Saturday, 11 May 2013 11:50

መንግሥት የግለሰቦች አገልጋይ ሳይሆን የሕዝብ ወኪል ይሁን!

Written by  ካሌብ ንጉሴ
Rate this item
(2 votes)

ለአንድ መንግሥት ህልውና ከሚያስፈልጉት ጉዳዮች ቀዳሚው የሚመራውን ህዝብ ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ነው፡፡ ደረቱን ነፍቶ ግብር የማስከፈል መብት እንዳለው ሁሉ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ግዴታውን ካልተወጣ መንግስትነቱ ለአደጋ ተጋልጧል ማለት ነው፡፡ ኢህዴግ በጉልበቱም ቢሆን በትረ መንግስት እንደጨበጠ ሰሞን ሌባንና ዘራፊን ተግቶ በመከላከሉ በህዝቡ ዘንድ መልካም ተቀባይነት ነበረው፡፡ አባላቱም ከሞላ ጐደል ጨዋዎችና ቁጥቦች ነበሩ፡፡

የመጡበት ማህበረሰብ (ገጠሬው) ጨዋና የሞራል ባለቤት ስለሆነ ስግብግቦችና አታላዮች አልነበሩም፡፡ የስልጣን ክፍፍል ሲጀመር፤ አንዳንዶች በቅጽበት ባለ ዘመናዊ መኪኖችና የሰማይ ጠቀስ ፎቆች ባለቤት ሲሆኑ፤ ትላንት የኔ ቢጤ የነበረው በቅጽበት “አንቱ…” የተሰኘ ባለፀጋ ሆኖ ሲመለከት ጨዋው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ይሉኝታና ዕምነቱን እንደ ጨርቅ አውልቆ መጣል ጀመረ፡፡ በቅጽበት ለመበልፀግ ሲልም በአቋራጭ የመክበሪያ ሩጫውን ተያያዘው፡፡ በአቋራጭ ለመክበር የቆረጠ ሰው ከበዛ ደግሞ ህግና ህጋዊነት አደጋ ላይ ይወድቃሉ፤ ወድቀዋልም፡፡

ትላንት ከትላንት በስቲያ በኬንያና ናይጀሪያ እንሰማው የነበረው ጉቦኝነት፣ አገራችን ውስጥ ያለሃይ ባይ ሰተት ብሎ ገባና ቁምስቅላችንን ያሳየን ጀመር፡፡ ምንም አይነት ቀላል ጉዳይ ቢሆን ሊከናወን የሚችለው በመደለያ ነው፡፡ ይህ አደገኛ ጉዞም ህዝቡን ቁምስቅሉን እያሳየው መጣ፡፡ “ኑሮ ጣራ ደረሰ፤ ኧረ የመንግስት ያለህ!” ሲባል “የኑሮ ውድነቱን ያመጣው ዕድገቱ ነው” የሚል የዋህ ወይም የጅል መልስ ይሰጣል፡፡ እርግጥ ነው ባለስልጣኖቻችን ከህዝብ በሚሰበሰብ ሃብት ባለሁለትና ከዚያም በላይ ዘመናዊ መኪኖች እንዲገዙላቸው ወይም እንዲመደቡላቸው ልዩ ዕድል ተሰጥቷቸዋል፡፡ የአብዛኞቹ ባለስልጣናት ልጆች የሚማሩት ከወር ደሞዛቸው በላይ በወር በሚያስከፍሉ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፡፡

