Saturday, 20 April 2013 11:28

የቦስተን ማራቶን የሽብር ጥቃትና የአትሌቶቻችን ድል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)
  • አትሌት ገ/እግዚአብሔር ስለፍንዳታው ያየውን ይናገራል
  • ባለቤቱ አትሌት ወርቅነሽና ሌሎች አትሌቶች በተዓምር ነው የተረፉት ይላል

ዘንድሮ በቦስተን ማራቶን ለሶስተኛ ጊዜ በመካፈል በሶስተኝነት ውድድሩን ያጠናቀቀው አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገ/ማርያም፤ ባለፈው ሰኞ በቦስተን የተከሰተው የሽብር ጥቃት ያደረሰው ጉዳት አሳዛኝ ቢሆንም ተወዳጁን የማራቶን ስፖርት ጥላሸት አይቀባውም አለ፡፡ ስፖርት የፖለቲካ ወይም የማንኛውም ተቃውሞ መግለጫ መድረክ አይደለም ያለው አትሌቱ፤ ጥቃቱ አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎትና መነሳሳት እንደማይቀንሰውም ተናግሯል - በቀጣዮቹ የኒውዮርክ እና የቦስተን ማራቶን ለመካፈል ያለውን እቅድ እንደማይሰርዝ በመግለፅ፡፡ አትሌት ገብረእግዚአብሄርን ጨምሮ በቦስተኑ ማራቶን የተሳተፉት ዘጠኝ የኢትዮጵያ አትሌቶች ባለፈው ረቡዕ ምሽት በሰላም አገራቸው የገቡ ሲሆን ውድድሩን በአንደኝነት ያሸነፈው አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ አንዳንድ የግል ጉዳዮቹን ለማጠናቀቅ እስከ ትላንት ድረስ እዚያው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አትሌት ሌሊሳ በውድድሩ ከጎኑ ሆኖ ሲፎካከረው የነበረውን የኬንያ አትሌት በ5 ሰከንድ ቀድሞ በመግባት ነው ታሪክ ያስመዘገበው፡፡ በዚሁ የቦስተን ማራቶን በሴቶች ምድብ የተወዳደረችው አትሌት ሂሩት ደግሞ ሦስተኛ ወጥታለች፡፡ አትሌት ገ/እግዚአብሔር ከትላንት በስቲያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ በተወዳደረበት የቦስተን ማራቶን ስለደረሰው የሽብር ጥቃት ሲናገር፤ ‹‹ዓለምአቀፍ ደረጃ ያለን ታዋቂ አትሌቶች ውድድሩን እንደጨረስን በቀጥታ የሄድነው ጋዜጣዊ መግለጫ ወደምንሰጥበት አዳራሽ ነበር፡፡ ከዚያም የሽንት ምርመራ አደረግን፤ ሁሉን ነገር አጠናቀን ከአንድ ሰዓት ተኩል ገደማ በኋላ ሆቴሉ ውስጥ እያለን ፍንዳታው ተከሰተ፤ እኛ ከነበርንበት ሆቴል ፊት ለፊት ነበር የፈነዳው፡፡

ከፍተኛ ጆሮ የሚያደነቁር ፍንዳታ ነው፤ የሚያፍን ሽታው ሁሉ እኛ ጋ ደርሷል፡፡ አትሌቶች አካባቢ ከፍተኛ ድንጋጤ የተፈጠረው ግን በመጀመርያው ሳይሆን ከ12 ሰከንዶች በኋላ ሁለተኛው ፍንዳታ ሲሰማ ነበር፡፡ አትሌቶች መሸበር ሲጀምሩ የውድድር አስተባባሪዎች እና የፀጥታ ሃይሎች ሁላችንንም አንድ ላይ ሰብስበው በሆቴሉ የእንግዳ ማቆያ ክፍል ውስጥ አስገብተው ዘገቡን፡፡ ሆቴሉም በበርካታ የፀጥታ ሰራተኞች ተከብቦ ጥብቅ ጥበቃ ይደረግለት ጀመረ፡፡›› ሲል የነበረውን ሁኔታ ገልጿል፡፡ ከማራቶን ውድድሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተካሄደው የ5ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ የተሳተፉት ባለቤቱ አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔና አትሌት ደጀን ገ/መስቀል ከአደጋው የተረፉት በተዓምር ነው ይላል - ገ/እግዚአብሔር፡፡

