Saturday, 27 April 2013 10:43

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(8 votes)

     መልክአ ኢትዮጵያ - ፲፭

ከየሆቴሉና ሬስቶራንቱ የሚሰበሰቡ ትርፍራፊ ምግቦች በጉርሻ ምጣኔ ከሚቸረቸርባት፣ ከየቤቱ የተራረፈው ለነዳይ ከሚመጸወትባት አገር ወደ ባሕር ማዶ ለተሻገሩቱ ኅሊናቸውን ከሚሞግታቸው ነገሮች አንዱ ትራፊ ምግብ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ መድፋት ነው፡፡ ልጅ ኾኜ በማዕድ ላይም ይኹን በአጋጣሚ ብጣቂ እንጀራ ካንጠባጠብኩ ‹‹ዋ! የእህል ጡር አለው›› የሚለው የአያቴ ቁጣ አዘል ማስጠንቀቂያ አይቀርልኝም፡፡ አያቴ ልጆቿንም ያሳደገችው ይህን ዐይነቱን ማስጠንቀቂያ እየነገረች ነበር፡፡ ልጆቿም ኾኑ የልጅ ልጆቿ ጡሩ ወደፊት ጦስ እንዳያመጣብን በመስጋት ተልከን ይኹን ወደ ትምህርት ቤት ስንሄድ መንገድ ላይ የወደቀ እንጀራ አልያም ዳቦ ካገኘን ቢያንስ ወፎች እንዲመገቡት በሚል እናነሣና የተሻለ ቦታ እናስቀምጠው ነበር፡፡

መቼም በአሜሪካ ከሚኖረው ሐበሻ የሚበዛው ምግብ ነክ ነገርን መድፋት ይቅርና አንጠባጥቦ መተው ‹‹ጡር›› መኾኑ ከወላጅ ከጎረቤት ሳይመከር ያደገ ያለ አይመስለኝም፤ ነገር ግን የተረፋቸውን ምግብ ያለስጋት ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ሲዘረግፉት መመልከት እንደከበደኝ ሰንብቷል፡፡ ወዲህም ደግሞ አሜሪካ የአገራችንን ሴቶች ጡር ቆጥራ አግኝቻታለኁ፡፡ ወፍ ሲንጫጫ ተነሥታ ያለትዳር አጋሯ ብቻዋን ስትዳክር ውላ እኩለ ሌሊትን አሳልፋ ትተኛ የነበረችው አያቴን እያስታወስኹ፣ ምናለ አያቴ ‹‹የሴት ልጅም ጡር አለው›› እያለች ባሳደገችኝ ብያለኹ፡፡ ከደመወዙ ለኪሱ አስቀርቶ የወር አስቤዛ ከመስጠት ውጭ ከቤት ውስጥ ጫና ራሱን አግልሎ ሲኖር የነበረውን የአገሬን ወንድ ሁሉ በአሜሪካ ለቤቱ እንደ አገሬ ሴቶች ኾኖ አይቼዋለኹ።

                           *******************

አቶ አንተነህ በተማሪነቴ ከማስታውሳቸው መምህራን አንዱ ነበር፡፡ አንተነህ ከሚኖርበት አዲስ አበባ ተወልጄ ወዳደግኹባት ድሬዳዋ ከተማ የሚመጣው በአንድ አጥር የሚጎራበቱንን ወላጆቹን ለመጠየቅ ነበር፡፡ በወቅቱ በዲግሪ ተመርቆ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ይሠራ ስለነበር ነፍሳቸውን ይማረውና አባቱ አባባ ተሰማ ሁሌም ከአፋቸው የማይለዩት ኩራታቸው ነበር፡፡ በየዓመቱ ሁለት ሦስት ጊዜ በተለይ በአጥቢያችን በደመቀ ኹኔታ ለሚከበረው የታኅሣሥ ገብርኤል ባለቤቱንና ሁለት ሴት ሕፃናት ልጆቹን ይዞ ለጥየቃ ይመጣ ነበር፡፡ መቼም ያኔ እንዲህ እንደ አሁኑ ጊዜው ሳይበላሽ የጎረቤት እንግዳ የራስ ነውና ልጆቹን የማጫወት ሓላፊነት የኛ የጎረቤት ልጆችም ጭምር ነበር፡፡ በዚህ ላይ እንግዶቹ የሚመጡት ከአዲስ አበባ በመኾኑ የተለየ ነገር ለማየት ሥር ሥራቸው እያልን ስለእያንዳንዷ እንቅስቃሴ በትኩረት እንከታተላለን፡፡

ሁለት ልጆቿን ይዛ ባሏን ተከትላ አማቾቿ ቤት በእንግድነት ትመጣ የነበረችው ባለቤቱ ሮዛ አንድ ቀን እንደ ባሏ ተረጋግታ ስታርፍ አይቻት አላውቅም፡፡ ጥዋት ተነሥታ ልጆቿን አጣጥባ ምግብ ሠርታ ታበላለች፡፡ ትዝ የሚለኝ ሁለተኛ ልጇ አንድ ቦታ ላይ ቆማ ስለማትበላላት ግቢ ለግቢ አብራት እየተሯሯጠች ትመግባታለች፡፡ ቀጥሎም ምሳ ወደ ማዘጋጀት ትሻገራለች፡፡ እንደ ቁርሱ ሁሉ ምሳ አብልታ አጣጥባ ታስተኛና ወደ ራት ትዞራለች። አገሩ ሞቃት ስለኾነ ሕፃናቱ ድሬ በመጡ ቁጥር ገላቸው ላይ ሽፍ የሚል ነገር ይወጣባቸዋል፡፡ እሱን መድኃኒት ስትቀባ ከልቅሷቸው ስታባብል ትውላለች፡፡ የልጆቹ ሙሉ ሓላፊነት የወደቀው እርሷ ላይ ነበር፡፡

አዲሳባ ቤቷ ውስጥ ስትኾን ደግሞ ሌላም ሥራ የሚደራረብባት ናት፡፡ እርሷ እንዲህ ስትባትል አንተነህ ግን ግቢው ውስጥ በሚገኝ የዛፍ ጥላ ሥር የመሬት ላይ መቀመጫ ምንጣፍ በጥሩ ኹኔታ ተሰናድቶለት እርሱ ሲመጣ ጎራ ከሚሉት ጓደኞቹ ጋራ ጫት እየቃሙ ይጨዋወታሉ፡፡ የልጅነትና የተማሪነት ጊዜያቸውን እያነሡ በሣቅ ሲደሰቱ ይውላሉ፡፡ ጨዋታቸው ሌሎችንም ለሣቅ የሚጋብዝ በመኾኑ የሌላውን ቤተሰብ ትኩረት የሚስቡት እነርሱ እንጂ ከልጆቿ ጋራ የምትዳክረው ሮዛ አልነበረችም፡፡ በተለይ ከምሳ በኋላ ሮዛን የሚያስታውሳት አንድም ሰው እንዳልነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ምግብ በመሥራት ሊያግዛት ፍላጎት ያለው እንኳን ቢኖር አንተነህ፣ ‹‹የእኔ ልጆች እናታቸው ከሠራችው ውጭ አይበሉም›› እያለ ስለሚፎክር ሊረዳት የሚያስብ አልነበረም፡፡ ከእርሷ ውጭ ወላጅ እናቱ እንኳን የልጆቹን ምግብ እንዲሠሩ አይሻም ነበር። እርሱ በደስታ እየተፍለቀለቀ ልጆቹ ወደርሱ መሄድ ቢያዘወትሩ ‹‹ሮዛ፣ ያዣቸው እንጂ›› በማለት ባለቤቱን በትእዛዝ ቃል ሲናገራት አስታውሳለኹ፡፡

