Saturday, 11 May 2013 12:47

“እኔ የሥልጣን ጥም የለብኝም”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ በመሆን ለአስር አመታት ያገለገለው አቶ ማሙሸት አማረ “በፓርቲው ህልውና ላይ ጉዳት አድርሰሀል” በመባል እሱን ