Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 November 2011 07:38

Mon General! “መዝናናት፣ መዝናናት፣ አሁንም መዝናናት!” ጓድ ሌኒን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የተከበራችሁ አንባብያን፡- 
ፈረንሳይ ሁለት አመት የተማርኩት በፕሬዚዳንት ደጎል እና ፕሬዚዳንት ኬነዲ ዘመነ መንግስት ነበር፡፡ በአካል ባንገናኝም በግል የማውቃቸው ይመስለኛል፡፡ ከአድናቆት፣ ከአክብሮት እና ከሳቅ ጋር!
የፈረንሳይ አብዮት ተለኮሰ፡፡ ስራ ፈት፣ ጨቋኝ እና በዝባዥ የነበረውን የመሳፍንት፣ የመኳንንት እና የሀብታም ነጋዴዎች መደብ ገለበጠ፡፡ “ደም ሳይፈስ ስርየት የለም” እንደሚባለው፣ Madame La Guillotine (ጊዮቲን) የምትባለው አንገት መቁረጫ ስራዋን በትጋት ስታካሂድ፣ በፓሪስ ጐዳና፣ ቱቦ ደም እንደ ዝናብ ውሀ ፈሰሰ፡፡
ከጥቂት አመታት በኋላ ግን አብዮቱ ተቀለበሰ፣ ጀኔራል ናፖሊዮን ቦናፖርት ንጉሰ ነገስት ሆነ፣ አብዮቱ “ተቀለበሰ”፡፡ የቀድሞው ገዢ መደብ አባላት ክብርና ማእረጋቸው ከነንብረታቸው ተመለሰላቸው፡፡ ከነዚህ ቤተሰቦች አንዱ የጄኔራል ደጎል ቅድመ አያቶች ነበሩ፡፡

ሞን ዤነራል እጅግ መልከ መልካም ናቸው፡፡ የአብዛኛ ሰው ቁመት ከትከሻቸው በታች ነው፡፡ 
Charles Degaule እና Me’re Patrie አገር እና ዜጋ ናቸው ቢባልም፣ በሰውየው ቤት ግን እናትና ልጅ ናቸው፡፡ በምርጫ ጊዜ Gaulist ፓርቲ የተሸፈነ ጊዜ፣ እናት አገርን ያኰርፉዋታል፡፡ ለጊዜው ታሪክ መስራት ስለማይችሉ ከፓሪስ ውጪ በሚገኘው መኖሪያቸው ቤታቸዉ ታሪክ እና ግለታሪክ ይፅፋሉ፡፡ እናት አገር ልጇ በሚያስፈልጋት ሰአት ስትጠራቸው እንዲያደርሱላት “ዘወትር ዝግጁ” ናቸው፡፡ . . . 
. . . otto Von Bismark እንደ አፄ ቴዎድሮስ ጀርመንን በአንድ መንግስት የምትተዳደር ሉአላዊት አገር ካደረጋት በኋላ፣ ፈረንሳይና ጀርመን ሁል ጊዜ እንደተፋጠጡ ነበር፡፡ ከጀርመን ጥቃት ለመከላከል ፈረንሳዮች የጋራ ወሰናቸውን ተከትሎ የሚሄድ የካብ አጥር ገንብተው ነበር፡፡ The Majino Line የሚሉት፡፡ ምንም አይነት ብልሀትና መሳርያ ሊጥሰው እንደማይችል እርግጠኛ ነበሩ፡፡ ሞን ዤነራል ገና ኮሎኔል እያሉ፣ እናት አገርን ባኮረፉበት ጊዜ አንድ ሚሊተሪ መፅሀፍ አሳተሙ፡፡ ጭብጡ “የማዢኖ አጥር ጊዜው አልፎበታል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የወለደው ታንክ አለ፡፡ በሚቀጥለው ጦርነት ከጀርመን ጥቃት መከላከል የምንችለው ታንከኛ ክፍለ ጦራችንን አደራጅተን የቆየናቸው እንደሆነ ብቻ ነው አለዚያ የማዢኖን ካብ እንደ ካርድቦርድ ካብ እያፈራረሱት ያልፋሉ፡፡መፅሀፉን ፈረንሳዮች ከፊሎቹ አደነቁት ከፊሎቹ አቃቂር አወጡለት፡፡ ከዚያ ውጪ ከቁብም አልቆጠሩት፡፡ ጀርመኖች ግን የደጎልን መፅሀፍ ተከተሉ፡፡ ከባድ የታንክ ክፍለ ጦር ገምብተው፣ የማዢኖ ካብን እያፈራረሱ መርሸው፣ ከአስራ አምስት ቀን በኋላ በድል አድራጊነት ፓሪስን ተቆጣጠሩዋት . . . 
