Saturday, 20 April 2013 12:09

በሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ሙት ዓመት ምን ተባለ?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

              “የስዕል ብቻ ሳይሆን የሰዓሊያን ጉዳይ ያገባኛል ያለ ታላቅ ሰዓሊ”

 ለሎሬት አፈወርቅ ተክሌ አንደኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ረቡዕ ሚያዝያ 2 ቀን 2005 ዓ.ም በብሔራዊ ሙዚየም የሰዓሊው ሥራዎች ለእይታ ቀርበው፣ ለአራት ተከታታይ ቀናት በሕዝብ የተጎበኘ ሲሆን የስዕል ኤግዚቢሽኑ በተከፈተ ማግስት በቅርስ ጥበቃና ምርምር ባለስልጣን አዳራሽ፣ በሰዓሊው የሕይወትና የሥራ ታሪክ ዙሪያ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ፤ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር የዕውቀት ሽግግር አሰፈላጊ መሆኑን አመልክተው፣ በዚሁ ዓላማ መሠረት የሎሬት አፈወርቅ ተክሌን አስተሳሰብ፣ ራዕይና ፍልስፍናን ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ታስቦ የእለቱ የፓናል ውይይት መድረክ መሰናዳቱን ገልፀዋል፡፡

በባለታሪኩ የሕይወትና የሥራ ታሪክ ዙሪያ የተለያዩ መድረኮችን አዘጋጅቶ ከመወያየትም ባሻገር፣ ለሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ሐውልት ለማሰራትና “ቪላ አልፋ” ቋሚ መታሰቢያቸው እንዲሆን ተወስኖና ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ የጥበብ ሥራ ለአርቲስቶች ከአክብራካቸው ከተገኘ ልጅ በተሻለ መጠሪያና መከበሪያ ይሆናቸዋል በማለት ጥናታቸውን ማቅረብ የጀመሩት ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፤ ለዚህ አባባላቸው የከበደ ሚካኤልንና የሀዲስ አለማየሁን ሥራዎች በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ አርቲስቶች በጥበብ ሥራዎቻቸው የሚወቀሰውን ይተቻሉ፡፡ የሚመሰገነውን ያደንቃሉ። የአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ግጥሞችን ስንመለከት ቴዎድሮስን የተቸ ገጣሚ በሌላ ጊዜ የሚያስመሰግን ነገር ሲያይ ሲያወድሳቸው የምናገኘው ለዚህ ነው ያሉት አያልነህ ሙላቱ፤ “ለሕብረተሰቡ ቅርብ የነበረው አፈወርቅ ተክሌ አገሩን፣ ዘመኑንና ሕብረተሰቡን በምን መልኩ ይመለከት እንደነበር ሥራዎቹ መጠናት ይኖርባቸዋል” ካሉ በኋላ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን በሦስት የተለያዩ ርዕሶች በመከፋፈል አቅርበዋል፡፡

በመጀመሪያ ስለ “ቪላ አልፋ” ስያሜ፣ አመሰራረትና ይዘት ገለፃ አደረጉ፡፡ የስዕል ስቱዲዮ፣ የጥበብ ሥራዎች ማከማቻና የሰዓሊው መኖሪያ ቤት ሆኖ ያገለገለው ቪላ አልፋ፤ ስያሜውን ያገኘው በአንድ እንግሊዛዊ ፕሮፌሰር ምክንያት ነው፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በወጣትነታቸው በእንግሊዝ የስዕል ትምህርት ቤት ሲማሩ ሊያነጋግሯቸው የሚመኙት አንድ ፕሮፌሰር መምህር ነበሯቸው፡፡ ለዚህ ብልሐት ሲፈልጉ ፕሮፌሰሩ ለሚሰጡት ፈተና ተቃራኒ መልስ መስጠት ጀመሩ፡፡ የኢትዮጵያዊው ተማሪ ተግባር ያስገረማቸው ፕሮፌሰር ተማሪዎቻቸውን ይሰበስቡና በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሲጠይቋቸው፤ አብዛኛው ተማሪ “ለአፈወርቅ ዜሮ ይሰጠው” ይላል፡፡ ተማሪያቸውን በግል ሲያነጋግሩት ግን ከገመቱት በላይ ባለ ልዩ ተሰጥኦ መሆኑን አስተዋሉ፡፡ ሌሎች ተማሪዎች መፍጠር ባልቻሉት ብልሐት ወደ መድረኩ ለውይይት ለጋበዛቸው ኢትዮጵያዊ ተማሪ፤ ሊሰጠው የሚገባው ውጤት ዜሮ ሳይሆን “አልፋ ፕላስ” ነው በማለት በጓደኞቹ ፊት መሰከሩለት፡፡ ያ ታሪክ ከዓመታት በኋላ ለ “ቪላ አልፋ” ስያሜ ሆነ፡፡