የወር ደመወዝ ከሚያገኝበት ሥራው በቀር ሓላፊነት ያልነበረበት የድሮው አንተነህ ከዓመታት በኋላ አሜሪካ አገኘኹት፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ያዘጋጀው የጉብኝት መርሐ ግብር አብቅቶ ዘመድ ጓደኞቼን ለመጠየቅ ጎራ ካልኩባቸው መኖሪያ ቤቶች አንዱ በካሊፎርኒያ የሚገኘው የእነ አንተነህ ቤት ነበር፡፡ አንተነህ ቤተሰቡን ይዞ አሜሪካ ከገባ ቆይቷል፡፡ አንድ ሴትና ወንድ ልጅ በመድገሙ አራት ልጆቹን አፍርቷል፡፡ ቤተሰቡ ከሚኖርበት ከተማ ሥራ ቦታው ድረስ በየቀኑ የአራት ሰዓት የደርሶ መልስ መንገድ ይነዳል፡፡ እንዲህ ተመላልሶ መሥራቱ የቤት ውስጥ ሓላፊነትን ከመጋራት አላስጣለውም፡፡ ከቤት ማጽዳት ጀምሮ በማሽንም ቢኾን እስከ ልብስ ማጠብ፣ ከቡሆ እስከ ጋገራ ባለው የማዕድ ዝግጅት ተሳታፊ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ምግቡ እንዳይበላሽ ቆራርጦ በላስቲክ አሽጎ ፍሪጅ ውስጥ ማስቀመጥ ከባለቤቱና ልጆቹ ጋራ ተራ ገብቶ ይሠራል፡፡ የልጆቹን ትምህርትና ኑሮ መከታተል፣ የሚያስፈልገውን ወጪ በሙሉ ተሳስቦ ማገዝ፣ ገበያ ወጥቶ መሸማመት የእርሱም የተለመዱ ሥራዎች ናቸው፡፡

በእንግድነቴ ማግሥት ማምሻውን ከሥራ ሲመለስ ራሱ አቡክቶ ያዘጋጀውን ሊጥ ለመጋገር ዝግጅት ጀመረ፡፡ የእንጀራ ጋገራ ተራው የእርሱ በመኾኑ ካሊፎርኒያ ውስጥ የሚመረት ነው የተባለለትን የጥቁር ጤፍ እንጀራ በአነስተኛዋ ምጣድ ላይ በጥንቃቄ እያሰፋ የበሰለውን በመሳቢያ ሳብ እያደረገ ሲያወጣ ስመለከተው ዐይኔን ማመን አቅቶኛል፡፡ የመጨረሻውን ልጁን አጥቦ፣ ልብስ ቀይሮና መግቦ አብልቶ ሲያስተኛ ሳየውማ እነርሱ የረሱትን የድሬዳዋ ታሪካቸውን እያስታወስኹ መሣሣቅ ጀመርን፡፡ አንተነህ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ተግባራትን ከባለቤቱና ልጆቹ ጋራ ተራ ገብቶ ይከውናል። በውጭ ሠርቶ የሚያመጣውን ገንዘብ ሰጥቶ ሌላውን ሓላፊነት ለሮዛ በመተው እንደ ኢትዮጵያ እግሩን ሰቅሎ ጫት እየቃመ ሲሥቅ መዋል በአሜሪካ የለም፡፡ የአገሩ ሕግ ለእንዲህ ያለው የቤት ውስጥ አስተዳደር ቦታ የለውም፡፡ ሮዛና አንተነህ በአንድ ቤት እስከ ኖሩ ድረስ እያንዳንዷ ሓላፊነት የጋራ ናት፡፡ ሮዛም እንደ ትውልድ አገሯ ከአንድ ቤተሰብ የአንድ ሰው ደመወዝ በሚጠበቅበት አገር ላይ ባለመኾኗ አሜሪካ ላይ የቤት እመቤት አይደለችም፡፡ ጥራ ግራ ሠርታ ትገባለች፡፡ ሁለቱም እኩል ሠርተው የተካለለ ሓላፊነት ወስደው ይኖራሉ፡፡

ከዚህ ዐይነቱ የኑሮ ዘይቤ ውጭ ‹‹እጄን ኪሴ ከትቼ ቀብረር ብዬ የወር አስቤዛ ብቻ እየሰጠኹ እኖራለኹ›› የሚል አባወራ ካለ ትዳሩን አይፈልገውም ማለት ነው፡፡ ሴቶቹ እንዲህ ያለውን ነገር በኢትዮጵያ የሚታገሡትን ያህል በአሜሪካ አይታገሡትም፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው ገቢ ስለሚኖራቸው የባል ገንዘብ ለቤት ውስጥ የሥልጣን መመኪያ ኾኖ አያገለግልም፡፡ ተስማምተውና ተከባብረው እንደ አገሩ ሕግ ካላደሩ ይፋታሉ፡፡ ጠብ ቢነሣ ‹‹ሴት ነሽ፤ ቤትሽንና ጓዳሽን ጥንቅቅ አድርገሽ መያዝ አለብሽ፡፡ ወንድ ልጅ እንዴት ጓዳ ይገባል›› ብሎ የሚያስታርቅ ሽማግሌ በአሜሪካ የለም፡፡ ትዳሩን የፈለገ ከሚስቱ እኩል የልጁን ዳይፐር እየቀየረ ይኖራል፡፡ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ወንዶች ወደ አሜሪካ ሲያቀኑ ስለ ቤት ውስጥ ሞያ የሚያውቁት ነገር ባለመኖሩ ግራ ይጋባሉ፡፡ በዝና የሚያውቁት “እኩልነት” ዐይኑን አፍጥጦ ሲመጣ ይደናገራሉ፡፡ እየቆዩ ሲሄዱ ግን ይላመዱታል፡፡ በዲቪ ሎተሪ ከስምንት ዓመታት በፊት አትላንታ በገባው ዘመዴ ቤት በቆየኹ ጊዜ ያስተዋልኁትም ይህን ነው፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ስለገጠመው ነገር አጫወተኝ፡፡

