Saturday, 20 April 2013 12:27

“ኤል ጂ” የተስፋ መንደር ያደረጋት ዱግዴደራ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    “ቱዴይ ኢዝ ኤ ሆሊዴይ!”

በኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ዙሪያ በረኻ ወረዳ፣ ዱግዴደራ መንደር ከሠንዳፋ በቀኝ በኩል 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ አካባቢው ከአዲስ አበባ ብዙ ባይርቅም የስልጣኔ ጮራ አልደረሳትም፡፡ ነዋሪው ንፁህ የመጠጥ ውሃ የመጠቀም እድል አላገኘም፡፡ የጉድጓድ ውሃ የሚገኘው ከመንደሩ በብዙ ርቀት ላይ በመሆኑ የእናቶችና ህፃናት ወገብ እንሰራ እና ጀሪካን በመሸከም ሲጐብጥ ኖሯል፡፡ የመኪና መንገድም አልነበራቸውም፡፡ አሁን ግን መንደሯ የተስፋ ጭላንጭል እየታየባት ነው፡፡ እነዚህ ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክቶች፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ፀሐይ የሚገኝ ኃይል (ሶላር ኤነርጂ) የመንግድ ሥራና የዘመናዊ ግብርና ስልጠና ናቸው፡፡ ወይዘሮ ጫልቱ ኢብሣ የ48 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡

ሰባት ልጆቻቸውን ወልደው ያሳደጉት እንስራ እየተሸከሙ ነው፡፡ “ልጆቼ እስኪደርሱ ለረጅም ዓመታት እንስራ ስሸከም ኖሬያለሁ” በማለት የውሃው ጉድጓድ ያለበትን ሥፍራ ርቀት በጣታቸው አመለከቱኝ፡፡ አህያ ያለው በአህያ፣ የሌለው በወገቡ ጀሪካን እየተሸከመ የኖረው ማህበረሰብ፣ አሁን ንፁህ ውሃ ለመጠጣት ተቃርቧል፡፡ በዱግዴደራ መንደር ተወልደው የልጅ ልጅ እንዳዩ ይናገራሉ፡፡ የ62 ዓመት እድሜ ያላቸው አቶ መኮንን ኢማና “ዛሬ ዳግም የተወለድኩ መስሎኛል፡፡ ሳልሞት ይህን በማየቴ እድለኛ ነኝ፡፡ ሰው እድሜ ከሰጠው ብዙ ያያል” ሲሉ በውሃው መውጣትና ወደፊት በተያዘው እቅድ መደሰታቸውን ይናገራሉ፡፡

አርሶ አደሩ ከልጅነታቸው ጀምሮ ውሃ በመቅዳት ቤተሠባቸውን ይረዱ እንደነበር ገልፀው፤ እርሳቸው በህይወት እያሉ የቧንቧ ውሃ መንደራቸው ይደርሣል ብለው አስበው እንደማያውቁ አጫውተውኛል፡፡ አቶ መኮንን ባላቸው እድሜ ከኩራዝ ብርሃን ወደ ኤሌክትሪክ ብርሀን ተሸጋግረውና ተደስተው ማለፍ እንደሚመኙና እንዳስደሠታቸው ይናገራሉ፡፡ “ውሃው በማሽን ወጣ ሲባል አላመንኩም፡፡ በአይኔ ካየሁ በኋላ ገረመኝ፡፡ ከእንግዲህ የውሃ ችግር ደህና ሠንብት እያልን ነው፤ በጣም ተደስተናል” ይላሉ ወይዘሮ ደብሬ፡፡ “ሰሞኑን ከጐረቤቶቼ ጋር አብረን ቡና ስንጠጣ ወሬያችን ስለተቆፈረው ውሃ ሆኗል፡፡ እዚሁ አጠገባችን ውሃ እያለ የትና የት እየሄድን ጀርባችን ሲላጥ ከርሟል” አሉኝ ፊታቸው በደስታ እየበራ አጫውተውኛል፡፡ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ወፍጮ ቤት፣ መብራት… እንደሚቀራቸው እንደ ከተማው ሰው ወርቅ የመሠለ መንገድ ላይ (አስፋልት ለማለት) እንደሚሄዱና ጅምሩም ተስፋ እንደሠጣቸው አጫውተውኛል፡፡