ግን ገንዘቡ ከየት እንደሚመጣ እነሱና እግዜር ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ የቤት መስሪያ ቦታ ብዙውን ጊዜ 500 ሜ.ካሬ ቦታ ይሰጠቸውና (የመስሪያ ገንዘብ እንደሚመቻችላቸውም ይነገራል) የተንጣለለ ቤት ሰርተው፣ በወር 50 እና 30ሺህ ብር እያከራዩ የሚኖሩት ከመንግስት በሚሰጣቸው ምርጥ ቪላ ውስጥ ነው፡፡ ለሰፊውና በኪራይ እሳት ለሚጠበሰው ነዋሪ ግን ስንት ዓመት ደጅ ጠንቶ የሚሰጠው (ከ97 ወዲህ እሱም ቀርቷል) 72 እና ከበዛም 94 ሜትር ካሬ ነው፡፡ የቤት ፍላጐት ባለመሟላቱም ህዝቡ ከጅብ ጋር እየታገለ ሌሊት የወፍ ጐ ጆ የምትመስል ደሳሳ መጠለያ ሲያውገረግር ያድራል፡፡ ከመንግስት ጋር በአንድ ወይም በሌላ ንክኪ ያለው ደግሞ የአዲስ አበባንና የፊንፊኔ ዙሪያ ገባ መሬት እንደ ልቡ ይቸበችባል፡፡ (ራሱ መንግስት ያመነው ነው) በሰፊው መሬት የያዘውንና እንደ ራሱ ሃብት እንደ ልቡ የሚጨፍርበትን ማንም አይናገረውም፡፡ ሲፈራ ሲቸር የእንጨት ጐጆ ቀልሶ በሁለት ስጋቶች ተወጥሮ የሚኖረውን ምስኪን የኔ ቢጤ ግን ጐጆው በላዩ ላይ በግሬደር ስትፈርስበት ደጋግመን ታዝበናል፡፡

ሁለት ስጋቶች ያልሁት አንደኛው መብራትና ሌሎች የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች በሌሉበት ቤተሰቡን በአውሬ እንዳይነጠቅ፤ ጥቂትም ብትሆን ያለችው ጥሪቱ በወሮበሎች እንዳትዘረፍ ቀን የትም ሲኳትን ውሎ ሌሊትም በስጋት ሲባዝን ማደሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ስጋቱ ደግሞ ያችኑ የጭራሮ ቤቱን “መንግስት ድንገት መጥቶ ቢያፈርስብኝ የት እገባ ይሆን?” ከሚል ጭንቀት የሚመነጭ ነው፡፡ በመሠረቱ ህገወጥነት የሚበራከተው ከቅንጦት አይደለም፡፡ መንግስት መስራት የሚገባውን በጊዜ ባለማድረጉ ፤ ህዝባዊ ጥያቄዎች በወቅቱና በአግባቡ ተግባራዊ ምላሽ ሳይሰጥባቸው ሲቀር፤ በአንፃሩ ጥቂት ህገወጦች በቆረጣ ሲበለጽጉ ሲያይ ጨዋ የነበረው ሁሉ ወደ ህገወጥነት ይገባል - መንግስት በፈጠረው ጣጣ፡፡ የቀበሌም ሆኑ የክፍለ ከተማ ባለስልጣናት የሚኖሩት በህዝቡ መሃል ነው፡፡ “ህገወጥ” የሚባለው የመሬት ወረራ ሲካሄድም ያያሉ፤ ግን ትንፍሽ አይሉም፡፡ ይህን የሚያደርጉት በሁለት ምክንያት ነው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ አንደኛው ቤቱ ከተሰራ በኋላ “ላፈርስብህ ነውና ይህን ያህል ገንዘብ አምጣ” ለማለትና ለህገወጥ ብልጽግና ነዋሪውን ለማመቻቸት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በስልጣን ላይ ሳሉ እነሱም የጨዋታው ተዋናይ በመሆን በቤተሰባቸው ወይም በዘመድ አዝማድ ስም የሃገሪቱን መሬት ተቀራምተው ዘወር ለማለት ነው፡፡ ይህ እውነት መሆኑን የምናውቀው ሚያዝያ 28 ቀን 2005 ዓ.ም ማታ “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህገ ወጥ መንገድ ስለተያዙ ቦታዎች ሊያወጣው ነው” ስለተባለው መመሪያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተነገረውን ዜና በወጉ ስንመዝነው ነው፡፡ በመጀመሪያ “ህጋዊ የሚሆኑት ከ1988 ዓ.ም በፊት ይዘው የነበሩና ይዞታቸው ለመሆኑ የመሬት መጠቀሚያ ግብር የከፈሉበት ደረሰኝ ያላቸው ብቻ ናቸው” ሲባል ነበር፤ ቀጥሎ ደግሞ “እስከ 1994 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ቤት የሰሩ” ተባለ፤ ለሶስተኛ ጊዜም “እስከ 1997 ባሉት ጊዜያት የተያዙ ይዞታዎች ብቻ ህጋዊ ይሆናሉ” ተብሎ ሽርጉድ በዝቶ ነበር፡፡