አትላንታ እንደገባ የተቀበለው ጓደኛው በአንዱ ቀን ምሽት ሊያዝናናው ጓደኞቹን ሰብስቦ ይዞት ይወጣል፡፡ ወደ መዝናኛ ቦታው በመኪና እየሄዱ መኪና ውስጥ ካሉት ሴቶች አንዷ የያዘችው የስልክ ወሬ ቀልቡን ስቦት ጆሮውን ቀስሮ ያዳምጣል። ወጣቷ ‹‹አንድ ጊዜ ወደ ላይ ሲመጣ በጣም ሳታሸው መልሰውና ሁለተኛው ሲመጣ ኦቭኑ (የኤሌትሪክ ዳቦ መጋገሪያ) ውስጥ ክተተው፤ ትንሽ ቆይተኽ ለኩሰው፤ ቤቢ ከመተኛቱ በፊት ዳይፐሩን ቀይርለት፤›› እያለች ታወራለች፡፡ ወጣቷ ትእዛዙን የምትሰጠው እርሷ ከቤት ስትወጣ ከሥራ ውሎ ለገባው ባለቤቷ መኾኑን የተረዳው ዘመዴ የራሱ መጪ ኹኔታው አሳስቦት ሥቅቅ ይላል፡፡ ወንድ ልጅ ከሥራ ወደ ቤት ሲገባ ሴት ልጅ ለመዝናናት ወደ ውጭ ያውም አቡክታ የወጣችውን ሊጥ እንዲጋግር እያዘዘች መኾኑን ሲረዳ አልዋጥልኽ ይለዋል፡፡

ይህን ከነገረኝ ከቀናት በኋላ እርሱ ከቤት ቀርቶ ሁለት ልጆቹን ሊይዝ፣ ባለቤቱ ደግሞ እኔን ገበያ ልታሳየኝ ተስማምተው እኔና እርሷ ተያይዘን ወጣን። መንገድ ላይ እየሄድን ሳትነግረው የወጣችውን መልእክት አስታውሳ፣ ‹‹ድቅቅ አድርገኽ ፍጨውና ጥደኽ ውኃ ጨምረኽ አማስለው፤ ትክትክ ሲል አብላቸው፡፡ እኛ ስለምንቆይ ምሳኽን ሠርተኽ ብላ›› ስትል በስልክ ነገረችው፡፡ ከዳቦ ጋገራው ምሳሌ የማይተናነሰውን ትእዛዝ ስሰማ፣ ‹‹አሁንማ ለምጄዋለኹ›› ያለኝን የዘመዴን ንግግር አስታውሼ እውነትም ለምዶታል፤ እርሱም ከእነርሱ እንደ አንዳቸው ኾኗል አልኩ፡፡፡

