Saturday, 04 May 2013 10:28

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና እነአንዱአለም አራጌ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ፀናባቸው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(10 votes)

በሽብርተኝነት ወንጀል በከፍተኛው ፍርድ ቤት ተከሠው ጥፋተኛ የተባሉትና ከእድሜ ልክ እስከ 13 ዓመት እስራት የተፈረደባቸው የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና የእነ አንዷለም አራጌ የይግባኝ ጉዳይ ሀሙስ እለት ውሳኔ ያገኘ ሲሆን የሁለቱም የይግባኝ ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የተባለባቸውን አምስት መዝገቦች በዝርዝር ካየ በኋላ ሁሉም መዝገቦች ተያያዥና ተመሣሣይ ነገር የያዙ በመሆናቸው በአንድ ላይ መታየታቸውን የጠቆሙት የመሀል ዳኛው አቶ ዳኜ መላኩ፤ መዝገቡ በጥንቃቄ ታይቶ የተወሠነ በመሆኑ ይግባኝ ባዮቹ የስር ፍ/ቤት ውሣኔን እንዲቀበሉ መወሰኑን ገልፀዋል፡፡

“ይግባኝ ጠያቂዎቹ ከፍተኛ ጥፋት ፈፅመዋል የሚያስብሉ ነገሮች ስለተገኙባቸው ጥፋተኝነታቸው ትክክል ነው ብለናል” ያሉት የመሃል ዳኛው አቶ ዳኜ መላኩ፤ የ5ኛ ተከሣሽ ክንፈ ሚካኤል ደበበ ይግባኝ ተሻሽሎ፣ ከ25 አመት ወደ 16 ዓመት ዝቅ ያለ ሲሆን የሌሎቹ በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ በፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ጥፋተኛ በመባላቸው አንዷለም አራጌ እድሜ ልክ፣ ናትናኤል መኮንን 18 ዓመት፣ እስክንድር ነጋ 18 ዓመት፣ ክንፈ ሚካኤል ደበበ 25 ዓመት፣ የሺዋስ ይሁንአለም 15 አመት፣ አንዷለም አያሌው 14 ዓመትና ዮሀንስ ተረፈ 13 ዓመት የተፈረደባቸው መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

ከይግባኝ ጠያቂዎቹ መካከል ዮሀንስ ተረፈ፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንአለም እና አንዷለም አያሌው ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት በመዛወራቸው ጉዳያቸው በሌሉበት ከሌሎቹ ጋር ታይቷል፡፡ ችሎቱ ስራውን ጨርሶ ሲበተን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “እውነት አንድ ቀን ይወጣል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እውነቱን ይወቀው” በማለት ሲናገር፤ ክንፈ ሚካኤል በበኩሉ “የተከራከርነው ፍትህ እናገኛለን ብለን ነው፤ ከእኛ ጋር አብራችሁ ለምትንከራተቱ ሁሉ እናመሠግናለን” ብሏል፡፡ አንዷለም አራጌ ግን ዝምታን መርጧል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ጨምሮ በርካታ ታዳሚዎችና የታሣሪ ቤተሠቦች በውሳኔው አዝነው እንባ ሲያፈሱ ተመልክተናል፡፡

Read 3479 times