Saturday, 27 April 2013 11:38

ግማሽ ትዝታ

Written by  ከወንድምኩን
Rate this item
(15 votes)

በአንድ ክፍል ውስጥ ለሶስት አመት አብሮኝ የታሰረው አብዱ ከመሞቱ በፊት እጅጉን ይወዳት ስለነበረችው ልጅ የነገረኝን መልዕክት ይዤ ወደ ጅማ እየሄድኩ ነው- በመኪና፡፡ “ቆንጆ ናት! እንደወንዝ ዳር ቄጤማ ጠል ጠግባ ያደገች የምትመስል-ወዘናዋ የሞላ! ጥይምናዋ እንደመስታወት ውስጥ ጨረር አይንን የሚወጋ። በሳቀች ብለው የሚመኟት ጥርሰ በረዶ!. . .ገላዋ ልስልስ ሀመልማሎን የሚያስንቅ. . .” አቤት አብዱ እንዴት አድርጎ ነበር ስለሷ የገለፀልኝ፡፡ የሚሞት ሰው በመጨረሻ ሰዓት የተናገረው አይመስልም፡፡ ሳገኛት ምን እንደምላት እያብሰለሰልኩ ወሊሶን አልፈን ወደ ወልቂጤ ተንደረደርን፡፡ “ነዒማን እወዳት እንደነበረ ንገርልኝ! ልሞት የጊዜ ጭፍጫፊ በቀረኝ አፍታ እንኳ እሷን አስባት እንደነበር ንገርልኝ!. . . ስገረፍ፣ውሀ ውስጥ ስደፈቅ፣በወታደር ጫማ ወገቤ ሲደቆስ፣በሰደፍ ፊቴ ሲገመስ. . . ያንን ሁሉ መከራ ተቋቁሜ እስከዛሬ ድረስ የኖርኩት ከዚህ ወጥቼ እሷን አገኛታለሁ በሚል ተስፋ እንደሆነ ንገራት!. . . .” እንባ በፊቱ ላይ ቅርር እያለ ነበር እንዲህ ያለኝ፡፡ አብዱ የሞት ቅጣት ሊፈፀምበት አንድ ሰአት ያህል ሲቀረው አብሬው ነበርኩ- እስር ቤት ውስጥ። ምሽቱን ሊገደሉ እንደሚወሰዱ በሹክሹክታ ሲወራ ነው የሰነበተው፡፡ እኔና አብዱ በአንድ ክፍል ውስጥ ታስረን ስለነበር- የመጨረሻውን ሰዓት አጠገቡ ነበርኩ፡፡

በዛች የመጨረሻ ሰአት የነገረኝን መልዕክት ይዤ ጅማ እስክደርስ ቸኩያለሁ፡፡ የሞት ፍርዱ ሊፈፀምበት በጠባቂዎቹ ከመወሰዱ በፊት፣ የመጨረሻ ትንፋሹን ሲተነፍስ፣የመጨረሻ ተስፋውን ሲያምጥ፣የመጨረሻ ትዝታውን ሲኖር. . . አብሬው ነበርኩ! “ሞቴን የምጠላው ከሷ የሚለየኝ በመሆኑ ብቻ እንደሆነ ንገራት!. . . ቀን በሀሳቤ ለሊት በህልሜ ይዣት እንደኖርኩ አስረዳት!. . . ነዒማ. . . የሚለው ስሟ አብሮኝ እንዲቀበር ሰውነቴ ላይ እንደፃፍኩት ንገራት፡፡ እንዴት አድርጎ ካለችህ እስር ቤት ከገባሁ በኋላ ክንዴ ላይ እንዲነቅሱኝ እንዳደረኩ ንገራት. . . ” ክንዱን ገልጦ አሳየኝ፡፡ ላምን አልቻልኩም!! ክንዱ ላይ ስሟን ሳይ ሀዘን ሳይሆን አድናቆት ነበር የወረረኝ፡፡ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ያለፈ ሰው፣ ለፍቅር የሚተርፍ ልብ እንዴት ሊኖረው ቻለ? ብዬ በአድናቆት ነበር የተሞላሁት፡፡ እንኳንም ስለነዒማ አጫውተኝ ብዬ ጠየኩት እንድል አደረገኝ፡፡