‹‹የሚገርምህ ከኛ በፊት በተደረገው የ5 ኪሜ የጎዳና ላይ ውድድር የተሳተፉት አምስት አትሌቶች የክብር እንግዳ ሆነው የማራቶን ውድድሩን ለመመልከት የተቀመጡት አንዱ ቦንብ የፈነዳበት አካባቢ ነበር፡፡ እኛ የማራቶን ውድደሩን ጨርሰን ስንገባ ከተቀመጡበት ተነስተው ተቀላቀሉንና ተሰብስበን አካባቢውን ለቀን ወጣን፡፡›› በሌሎች ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጠው ውድድሮቹ ሙሉ ለሙሉ ከተጠናቀቁ በኋላ ነው ያለው አትሌቱ፤ በቦስተኑ ውድድር ግን አትሌቶቹ ውድድሩን ጨርሰው እንደገቡ መግለጫ የመስጠት አሰራር ስለሚከተሉ ወርቅነሽና ደጀኔ ከፍንዳታው ሊተርፉ ችለዋል፡፡ ጠቅላላ ውድድሩ እስኪጠናቀቅ እዚያው ቢቆዩ ኖሮ የጥቃቱ ሰለባዎች የሚሆኑበት እድል ነበር - በተዓምር ተርፈናል ብሏል፡፡

ፍንዳታዎቹ እንደተከሰቱ ካስገቡን ክፍል በምንም ዓይነት መንገድ እንድንወጣ አልተፈቀደልንም ያለው ገ/እግዚአብሔር፤ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በከፍተኛ የፀጥታ ሃይሎች ታጅበው ከሆቴላቸው በመውጣት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ የሚወስደውን አውሮፕላን እንደተሳፈሩ፤ ከዚያም በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ገልጿል፡፡ በቦስተኑ የ5 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በወንዶች ምድብ የ23 አመቱ ደጀን ገብረመስቀል የቦታውን ሪከርድ ሰብሮ ሲያሸንፍ ፤ በሴቶች ምድብ አምና በተመሳሳይ ውድድር ያሸነፈችው አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ አራተኛ ደረጃ አግኝታለች፡፡ የቦስተኑ ፍንዳታ ከተሰማ በኋላ የስፖርት ቤተሰቡ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ጥቃቱን አውግዘዋል-ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን በመመኘት፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ስለደረሰው የቦንብ ጥቃት የተሰማውን በትዊተሩ ሲገልፅ “ሩጫ ህዝቦችን አንድ ያደርጋል፡፡ በቦስተን ያጋጠመው ሁኔታ ግን አሰቃቂ ነው፡፡” በማለት ፅፏል፡፡ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፕሬዝዳንት ላሚን ዲያክ በበኩላቸው፤ የዓለም ስፖርት ቤተሰቦች በተፈጠረው ነገር ሳይደናገጡ ለስፖርቱ በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ጃኩዌስ ሮጌ በሰጡት አስተያየት “ማራቶን ህዝቦችን የሚያቀራርብ ልዩ የስፖርት መድረክ ነው፡፡

ከአሳዛኙ የቦስተን ማራቶን የሽብር ጥቃት በኋላም ይህ የተለየ ሚናው ይቀጥላል” ብለዋል፡፡ ከ20 ዓመት በፊት ትልልቅ የማራቶን ውድድር አዘጋጆች የሚያሳስባቸው ስፖርተኞች ተጠቅመው የሚጥሏቸውን የተለያዩ ቆሻሻዎች ማፅዳት እንደነበረ ያስታወሰው የታዋቂ አትሌቲክስ ባለሙያዎች ድረገፅ “ራኒንግኮምፒውቴተርስ”፤ ከአሁን በኋላ ግን ዋና ትኩረታቸው አስተማማኝ ፀጥታ እና ጥበቃ ማስፈን እንደሆነ በመጠቆም ለትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ቢያንስ የአንድ ዓመት ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ሲል መክሯል፡፡ በዓለም በአንጋፋነታቸው ከሚታወቁት የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው የቦስተን ማራቶን ዘንድሮ ለ117ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ከ96 አገራት የተውጣጡ ከ25ሺ በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈውበታል፡፡ ከተሳታፊዎቹ መካከል ከ5ሺ በላይ ስፖርተኞች ውድድሩን አልጨረሱም - በተከሰተው የሽብር ጥቃት፡፡ በቦስተን ማራቶን በተከሰቱት ሁለት ፍንዳታዎች፤ ሶስት ሰዎች ሲሞቱ ከ183 በላይ የውድድሩ ተመልካቾች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

Read 2986 times