Saturday, 12 November 2011 07:38

በሞዛምቢክ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የያዘ ይሸለማል

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(0 votes)

በታንዛንያ እስር ቤት ዓይናቸውን የታወሩ ኢትዮጵያውያን አሉ 
ታንዛኒያ 700 ኢትዮጵያውያን ታስረዋል
ባለፈው ሳምንት በታንዛንያ እስር ቤት ለ7 ወራት ታስረው በዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) አማካኝነት 472 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡  የአሁኑኖቹን ከቀደምት ስደተኞች የሚለያቸው ለስደት ካነጣጠሩበት አገር ደቡብ አፍሪካ ሳይደርሱ በመንገድና በእስር ቤት ተሰቃይተውና ተንገላተው ከወራት በኋላ መመለሳቸው ነው፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሰደድ ያነሳሳቸው ደግሞ በዋናነት ቀደም ብለው የተሰደዱ ዘመዶቻቸው ጓደኞቻቸውና የሚያውቋቸው ሰዎች ኑሮአቸው ተለውጦ በማየታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ለህገወጥ ደላሎች ብዙ ሺ ብር ከፍለው ጉዞአቸው ከታንዛንያ ተሰናክሎ ከተመለሱት ኢትዮጵያውያን መካከል ሁለቱን አነጋግሬአቸዋለሁ፡፡ 
ዳዊት ግርማ ይባላል፡፡ ዕድሜው 24 ሲሆን፤ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ተምሯል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩት አባቱ ለስደት ጉዞው ምክንያት እንደሆኑ ይናገራል፡፡ ከፊሉን የጉዞ ወጪ የሸፈኑለትም እሳቸው ናቸው፡፡ የጉዞ ታሪኩን ይናገራል፡፡
ከሆሳዕና ዲላ፣ ከዲላ ሞያሌ፣ ከሞያሌ ናይሮቢ ገባሁ፡፡
እኔ ፓስፖርት ስለነበረኝ ከደላላው ጋር የነበረን ስምምነት በህጋዊ መንገድ ቪዛ አስመትቶልኝ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ነበር፡፡ ነገር ግን ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ በህገወጥ መንገድ ልጓዝ ተገደድኩኝ፡፡
ስለጉዞው ሁኔታ ንገረኝ
በደረቅ መንገድና በውሃ መንገድ የሚሉት አላቸው፡፡ በደረቅ መንገድ ማለት በማላዊ በኩል ነው፡ በውሃ መንገድ ማለት በታንዛኒያ በባህር አቋርጦ የሚኬድበት ነው፡፡ በታንዛኒያ ሞምባሳ በውሃ መንገድ ሶስት ሰው ተላከ፡፡ እኔ በውሃ ከተላኩት ሶስት ልጆች አንዱ ነኝ፡፡ ጉዞውን ከጀመርን በኋላ ደላላው አንድ ጫካ ውስጥ ወስዶ አስቀመጠን፡ ጫካ ስልሽ… በግራም በቀኝም ውሃ አለ፤ እኛ ደሴት ላይ ነው የተቀመጥነው፤ ለአንድ ወር፡፡ ጉዞውን ስንጀምር ሦስት ብንሆንም በየመንገዱ እየለቃቀሙ ጫካ ስንደርስ 63 ሰዎች ነበርን፡፡
ለምንድነው ጫካ የተቀመጣችሁት?