እንዴት ነበር ስለነዒማ እንዲነግረኝ የጠየኩት? በአንድ ጠባብ የእስረኞች ክፍል ውስጥ አብረን ነበርን፡፡ በጨለማ በተዋጠች፣ሁለት ትንንሽ ፍራሾች በግድግዳው አንፃር እዚህና እዚያ በተቀመጡባት፣ በወበቅ በታመቀች ክፍል ውስጥ አብሬው ነበርኩ፡፡ አይኖቹን ባያቸው ደስ ይለኝ ነበር፤ ሊገደል አንድ ሰዐት የቀረው ሰው ዐይን ውስጥ ምን ይሆን የሚታየው? የእስር ክፍላችን በጨለማ ተውጣ ስለነበር፣ አብዱን ማየት አልችልም፡፡ ለሶስት አመት እዚችው በጨለማ በተዋጠች ክፍል ነበር የታሰርነው፡፡ . . . በጨለማው ውስጥ ጠጋ ብዬ ባቅፈው እወድ ነበር፡፡ “አይዞህ! በርታ” ብለው” ግን አልቻልኩም። እኔ እራሴ ፈርቼ ነበር፡፡ ሰው ከዛ በላይ ሊፈራ አይችልም! የፍርሀት የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሼ ነበር፡፡ “አብዱ!” አልኩት ድምፄን አለስልሼ፡፡ “አቤት!” ድምፁ ውስጥ ፍርሀት ሳይሆን ተስፋ ማጣት ነበር፡፡ “ፀሎት እናድርግ?” አንድ የሆነ ነገር መናገር ስለነበረብኝ የተናገርኩት ብቻ ነበር፡፡

“ቅጣታችንን በምድር ጨርሰናል!” አለኝና ፀጥ አለ፡፡ ከፍራሼ ላይ ተነሳሁና በዳበሳ ተጠጋሁት፡፡ እጆቹን አገኘኋቸው፡፡ ይሞቃሉ፡፡ “እጆችህ ይሞቃሉ. . . ” አልኩት “የመጨረሻ ሙቀቴ ነው!” አለኝ “አብዱ አልፈራህም አይደል? ” አልኩት “ፍርሀት ሳይሆን ምኞት ብቻ ነበረኝ!” አሁን ድምፁ ውስጥ ተስፋ ነበር “ምን አይነት ምኞት?” “እጅግ በጣም አፈቅራት ስለነበረች ልጅ ያለኝ ምኞት! . . . አንዴ እድሉን አግኝቼ አይቻት ብመጣ የሚል ምኞት ነው እንጂ ፍርሀት እንኳን የለኝም! ” አለኝ በእርግጠኝነት “አሁን ስለሷ እያሰብክ ነው ማለት ነው?” ሊሆን አይችልም በሚል ስሜት ጠየኩት፡፡ ሰው ሊሞት ሲል በፍርሀት ይዋጣል እንጂ ስለሚወዳት ሴት እያሰበ፣ በፍቅር ሀሳብ ይዋጣል የሚል ሀሳብ አልነበረኝም፡፡ “አዎ! የቀረኝን የነፍስ ጉዞ እሷን ለመውደድ ነው የምጠቀምበት! መሞቴ ሳይሆን እሷን ዳግመኛ ለማየት አለመቻሌ ነው የሚያፀፅተኝ!” አለኝ አብዱ ገረመኝ፡፡ እንዴት ቢወዳት ነው? የሚል ጥያቄ በአእምሮዬ ተመላለሰ፡፡ ሶስት አመት በእስር ቆይቷል። ሶስት አመት ሙሉ አልረሳትም፡፡ “ስሟ ማነው? ” አልኩት “ነዒማ! ነዒማ ሀሰን!” ስሟን ሲጠራ በድምፁ ውስጥ ልዩ ግርማ ነበር፡፡ በሹክሹክታ ቀስ ብሎ ነበር ስሟን የጠራው ፡፡ “እስቲ ንገረኝ!. . .ስለ ነዒማ ንገረኝ!” አልኩት “ ያ አላህ! እንዴት ነበር የምወዳት? የመጀመሪያዬም የመጨረሻዬም ነበረች፡፡ የጅማ ጣኦት ነበር የምላት፡፡

ጠይም ነበረች! እንደ ተቆላ ቡና ወዟ ግጥም የሚል ጠይም! ጅማ 01 ቀበሌ ኪነት ነበር የተዋወቅነው፡፡ ኪነት ውስጥ የምሔደው እሷን ለማየት ነበር፡፡ በአይን ፍቅር አንድ አመት ያህል ወደድኳት፡፡ ከዛ አንድ ቅዳሜ ቀን በርጫ ምናምን ከጓደኞቼ ጋር ስንቅም መጣች፡፡ አብረን ቃምን፡፡ እንደምወዳት ነገርኳት። ትቆጣለች ብዬ ነበር እሷ ግን ከመቆጣት ይልቅ ገረማት፡፡ አንድ ዓመት ሙሉ ሳፈቅራት አለማወቋ እኮ ነው ያስገረማት፡፡ የዛን ቀን ከንፈሯን ሳምኳት። . . .የመጀመሪያዬም የመጨረሻዬም ከንፈር የነዒማ ከንፈር ነው፡፡. . . ” አብዱ በትዝታ ተመስጦ ሔደ፡፡ “ከዛስ?” አልኩት፡፡ ስሜቱ ተጋብቶብኝ በጉጉት ነበር የማዳምጠው፡፡ “በጣም ወደድኳት! በጣም!. . . ለሶስት ወር ያህል በልዩ ፍቅር ውስጥ ከረምን! ከዛ በማላውቀው የፖለቲካ ምክንያት ታስሬ ወደ አዲስ አበባ ተላኩ፡፡ ግራ ገባኝ! በምን ምክንያት እንደታሰርኩ ራሱ በኋላ ነው የገባኝ! . ..” “እንዴት?” “እዚህ ዓለም በቃኝ ታስሬ እንደቆየሁ፤ ከጅማ እንደኔው ታስሮ የመጣ ልጅ አግኝቼ ሲያወራኝ፤ ያሳሰረኝ የከፍተኛው ሊቀመንበር ሻለቃ አሸብር እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ለምን? ነዒማን ስለወደዳት አይለኝም! ሻለቃው ሞኝ ነው ባክህ! ከፊቷ እኔን ዘወር ስላደረገኝ የምትረሳኝ መስሎታል. . ” አብዱ በቁጣ እጆቹ ተንቀጠቀጡ “እንዴት እስካሁን ይኼንን ነገር አልነገርከኝም?” “ስሟን በክፉ ማንሳት ስላልፈለኩ ነው፡፡ ደሞ ነገርኩህም አልነገርኩህም ለውጥ ለውም! ” አለኝ፡፡` “በእሷ ምክንያት እንደታሰርክ ታውቃለች?” “አይመስለኝም! እንድታውቅም አልፈልግም! ምንም ለውጥ ለሌለው ነገር ባስጨንቃት ምን ትርጉም አለው?” “ቅድም ባገኛት ምናምን ያልክ መስሎኝ?”ጠየኩት።

አብዱ ለአፍታ አቀርቅሮ ቆየ፡፡ “አዎ! ባገኛት ምን ያህል እወዳት እንደነበር! ምን ያህል አፈቅራት እንደነበር ነግሬያት ብሞት ደስ ይለኝ ነበር! የሚገርምህ ለሶስት ወር ያሳለፍነውን የፍቅር ጊዜ በየቀኑ ሳስበው ደስታን ነበር የሚሰጠኝ፡፡ ሶስት አመት ሙሉ ያቺን ሶስት ወር እያሰብኩ ነው የኖርኩት! ያንን የደስታ ጊዜ እያሰብኩ ነው የተፅናናሁት! . .በብዙ መከራ ውስጥ ያለፍኩት እሷን አስብ ስለነበረ ነው. . . ” አብዱ ንግግሩን አልጨረሰም፡፡ ወታደሮቹ ወደኛ ክፍል መምጣታቸውን የሚያረዳው የእርምጃቸው ዳና በቅርብ ይሰማን ነበር. . . . “ግም . . .ግም. . ግም. . . ” መላዕከ ሞት ከበሮ ይመስላል፡፡ “ዕድል ሰጥቶህ ከዚህ በህይወት የመውጣት እድል ካገኘህ. . . አንድ ነገር ብቻ አስቸግራት፡፡ የኔን መሞት ስትሰማ ብዙም እንዳታዝን አስምልልኝ! ሌላው አደራዬንም ንገራት፡፡ እንዳትረሺኝ ብሎሻል በላት. . . ዘላለም ከልብሽ ውስጥ አኑሪኝ! በልብሽ ውስጥ ካለሁ በህይወት እንደኖርኩ እቆጥረዋለሁ ብሎሻል በላት . . . . !” አብዱ ንግግሩን ሳይጨርስ በወታደሩ ተጎትቶ ከክፍሉ ወጣ!. . . በነጋታው መገደሉን ሰማን. . . . . . . . . ከአንድ አመት በኋላ ተፈታሁ፡፡ የትም ከመሔዴ በፊት ወደ ጅማ መሔድን መረጥኩ፡፡