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሰማነው ግን “እስከ ህዳር 2004 ዓ.ም የተሰሩ ህገወጥ ግንባታዎች ሁሉ ህጋዊ እውቅና ይሰጣቸዋል” የሚል ነው፡፡ የጽሑፌ ዓላማ “በህገወጥ መንገድ ቤት ለሰሩ ዜጐች ለምን ህጋዊ ዕውቅና ተሰጣቸው” የሚል ተራ ምቀኝነትና ክፋት አይደለም፡፡ ይልቁንም መንግስት ዜጐቹን መፈናፈኛ እያሳጣ ለችግርና ለህገወጥነት እንዴት እንደሚገፋፋቸው፤ ህገወጥነትን ለመቆጣጠርም አቅም እያጣ መምጣቱን ማሳየት ነው፡፡ ነዋሪው በየቀኑ እንደ ሮማን ፍሬ ከተሞችን አጨናንቆ ሊያነዳቸው ደርሷል፡፡ በገጠር ያሉ ወጣቶች በአዋጅ የተገደዱ እስኪመስሉ ድረስ በየቀኑ ወደ ከተሞች፤ በተለይ ወደ አዲስ አበባ ይጐርፋሉ፡፡ ከተማ ውስጥ በቂ ሥራ የለም፡፡ ዲግሪ ይዞ የሻይና የታክሲ መሳፈሪያ እያጣ ሳንቲም የሚለምን ወጣት እያየን ነው፡፡ ነዋሪ በበዛ ቁጥር የመኖሪያ ቤት ኪራይ ሰማይ ይነካል፡፡ ኪራይ ሲጨምር ዜጐች መፈጠራቸውን እስኪጠሉ ድረስ በኑሮአቸው ይንገሸገሻሉ፡፡ የአከራዮች ጭካኔ ወደር የለውም፡፡ መንግስት የጋራ ህንፃዎችን ለመገንባት ተፍተፍ ማለቱ የሚካድ ባይሆንም ከነዋሪው ፍላጐት ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ የጠብታ ያህል እንኳ ችግሩን መፍታት አልቻለም፡፡ በዚያ ላይ ብዙ ገንዘብ ወጥቶባቸው የተገዙና የታደሱ ቤቶች አመት ሳያገለግሉ ሊፈነገሉ መድረሳቸውን እያየን እየሰማንም ነው፡፡ (ጀሞ ሳይት ላይ የተፈጠረውን ልብ ይሏል) ይህ የሚያመለክተው የ “እንካ በእንካ” ሥራ ውጤት መሆኑንና የጥራት ጉዳይ ትኩረት እንደተነፈገው ነው፡፡

