Saturday, 11 May 2013 11:06

የፈንጂ ስልጠና ሰጥተዋል የተባሉት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የአቡነ ጳውሎስን ሃውልት የማፈንዳት እቅድ እንዳለ ተነግሯቸዋል አዲስ አበባ በመምጣት ሁለት ጊዜ ስልጠና መስጠታቸውን አምነዋል በግንቦት 7 አባልነት እና ከአመራሮች ተልዕኮ በመቀበል የሚያስከትለው ጉዳት እያወቁ የፈንጂ ስልጠና ሰጥተዋል ተብሎ እስካሁን በፍርድ ቤት ካልቀረቡት አንደኛ ተከሳሽ ሻለቃ ማሞ ለማ ጋር የተከሰሱት 2ኛ ተከሳሽ አበበ ወንድማገኝ ልደታ በሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ረቡዕ ዕለት ቀርበው በሠጡት ቃል የፈንጂ ስልጠና መስጠታቸውን አመኑ፡፡ ተከሣሹ ስለፈፀሙት ድርጊት ሲያብራሩም የፈንጂ ስልጠናውን የሠጡት ከሚኖሩበት እንግሊዝ ለንደን ከተማ ለእረፍት ቤተሠባቸውን ይዘው በመጡበት አጋጣሚ መሆኑንና በዚያው ኢትዮጵያ ስትሄድ የፈንጂ ስልጠናውን ስጥ የሚል ትዕዛዝ ከሻለቃ ማሞ እንደተላለፈላቸው ገልፀዋል፡፡

ፈንጂው የሚፈነዳው ቦሌ መድሃኔአለም በሚገኘው የአቡነ ጳውሎስ ሃውልት ላይ መሆኑ እንደተነገራቸው የጠቆሙት ተከሳሹ፤ ለምንድን ነው ሃውልቱ ላይ እንዲፈነዳ የተፈለገው ብለው ሲጠይቁ የተባልከውን ዝም ብለህ ፈፅም የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የእንግሊዝ ዜግነት እንዳላቸው በመግለፅም ወታደር የመሆን ፍላጐት ስላደረባቸው የእንግሊዝ መንግስትን በውትድርና ሰልጥነው እንዲቀጠሩ ጠይቀው እንደነበር የገለፁት ተከሳሹ፤ የእንግሊዝኛ ቋንቋቸው ደካማ በመሆኑ ተቀባይነት እንዳላገኙ፣ በዚህ መነሻነትም ለምን አላማ እንደሚሰለጥኑ ባይረዱም ይህን ፍላጐታቸው ለሻለቃ ማሞ ተናግረው እሳቸው ባመቻቹት መንገድ ወደ ኤርትራ በመግባት “ኢን” በተባለ ቦታ የፈንጂና የመሣሪያ ትምህርቶችን በኤርትራውያን አሰልጣኞች ለሦስት ሣምንታት መሰልጠናቸው ተናግረዋል፡፡ “በወቅቱ ፊልም ላይ እንደማየው አይነት ስልጠና እንዲሰጠኝ ነበር የፈለግሁት” የሚሉት ተከሳሹ፤ ነገር ግን እዚያ ከደረሱ በኋላ ከፈንጂና ከመሣሪያ ስልጠና በቀር የጠበቁትን እንዳላገኙ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ተከሣሹ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል ስልጠናውን ከመውሰዳቸው በተጨማሪ የቅንጅት አባል ባይሆኑም በተለያዩ የቅንጅት ስብሰባዎች ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ሻለቃ ማሞ ለማም አሁን ያለው መንግስት ያለ ትግል ሊቀየር እንደማይችል ነግሮኛል ያሉት ተከሳሹ፤ በወቅቱ እሳቸውም ያስፈልጋል ብለው ማመናቸውን ተናግሯል፡፡ በተደጋጋሚ በሰዎች ግፊት በስህተት ሳላውቅ የፈፀምኩት ድርጊት ነው ሲሉ ያስረዱት ተከሳሹ፤ ቀደም ሲል በ2003 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ፒያሣ ቸርችል ጐዳና 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ ፊትለፊት መኪና ውስጥ በገመድ የሚነሳ ፊውዝ የተባለውን ፈንጂ ማሰልጠናቸውን አምነዋል፡፡ ፖሊስ ጣቢያ በር ላይ ለማሰልጠን ለምን ፈለግህ የሚል ጥያቄ ከዳኞች የቀረበለላቸው ተከሣሹ ከእይታ ትኩረት ነፃ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ተከሣሹ ቃላቸውን ሲሰጡ የተልዕኮው ባለቤት ግንቦት 7 መሆኑን ያወቁት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ከመርማሪዎቹ መሆኑንም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ አቃቤ ህግም ተከሣሹ የፈንጂ ስልጠና መስጠታቸውን ብቻ እንዳመኑ በማስታወስ ድርጊቱን መፈፀማቸውን ሙሉ ለሙሉ ስላላመኑ ማስረጃውን ለማጠናከር እንዲረዳ ምስክሮችን አቅርቤ እንዳሰማ ይፈቀድልኝ ያለ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን ተቀብሎ ምስክሮቹን አቅርቦ እንዲያሰማ ፈቅዷል፡፡ የአቃቤ ህግ ምስክሮችም ግንቦት 26 ቀን 2005ዓ.ም እንዲሰሙ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ የተከሳሽ ጠበቃ ያቀረቡአቸውን መቃወሚያዎች በከፊል ውድቅ ያደረገ ሲሆን በመቃወሚያው የህግ አንቀፁ አልተጠቀሰም የተባለውን አቃቤ ህግ አንቀፁን ጠቅሶ ክሱን እንዲያቀርብ አዟል፡፡ ቀደም ሲል በዋለው ችሎት የተከሳሽ ጠበቃ፤ ክሱ ግልጽ አይደለም በተለይም የወንጀሉን አይነት በሚገባ አይገልጽም ሲሉ ያቀረቡትን መቃወሚያ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ የወንጀሉ አይነት በሚገባ ተጠቅሷል፤ ክሱ ግልጽ አይደለም የሚለው ማስረጃዎች ከታዩ በኋላ የሚወስን በመሆኑ ተቀባይነት አላገኘም ብሏል፡፡

Read 3323 times