የአብዱን መልዕክት ማድረስ ነበረብኝ፡፡ ጅማ ደርሼ ነዒማን በአድራሻዋ አገኘኋት፡፡ አንድ ካፌ ውስጥ ቁጭ አልን፡፡ ለምን እንደፈለግኋት አታውቅም፡፡ መርዶ ላረዳት እንደሆነ አልጠረጠረችም! የወጣትነት፣የእንቡጥነት ፍቅረኛዋ እንደሞተ አታውቅም!. . . ውስጤ በሀዘን ደማ፡፡ “እወዳት እንደነበር ንገራት! ይኼኔ እሷም በሀዘን ተጎድታ እያነባች ይሆናል!. . . .እስር ቤት እንደገባሁ አታውቅም፡፡ ጥያት የመጣሁ ይመስላት ይሆናል። እንዳልረሳኋት ንገራት፡፡ አባጅፋር ቤተመንግስቱ ጋ ሆነን ጅማን ቁልቁል እያየን የገባነውን ቃል እንዳላፈረስኩ ንገራት፡፡ ብረሳሽ ነፍስያዬ ከጀሀነም አትውጣ! ብረሳህ ነፍስያዬ ከጀሀነም አትውጣ! የተባባልነውን ይዤ እስካሁን እንደኖርኩ ንገራት!. . ..” የሚለው የአብዱ ንግግር ደጋግሞ አቃጨለብኝ፡፡ አብዱ እውነቱን ነበር፡፡ ነኢማ ቆንጆ ነበረች! . . . እንደተቆላ ቡና ወዟ ግጥም ያለ ጠይም. . . “እኔን አታውቂኝም! የአብዱ ጓደኛ ነኝ. . . ” ብዬ ጀመርኩ “እሺ!” አለችኝ ፊቷ ላይ ምንም አይነት ለውጥ ሳይታይ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ “አብዱን አወቅሽው የዛሬ አራት አመት. . . .; ” አፍጥጬ ተመለከትኳት “አላወቅሁትም! . . . ግን ልትነግረኝ የነበረውን ነገር ዝም ብለህ ለምን አትነግረኝም ?” አለች ረጋ ብላ፡፡

ልነግራት የምፈልገው ስለአብዱ ነበር፤አብዱን ረስታዋለች ማለት ነው? “አብዱ የሚባል 01 ቀበሌ ኪነት ትሰሩ የነበራችሁት እንኳ. . . አብራችሁ እንኳ?. . . .” በጥያቄ አስተዋልኳት “ኪነት ውስጥ እኮ ቢያንስ 200 ልጆች ነበሩ!” አለችኝ ከአፌ ቀልባ፡፡ “ፍቅረኛሽ ነበረ!” “የኔ?” ሳቅ አለች፣በግርምት ውስጥ ሆና. . . አንገቴን ላይና ታች በአዎንታ ነቀነቅሁ፡፡ ድንግርግር ብሎኝ ነበር. . . “እ. . ያው እንግዲህ አብረን ወጥተን ሊሆን ይችላል! ግን ስንቱን ታስታውሳለህ. . . ” ሰማይ የተደፋብኝ ያህል ደነገጥኩ! “ምናልባት ረስተሸው ሊሆን ይችላል. . . .” የምናገረው ጠፋኝ፤ንግግሬ እንደ ሁለት አመት ህፃን ተኮለታተፈ፡፡ “ሊሆን ይችላል!” አለች እንደተራ ነገር አቅልላ “ግን እንዴት ረሳሽው?” ገረመኝ፡፡ ለእሷ ብሎ እስር ቤት የገባን፣ለእሷ ብሎ የማያውቀው የፖለቲካ ታርጋ ተለጥፎበት፣ለእሷ ብሎ. . . .ነፍሱን እንዲያጣ ሆኖ. . . . . ትንሽ ፀጥ ብላ ከቆየች በኋላ ድንገት ከት ብላ ሳቀች፡፡ “ጥያቄህ ይገርማል፡፡ በልጅነት እኮ ብዙ ፍቅረኛ ሊኖርህ ይችላል… ልብህ ሳይሆን ስሜትህ ነው የሚመራህ. . ኸኸኸኸ” ሳቀች. . . “አሁን ሁሉ ነገር ሰክኖ አግብቻለሁ!” አለችኝ ፈገግታዋ ከፊቷ ላይ ሳይጠፋ፡፡