. . . General Pe’tain ከሂትለር ጋር በመስማማት Vichy ከተማ ውስጥ መንግስት መሰረተ፡፡ “ፈረንሳዮች ሆይ፣ አሻንጉሊቱን የቪሺ መንግስት እናወግዛለን!” ካሉ በኋላ፣ ለህዝባቸው ሽምቅ የአርበኛ ውጊያ አወጁ “በአንድ ውጊያ ተሸንፈናል እንጂ፣ ጦርነቱ ገና ይቀጥላል፡፡ Viva la France Libre!” (ነፃዋ ፍራንስ ትለምልም) ጦርነቱ አብቅቶ ሞን ዤነራል በድል አድራጊነት ፓሪስ ሲገቡ ሊቀበላቸዉ የወጣው ህዝብ ብዛት “ታይቶ አይታወቅም” ይባላል፡፡ በምርጫ ጊዜ ሞን ዤነራል “record majority” ድምፅ አግኝተው ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡ እና በፍራንስ ህገ መንግስት መሰረታዊ ለውጥ አመጡ፡፡ የለውጡን ከባድነት ለመገመት እንዲያስችለን፣ ከሳቸው በፊት ለአመታት የፍራንስን ፖለቲካዊ ሂደት የአለም መሳቅያ አድርጎት የነበረውን ሁናቴ እንቃኛለን፡፡ 
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአስር በላይ ናቸው፡፡ በቡድን ሲወዳደሩ፣ አንዱ ፓርቲ ላሁኑ ሳይሆን ከጥቂት ወራት በኋላ ለሚከተለው ምርጫ እየተዘጋጁ፣ የፓርላማው (የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) ጫጫታ የተቀረው የፈረንጅ አለም ማላገጫ ሆኖ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሁለት የምክር ቤት አባላት ለተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ከፓሪስ ወደ ኒው ዮርክ አብረው እየበረሩ እያለ፣ አንዳቸው እንቅልፍ ወሰደው፡፡ ከሶስት ሰአት በኋላ ሲነቃ፣ ያልተኛው አባል “ሁለት ዜና ሰማን፡፡ የሚያሳዝነውን ላስቀድምልህ ወይስ የሚያስደስተውን?”“የሚያስደስተውን” 
“ምክር ቤቱ በሌለህበት ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾሞሀል እንኳን ደስ ያለህ!”
“በአምላክህ! መጥፎው ዜናስ ምን ይላል?”
“ምክር ቤቱ በሌለህበት ከስልጣን አውርዶሀል፡፡ አይዞህ አይክፋህ! በሚቀጥለው ወይም ከዚያ በሚከተለው ስብሰባ እንሾምህ ይሆናል” . . .
. . . ሞን ዤነራል ለህዝባቸው ባስጨበጡት ህገ መንግስት (እስከ ዛሬ ቋሚ ነው) የተሳቀበትን ጫጫታም ህገ መንግስት ጠራርገው አስወገዱት፡፡
አዲሱ ህገ መንግስታቸው ገና በምክር ቤቱ ከመፅደቁ በፊት ሲወያይበት፣ አንዳንድ መማክርት “ደጎል ፈላጭ ቆራጭ ገዢ ለመሆን እያነጣጠረ ነው” ብለው አንዱን አንቀፅ ተቃውመው በድምፅ ብልጫ ሊያጨናግፉት በተነሱ ቁጥር፣ አንቀፁን በቀጥታ ለህዝቡ ያቀርባሉ፡፡ “Referendum” ይባላል፡፡ የህዝባቸዉን የልብ ትርታ ጠንቅቀው የሚያውቁት በመሆናቸው በከፍተኛ ድምፅ ያፀድቅላቸዋል፡፡
(በፈረንሳይ ረዥም ታሪክ ውስጥ ከሁሉም መሪዎች እጅግ የተሳካለት ፈላጭ ቆራጭ ሉዊ አስራ አራተኛ (“ፀሀዩ ንጉስ”) ነበር ይባላል፡፡ የፕሬዚዳንት ደጎል ስልጣን ከዚያም የጠነከረ ነበር) . . .
