Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 November 2011 08:00

በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ ያለውን ስር የሰደደ ችግር፣ ለችግሩ ምክንያት በሆነ አስተሳሰብና አሰራር መፍታት አይቻልም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በቅርቡ ዜጐች የከተማ ቦታን በሊዝ ብቻ እንዲይዙ የሚያስገድድ አዲስ አዋጅ ታውጇል፡፡ ይህ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታወጀ አዋጅ “ለተሳለጠ፣ ለውጤታማ ለፍትሐዊና ለጤናማ የመሬትና የመሬት ነክ ንብረት ገበያ ልማት፣ ቀጣይነት ለተላበሰ የነጻ ገበያ ሥርዓት መስፋፋት፣ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም እንዲኖር ለማድረግ” እንደታወጀ በዚሁ በአዋጅ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ስለ አዋጅ አስፈላጊነት የተሰጠው ምክንያትና የአዋጅ ይዘት ሲታዩ ለየቅል ናቸው፡፡

በአዋጁ መሰረት ዜጐች በከተማ ቦታ ላይ ያላቸው የባለይዞታነት መብት በሊዝ ስምምነትና ኪራይ መሠረት ብቻ ይሆናል፡፡ አዋጁ ማንኛውም ግለሰብ በግዢም ሆነ በተለያየ መንገድ ለዘመናት ንብረቱ ሆኖ የቆየውን የመሬት ባለቤትነት መብት ወደ መንግስት አዛውሯል፡፡ 
ማንኛውም ዜጋ በስሙ በተመዘገበለት የከተማ ቦታ ላይ ባፈራው ቋሚ ሀብትና ይህንኑ ሀብት ለማፍራት ምክንያት በሆነው መሬት መካከል ምናባዊ ልዩነት በመፍጠር ዜጐች የተረጋገጠላቸው መብት ይዞታው ላይ ላፈሩት ንብረት ብቻ እንዲሆን ይደነግጋል፡፡ ከሊዝ አሰራሩ ውጭ ቀደም ብለው የተያዙ ቦታዎች ላይ የባለይዞታነት ዝውውር በተደረገ ቁጥር ከውርስ ውጪ ቦታው የተላለፈለት ሰው ባለይዞታነት የሚረጋገጠው ወይም ባለይዞታው ንብረቱን ማዘዋወር የሚችለው በሊዝ ሥሪት ብቻ እንዲሆን ደንግጓል፡፡
የማንኛውም ይዞታ የሊዝ ዋጋና ተመንም ተለዋዋጭነትና እንደ አካባቢው ሁኔታ በየጊዜው የሚወሰንና የመሬት አቅርቦቱም በጨረታ የሚከናወን እንዲሆን ከማወጁም በላይ በሊዝ ሥሪቱ መሰረት ባለይዞታ ሆኖ የቆየ የሊዝ ባለመብትም የሊዝ መብቱ ሊታደስለት የሚችለው በቅድመ ሁኔታ መሆኑንና አፈጻጸሙም የመንግስትና የአስፈጻሚዎች የሁንታ በሚሰጥ መልኩ በአዋጁ ላይ ተደንግጓል፡፡ የአዋጁ አንቀጾች በዝርዝር ሲታዩ በዜጐች ነባር ይዞታ ሥር ባሉ የከተማ ቦታዎች ላይ ጭምር የንብረት ባለመብትነትን በመግፈፍና የመንግስት ባለመብትነትን ፍጹማዊ በሆነ ደረጃ በማጠናከር በመሬት ላይ የሚኖር አቅርቦትን፣ ዝውውርንና መሰል አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን መንግስት በብቸኝነት እንዲያከናውን ስለሚያዝ፣ ዜጐች ህጋዊ በሆነ መንገድ ከመሬት ጋር በተያያዘ ሀብት የማፍራት መብታቸውን የሚጻረር ነው፡
ኢዴፓ ከመሬት አጠቃቀም ጋር ተያይዘው የሚነሱ ውስብስብ ችግሮች አይነተኛ ምንጮች በተለይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማትና አስፈጻሚዎቹ እንዲሁም ከነዚህ አስፈጻሚዎች ጋር ህገወጥ በሆነ መንገድ ትስስር በመፍጠር የመሬት ዝውውሩን የተቆጣጠሩ ጥቂት ግለሰቦች እንደሆኑ ያምናል፡፡ መንግስት ይህንን ችግር ለማስወገድም ጓዳውን በማጥራት ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ ያለበት መሆኑን ኢዴፓ የሚያምን ቢሆንም ይህ አዋጅ በሚከተሉት ምክንያቶች ለመሬት አሰራር መመሰቃቀል ዓይነተኛ ተጠያቂዎችንና ምክንያቶችን በቅጡ ግምት ውስጥ ሳያስገባ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጐችን ባለመብትነት የሚጋፋ በመሆኑ ሕጉን እንዲለውጥ አጥብቆ ያሳስባል፡፡