“ባለቤትሽ ኪነት ውስጥ የነበረ ነው?” በአሉታ ራሷን ግራና ቀኝ ነቀነቀች፡፡ “አይደለም!. . .” አለችኝ ድምጿ ውስጥ `ስለባለቤቴ ማንነት ምን አገባህ!` የሚል እብሪት ነበር፡፡ “ባለቤትሽ ሻለቃ አሸብር ነው?” አልኳት የኔ ባልሆነ ድም፤ ቀና ብላ አየችኝ፤ ሳቅ አለች፡፡ “ከአሼ ጋር ትተዋወቃላችሁ እንዴ?” አእምሮዬ ድንገት በደራሽ እና ተስፈንጣሪ ሀሳቦች የተሞላ መሰለኝ፡፡ ነገር ዓለሙ የተገለባበጠብኝ፣ህይወት እና ሞት የተሳከሩብኝ መሰለኝ. . . ተስፈንጥሬ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ፡፡ ከዚች ሴት ጋር የምቆይበት ሽራፊ ምክንያት አልነበረኝም! ፍቅር ለእሷ ተራ ተኝቶ የመነሳት ነገር ነበር፤ለአብዱ ግን ዘላለማዊ ሥጦታ ነበር፡፡ ፍቅር ለእሷ ተራ የስሜት ሞቅታ ነበር ፤ለእሱ ግን የእውነተኛ ስሜት ነበልባል፡፡ አብዱ አሁን ገና የሞተ ያህል ትኩስ እንባ ከአይኖቼ ኩልል ብለው ወርደው ከጅማ አፈር ጋር ተደባለቁ. . .እውነት ነው የጅማው ጓደኛዬ ዛሬ ነው የሞተው. . . ሞት ማለት ከሚወዱት ሰው ልብ ውስጥ መሰረዝ ነው. . . የአብዱ ድምጽ በህሊናዬ እያስተጋባ ጅማን ለቅቄ ለመውጣት ተጣደፍኩ. . . “. . . .አባጅፋር ቤተመንግስቱ ጋ ሆነን፤ ጅማን ቁልቁል እያየን የገባነውን ቃል እንዳላፈረስኩ ንገራት፡፡ ብረሳሽ ነፍስያዬ ከጀሀነም አትውጣ! ብረሳህ ነፍስያዬ ከጀሀነም አትውጣ! የተባባልነውን ይዤ እስካሁን እንደኖርኩ ንገራት!. . .አልረሳሁሽም በላት. . . . “ “መለያየት ሳይሆን መረሳት ነው ሞት!!!” ይላል ከውስጤ አንድ ድምፅ! የአብዱ ድምፅ! አብዱ አሁን እንደሞተ ገባኝ. . .ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ . . . . . እንባዬ የጅማን አፈር እያራሰው. . . . ጅማን ለቅቄ ለመውጣት ተጣደፍኩ .

**********

ምክንያቴ እውነቱን ልንገርሽ? ስለተለየሽኝ. . . . ቃላት ካንደበቴ፣ ሙቀት ካካላቴ፡፡ ቆየ ከተለየ፡፡ እውነቱን ልንገርሽ? ስለተለየሽኝ. . . እንባ `ንኳ ላዘኔ፣ ሳቅ ለደስታ ቀኔ፡፡ ቆየ፣ ከተለየ፡፡ ስሜት የሌለበት፣ ቀረኝ ቁንፅል ህይወት፡፡ ሰው እንኳን. . ሰው እንኳን የኔ ውድ፣ ጠፍቶ የማያውቀው ከመግቢያዬ አውድ፡፡ ራቀኝ ..ሸሸኝ. . አንቺ ስለተውሽኝ፡፡ እውነቱን ልንገርሽ? ስለተለየሽኝ. . . ፃ`ይ ፀናች በ`ምራብ፣ ብርሀን እስክራብ፡፡ አፀድ ረገፉ፣ ፀደዮች አለፉ፡፡ የወፎች ዝማሬ፣ የአራዊት ፍካሬ፡፡ ቆየ ከተለየ፡፡ ውበት የሌለበት፣ ፀዳል የሌለበት፣ ቀረኝ ቁንፅል ህይወት፡፡ ሁሉንም አጥቼ፣ የኖርኩት ፀንቼ፡፡ ለምን ይመስልሻል? ብዙ ተዘርፌ፣ እልፍ እልፉን አጥቼ፣ ለምን ይመስልሻል? ለእስካሁኗ ቅፅበት የኖርኩት ፀንቼ፡፡ ተስፋዬን ቀብሬ፣ እምነቴን ከስሬ፣ ለምን ይመስልሻል እስካሁን መኖሬ? አንድ ነው ምክንያቴ፣ ለቆየች ህይወቴ፡፡ እንድኖር የሆንኩት በሞት ሳልረታ፣ ብርታት ሆኖልኝ ነው በልቤ የቀረው የአንቺው ት. . ዝ . ታ . . ክፋዬ፣ ለቆየች ህይወቴ፣ አንቺ ነሽ ምክንያቴ፡፡

Read 4938 times