. . . አሁን Mon General ያ የተደነቀው “እንደ ብረት የጠነከረ ወኔ” እና የተመሰገነ አርቆአስተዋይነት ባይኖራቸው ኖሮ፣ እና ያ ለናት አገራቸው ያላቸው ፍቅር መንፈሳቸውን ባይመራው ኖሮ፣ “ፍራንስ ከእርስ በርስ ጦርነት” እልቂት በኋላ፣ ተሰንጥቃ ለዘለቄታው ሁለት አገር ትሆን ነበር” ይላሉ የታሪክ ሊቃውንት፡፡ ጉዳዩ ባጭሩና በግርድፉ እንደሚከተለው ነበር፡-
አልጀሪያ የምትገኘው ከፍራንስ ተነስተን፣ ሜዲቴሪንያን ባህርን ተሻግረን ሰሜን አፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከሆነች አራት ትውልድ ተቆጥሯል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ፈረንሳዮች እንደ ኮሎኒያሊስቶች የመጡ ቢሆንም፣ ተከታዮቹ አራት ትውልዶች ግን ከአገሬው ጋር እንደ እኩያሞች ዜጎች ነበር የሚኖሩት፡፡ እንድያውም አልጄሪያ ስምዋ “የባህር ማዶ ፍራንስ” ነበር፡፡
ዳሩ ምን ይሆናል፣ ዘመን ተለዋወጠ፡፡ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ቅኝ አገሮችን የነፃነት ማእበል አናወጣቸው፡፡ ጀግኖች ተዋጊዎች ኤውሮፓውያኑ ገዢዎች በአርበኝነት ሽምቅ ውጊያ እያስጨነቁ አባረሩዋቸው፡፡
አልጀሪያ ውስጥ በቤን ቤላ መሪነት የነፃነት እንቅስቃሴው ታወጀ “ፈረንሳውያን በሰላም ወደ አገራችሁ እንድትገቡ ተጋብዛችኋል፡፡ እምቢ ብትሉ፣ ወደ አገራችን በጦር እንደገባችሁ ካገራችን በጦር እናስወጣችኋለን”
ፈረንሳዮቹ “እኛ አልጄሪያውያን ነን፡፡ እዚህ ነው ተወልደን ያደግነው፡፡ ከአልጄሪያ ሌላ መሬትም ሰማይም አናውቅም፡፡ እንሞታታለን እንጂ ካገራችን ማንም አያባርረንም” አሉ፡፡
አልጄሪያ ተመድቦ የነበረው ክፍለ-ጦር “አገራችን ነው፡፡ ሰላም እናስከብራለን፡፡ የመንግስት ተቃዋሚዎችን እናወድማለን” ሲል አቋሙን ገለፀ፡፡
አለም ቀውጢ ልትሆን ስትል ሞን ዤነራል ለናታቸው ለፍራንስ ደረሱላት፡፡ ወደ አልጄሪያ በረሩ፡፡ የጠቅላይ ጦር አዛዥ የማእረግ ልብሳቸውን እንደለበሱ ወደ ጦር ሰፈሩ መጡ፡፡
አዛዡን አስጠሩት፡፡ መጣ፡፡ ከተቀመጡበት እየገረመሙት “ስሜታችሁ ገብቶኝ እያዘንኩላችሁ ሆነና ነው እንጂ፣ አንተ የወሰድከው እንደ ሚሊተሪ አዛዥነትህ ጦር ፍርድ ቤት አስቀርቤ አስረሽንህ ነበር፡፡ ገብቶሀል?”
“ገብቶኛል፣ ሞን ዤነራል”
“ይህ ክፍለ ጦር ወዴት እንደሚዛወር እስኪነገርህ ድረስ ተገቢው ዝግጅት እንዲደረግ” ፕሬዚዳንት ደጎል በሬድዮ በደም ፈረንሳዊያን የሆናችሁ አልጄሪያውያን ሆይ፣ ትውልድ አገራችሁን እስከ ሞት ብትወዱዋትም ቅሉ፣ አለማቀፋዊ ህግ ወደናት አገራችሁ ወደ ውቢቱ ፍራንስ መመለስ ይኖርባችኋል፡፡ እቅፏን ዘርግታ እንደምትጠብቃችሁ ታውቃላችሁ፡፡”
የክፍለ ጦሩ ሹማምንት ፕሬዚዳንት ደጎልን ለማስገደል ባለሙያ ቡድን ልከው ነበር፣ የፈረንሳይ የስለላ ድርጅት አከሸፈው፡፡ (ምናልባት The Day of the Jackal የሚባል ፊልም ያያችሁ ካላችሁ?)
በታሪክ እንደተመዘገበው፣ ፍራንስ ለሁለት ልትከፈል ስትል Mon General ደርሰው ያዳኑዋት በንዲህ አይነት ነበር . . .
. . . የሞን ዤነራል ታሪክ ሌላው ምእራፍ አፍሪካ ውስጥ የነበሩዋትን አስራ ሶስት ቅኝ ግዛቶች ይመለከታል፡፡
ገዢው ፓርቲ የትኛውም ቢሆን፣ የፈረንሳይ መንግስት ቅኝ ግዛቶችን በተመለከተ አንድ ዘላቂ ፖሊሲ (መመርያ) ነበረው፡፡ ያገሬው የንጉስ ልጅ፣ የነገድ መሪ ልጅ፣ የጎሳ ሹም ልጅ የፈረንሳይ የህዝብ ተወካዮች ሙሉ አባል ሆኖ፣ አገሩን ከሚጠቅም ወገን ጋር እየወገነ ድምፅ ይሰጣል፣ ካሰኘው የሚያምንበትን የመንግስት ፖሊሲ የሚያራምድ ንግግር ያሰማል፡፡
ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ኮሎኒያሊዝም ጊዜው እንዳለፈበት ግልፅ ሆነ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሞን ዤነራል የሚከተለውን ቆራጥ እርምጃ ወሰዱ፡፡
የአስራ ሶስቱን ኮሎኒዎች የሚወክሉትን የፈረንሳይ ምክር ቤት አባላት ሰበሰቡዋቸው፡፡
“ከአንድ አመት በኋላ እያንዳንዳችሁ በፓሪስ ምክር ቤት የህዝቡ ተወካይ መሆኑ ያበቃና፣ የነፃ ሉአላዊነት አገሩ መሪ ይሆናል፡፡ ህዝባችሁን ለማዘጋጀትና የመንግስታችሁን መዋቅር ለመንደፍ በመሰላችሁ መንገድ ትጓዛላችሁ፡፡ ይቅናችሁ!”
በታሪክ እንደተመዘገበው አስራ ሶስቱ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች እንደነ እንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች ለነፃነታቸዉ ብዙ ደም መፋሰስ አላስፈለጋቸውም፡፡ ሞን ዤነራል ነፃነታቸውን በነፃ አበረከቱላቸው . . .
. . . ሞን ዤነራል አንዲት ድክመት አለችባቸው፡፡ ከናት አገር ከውቢቱ ፍራንስ ቀጥሎ የሚወዱት የገዛ ውበታቸውን ነው፡፡ በዚህ የተነሳ እድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ እነዚያ ድንቅ የሆኑ ረዣዥም ንግግሮቻቸውን ለማንበብ መነፅር አስፈለገ፡፡ መነፅር ደሞ መልካቸውን ሊያበላሽ ሆነ፡፡ ይህ ደሞ አይደረግም! ስለዚህ ንግግሮቻቸውን አስቀድመው በቃል ማጥናት ነበረባቸው!