ጫካ ውስጥ የተቀመጥነው ባህሩን ለማሻገር ሰው አልሞላም ተብሎ ነው፡፡ በ24 ሰዓት አንዴ ነበር ምግብ የሚሰጠን፡፡ ምግቡም የበቆሎ ገንፎ ነበር፡ እሱንም የሚሰጡን ሰዎች አንዳንዴ ስለሚጠፉ “ኦቱጐሬ” የተባለ ዛፍ እየቆረጥን እንመገብ ነበር፡ የዛፉን ቅጠል ደግሞ ለመኝታ እንጠቀምበታለን፡ ውሃው ጨዋማ ስለሆነ ለመጠጣትም ሆነ ለመታጠብ ስቃይ ነበር፡፡
ቅጠል እየተመገብን …ህይወታችንን አቆየን፡ በጫካው ውስጥ የምንተኛው በየተራ ነበር፤ አንበሳና ሌሎች አውሬዎች ስላሉ ግማሾቻችን ስንጠብቅ ግማሾቹ ይተኛሉ፡፡ ከሁሉም ያስቸገረን ግን እባብ ነበር፡፡
ዝናብ ዘንቦ እስኪያባራ ቁጭ ብለን በዝናቡ እንመታለን፤ ፀሐይ ወጥታ እስክትጠልቅ እንሰጣለን፤ መጠለያ አልነበረንም፡፡ በቃ ህይወታችንን ለአንድ ወር በዚህ አይነት መልኩ አቆየናት፡፡
ታንዛኒያ ጫካ ውስጥ ለአንድ ወር ተቀመጣችሁ፡ከዚያስ?
ችግራችን ፀና፤ ቅጠል እየበላን ድርቀትና ህመሙ ፀናብን፡፡ ከዛሬ ነገ ሞትን እያልን አንድ ቀን ጉዞ ጀመርን - ባህሩን በጀልባ ለማቋረጥ ማለት ነው፡፡
በጀልባው ውስጥ በሶስት ቀን አንዴ ነበር የምንበላው፡ እሱም አለቀ ተባለና በባህሩ ላይ የሚተላለፉ ሌሎች ጀልባዎችና መርከቦች ኮቸሮ ሰጥተውን በላን፡፡ 11 ቀንና 11 ሌሊት ስንጓዝ 5 ቀን ብቻ ነው ምግብ ያገኘነው፡፡ ከዛ በኋላ የሚላስ የሚቀመስ አልነበረም፡፡ ዝናብ በላያችን ላይ ይዘንባል፤ ፀሐይ በላያችን ላይ ወጥታ ትጠልቃለች፡ ሞት አንዣበበብን፡፡ ከመካከላችን አንዱ ተጓዥ ሞተ፡ ከበርካታ ቀናት በኋላ ከጀልባ ስንወርድ እግራችን ሁሉ ተሳስሮ፣ መራመድ አቅቶን እንወድቅ ነበር፡፡ ጀልባው እኛን ጭር ያለ ጫካ ውስጥ ጥሎን ሄደ ፡ ሞዛምቢክ ደረስን ማለት ነው፡፡
ከዛስ ቀጣዩ ጉዞ ወዴት ነበር?
ኢትዮጵያኖቹ ሰብሰብ ብለን ተቀመጥን፡ሱማሌዎቹ ግን ጥለውን ሄዱ፡፡ ወዴት እንደሆነና ምን ስልት እንደዘየዱ አላውቅም፡፡ እኛ እዛው ተቀምጠን እያለ አንድ የሞዛምቢክ ገበሬ መጣ፡ “እናንተ ኢትዮጵያውያኖች ናችሁ?”ፈርተን ዝም አልን፡ ቀጠለና “ኢትዮጵያ? ሶማሌ? አለን፡ “ኢትዮጵያ” አልነው፡፡ “ሪፊውጂ (ስደተኞች ካምፕ )አስገባችኋለሁ፡፡ ምግብ አስመጣላችኋለሁ፤ አንዳንድ ዶላር አዋጡና ስጡኝ” አለ፡፡ ሰብስበን ሰጠነው፡፡
ምን ያህል አዋጣችሁ?
72 ነበርን፤ 72 ዶላር ሰጠነው፡፡ እኛ መሀል የዲፕሎማ፣ የዲግሪና የማስትሬት ምሩቅ ተማሪዎችም ነበሩ፡፡ ሶስት እንግሊዝኛ የሚችሉ ልጆች መርጠን ከሰውዬው ጋር ምግብ እንዲያመጡ ላክናቸው፡፡ ልጆቹ ምግብ ይዘውልን ይመጣሉ ብለን ስንጠብቅ በፖሊስ ተደብድበው ደም በደም ሆነው መጡ፡፡
እንዴት?