“አፈወርቅ ተክሌ የእንግሊዝ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ አገሩ ሲመጣ የስዕል ስቱዲዮ የነበረው ሰዓሊ ማንም ስለለነበረ፣ ቪላ አልፋን የሰራው በዚህ መነሻ ነው” ያሉት ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፤ የሥራ ሂደቱን ሲያብራሩም፤ “አሁን ቪላ አልፋ በሚገኝበት ጦር ኃይሎች ሆስፒታል አካባቢ በ1948 ዓ.ም ታላቅ የኢዮቤልዩ ኤግዚቢሽን ተካሂዶ ነበር፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌም በኤግዚቢሽኑ ላይ ሥዕሎቻቸውን ይዘው በመቅረብ ተሳትፈዋል፡፡ ለተለያዩ አገልግሎቶች የዋሉ 22 ክፍሎች ያሉት ቪላ አልፋ የሚሰራበት ቦታ ጦር ኃይሎች አካባቢ እንዲሆን የወሰኑት በዚያ አጋጣሚ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ነገሮች እንዲወክል ተደርጎ የተሰራው ቪላ አልፋ፤ ግንባታው 15 ዓመታትን የወሰደ ሲሆን የመሬት መግዣውን ጨምሮ ሙሉ ወጪው በሎሬት አፈወርቅ የተሸፈነ ነው፡፡ 42 ደረጃዎች ከተወጣ በኋላ የሚደረስበት የቪላ አልፋ ሰገነት አዲስ አበባ ከተማን በአራቱም አቅጣጫ መመልከት ያስችላል፡፡

በጥናታዊ ጽሑፋቸው ሁለተኛ ርዕስ፤ ስለ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ሥራዎች ማብራሪያ ያቀረቡት አያልነህ፤ “አፈወርቅ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ልዩ አክብሮት አለው” በማለት ሥራዎቻቸውን እየጠቀሱ መስክረዋል፡፡ ወደ ቪላ አልፋ ሰገነት ለመወጣጫ የሚያገለግሉት 42 ደረጃዎች የአንኮበር ተራራዎችን የሚወክሉ መሆናቸውን፣ ሰዓሊው ለኢትዮጵያ የባህል አልባሳት ልዩ ክብር እንዳላቸው፣ ከሥራዎቻቸው አስር ከመቶ የሚሆኑት ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው እንደሆኑ … በሰፊው ተናግረዋል፡፡ ሦስተኛው ርዕሳቸው የሰዓሊውን ሰብዕና የተመለከተ ነበር፡፡ በንጉሡ ዘመን ውጭ አገር ሄደው ተምረው የተመለሱ ኢትዮጵያዊያን አብዛኞቹ ስልጣንና ገንዘብ ከመንግስት በማግኘት ለታላቅነት ሲጣጣሩ፣ በተቃራኒ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በእድሉ እንዲጠቀሙ ሲጠየቁ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ እርዳታና ልመናን ተጸይፈው በራስ ጥረትና ሥራ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ መሆን እንደሚቻል ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን ጥረዋል፡፡ ብዙ አገራትም መሬት፣ መኖሪያ ቤትና ዜግነት ሲሰጣቸው ቢያግቧቧቸውም በኢትዮጵያዊነታቸው ሳይደራደሩ ፀንተው ቆይተዋል፡፡