ያገራቸው ልጆችም የውጪ ሰዎችም በዚህ ይስቁባቸው ነበር፡፡ አይናቸው እየከዳቸው ሄዶ፣ ፊታቸው ያለውን ሰው መልኩን ለይተው የሚያውቁት አንድ አምስት እርምጃ ያህል ሲቀርባቸው ብቻ ነበር፡፡ ሌላው ብዥታ ብቻ ነው፡፡ (ይባላል እንግዲህ ለመሳቅ እንዲያመች)
ወዳጅ አገር ለጉብኝት ደርሰው ከኤሮፕላን ሊወርዱ ሲሉ፣ ጋሻ ጃግሬያቸውን ዝግ ባለ ድምፅ “ህዝቡ በየት በኩል ነው?” ይሉታል፡፡ ሲነግራቸው ወደዚያ በኩል ፈገግ እያሉ እጃቸውን ያውለበልባሉ፣ ህዝቡ ይጮሀል!
እንደሚታወቀው፣ የላቲን አሜሪካ ሰዎች ሲገናኙም እንደ ፈረንሳይ ጉንጭ ለጉንጭ ይሳሳማሉ፡፡ እና አንድ ቀን ከአንዱ ላቲን አገር ጉብኝት ሊመለሱ አየር ጣቢያ ድረስ ባለስልጣናቱ እየሸኙዋቸው ነው፡፡ የስንብት ተራ በተራ እየሳሙዋቸውና፣ አይናቸው የባሰውን ስለከዳቸው፣ የመጨረሻውን ሸኚ ከሳሙት በኋላ፣ የገዛ ጋሻ ጃግሬያቸውን ትከሻና ትከሻቸውን ይዘው ሁለት ጉንጩን ሲስሙ፣ በቀስታ “Mon General!” ሲላቸው
“Pardon!” (ይቅርታ!) ብለው ወደዚያ ገፈተሩት . . .
. . . እናት አገር የውስጥ ውጥረት በሌለባት ወቀት ሞን ዤነራል መልካቸውን ከሚወዱት እኩል መተግበር የሚወዱት Anglo-Saxon የሚሉዋቸውን እንግሊዝኛ ተናጋሪ አገሮች (በተለይም አሜሪካን) መቃረን እና ሲቻላቸው ማበሳጨት ነበር፡፡
በትልቁ ቁም ነገር እንጀምርና፣ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ አለም በኮሚኒስቱ የሶቭየት ህብረት እና በካፒታሊስቱ የአሜሪካ ጎራዎች ተከፋፈለች (የምስራቅ አውሮፓ አገሮች ለራሽያ፣ የምእራብ ኤውሮፓዎች ለአሜሪካ ተሰለፉ በሁኔታዎች አስገዳጅነት፡፡)
አሜሪካ ምእራብ ኤውሮፓውያኑን አገሮች “Nuclear ቦምብ አትፈብርኩ፣ የኔ ኒዩክሊየር ቦምብ ከሶቭየት ጥቃት መከላከያ ጃንጥላ ይሆናችኋል” አላቸው (Nuclear umbrella)
ሞን ዠነራል ግን አሻፈረኝ አሉ! ፍራንስ የራስዋ force de frappe (የማጥቃት ሀይል) ይኖራታል አሉ፡፡ ፍራንስ ሉአላዊት Nuclear Power ሆነች፡፡
ይሄ በበቃ ነበር፡፡ ሞን ዠነራል ጨመሩበት “ፍራንስ ከምስራቁም (ኮሚኒስት) ከምእራቡም (ካፒታሊስት) ጎራ የለችበትም” አሉና፣ በብዙ ብዙ የመገናኛ ብዙኃን ጭበጨባ፣ ሽለላና እልልታ ለወዳጅነት ጉብኝት ወደ ሞስኮ በረሩ፡፡ ከጉብኝቱ መልስ የራሽያና የፍራንስ የረዥም ዘመናት ወዳጅነት ተነገረን፣ ተደጋገመልን፡፡
ፈረንሳዊው Number one አቀንቃኝ፣ ሞስኮ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከሆነችው ከናታሊ ጋር ፍቅር እንደያዘው እየዘፈነ ኤውሮፓን ዞረ (አሜሪካ በንዴት እርር ድብን!)
