስፖርት ባለስልጣን መካከል የነበሩ የአፈፃፀም ውስንነቶችን ለማስተካከል ጊዜ መውሰዱን ተናግረዋል፡፡

Read 6610 times