Saturday, 27 April 2013 10:31

በአዲስ አበባ ከሚገኙ 26 የትራፊክ መብራቶች የሚሰራው አንዱ ብቻ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

በአዲስ አበባ ከሚገኙ 26 የትራፊክ መብራቶች አገልግሎት የሚሰጠው አንዱ ብቻ በመሆኑ የትራፊክ መጨናነቅና የአደጋ መንስኤ ከመሆኑም በላይ በትራፊክ ፖሊሶች ላይ ከአቅም በላይ የሆነ የስራ ጫና መፈጠሩ ተገለፀ፡፡ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠሩት የከተማዋ የትራፊክ መብራቶች ሲበላሹ ጥገና ስለማይደረግላቸው ለበለጠ ብልሽት እየተዳረጉ ከጥቅም ውጪ እንደሆኑ የተናገሩ አሽከርካሪዎች፤ የትራፊክ መብራቶቹ በፍጥነት ታድሰው ወደ ሥራ ካልገቡ፣ አሁን የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅና የመኪና አደጋ ሊያባብስ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

ከስታዲዬም መገናኛ ባለው መስመር የሚሰራው የታክሲ ሹፌር ዮሐንስ ጥጋቡ፤ ቀደም ሲል የለገሃሩን ሳይጨምር አምስት ቦታዎች ላይ የትራፊክ ማሳለጫ መብራቶች የነበሩ ቢሆንም አሁን አንዳቸውም እንደማይሠሩ ገልፆ ፤ በተለይ መስቀል አደባባይ እና እስጢፋኖስ ቤ/ክርስቲያን እንዲሁም ለም ሆቴል አካባቢ የመብራቶች አለመኖር ለመኪና አደጋ መከሰት ሰበብ ሲሆኑ መታዘቡን ይናገራል፡፡ ለገሃር አካባቢ በሥራ ላይ ያገኘናቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ ፤ የመብራቶቹ መበላሸት የስራ ጫና እንደፈጠረባቸውና ሌሎች የደንብ መተላለፎችን በትኩረት እንዳይከታተሉ እንዳደረጋቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ “ቀኑን ሙሉ መብራት በሌላቸው ቦታዎች ተሽከርካሪዎችን እያስተናበሩ መዋል በራሱ ከፍተኛ ድካም አለው” ብለዋል - የትራፊክ ፖሊሱ፡፡ የአዲስ አበባ ትራፊክ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡ በዚህ ይስማማሉ፡፡

የመብራቶቹ መበላሸት በአባሎቻቸው ላይ የስራ ጫና ከመፍጠሩ ባሻገር አደጋን በማባባስም ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡ ግንባታቸው በተጠናቀቁ የመዲናዋ መንገዶች ላይም የመብራት ተከላው በፍጥነት ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ያመለከቱት ዋና ሳጅን አሰፋ፤ የትራፊክ መብራት መኖር ለትራፊክ ፖሊሶችም ሆነ ለእግረኞች ደህንነት ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ፤ እነዚህን ዘመናት ያስቆጠሩ የትራፊክ መብራቶች ሙሉ ለሙሉ በአዲስ ለመተካት በቅርቡ ጨረታ አውጥቶ ሁለት ድርጅቶች ማሸነፋቸውንና በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ የባቡር መስመሩ በማያልፍባቸው ቦታዎች እንዲተክሉ መወሰኑን ገልጿል፡፡ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን ስራ እንዲከታተሉ በስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የተመደቡት አቶ ጌታቸው ሞላ፤ በከተማዋ በ26 ቦታዎች የትራፊክ መብራቶች እንዳሉ ጠቁመው፤ በአሁን ሰአት ፖስታ ቤት አካባቢ ያለው አንዱ መብራት ብቻ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የትራፊክ መብራቶች በተለያዩ ምክንያቶች ከአገልግሎት ውጭ እንደሚሆኑ የገለፁት አቶ ጌታቸው፤ ከመንገድ ስራዎች ጋር በተገናኘ በሚፈጠር የኤሌክትሪክ መስመሮች መቆራረጥ እንዲሁም ከእድሜ ብዛት በሚከሰት ብልሽት ከአንዱ በቀር 25ቱም አገልግሎት ማቋረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

የተበላሹትን ለማስጠገን በሚደረገው ጥረትም የመለዋወጫ ችግር በተደጋጋሚ ያጋጥማል ይላሉ፡፡ በአሁን ወቅት የመለዋወጫ እቃዎቹ በገበያ ላይ እንደሌሉ የገለፁት ሃላፊው፤ ኩባንያዎች “እስካሁን ይሄ እቃ አለ እንዴ?” በማለት በአግራሞት እንደሚጠይቋቸውና ዘመን ያለፈበት መሆኑን እንደሚነግሯቸው ይናገራሉ፡፡ ቀደም ሲል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመለዋወጫ እቃዎችን ከደህናው ወደተበላሸው በማቀያየር ሲጠግን መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፤ ይህ አሰራር የማያዛልቅ መሀኑ ስለታመነበት ችግሩን ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ዘመኑ የሚፈቅደውን የመብራት አይነት መጠቀም አስፈልጓል ይላሉ፡፡ በከተማዋ የሚገኙት 26 የትራፊክ መብራቶች ሙሉ ለሙሉ በአዲስ እንደሚቀየሩና በሾላና በአራት ኪሎ እንዲሁም በሌሎች የትራፊክ ፍሰቱ በሚያይልባቸው አካባቢዎች አዳዲስ መብራቶች እንደሚተከሉም ገልፀዋል፡፡

Read 2398 times