                                               *******************

የእህል እንጂ የሴት ልጅ ጡር ያልተገለጠላት፣ ለደረሱት ወንድ ልጆቿ ‹‹የእገሌ ልጅ ትሻለዋለች…የእገሌ ልጅ›› እያለች ከልጆቹ አልፋ አሳዳጊዎቻቸውን ጭምር እያማረጠች እንዳሻት ስትድር የነበረችው አያቴ በአሜሪካ ያለውን የሚስት እጥረት ብታይ ምን ትል ይኾን? በአሜሪካ ሚስት አማርጦ ማግባት የለም፡፡ የዐሥራ አንድ ዓመት ልጅ ሳትቀር ያለፍላጎቷ ተጎትታ ከምትዳርበት አገር የሚሰደዱት ወንዶች አሜሪካ ደርሰው ዕድል ከሚቀናቸው ጥቂቶቹ በቀር ‹‹የሚስት ያለህ!›› ማለታቸው የማይቀር ነው፡፡ ጋብቻና ፍቺ በአሜሪካ ብዙ ታሪክ አላቸው። ተጋቢዎቹ ኢትዮጵያውያን ቢኾኑም ኑሯቸው ግን ከኢትዮጵያ በብዙ ይለያል፡፡ ሕግና ሥርዐቱን ጠብቀው የሚኖሩ የተሳካላቸው ባለትዳሮች ተግባብተው ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ፡፡ ያልተካላቸው ደግሞ የአሜሪካንን የፈቶች ሰንጠረዥ ይቀላቀላሉ። ጥቂት የማይባሉ ትዳር ፈላጊዎች ጥሪት ቋጥረው ወደ አገር ቤት ያቀናሉ፡፡ ራሳቸው ሞክረው ካልተሳካላቸው በወዳጅ ዘመድ አማካይነት የትዳር አጋር ፍለጋ ይገባሉ፡፡ እርስ በርስ ተፈላልገው በፍቅር ለተጣመሩ ባለትዳሮች አሜሪካ ቀና ናት፡፡

በየወሩ የሚመጣባቸውን ቢል በጋራ ይከፍላሉ፡፡ ተሳስበውና ተጋግዘው ይኖራሉ፡፡ ማንኛውንም ጉዳይ ተመካክረው ይፈጽማሉ፡፡ ቀና ትዳር ያላቸው ከኾኑ ከዚህም በላይ ይተጋገዛሉ፡፡ ቤተሰቦቻቸውን በጋራ ይረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤት ይኹን ሌሎች ቢዝነሶችን የሚሠሩም ከኾነ በጋራ ይገነባሉ። ዋሽንግተን ያገኘኹት ዘመዴ ስለ ባለቤቱ ሲያጫውተኝ÷ “የአሜሪካን አገር ነጋዴዎች ካልነቃሽባቸው ያሳብዱሻል፡፡ ራሄል (ባለቤቱን ማለቱ ነው) የነጋዴዎቹ ሰለባ ነበረች፡፡ ቦርሳዋ ውስጥ ከዐሥር በላይ የዱቤ ካርዶች ነበሯት፡፡ በየሄደችበት ሱቅ የአባልነት ካርድ መውሰድ ቅናሽ እንደሚያስገኝ ስለሚያሳምኗት በወሰደችው ካርድ በዱቤ ዕቃ ትገዛለች፡፡ በዛ ላይ በየቀኑ በሚላኩ ጋዜጣና መጽሔቶች ላይ የሚገኙ የቅናሽ ኩፖኖችን እየተከታተለች ትገዛለች፡፡

እርሷ የምታየው ያገኘችውን ቅናሽ እንጂ የምታወጣውን ገንዘብ አልነበረም፡፡ አገር ቤት ያሉት ቤተሰቦቿም ላኪ ያሏትን ዕቃ ሁሉ የለኝም ላለማለት ዱቤ ወስዳ ትልክላቸዋለች፡፡ ወር ላይ የቤት የወር ክፍያና የመኪና ዕዳን ጨምሮ ሁሉም ሱቆች የየድርሻቸውን ከደሞዟ ስለሚወስዱ ምንም ገንዘብ አይተርፋትም፡፡ እንዲያውም ለሁሉም ስለማይበቃት የምትንቀሳቀሰው በዕዳ ነው። አሁን ግን አስተካክያታለኹ፡፡ ያለባትን ዕዳ በሙሉ ከፍላ ባላት አቅም በዕቅድ ካልኾነ ምንም ነገር በዱቤ አትወስድም፤›› ብሎኝ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ሚስት አግብተው የሚወስዱም ሰዎች የትዳር አጋራቸው በተሳሳተ መሥመር ከሚጓዙ ሰዎች ጋራ ገጥመው ኑሯቸው እንዳይናጋባቸው ይጠነቀቃሉ፡፡ በተለይ ለአልባሳትና ለታይታ ለሚኾኑ ቁሳቁሶች ከፍተኛ ገንዘብ በሚያስወጡ ነገሮች ተታለው ያለአቅማቸው በዕዳ እንዳይዘፈቁ ስለሚሰጉ የነቁ ጓደኛ ይመርጣሉ፡፡