አንደኛ፤ ይህ አዋጅ ዜጐች በአገራቸው ቋሚ ሀብትና ንብረት ለማፍራትና ይህንንም ሀብት እያደገ፤ እየተስፋፋና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ለማድረግ ያላቸውን መብት የሚገድብ ከመሆኑም በላይ በግዢም ሆነ በረጅም ጊዜ ያፈሩት ሀብትና ንብረት ላይ ያላቸውን ነጻነት በእጅጉ የሚጻረር ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሰረት ከእንግዲህ በከተማ የሚኖሩ የከተማ ቦታ ለባለይዞታዎች ይዞታውን ከመንግስት፣ ከመንግስታዊ ተቋማት፣ ከግለሰቦች፣ ህጋዊ እውቅና ካላቸው ድርጅቶች ወይም ከባንኮች በግዢ ወይም ከቤተሰብ በውርስና በዝውውር ባገኙትና ባፈሩት ቋሚ ሀብት ላይ ለገጠር መሬት ባለይዞታዎች የሚሰጠው የይዞታነት ማረጋገጫ ደብተርን ያህል እንኳን መብት እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡
ሁለተኛው አዋጁ ወትሮውንም ቢሆን ታዳጊውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ጨምድዶ በመያዝ የስልጣን ጡንቻውን ማፈርጠምን ሥራዬ ብሎ ለተያያዘው የኢህአዴግ መንግስት ተጨማሪ ክንድ እንዲሆን ሁኔታዎችን ይበልጥ የሚያመቻች ነው፡፡ በተጨማሪም አዋጁ መሬትን በመንግስት ብቸኛ ባለቤትነትና ቁጥጥር ስር ቆልፎ በመያዝ የኢኮኖሚያዊ ሁደትና የካፒታል ምንጭ ሆኖ ከማገልገል የሚያግድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያም አዋጁ ከነጻ ገበያ መርህም ሆነ ከጤናማ የንብረትና የሀብት ልማት ጋር ፈጽሞ የማጋጭ ነው፡፡
አዋጁ በነጻ የገበያ መርህ መሰረት እንደወዳደሩ ተፈቅዶላቸው በአገሪቱ ፖሊሲና ህግ መሰረት የተቋቋሙ በርካታ የግል ባንኮች እያሉ ከመሬትና ከሊዝ አያያዝ ጋር በተያያዘ የሚዘዋወረው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የመንግስት ንብረት በሆነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ብቻ እንዲከናወን ይደነግጋል፡፡ ይህ አዋጅ በሚፈጥረው አስገዳጅ የግብይት ግንኙነት የተነሳ የግል ባንኮች ዋነኛ የማበደሪያ መሳሪያ ከሆነው የቋሚ ንብረት ሽያጭና ዝውውር ውጭ እንዲሆኑ ያስገድዳል፡፡
ሦስተኛው አዋጁ መሬትና መሬት ነክ ጉዳዮችን ከዜጐች ጉዳይነት አውጥቶ ሙሉ በሙሉ ለአንድ መንግስታዊ ተቋም የሚሰጥ በመሆኑ በብቃት ማነስ፤ በአቅም ውስንነት እና ሙስናን ለመሳሰሉት ተጠቃሽ ምክንያቶች አፈጻጸሙን ተጋላጭ ያደርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አዋጁ ላይ የተዘረዘሩን ችግሮች ሊፈታ የማይችል ከመሆኑም በላይ ይበልጥ ሊያባብስ ይችላል፡፡
በኢዴፓ እምነት መሬት ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር መሆኑ በራሱ በዘርፉ ለሰፈነው ሙስና ዋንኛ ምክንያት ነው፡፡ ምንም እንኳን በህገ-መንግስቱ መሬት የህዝብና የመንግስት መሆኑ ቢደነገግም ባለፉት ዓመታት መታዘብ እንደተቻለው የዚህ ድንጋጌ መሰረታዊ ስህተት ካስከተላቸው ውጤቶች በዋነኛነት ሊጠቀስ የሚችለው በሕጉ መሰረት መሬት የህዝብም ሆነ የመንግስት ሳይሆን ዛሬ እስርቤትን እያጣበቡ የሚገኙ የኢህአዴግ ካድሬዎች መነገጃ መሆኑ ነበር፡፡ ከዚህ እውነታ መረዳት እንደሚቻለው መሬት መሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር በሚሆንበት ጊዜ መሬቱ የመንግስት ጥቂት ሹመኞች እንጂ የህዝብ ሀብት ሊሆን እንደማይችል የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ መንግስት ኢኮኖማን በመምራትና ፖሊሲ በመቅረጽ እንዳስፈላጊነቱም ጉድለትን ለማሟላት አምራችና አቅራቢ በመሆን የሚያደርገው ንቁ ተሳትፎ ዓለም አቀፍ በሆነ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ መሰረት አጠቃላይ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም መንግስት ከልክ ባለፈ ኢኮኖሚን ለመቆጣጠር የሚያደርገው እንቅስቃሴ በአገር ኢኮኖሚ፤ በህዝብ አጠቃላይ መብትና በተለይ በፖለቲካ ውስጥ በነጻነት የመሳተፍ መብት ላይ ፈርጅ ብዙ ጥፋት እንደሚያስከትል ኤዲፓ በጥብቅ ያምናል፡፡