የደቡብ ኮሪያው የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አምራች ኩባንያ “ኤል ጂ” የአካባቢውን ችግር በመረዳት “ወርልድ ቱጌዘር” ከተሰኘ የኮሪያ በጐ አድራጐት ድርጅት ጋር በመተባበር፣ በ29 ሚሊዮን ብር ሦስት ፕሮጀክቶችን ለመስራት ዕቅድ አለው፡፡ ሦስት ዓመት የሚፈጀው ፕሮጀክቱ፤ በመጠጥ ውሃ፣ በሶላር ኤነርጂ፣ በመንገድ ሥራና በዘመናዊ ግብርና ዙርያ የሚሰራ ነው፡፡ ኤል ጂ “አውራ ድሪሊንግ ኤንድ ትሬዲንግ” ከተባለ ኩባንያ ጋር ኮንትራት ሲፈራረም 150 ሜትር ጥልቀት ተቆፍሮ ውሃ እንዲወጣ ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ኩባንያው ገና 128 ሜትር ጥልቀት እንደቆፈረ ከፍተኛ ኃይል ያለው ውሃ አግኝቶ የአካባቢውን ማህበረሰብ አስፈንድቋል፡፡ የ“አውራ ድሪሊንግ ኤንድ ትሬዲንግ” ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ዮሴፍ ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፤ “ከኤልጂ ጋር የተስማማነው 150 ሜትር ጥልቀት ልንቆፍር ነበር፡፡

እነሱም ቦታውን ሲያስጠኑት 150 ሜትር መቆፈር እንዳለበት ተነግሯቸዋል” ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ መሬቱ ሲቆፈር 128 ሜትር ላይ ውሃ ማግኘታቸውን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ጉድጓዱ በሰከንድ አምስት ሊትር ውሃ የማፍለቅ ኃይል እንዳለውና በ15 ቀን ቁፋሮ ውሃው እንደወጣ ጠቁመዋል፡፡ የኤል ጂ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ሽመልስ በበኩላቸው፤ ከኤል ጂ ጋር በመተባበር ለመንደሩ የመንገድ፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎት እንዲሁም የዘመናዊ ግብርና ሥልጠና ለመስጠት ዕቅድ ያላቸው ሲሆን ለዚህም ከአካባቢው ማህበረሰብ አምስት ሄክታር መሬት ማግኘታቸውን፣ “ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የተሰጠው ለንፁህ የመጠጥ ውሃ ስለነበር እሱን አስቀድመን እውን አድርገናል“ ብለዋል፡፡ ሥራው “ለአውራ ድሪሊንግ ኤንድ ትሬዲንግ” ኩባንያ በኮንትራት ሲሰጥ፣ 732 ሺህ ብር ተፈራርመው እንደነበር ጠቅሰው፣ የመጀመርያው ዕቅድና ስምምነት 128 ሜትር ተቆፍሮ የተገኘውን ውሃ በፓይፕ ወደየመንደሩ ማሰራጨት ነበር፤ ሆኖም የውሃው ኃይል ከፍተኛ በመሆኑ በብረት ቧንቧ ለማሰራጨት ተወስኗል ያሉት የፕሮጀክቱ ኃላፊ፤ ይኼ ደግሞ ወጪውን ከ732 ሺ ብር ወደ 850ሺ ብር ከፍ እንደሚያደርገው ገልፀዋል፡፡

በቁፋሮ ድንገት የወጣው ውሃ አካባቢውን ረግረጋማ አድርጐታል፡፡ ለምርቃቱ ለተጠሩት እንግዶች ላስቲክ ቦት ጫማ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ለምርቃቱ የተዘጋጀውን ዳስ ሞልቶታል፡፡ የአካባቢው ትምህርት ቤት ተማሪዎችም በአስተማሪዎቻቸው ረዳትነት በሰልፍ ወደምርቃት ቦታው እየዘመሩ መጥተው ተቀላቅለዋል፡፡ “ቱ ዴይ ኢዝ ሆሊዴይ” የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ የመድረክ መሪ፤ ህብረተሰቡ ለሁለቱ ድርጅቶች (ኤል ጂ እና ዎርልድ ቱጌዘር) ደስታውንና ምስጋናውን ለመግለፅ፣ የአካባቢውን አነስተኛ ባህላዊ መሶብ በስጦታ እንደሚያበረክት አስታወቀ፡፡ ቀጠን ረዘም ያለ ጠይም የአካባቢው ተወካይ አቶ አሸኔ ቱምሴ ትንሿን መሶብ በዳንቴል እንደተሸፈነች ወደ መድረኩ ይዘው ወጡ፡፡ ስጦታውን ለድርጅቱ ተወካዮች ከሰጡ በኋላ ብዙዎችን ያስገረመና ያስደመመ ንግግር አደረጉ፡፡ ምስጋናቸውን ለመግለፅ ንግግር የጀመሩት “ቱ ዴይ ኢዝ ሆሊዴይ” በማለት ነው - ጮክ ብለው፡፡ ከዚያማ እንግሊዝኛውን እንደ ጉድ ለቀቁት፡፡ “እኛ ለረጅም ዓመታት ከከብት ጋር ያልተጣራ የጉድጓድ ውሃ ስንጠጣ ኖረናል፣ ለበሽታም ስንጋለጥ ነበር፡፡ ዛሬ ታሪክ ተቀይሮ የቧንቧ ውሃ ልንጠጣ ነው፡፡ ይህን ፕሮጀክት እዚህ አምጥተው ወግ ያሳዩንን እናደንቃለን፡፡