ለካስ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን የያዘ ይሸለማል፡ “ማንኛውም የሞዛምቢክ ገበሬ ስደተኛ ኢትዮጵያዊ ከያዝክ ቤትህ አስገብተህ አሰራው፤ በፖሊስ አስይዘው” የሚል ህግ መውጣቱን አላወቅንም ነበር፡፡ ያ ገበሬ ፖሊሶቹን ወደኛ ይዟቸው መጣ፡፡ በመሳሪያ ከበው ያዙንና ደብድበው ሞዛምቢክ ደረቅ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን፡፡
ደረቅ ፖሊስ ጣቢያ ምንድነው?
የሞዛምቢክ እስር ቤት ስም ነው፡፡ እንደገና እስር ቤት ወስደውን ገረፉን፤ የያዝነውን ዶላር፤ ያደረግነውን ጫማ፣ ልብሳችንን ጭምር ወስደው ፓንት ብቻ አስቀርተው ደበደቡን፡፡ ከዛም “ሪፊውጅ ሞልቷል፡፡ ተመልሳችሁ ብትመጡ እንገላችኋለን፡፡” ብለው አስፈራሩንና በመኪናና በጀልባ የሞዛምቢክና የታንዛኒያ ድንበር ላይ ወስደው ጣሉን፡፡ ከዛም እንደገና የታንዛኒያ ፖሊሶች ያዙንና እስር ቤት ከተቱን፡፡
ታንዛኒያ እስር ቤት ኢትዮጵያውያኖች ነበሩ?
በጣም ብዙ ነበሩ፡፡ በአንድ ክፍል ውስጥ 63 ሰዎች ታስረው ነበር፡፡ ምግብ በቀን አንዴ ነው የሚሰጠን፡፡ ምግቡ ስለማይስማማ ብዙዎቻችን ታመን ነበር፡፡
እስር ቤቱ ውስጥ “ፈንገስ” በተባለ በሽታ ብዙ ጓደኞቻችን አይነ ስውር ሆነዋል፡፡ ሰውነታቸው የቆሳሰለ ኢትዮጵያውያኖችም ነበሩ፡፡ ሌላው ችግር ስንታመም ከሃኪሞች ጋር በቋንቋ መግባባት ስለማንችል (ቋንቋቸው “ስዋሊኛ ነው) የሆድ ህመም መድሀኒት ስንጠይቅ የራስ ምታት እየሰጡን ለህመማችን መፍትሔ ሳናገኝ ስንሰቃይ ከርመን መጣን፡፡
አሁን ቤተሰብህ መመለስህን አውቋል?
አልነገርኳቸውም፡፡ ነገር ግን የእኛ አካባቢ ሰዎች የተመለሱ ስላሉ ከእነሱ መስማታቸው አይቀርም፡፡
ከአሁን በኋላ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ትሞክራለህ?
ደቡብ አፍሪካ ሞያሌ ነው ቢሉኝ እንኳን እግሬን አላነሳም፡፡
* * *
ተመስገን ላንገኖ ይባላል፡፡ 25 ዓመቱ ነው፡፡ እስከ ሶስተኛ ክፍል ተምሯል፡፡
ከአገሬ ሆሳዕና ጃጅራ ከተባለ ቦታ ተነስቼ ነው ወደ ደቡብ አፍሪካ ጉዞ የጀመርኩት፡፡ እንደ ጓደኞቼና ዘመዶቼ እሆናለሁ ብዬ ነው ለጉዞ የተነሳሁት፡፡
በእግሩ እያቆራረጠ ባህር ተሻግሮ ደቡብ አፍሪካ የገባ ወንድም አለኝ፡፡ እሱ ነው ለጉዞው ያነሳሳኝ፡፡
ወንድምህ ከሄደ ስንት ጊዜ ሆነው?
አራት ዓመቱ ነው፡፡ ኑሮው ተሻሽሏል፤ እሱም በገንዘብ አግዞኝ ነበር፡፡
ጉዞው እንዴት ነበር?
ከሆሳዕና እስከ ሞያሌ፤ ከሞያሌ ጋቦ፤ ከጋቦ ሴሎ፤ ከሴሎ ናይሮቢ፤ ከናይሮቢ ሞምባሳ፤ ከሞምባሳ የታንዛኒያ ገላን ባህር በጀልባ ተጓዝን፡ ከታንዛኒያ ተሻግረን የተወሰነውን በእግር ሄደን ሞዛምቢክ ደረስን፡ ሞዛቢክ ከደረስን በኋላ የሞዛምቢክ ፖሊሶች በዱላ ቀጥቅጠው ወደ ታንዛኒያ በጀልባ ዲፖርት አደረጉን፡፡
ይሄን ሁሉ መንገድ በመኪና ነው በእግር?