በኢኮኖሚ ትንታኔ መስክ እንደሚታወቀው ከነጻ ገበያ መርህ ጋር በሚጣረዝ መልኩ የመንግስት ቁጥጥር ሲገዝፍ መንግስት ለህዝብ ያለውን ተጠያቂነትም ሆነ የመንግስት አስፈጻሚዎች ለራሱ ለመንግስት እና ለህዝብ ያላቸውን ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደሚያስቸግር በዚህም ምክንያት ሙስና እንደሚስፋፋ የታወቀ ነው፡፡ መንግስት “ለህዝብ ጥቅም” በሚል መፈክር መሬትን የመሰለ ትልቅ ሃገራዊ ሐብት ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ እራሱን ብቸኛ ባለይዞታ ሲያደርግ፤ ለመንግስት አስፈጻሚዎች ያልተገደበ ስልጣን ይሰጣል፡ ይህም አሠራር ፖለቲካዊ አድሎና ሙስናን የመሳሰሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠንቆችን በማስፋፋት ዜጎች በህጋዊ መንገድ ብቻ መብታቸውን ለመጠቀም የሚቸገሩበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነወ፡፡ የዜግነት መብትን ለማስከበርም ሆነ ሠርቶ ለመክበር በፖለቲካ ማህበርተኝነት መታቀፍና ከሕገ-ወጥ ባለሥልጣናት ጋር በጥቅም መተሳሰር አስተዳደር ላይ አሁን የተወሰደው እርምጃ ጠቋሚ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ ወሰን ባጣ መልኩ በአገሪቱ ሰፍኖ የቆየው ሙስናም ይህን እውነታ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
በሌላ በኩል ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ከስርዓቱ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለመቻል ባሻገር በአገሪቱ ተንሰራፍቶ ከቆየው የተጠያቂነት እጦትና ሙስና መስፋፋት ተነጥሎ የሚታይ ችግር አይደለም፡፡ በሀገሪቱ የፖለቲካ አስተዳደር ውስጥ ሙስና ዋነኛ ችግር በሆነበት በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ስራ መስራት የተረጋገጠ ውጤት እንደማያስገኝ ባለፉት አመታት በዘርፉ የሰፈነውን ሙስና ለማስወገድ ተብለው ከተሰወዱ እርምጃዎች ውጤት አልባነት የበለጠ ማረጋገጫ አይገኝም፡፡ ለዚህም ውስብስብ ችግር አለመፈታትና ለመፍትሔው መራቅ አይነተኛ ምክንያቶች የሚሆኑት በተሟላ መልኩ የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ ለሕዝብ ተጠያቂነት አለመኖር፣ የነጻና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አለመስፋፋት ከችግሩ ጋር ያላቸውን ትስስር ከግምት ውስጥ አለማስገባትና ወጥ የሆነ መፍትሔ አለመሻት ነው፡፡
በመጨረሻም እንደ ኢዴፓ እምነት የችግሩ መፍትሔ መሬት ሙሉ በሙሉ የመንግስት ሐብትና ንብረት ሆኖ የሚገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ በመለወጥ የመሬት ይዞታና አጠቃቀምን ከብቸኛ የመንግስት ቁጥጥር ስር በማውጣት የዜጎችን የመሬት ባለቤትነት፣ ኢኮኖማያዊ ተጠቃሚነት፣ ነጻ ገበያ ስርዓትን በሚያጠናክር መልኩ መታረም አለበት፡፡
ኢህአዴግ ይህ እንዲሆን የሚያስችል የፖሊሲ ለውጥና በአገሪቱ የህግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ የተሟላ የተጠያቂነት አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ሙስናን በህዝብ እውነተኛ ተሳትፎ ላይ በተመሰረተ መንገድ ለመታገል የሚያስችል አዲስ የፖሊሲ ማዕቀፍ መፍጠር አለበት፡፡ ኢዴፓ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በመሬት አጠቃቀም ዙሪያ ሲታዩ የቆዩ ችግሮችን ችግሩን ሲፈጥር በቆየው አስተሳሰብና አሰራር ለማስወገድም መሞከር ችግሩን ከማወሳሰብ በስተቀር የተለየ ለውጥ ያመጣል ብሎ አያምንም፡፡ ዜጎችም አዲሱ የሊዝ አዋጅ መብታቸውን የሚያጠብና በዘርፉ ሥር ሰደው የቆዩ ችግሮችንም ሊፈታ የማይችል መሆኑን ተረድተው ኢህአዴግ የተሻለ አስተሳሰብና የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ኢዴፓ በሚያደርገው ትግል እንዲሳተፉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ሰላምና ሕብረ-ብሔራዊነት ዓላማችን ነው!
ከኢዴፓ ስራ-አስፈጻሚ ኮሚቴ
ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም

 

Read 4878 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 08:03