Saturday, 27 April 2013 10:58

የሐረሯ ወይዘሮ ስለ ሐረር ስፌት ምን ይላሉ?

Written by  ዘሪሁን ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ የሚሰራቸውን ተግባራት ለማመልከት፤ ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበቻቸውን ታሪካዊ ነገሮች ለማስተዋወቅ፤ ቱሪዝም ለልማት ያለውን ጠቀሜታ ለመግለጽ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመጠቆም…አዘጋጅቶ ባሰራጨው በራሪ ወረቀት ላይ ከቀረቡ አስደማሚ መረጃዎች አንዱ፤ ኢትዮጵያ ከ2.8 ሚሊዮን ዓመት በፊት የእጅ መሣሪያ መጠቀም የተጀመረበት አገር ናት ይላል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚያዝያ 3 እስከ 7 ቀን 2005 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል ባዘጋጀው 2ኛው ዓለም አቀፍ የቱሪዝምና የጉዞ ንግድ ትርዒት ላይ ከተሳተፉት መሐል የእጅ መሣሪያን ለማምረቻነት የሚጠቀሙ ብዙ ባለሙያዎች ይገኙበታል። ከሐረር የመጡት የመሶብ ስፌት ባለሙያዎች ምርትና አመራረት የተመልካቹን ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ ከሐረር የመጡት ወይዘሮ አሚና አህመድ ስለ ሙያና አሰራራቸው ይናገራሉ፡፡

በኤግዚቢሽኑ የተሳተፉት በግል ነው በማህበር? “ኢናይ አሲያ” የሚባል ማህበር አለን። የማህበራችንን የስፌት ሥራዎች ይዤ ነው በኤግዚቢሽኑ ላይ የተገኘሁት፡፡ የማህበራችሁ መጠሪያ ትርጉሙ ምንድነው? “ኢናይ አሲያ” በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ ያሉ ታላቅ ሥምና ተግባር ያላቸው ትልቅ ሴት ናቸው። የእኛም ማህበር አባላት በዕድሜ አንጋፋ ስለሆንና ሰርተን እንለወጣለን የሚል ትልቅ ምኞትና እቅድ ስላለን ነው የማህበራችንን መጠሪያ ኢናይ አሲያ ያልነው፡፡ ማህበራችሁ እንዴትና መቼ ተመሠረተ? ምን ያህል አባላትስ አላችሁ? በሐረር ባህል ቤትን በስፌት ዕቃዎች ማስጌጥ የተለመደ ነው፡፡ ሁሉም ሴቶች በዚህ ሙያ የሰለጠኑ ናቸው፡፡ የሐረር ሴት ከጋብቻ በፊትና በኋላ የቤተሰቦቿንና የባሏን (የራሷን) ቤት በስፌት ዕቃዎች ማስጌጥ መደሰቻዋ ነው፡፡

የመሶብና ሙዳይ መሰል ምርቶቻቸውን ለገበያ የሚያቀርቡ ሴቶችም አሉ፡፡ የእኛ ማህበር አባላትም በየግላችን እየሰራን ለገበያ እናቀርብ ነበር፡፡ የዛሬ 13 ዓመት የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አደራጅቶን በጋራ መንቀሳቀስ ጀመርን። ማህበራችን 20 አባላት አሉት፡፡ መደራጀቱ ምን ጥቅም አስገኘላችሁ? በፊት በየግላችን ስንሰራ ሰዎች በየቤታችን መጥተው ወይም እኛ ዞረን ነበር ገበያ የምናገኘው። አሁን በጣም ብዙ ጥቅም ነው ያገኘነው፡፡ መንግሥት ለማህበራችን 200ሺህ ብር በብድር ሰጥቶናል፡፡ በታሪካዊው አርተር ራምቦ ቤት ሁለት ክፍል ተሰጥቶን በአንዱ እያመረትን በሌላኛው ምርቶቻችንን ለቱሪስቶች እንሸጥበታለን፡፡ ሙያችንን ለወጣቶች ለማስተማርም ዕድል ፈጥሮልናል፡፡ በተለያዩ ክልሎች በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ በመሳተፍ የልምድ ልውውጥ ከማድረጋችንም በላይ የስፌት ሥራዎቻችንን እንሸጣለን፡፡ በፊት ለስፌት የምጠቀመው ስንደዶ፣ አለላና አክርማን ነበር፡፡ በኮባ መጠቀም የጀመርነው በየክልሉ ዞረን ከሌሎች ልምድ ከወሰድን በኋላ ነው፡፡ በኤግዚቢሽን ለመሳተፍ የት የት ሄዳችኋል? የማህበራችን አባላት በመፈራረቅ ነው በተለያዩ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ የምንሳተፈው። ትግራይ፣ ሻሸመኔ፣ ሐዋሳ…የመሳሰሉት ቦታዎች ሄደናል። በአንድ የትርዒት ቦታ ከተለያየ ስፍራ ብዙ ባለሙያዎች ስለሚመጡ ብዙ ዕውቀትና ልምድ ነው የሚገኘው፡፡

ለምሳሌ በአሁኑ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ጋምቤላዎች በጨሌ የሚሰሩትን የጥበብ ሥራ፣ ከጉራጌ ክልል (ከአገና) የመጡ ተሳታፊዎችን የሸክላ እንዲሁም የስፌትና የቀንድ አሰራር…ማየታችን ብዙ ያስተምረናል፡፡ የሐረር ባህላዊ የስፌት ምርቶች ስያሜና አገልግሎታቸውን ይንገሩኝ እስቲ… ለሁለት ዓላማ ነው የምንጠቀምባቸው። አንደኛው መኖሪያ ቤቶቻችንን በማስዋቢያነት ስንገለገልባቸው ሁለተኛው ደግሞ በየእለቱ እንቅስቃሴያችን በሠርግ፣ በሀዘንና ደስታ ወቅት ለተለያዩ አገልግሎቶች እንጠቀምባቸዋለን። የስፌቱ አይነትና ስያሜ ብዙ ነው፡፡ የእጣን ማስቀመጫ ሙዳይ አለ፡፡ ሙሽሮች ከረሜላና ማስቲካ የሚያስቀምጡበት “ቢሸሙዳይ” ሲባል፤ ሻሽና የተለያዩ መጋጊያጫዎቿን የምታስቀምጥበት ደግሞ “ጉፍተ ሙዳይ” ይባላል፡፡ “መጠበቅ” እና “ቢጃንጋሪ” የሚባሉ ሙሽሮች የሚጠቀሙበት የስፌት ምርትም አለ፡፡ “ጉንዶ” የሚባል ለግድግዳ ማስጌጫነት ብቻ የሚውልና መሰል የስፌት ምርቶቻችን ብዙ ናቸው። የመሸጫ ዋጋችሁ ምን ይመስላል? በተለያዩ ቦታዎች ካየሁት አንፃር የእኛ የስፌት ምርቶች በዋጋ ውድ ሊባሉ እንደሚችሉ አስተውያለሁ፡፡

በሐረር ባህል በግድግዳ የምንሰቅላቸው የስፌት ምርቶች ጥንድ የሚሆኑበት ጊዜ አለ፡፡ ጥንዱ “ቢጃንጋሪ” 2200 ብር ነው የምንሸጠው፡፡ “ሰጋሪና”ም ተመሳሳይ ዋጋ ያወጣል። “ቢካኮ መስኮንባይ” ጥንዱ 5000 ብር ነው፡፡ “ቢካኮ መኮንባይ” ቤት ውስጥ ጌጥ ሆኖ ሲያገለግል ከመስኮት (ጣቄት) ግራና ቀኝ ነው የሚሰቀለው። በበዓል፣ በሀዘንና በሠርግ ወቅት ደግሞ ለምግብ ማቅረቢያነት እንገለገልበታለን፡፡ የእንጀራ ማቅረቢያ “ማሀዝሙት” ይባላል፡፡ “ሰጋሪዮ ወስከንባይ” ሦስቱ ጥንድ 2000 ብር ይሸጣል፡፡ ሰሀን መሳይ ቅርፅ ያለው “ሰሀን ሰጋሪ” ሦስቱን በ600 ብር እንሸጠዋለን፡፡ የአንዱ “ጉንዶ” ዋጋ 30 ብር ነው፡፡ የሐረር ስፌት አንዱ መለያው በተለያዩ ቀለማት መድመቁ ነው፡፡ ምክንያቱ ምንድነው? በስንደዶ፣ በአክርማና በአለላ ስንጠቀም በተለያዩ የቀለም አይነቶች እናቀልማለን፡፡ በተለያዩ የክር አይነቶች የምንሰራቸው ስፌቶች አሉ፡፡

ስፌቱን በአጐዛ፣ በልብስ ቁልፍና በቆዳ በመጠረዝ ይበልጥ ውበት እንዲኖረው እናደርጋለን፡፡ ጠርዙን በቆዳ የመጠረዝ ሥራውን የሚያከናውኑልን ሌሎች ባለሙያዎች ናቸው፡፡ የስፌት ሥራዎቻችንን በተለያዩ ቀለማት የምናስውብበት ዋናው ምክንያት ከመገልገያነትም ባሻገር ለቤት ማስጌጫነት ስለምንጠቀምባቸው ነው፡፡ በሐረሪዎች ቤት በዘፈቀደ የሚሰቀል ስፌት የለም፡፡ እያንዳንዱ ስፌት የየራሱ የሆነ መስቀያ ቦታ አለው፡፡ የእኛም ማህበር በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች የመሳተፍ እድል ሲያገኝ የስፌት ምርቶቹን ሰቅለን ለተመልካች የምናቀርበው ባህላችንን በጠበቀ መልኩ ነው፡፡ የማህበራችሁ ቀጣይ አላማዎቹ ምን ይመስላሉ? በስንደዶ ፈንታ ኮባን ለስፌት መጠቀም የጀመርነው ተደራጅተን ስልጠና በማግኘታችን ነው፡፡ ተመሳሳይ ስልጠናዎችን ወስደን አሰራራችን የማሳደግ እቅድ አለን፡፡ ምርቶቻችንን ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ገበያ የማቅረብ እቅድ አለን፡፡

Read 1703 times Last modified on Saturday, 27 April 2013 11:07