ባለስልጣናቱ ለተሰጣቸው ኃላፊነት ሳይሆን ለመሞዳሞድ ቅድሚያ የሰጡ ይመስላሉ፡፡ ይህ ካልሆነ ተቆጣጣሪ መሃንዲሱ የት ነበር? በየጊዜው “ሳይቶችን ሲጎበኙ” የምናያቸው ባለስልጣናትስ ምኑን ነው ሲጎበኙ የከረሙት? ነዋሪው ተበድሮም ሆነ በአቅሙ ቤት ለመስራት ቦታ እንዲሰጠው የባለስልጣናትን ደጅ መጥናት ሰልችቶታል፡፡ በህጋዊ መንገድ ጠይቆ ህጋዊ መልስ ሲያጣ ወደ ህገወጥነት ያመራል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ሲጠቀም የሚስተዋለው ህግን አክብሮ መንግስትን አምኖ የተቀመጠው ሳይሆን ህግን መረጋገጫቸው ያደረጉ ባለስልጣናትና ህገወጥ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በመሠረቱ ኢትዮጵያ የሁላችን ሃብት ናት፤ መከራዋ መከራችን፤ ደስታዋ (አይተንባት ባናውቅም) ደስታችን ነው፡፡ አብዛኞቹ የመንግስት ባለስልጣናትና ካድሬዎች የሚያስቡትና የሚተገብሩት ግን በግልባጩ ነው፡፡ አገሪቱን እንደ ግል ሃብታቸው፤ ህዝቡንም እንደ መጫወቻ አሻንጉሊታቸው የመመልከት አባዜ ተጠናውቷቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ንግግር ባደረጉ ቁጥር “ህዝባችን፣ አርሶ አደራችን! …” እያሉ የሚመጻደቁት፡፡ በመሠረቱ የእነሱ የግል ሃብት የሆነ ህዝብ የለም፤ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ግን አለ፡፡ የእነሱ የሚባል አርሶ አደርም የለም፤ ፋትሮና መከራ አይቶ የሚኖር አርሶ አደር ግን በሽ ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ይህ በሽታ የተጠናወታቸው ከአፄው ስርዓት ነው፡፡ ንጉሡ ሲናገሩ “የሚወደንና የምንወደው ህዝባችን …” ማለት ያዘወትሩ ነበር፡፡ ግን ሁለቱም የምር ባላንጣዎች እንደነበሩ በ1966 ዓ.ም በተካሄደው አብዮት ተመልክተናል፡፡ ኢህአዴግ በርካታ ህጐችን በማውጣት የሚቀድመው የለም፡፡ ግን ቀድሞ ህግጋቱን የሚጥስ ራሱ ነው፡፡ “እሞትለታለሁ” እያለ የሚምል የሚገዘትበት ህገ መንግስቱ፤ ማንኛውም ዜጋ በሃገሪቱ ውስጥ ተዘዋውሮ የመስራትና ሃብት የማፍራት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡

ግን በመጣበት መንደር እየተለየ መከራ የሚያየውና በገዛ አገሩ ላይ ስደተኛ የሆነው ህዝብ እጅግ በርካታ ነው፡፡ ለምሳሌም ወለጋ፣ ጉራፈርዳና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ላይ የተፈፀመውን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም ላይ በየክልሉ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ግብር ተጣለ፡፡ በዚህም የንግዱ ማህበረሰብ አባላትና ቤተሰባቸው እጅግ አዘነ፤ አቤት ቢልም የሚሰማው አጣ፡፡ ባለታክሲዎች ላይም ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጸመ፡፡ ቅሬታ የሚቀበል ባለስልጣንና የቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓትም አልነበረም፡፡ “ማብቃት” በሚል ማደናገሪያ ቃል በርካታ የአማራ ክልል ሰራተኞች የስራ ዋስትናቸውን አጥተው ለከፍተኛ ችግር ተዳረጉ፡፡ ለዚህም ይግባኝ የሚባልበት አካል አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ “ይህ መንግስት መንግስቴ ስለሆነ ህግና ስርዓቱን አክብሬ መጓዝ አለብኝ” የሚለው ቁጥር እጅግ እየቀነሰ መጥቶ “ምን አለ ከዚህ መንግስት የሚገላግለኝ ተዓምር ቢፈጠር” ባዮች በረከቱ፡፡ በመጨረሻም ምርጫ 97 መጣና ኢህአዴግ ልኩን የሚያውቅበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውን የምናውቀው ነው፡፡ ሌላም ህግ የሚጣስበትን መንገድ ልጠቁም፡፡ የመናገር፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና የጽሁፍ ነጻነት በህገ መንግስቱ ላይ ሰፍሯል፡፡