ሞን ዤነራል መጨመር አሰኛቸው፡፡ UNESCO ዋና መስሪያ ቤቱ ፓሪስ ውስጥ የሚገኘው እጅግ የተዋበ (architectural masterpiece) ህንፃ ነበር፡፡ ሞን ዤነራል “ፍራንስ ለላቀ ጉዳይ ትፈልገዋለች” ብለው ዩኔስኮን አባረሩ፡፡ ህንፃው Muse’e de l’Homme (የሰው ዝርያ ሙዝየም) ሆነ፡፡
. . . በታሪክ መድረክ ላይ አንግሎ ሳክሰኖቹ ሞን ዤኔራልን አልቻሉዋቸውም፡፡ ስለዚህ የቀራቸው አማራጭ በሳቸው ዙሪያ Joke እየፈጠሩ ማውራት ብቻ ሆነ፡፡ ለናሙና ያህል ሁለቱን እነሆ፡-
አንድ ቀን “በአሳቻ ሰአት” ሚስታቸው የፊኛ ጥያቄ እያጣደፋት ሽንት ቤቱን ብርግድ ብታረግ፣ ሞን ዤነራል እዚያ ተኮፍሰዋል!
“Oh, mon Dieu!” (ውይ አምላኬ!) አለች በድንጋጤ ትንፋሽዋን እየሳበች “አይዞሽ! ብቻችንን ስንሆን’ኮ ሻርል ልትይኝ ትችያለሽ”
ከእለታት አንድ ቀን ፕሬዚዳንት ደጎል ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን “ፖምፒዱ” አሉት “እንበል ሰው ነኝና፣ ምናልባት ከእለታት አንድ ቀን መሞት ሊኖርብኝ ይችል ይሆናል፡፡ እና የት ብቀበር ይመረጣል ይመስልሀል?”
“ሞን ዤኔራል፣ የሞት ጥላ ቢሆን እንኳ አጠገብዎ አይደርስም”
“እሱስ ነው፡፡ ግን እንድያው ለምናልባቱ ቢመጣስ?”
“እንድያ ከሆነማ ቦታው አስቀድሞ የታወቀ ነው”
“እየሰማሁህ ነው”
“Les Invalides!” [ሌዘንቫሊድ ለናፖሊዮንና ለናት አገር ሲዋጉ በየጦር ሜዳው የሚያምር ፅጌሬዳ ቀለም የተቀባ ቤተ ክርስትያን ነው፡፡ ሁልጊዜ ወለል ብሎ ይታያል፡፡ የሚንቁት ሰዎች ናፖሊዮንን “ሃምሳ አለቃ” ይሉታል]
ሞን ዤኔራል ፖምፒዱን እየገላመጡ “ምነው አንተ?” አሉት “ከማንም ሀምሳ አለቃ ጋር?”
“ይቅርታ፣ ሞን ዤኔራል! እንደገና ልሞክር ይፈቀድልኝ”
በነጋታው ቢሮዋቸው መጥቶ “አገኘሁዋት!” አላቸው
“እየሰማሁህ ነው”
“Place de l’Etoile!” [ፕላስ ሌትዋል በጂኦሜትሪ design የተገነባችው ፓሪስ ከተማ እምብርት ናት፡፡ የትልቅ በአል ሰልፍ ሁሉ የማለቅያ ስነ ስርአት በመንፈሳዊ ስሜት ደረጃ ሲገመት ለናት አገር በየጦር ሜዳው የሞተውና ቀባሪ ያላገኘው ወታደር ሁሉ እዚያ ተቀብሯል፡፡ በመላው ፈረንሳይ ምድር ከዚህ ቦታ እኩል ቅዱስ የለም]
ሞን ዤኔራል የፖምፒዱ ደደብነት እያሳዘናቸው “አሁንስ ባሰብህ፣ ፖምፒዱ” አሉት “ብለህ ብለህ ከማንም ስም-የለህ ጋር ትቀብረኝ?!