ከሆሳዕና ተነስተን እስከ ናይሮቢ ሞምባሳ ድረስ በመኪና ነው፡፡ የተወሰነውን በእግርና በጀልባ አቋርጠናል፡፡
ስንት ብር ከፈለክ?
35ሺ ብር ለደላላ ከፍዬአለሁ፡፡
35ሺ ብር ከየት አገኘህ?
ግማሹ የራሴ ነው፤ ሰርቼ ያገኘሁት ነው፡ ግማሹን ደቡብ አፍሪካ ያለው ወንድሜ ልኮልኝ ነው፡፡
እዚህ ምን ነበር የምትሰራው?
የወንድ ጫማ እሸጥ ነበር፡፡ ነጋዴ ነኝ፡፡ ከጐን ደግሞ ግብርና እሰራ ነበር፡፡
ጉዞ ላይ ችግር አልገጠማችሁም?
በህጋዊ መንገድ አይደለም የሚያጓጉዙን፡፡ ጫካ ለጫካ ነው የሚወስዱን፡፡ በየጫካው አንበሳ፤ ተናዳፊ እባብና አስፈሪ አውሬዎች ይገጥመን ነበር፡፡ ግን እግዚአብሔር ይመስገን ጉዳት አልደረስብንም፡ ሰው ይታመም ነበር፡፡ ሊሞት የሚያጣጥር ነበር፡፡ በጣም ጭንቅ ነው፡፡ ከሁሉም የማልረሳው የሞምባሳ ጫካ ውስጥ የነበረንን ሁኔታ ነው፡፡
እስቲ ንገረኝ?
ሞምባሳ ጫካ ከደረሰን በኋላ ደላላው አላሻግርም አለ፡፡ ከዛሬ ነገ ወደ ጀልባ ትወጣላችሁ እያለ ሲዋሸን፣ አንድ ወር ሙሉ አውሬ በላኝ፣ እባብ ነደፈኝ እያልኩ እየተጨናነኩ ስፀልይ ከረምኩ፡፡ አንድ ታንዛኒያዊ እየመጣ በቀን አንዴ ዳቦና ሻይ፤ ማምሻ ላይ ሩዝ ቆንጥሮ ይሰጠን ነበር፡፡ በተረፈ ሜዳ ላይ ተኝተን ነበር የምናድረው፡፡ በየቀኑ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ባህር ለመሻገር ይመጣሉ፡ እዛው ቦታ ላይ ተሰጥተን እናድራለን፡፡ በብዛት ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ነበርን፡፡ ከወር በኋላ ባህር አሻገሩን፡፡
እንዴት ነበር የባህር ላይ ጉዞዋችሁ?
አስር ቀንና እና አስር ሌሊት ተጉዘን ነው መሬት የረገጥነው፡፡ የባህሩ ሽታና ጨዋማነት አስጨንቆን በንፁህ አየር እጦት፤ ወደ ላይና ወደ ታች ይለን ነበር፡፡ ጭንቀቱን ምን ልንገርሽ…ራስን ባህር ውስጥ ለመወርወር ያስመኛል፡፡
ባለ ጀልባዎቹ እንድንፀዳዳ አይፈቅዱልንም፡ ስንጠይቅ ዱላውና ድብደባው መከራ ስለሆነ ብዙዎቻችን እዛው እንደተቀመጥን እንፀዳዳ ነበር፡ከቤት ከወጣን ቀን ጀምሮ ርሃብና እንግልት ብቻ ነበር፡፡
ባህሩን ከተሻገራችሁ በኋላስ ምን ገጠማችሁ?