በተግባር ግን እጅግ ብዙ ይቀረዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች/ተቃዋሚ ናቸው ብለን እንቀበልና ስብሰባ ሲጠሩ በሰበብ አስባቡ እንዲደናቀፍባቸው ይደረጋል፡፡ በመሆኑም በግልፅ መሰብሰብ ካልቻሉ በህቡዕ ለመንቀሳቀስ ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ ጋዜጠኞች ማስረጃ እስካላቸው ድረስ በፈለጉት ርዕስ ላይ መጻፍ ካልቻሉ ስደትን ይመርጣሉ፡፡ ወይም ህሊናቸው ዓመጽ ያረግዛል፡፡ ሙስና ከምንም ጊዜ በላይ እየከፋ መጥቷል፡፡ አሁን የቀረው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ወደ ፓርላማ ወስዶ “ሙስናን ህጋዊ አድርጉልን፣ በሙስና ልናገኘው የሚገባንን ሃብት መጠንም በአዋጅ ወስኑልን” ማለት፡፡ ለዚህ ሁሉ ጣጣ መንስኤው የባለስልጣናት ፍርደ ገምድልነት ነው፡፡ ከላይ እንደ ጠቀስሁት በመሬት ወረራ ላይ የተሰማሩትን ሰዎች ወደ ህገ ወጥነት የገፋፋቸው ራሱ መንግስት ነው፡፡ የመሬት ጥያቄ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ቢመለስ ነዋሪው “ነገ ይፈርስብኛል” በሚል ስጋት ስጋው እያለቀ ወደ ህገወጥነት አያመራም ነበር፡፡ ለስንት ጊዜ ደጅ ጠንቶ፣ በማህበር ተደራጅቶና ስምንት ሺህ ብር በዝግ ሂሳብ አስቀምጦ ያገኘው ቦታ መጠን እንኳን ለሰው ለአህያ ማሰሪያ የሚበቃ አይደለም፡፡ እሱም ከ1977 በኋላ ከአነካቴው ቆሟል፡፡

ታዲያ ዜግነት ትርጉሙ ከምን ላይ ነው? ጐጆውን የሚቀልስበት የበሬ ግንባር የምታህል መሬት ካላገኘ፤ በኑሮው ላይ ለውጥ ማየት ካልቻለ፤ የትምህርት ቤት፣ የትራንስፖርት፣ የቤት ኪራይና የዳቦ መግዣ አጥቶ የተወለደበትን የሚረግም ከሆነ፤ በአንፃሩ የአገሪቱ ሃብት እጅግ ጥቂት በሆኑ ግለሰቦች እጅ ከተግበሰበሰ፣ ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ነቢይ መሆንን የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ስለሆነም መንግስት ምክንያታዊ የሆነ ህግ ማውጣትና ሚዛናዊ የሆነ አተገባበር ልምድ ሊኖረው ይገባል፡፡ አለዚያ ትላንት ያወጣውን ህግ ራሱ እየሻረ፣ ህዝቡን ግራ የሚያጋባ ከሆነ “መንግስት ባይኖርስ?” ወደሚል ጥላቻ ያመራል፡፡ መንግስት ህግን አክብሮ የማስከበር አቅሙን ካላዳበረ፤ የቦታ ጥያቄን በአግባቡና በፍጥነት ካልመለሰ የነዋሪው ችግር በራሱ ላይ የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም መንግስት በህገ ወጥ መንገድ ለተፈፀመ ድርጊት ሁሉ ህጋዊ እውቅና የሚሰጥ ከሆነ መቼም ቢሆን ህጋዊነት ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህም መንግስት የህዝብ ሞግዚትነቱን አይዘንጋ፤ ህግን ያክብር፤ ህግን በአግባቡ ያስከብር፤ የግለሰቦቹ ሞግዚት ሳይሆን የህዝብ ወኪል ይሁን፡፡

Read 3041 times