ዛሬ ለእኛ ቀኑ ቅዱስ ቀን ነው፤ የተለየ በዓል ነው” በማለት ጮኹ፡፡ የፕሮግራሙ ታዳሚዎች ከመቀመጫቸው በመነሳት በአድናቆትና በጭብጨባ ተናጋሪውን አጀቧቸው፡፡ ደስታቸውንና ምስጋናቸውን ከፈረንጅ አፍ ሌላ ለማይሰሙት ለጋሾች መግለፃቸው ሌላ ደስታ ጨምሮላቸው ነበር፡፡ እናም ብዙዎች የአካባቢው አስተማሪ ያውም የእንግሊዝኛ አስተማሪ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት ነበራቸው፡፡ ሰውየው ግን ቆፍጣና አርሶ አደር ናቸው፡፡ በቦታው ሲወራ እንደሰማነው አቶ አሽኔ ቱምሴ ቀደም ሲል 12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ በአሁኑ ሰዓት ግን በግብርና ስራ የሚተዳደሩ አርሶ አደር ናቸው፡፡ በቦታው የሚገኙ አንዳንድ ታዳሚዎችም ከአሁን ዘመን የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች የድሮ 12ኛ ክፍል ምን ያህል እንደሚልቅ አስተያየት ሲሰነዝሩ ተደምጠዋል፡፡ ኤል ጂ፤ በያዘው የሦስት ዓመት ፕሮጀክት፤ የአካባቢው አርሶ አደር በዘመናዊ ግብርና ሰልጥኖ የተሻለ ህይወት እንዲመራ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘመናዊ አመራረት ሊያሰለጥን በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ከፀሐይ ሀይል መብራት ለአካባቢው ማህበረሰብ መስጠት የፕሮጀክቱ አንድ አካል ነው፡፡

የአካባቢው ዋነኛ ችግር የሆነው መንገድም በዕቅዱ ውስጥ ተካትቷል፡፡ በሦስት ዓመቱ ፕሮጀክት ይህ ሁሉ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ፣ ኤል ጂ ለህብረተሰቡ የመሪነት ክህሎት ስልጠና በመስጠት፣ ለአካባቢው አስረክቦ እንደሚወጣ ተገልጿል፡፡ የደቡብ ኮሪያው ዓለምአቀፍ የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ፣ ከቢዝነስ ሥራው ጐን ለጐን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ኩባንያው እዚህ አዲስ አበባ የሙያና የቴክኒክ ት/ቤት በመክፈት ተማሪዎችን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በኤሌክትሪክ፣ በኤሌክትሮኒክስና በተንቀሳቃሽ ስልክ ጥገና ሥልጠና ሊሰጥ መዘጋጀቱን የገለፀ ሲሆን በተለይም በኮሪያ ጦርነት ላይ ለተሳተፉ ኢትዮጵያውያን የኮሪያ ዘማች የልጅ ልጆች የነፃ ትምህርት ዕድል እንደሚሰጥም ተነግሯል፡፡

የ“ኤል ጂ” አስመጪው ሜትሮ ፒኤ ሲ ባለቤትና ዳይሬክተር አቶ አብዱል ሀሚድ አብደላ “ኤል ጂ” ኩባንያ በአሁኑ ሰዓት የቴሌቪዥን እና የዲቪዲ መገጣጠሚያ ፋብሪካ እንዳላቸውና ለወደፊቱ በዓለም የቴክኖሎጂ ምጥቀት የተፈጠሩትን 3D (3 ዳይሜንሽን) ቴሌቪዥኖችን ለመገጣጠም እቃዎች ከውጭ ማዘዛቸውን ተናግረዋል፡፡ ከ3D ቴሌቪዥን በተጨማሪ የልብስ ማጠቢያ ማሽንም እዚሀ ለመገጣጠም እቅድ ተይዟል፡፡ ከሦስትና አራት ወር በኋላ እቃዎች ሲገቡ አለም ላይ ያለው ቴክኖሎጂ እዚህም እንዲሠራ በማድረግ ከላይ የተጠቀሱት እቃዎች ይገጣጠማሉ ብለዋል፡፡ “ኤል ጂ” ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የገበያ ሁኔታና ተቀባይነት በተመለከተ ተጠይቀው “ገበያው ጥሩ ነው ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ይቀረዋል” ያሉት አቶ አብዱልሀሚድ የ“ኤልጂ” ምርቶች በከተማ ብቻ ሳይሆን ገጠር ውስጥ አርሶ አደሩም እንዲጠቀም ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ በከተማ ውስጥ ያለው አመታዊ የሽያጭ መጠንም ወደ 100 ሚሊዮን አካባቢ መሆኑን አቶ አብዱልሀሚድ አብደላ ጠቁመዋል፡፡

Read 2704 times