ሁለተኛውን የጥናት ፅሁፍ ያቀረቡት የስነጥበብ ታሪክ ባለሙያ እሰየ ገብረመድህን፤ “አፈወርቅ የስዕል ብቻ ሳይሆን የሰዓሊያን ጉዳይ ያገባኛል ያለ ታላቅ ሰዓሊ ብቻ አይደለም፤ በሕይወት እያለ ብዙ ያልተነገረለት የአገር ባለውለታ ነው” በማለት ነው ስለ ሰዓሊው መናገር የጀመሩት፡፡ ከሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በፊትም በሰዓሊነት የሚታወቁና በውጭ አገር የመማር እድል ያገኙ ሰዓሊያን የነበሩ ቢሆንም የሰዓሊያኑ ለውጥ የማምጣት እንቅስቃሴና ፍላጎት በተለያዩ ምክንያቶች የተገደበ ነበር ያሉት ጽሑፍ አቅራቢው፤ “በ1950ዎቹ አለፈለገ ሠላም የስዕል ትምህርት ቤት ለማቋቋም ሲንቀሳቀስ እና አፈወርቅ ተክሌ የግል የስዕል ስብስቦቹን ለሕዝብ ሲያቀርብ ችግር ገጥሟቸዋል” ሲሉ የፈተናውን ቀጣይነት ገልፀዋል፡፡ “አፈወርቅ በ15 ዓመቱ ለትምህርት ወደ እንግሊዝ የሄደው ኢንጂነሪንግ እንዲማር ነበር፡፡ አፈወርቅ እንግሊዝ የሄደው በአገር ውስጥ የአገኘው እንግዳን መገደል አይቶ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ ኢንጂነሪንጉን በመተው ስዕል ነው ያጠናው፡፡ የጥበብ ሰው ታላቅ ነገር ለመሥራት ከውስጡ የሚገፋው ነገር ያስፈልገዋል፡፡

አፈወርቅ በእንግሊዝ አገር በመማሩ ማንነቱን እንዲያጣ አላደረገውም፡፡ ዘመናዊነትን ከምዕራባዊያን አመለካከት ውጭ መተግበር እንደሚቻል በስዕሎቹ ማሳየት ቻለ፡፡ ከ1940-1960ዎቹ የአፈወርቅ ዘመን ሊባሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ አፈወርቅ በአገራችን ስዕልና አሳሳል ታሪክ ላይ ብዙ አነጋጋሪ ነገሮችን አምጥቷል፡፡ አፈወርቅና ሥራዎቹ ታላቅ የሆኑትም ለዚህ ነው፡፡” በታሪክ አጋጣሚ በድንገት ብቅ የሚሉ ሰዎች ናቸው በአገርና በሕዝብ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ነገር መሥራት የሚችሉት ያሉት ባለሙያው፤ “ለሙያው ሲል እንደ ባህታዊ ራሱን ከሌሎች አግልሎ እያሰበ፣ እየተመራመረ የሰራቸው ሥራዎች ለታላቅ ደረጃ አብቅተውታል፡፡ የራሱን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ፍላጎት ለማንፀባረቅ ብዙ ሰርቷል፡፡ ‘የሚያሳዝኑ ሳይሆን ተስፋ ሰጪ ገፀ ባሕርያትን መሳል ያስደስተኛል” ይል ነበር” ብለዋል፡፡ ሰዓሊውን በርቀት ከሚያውቁት አንዱ ነኝ፡፡ መፃሕፍት አገላብጬ ካልሆነ በስተቀር ስለ አፈወርቅ ተክሌ የተለየ ነገር ማቅረብ አልችልም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በ1973 ዓ.ም ተማሪ እያለሁ ነው በሚል የመግቢያ ንግግር ሦስተኛውን የጥናት ወረቀት ያቀረቡ ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን በበኩላቸው፤ ለውይይት ወይም ለጥናት ይጠቅማሉ ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡

“አፈወርቅ በሙያው ሁሉንም ዲስፒሊኖች የሰራ ታላቅ ሰው መሆን የቻለው እንዴት ነው? በስዕሎቹ ወፍራም መስመሮች፣ የተለጠጡ የሚመስሉ የቀለም አቀባቦቹ ምክንያቱ ምን ይሆን? ትውፊታዊውን ጥበብ ከዘመናዊው ትምህርት ጋር አጋብቶ ነው ወይ የሚስለው? ለግል እምነቱ፣ አቋሙና ነፃነቱ ምን ያህል ዋጋ ከፈለ? ደመናን ሲስል የሚሮጡና ድራማዊ የሚያደርጋቸው ለምን ይሆን? የአፈወርቅ ራዕይ፣ እምነት፣ አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና አሳሳል የተከተለ ደቀ መዝሙርስ ይኖር ይሆን?” የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎችም የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ በባህላችን የሰዎች ታላቅነት የሚነገረው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ነው፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ከመሞታቸው በፊት በስዕል ትምህርት ቤት አካባቢ ሙያውና ባለሙያው እንዲያድግ አልረዱም ይባል ነበር፡፡ ለዚህ ልዩነት ምላሻችሁ ምንድነው? ቪላ አልፋ ለውጭ ዜጎች ካልሆነ ለኢትዮጵያዊያን ዝግ ነበር ይባላል፡፡ እውነት ከሆነ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ለሕብረተሰቡ ሩቅ እንደነበሩ አያመለክትም ወይ? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ስዕል ሲስሉ መስመሮችን ከጥንት የአገራችን ሰዓሊያን፣ ፀሐይን ከአፍሪካ ሰማይ፣ የቀለም አጠቃቀምን ከአውሮፓውያን ነው የተማርኩት ይሉ ነበር ተብሏል፡፡ ይህንን ዕውቀታቸውን በትምህርት ቤቶች ተገኝቶ ለተማሪዎች የማስተማር ፍላጎቱ የነበራቸው ቢሆንም “ቋሚ ሆነህ አስተምር” ሲባሉ አለመስማማታቸውም ተነግሯል፡፡ በመፃሕፍቶቻቸው የተማረ አንባቢ፤ ደራሲያኑን አስተማሪዬ እያለ እንደሚጠራቸው ሁሉ ወጣት ሰዓሊያንም የአንጋፋዎቹን ሥራ በመመልከት ብዙ ሊማሩ ይችላሉ ተብሏል፡፡ ቪላ አልፋ ለኢትዮጵያዊያን ዝግ ሆኖ አያውቅም የተባለ ሲሆን ችግሩ የተፈጠረው ኢትዮጵያዊያን ወደ ምንፈልገው ቦታ ያለ ቀጠሮ የመሄድ ባህል ስላለንና በተቃራኒው ደግሞ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ያለ ቀጠሮ ማንም ሰው ቢሄድ አለማስተናገዳቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ የስዕል ሀሳቦቹ በሙሉ አገራዊ የሆነ ሰዓሊ፤ የታሪኩን ባለቤት ያገላል ማለት የማይታመን ነው ተብሏል፡፡

ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በአስተሳሰብና በአሰራር ማን ተከተላቸው ለሚለው ጥያቄ ምላሹ በጥናት የሚሰጥና በቀጣዩ ዘመናት ግልፅ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡ ጥበብን በመሰለ ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ስንነጋገር ሰውየውንና ሥራውን ለያይቶ መመልከት ስላለው ጠቀሜታ ሲነገርም፤ አንድ ነገር ጠይቀነው የከለከለንን፣ ገንዘብ አበድረነው ያልመለሰልንን፣ በእንግድነት ጋብዘነው ያልመጣልንን … ሰው በዚህ ጥላቻ ላይ ሆነን ስለ ሥራው ጥሩነት መናገሩ ስለሚያስቸግረን፤ ሁለቱን ነጣጥሎ መመልከቱ ይጠቅማል የሚል ሀሳብ ተሰንዝሯል፡፡ በመጨረሻም የብሔራዊ ሙዚየም ሥራ አስኪያጅ ወ/ት ማሚቱ ይልማ፤ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎቹንና የፓናል ውይይት ተሳታፊዎቹ በማመስገን ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

Read 2777 times