                                              *******************

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መልክአ መልኮች በርካታ ነው፡፡ ከለመዱት የአገራቸው ባህልና ወግ ተነጥለው ከወዳጅ ዘመዶቻቸው በብዙ ርቀው በሰው አገር ባህል፣ ወግና ሕግ ታስረው ስለሚኖሩ እንደየአቅምና ችሎታቸው ተጋፍተውና ተጋፍጠው ይኖራሉ፡፡ ሁሉንም አሸንፈው የሰው አገር መኾኑ ሳይበግራቸው በትምህርትና በሥራቸው ተሳክቶላቸው ተጠቃሽ የኾኑ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ ከታዋቂ ነጋዴ እስከ ፕሮፌሰር፡፡ ከናሳ የጠፈር ምርምር ማእከል እስከ ሆሊዉድ የመዝናኛ ኢንደስትሪ የዘለቁ፡፡ ከዕውቅ ሞዴል እስከ ዓለም አቀፍ ዲዛይነር፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ እስከ የተለያዩ የምርምር ማእከላት የኢትዮጵያውያን ሞያ ያልገባበት ዘርፍ የለም፡፡ በተሰባሰቡበት ሁሉ አንድ ላይ ኾነው ችግር እንዳይገጥማቸው ቢሳካላቸውም ባይሳካላቸውም ትንሿን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ይሞክራሉ። በአገራቸው ፖሊቲካዊ ጉዳይ ቢስማሙም ባይስማሙም በዐደባባይ ወጥተው ውስጣቸው እስኪታመም ቢጯጯኹም በሰው አገር ጥረው ግረው ከሚያገኙት ገቢ ላይ አገር ቤት ላሉ ዘመዶቻቸው ለማካፈል አይሰስቱም፡፡ የተሳካላቸው ኑሯቸውን በአግባቡ እየኖሩ ከተረፋቸው ላይ ቤተሰቦቻቸውን ሲያግዙ አብዛኞቹ ግን እነርሱ ተቸግረው ቤተሰቦቻቸውን ይረዳሉ፡፡ አትላንታ ከተማ ውስጥ ቁጥራቸው በርከት ያሉ በኢትዮጵያውያን የሚተዳደሩ ንግድ ቤቶች ይገኛሉ፡፡

የሴት እና የወንድ ፀጉር ቤቶች፣ የአገር ባህል ልብስና ቅርጻ ቅርጽ መሸጫዎች፣ በርካታ ባህላዊ ሬስቶራንቶች፣ ሱፐር ማርኬትና ሥጋ ቤቶችና ሌሎች የንግድ ቤቶች ባለቤቶቻቸውም ኾነ ሠራተኞቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በወ/ሮ ኤልሳ የሚተዳደረው ‹‹ኤልሳ ማርት›› ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ኤልሳ የደስ ደስ ያላት ተጫዋች ናት፡፡ መጀመሪያ አሜሪካ የገባችው ብቻዋን እንደኾነ አጫውታኛለች። ባለቤቷና ልጆቿ እስኪመጡ በርካታ ውጣ ውረዶችንም አሳልፋለች፡፡ ብቻዋን ዕንቅልፍ አጥታ ሠርታም ነገሮች ተሳክተው ባለቤቷና ሦስት ልጆቿ ከእርሷ ጋራ ሲቀላቀሉ ቤት ገዝታ ነበር የጠበቀቻቸው፡፡ ከስምንት ዓመት እልክ አስጨራሽ ትግል በኋላ ኑሮ ዛሬ ቀና ኾኖላታል፡፡ ሴት ልጇን ድራ የልጅ ልጅ አይታለች፡፡ ሁለት ወንድ ልጆቿን ዘንድሮ በኢንጂነሪንግ ታስመርቃለች፡፡ ብርቱዋ ኤልሳ ሁለተኛ ቤትም እዛው ገዝታለች፡፡ አሁን ሱፐር ማርኬቱንና ምግብ ቤቱን ከባለቤቷ ጋራ ያስተዳድሩታል፡፡ ተቀጣሪ ሠራተኞችም አሏቸው። ወ/ሮ ኤልሳን በቅርበት የሚያውቋት ‹‹ለማንም የጥንካሬ ምሳሌ ናት፤›› ይሏታል፡፡ (ይቀጥላል)

Read 4596 times Last modified on Saturday, 27 April 2013 11:27