ሞዛምቢክ ደረስን፡፡ እንደደረስን ግን የሞዛምቢክ ፖሊሶች ያዙን፡፡ አስተኝተው ጭንቅላት ወገብ ብለው ሳይለዩ በዱላና በሰደፍ ቀጠቀጡን፡፡ ብዙ ጓደኞቻችን ቆሳስለዋል፡፡ አካል ጐደሎ የሆኑም አሉ፡
ምን ብለው ነው የደበደቡዋችሁ?
“ሪፊውጅ ሞልቷል፤ ለምን መጣችሁ? ሪፊውጅ በእናንተ አገር ዜጐች ተጠቅጥቋል አትድረሱብን” ብለው ነው የደበደቡን፡፡ “ከእንግዲህ ለሌሎችም ንገሩ፤ አትምጡብን” ብለውናል፡፡ ከዛ በጀልባ አሻግረው ታንዛኒያ ድንበር ላይ ጣሉን፡፡
ከዚያስ?
ከአሻገሩን በኋላ ግማሾቻችን ደክመናል፤ ታመናል፤ ስለዚህ አይናችን እያየ ከምንሞት እጃችንን እንስጥ ብለን ተስማማን፡፡ እጃችንን ሰጠንና “ፍሪዞኒ” የተባለ የታንዛኒያ እስር ቤት ውስጥ ሰባት ወር ታሰርን፡፡
እስር ቤቱ እንዴት ነበር?
አገር ቤት ያለሽ ነው የሚመስልሽ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን በግቢው ውስጥ ይርመሰመሳሉ፡ሰባት መቶ አካባቢ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያኖች ነበሩ፡፡ በየቀኑ ደግሞ ቁጥራቸው ይጨምራል፡፡
ጠዋት በቆሎ ተበጥብጦ በኩባያ ይሰጠናል፤ እሱን ጠጥተን ማታ ላይ ደግሞ የበቆሎ ገንፎ ይሰጡናል፡ ሽንት ቤቱና መኝታው አንድ ነው፡ የሚታመመው እስረኛ ስፍር ቁጥር የለውም፡፡
ይህ በሽታ በአንድ ክፍል ታጉረው በሚኖሩ እስረኞች ላይ እየተዘዋወረ ብዙዎችን ገላቸውን አበላሽቷል፡፡ (እጁን ዘርግቶ አሳየኝ፡፡ ጥቁር ነው፤ ውሃ አጥቶ የተሰነጣጠቀ ጥቁር መሬት ይመስላል) ቋንቋ ስለማናውቅ በምልክት ነው የምናወራው በሽታችንን ይህ ነው ብለን ለመናገር እንቸገር ነበር፡፡ በታንዛኒያ እስር ቤት የወንዱ ኢትዮጵያዊ ግፍና ሰቆቃ ተነግሮ አያልቅም፡፡ ወንዶች የሚደርስባቸው ግፍ ይህን ነው አልልሽም፡፡
ሴቶችም ነበሩ?
እንኳን ለሴት ለወንዱም አይበጅ፡፡ ሴቶችም ነበሩ፡ በየመንገዱ የደረሰብን ግፍ… ወንዱ በወንዱ ላይ… (በፀፀት አጐነበሰ) ከሰባት ወር በኋላ መምጣቴ ግን አስደስቶኛል፡፡
ቤተሰቦችህ ስለደረሰብህ ችግር ያውቃሉ?
አያውቁም፡፡ መንገድ ላይ ምን እንደገጠመኝ …ልኑር ልሙት ምንም ነገር አያውቁም፡፡ ምናልባት እንደሞትኩ ያስቡ ይሆናል፡፡
ዛሬ ወደ ትውልድ ቀዬህ ልትመለስ ነው?
(ሳቅ) አዎ ዛሬ ወደ አገሬ ልሄድ ነው፡፡
ከአሁን በኋላስ ተመልሰህ ለመሰደድ ታስባለህ?
እግሬን አላነሳም፡፡ ሞቴን በአገሬ ያድርገው፡ ከአሁን በኋላ እርሻዬን እሰራለሁ፤ ንግድም እነግዳለሁ፡፡ እንደ እኔ ባህር አቋርጠው ለመሄድ ያቀዱ ካሉ የደረሰብኝን ሁሉ እነግራቸዋለሁ፤ ተው እላቸዋለሁ፡፡

 

Read 3223 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 07:42