“በጣም ይቅርታ፣ ሞን ዤኔራል፡፡ የመጨረሻ እድል ይሰጠኝና ልሞክር” ከሶስት ቀን በኋላ ተመልሶ መጥቶ “ሞን ዤኔራል፣ ዛሬስ በእርግጥ አግኝቻታለሁ”
“እየሰማሁህ ነው”
“ኢየሩሳሌም!”
“እሱ’ንኳ ይሻላል” አሉት ሞት ዤኔራል “መቃብሩን እተገቢ ቦታ መርጠህ ግዛና ተመልሰህ ንገረኝ”
“Oui mon Ge’ne’ral!” ብሎ ወጣ
ከሶስት ቀን በኋላ ተመልሶ “የታዘዝኩትን ፈፅሜያለሁ፣ ሞን ዤኔራል”
“ሶስት ቀን ፈጀብህ ምነው?”
“ዋጋና ቦታ ስንደራደር ብዙ ትእግስት አስፈልጎኝ ነበር፡፡ እና ገንዘቡን በቅድምያ አስከፈሉኝ፡፡ በአሜሪካን ዶላር!”
“እና ስንት አስከፈሉን?”
“ሀያ ሚልዮን ዶላር”
“ኧረ ይሄ ቆንቋና ዘር! ሀያ ሚልዮን?! ለሶስት ቀን ብቻ!?”
ምርቃት
የተከበራችሁ አንባብያን፡-
የፓሪስ ውበት የማይማርከው ያልታደለ ሰው መሆን አለበት፡፡ በየአደባባዩ ብቻ አይደለም ውበትዋ የሚደምቀው፡፡ በየስርቻው፣ በየጉሮኖው ውበት በየአይነቱ ከየዘመኑ! በ19060ዎቹ “When a wealthy American dies, his soul goes to Paris” ይባል ነበር፡፡
ፓሪስ ማንም ሌላ ከተማ ውስጥ የሌለ የማህበረሰብ ክፍል (Social Class) ይታይባታል፡፡
Clochard (ክሎሻር) ይባላል፡፡ ክሎሻር ለመኖሪያ (ቋሚ አድራሻ) ድልድል ስር፣ ወንዙ የማይደርስበት ጥግ፣ ካርቶን ጨርቅ ነገሮች፣ ውራጅ ምናምን ይጎዘጉዛል፡፡ በመልካም አየር ለመዘዋወር ካልወጣ በስተቀር፣ ሁልጊዜ እዚያው ይገኛል፡፡
ክሎሻር ለመሆን ከመምረጡ ወይም ከመገደዱ በፊት ምናልባት የባንክ ሹም ነበር፣ ወይም ነጋዴ ወይም የመንግስት ሰራተኛ ወይም ጋንግስተር ወይም ወዘተ፡፡
ብዙ ሰው ለክሎሻር ለጋስ ነው፡፡ ክረምት እየመጣ ከሆነ ለሰፈሩ ክሎሻር ፋሽኑ ያለፈበት ወይም ሳልቫጅ ወይም አሮጌ ካፖርት፣ ብርድልብስ፣ ፍራሽ ይሰጣል፡፡ ፀደይ ሲመጣም እንደዚሁ ለወራቱ የአየር ጠባይ የሚስማማ ልብሳ ልብስ፡፡
አንድ ፀደይ ጧት አይኑን ሲከፍት፣ ከመሬት ተነስቶ በደስታ እየፈነደቀ “በፀሀዩና በንፋሱ እየዘለልኩ እየተጓዝኩ” የሚለውን በዚያን ወራት ፓሪስን አጥለቅልቆ የነበረውን ዘፈን እየዘፈነ ከከተማ ወጣ፡፡
በገጠሩ በዝግታ ሲራመድ ውሎ፣ ሊመሽ ሲል አንድ ቤት ደረሰ፣ የመሸብኝ እንግዳ አሳድሩኝ ብሎ ተቀበሉት፡፡ ባልና ሚስት ብቻቸውን ስለሚኖሩ ሰው ይናፍቃቸዋል፡፡ ክሎሻር የተከበረ እንግዳ ሆኖ አመሸ፡፡
እራት እስኪደርስ ጠርሙስ ወይን ጠጅ ተከፈተ ተቀዳ ተጠጣ፤ ሞቅ ያለ ወግ ተከተለ፡፡ ባለ አራት ኮርስ (ተከታታይ የምግብ አይነት) እራት ከተበላ በኋላ፣ ለማሳረገያ Camembert ቺዝ ቀረበ፡፡ ባለቤቴ ለሶስቱም አንድ አንድ ቁራሽ ከሰጠ በኋላ ከደነው፡፡
“ካመምቤር ነብሴ! ናፍቆቴን አውቀህ አልፈህ እዚያ ቆየኸኝ?!” ና’ስቲ አንዴ ልቅመስህ! [በፀጥታ አኝኮ ውጦ በወይን ጠጅ ይጉመጠመጣል] እግዚአብሔር እቺን አገራችንን ምን ያህል ቢያፈቅራት ይሆን ካመምቤርን የለገሳት፡፡ እፁብ ድንቅ” እያለ ድርሻውን ጨረሰ፡፡
እንደ ደምቡ ቢሆን ቺዝ በቃ፣ ቡና ወደ ሻይ ይከተላል፡፡ ክሎሻር ግን ንግግሩን ቀጠለ “መቼስ ካመምቤር ጣእሙና ቃናው እፀ በለሲቱን ያስንቃል፡ጨዋነትንም ያስረሳል፡፡ መስየ እንግዳ ተቀባዩ፣ እባኮትን አንድ ድርሻ ካመምቤር ይድገሙኝ”
ባለቤት እምቢ ሊል አልቻለም፡፡ ቁራሹን ሰሀኑ ላይ ጣለለት፡፡ ልፍለፋውን እየቀጠለ ካመምቤሩን ዋጥ ስልቅጥ ካደረገ በኋላ “አሁንም አላስቻለኝም ጌታዬ! ቢፈልጉ በጥፊ ይበሉኝና አንድ ቁራሽ ካመምቤር ይለግሱኝ”
ባለቤት “ኤድያ!” ብሎ አመናጭቆ ቁራሹን ጣለለትና፣ ተነስቶ የተረፈውን ወስዶ ፍሪጅ ውስጥ ዘጋበት፡፡ ክሎቫር ተስፋውን ቆረጠ፣ በሞቅታው ስለ ድልድል ስር ኑሮው ሲተርክላቸው አፋቸውን ከፍተው ሲስሙት አመሹ፡፡ ሌላ ጠርሙስ ወይን ጠጅ ተከፈተ፡፡ ባለቤት የካመምቤር ቁጣውን ረስቶ ክሎሻርን እየወደደው ሄደ፡፡
የመኝታ ሰአት ደረሰ፡፡ ሶስቱም ሰክረው ስለነበረ ባልና ሚስት ክሎሻርን እጐናቸው አስተኙት . . .
. . . ሌሊት ክሎሻርን ያልለመደው ድምፅ ቀሰቀሰው፡፡ ከብቶቹ በረት ጥሰው እየወጡ ናቸው፡፡ ባለቤቱን ሲቀሰቅሰው እያጉረመረመ፣ ልብስ እየደረበ ወጣ፡፡
ሚስት ክሎሻርን “አሁን ትችላለህ” አለችው በሹክሹክታ፡፡ ስካሩ ጨዋነትዋን አስረስቷት ክሎሻር ላይ ልትወጣበት ምንም አልቀራት፡፡
“ተመልሶ ቢደርስብኝስ?”
“የከብቶቹን ልማድ አውቀዋለሁ፡፡ ከተበተኑበት እስኪሰበስባቸው ገና አንድ ሰአት ይወስድበታል”
“እንግድያው መልካም!” አለና ክሎሻር ከአልጋ ወርዶ ወደ ፍሪጅ እየተራመደ “እሰይ! መጣሁልሽ ካመምቤር ነብሴ!”
የካመምቤር ነገር ለሚስት እንቁልልጭ አተረፈ፡፡
ቸር ይግጠመን አሜን፡፡

 

Read 2498 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 07:47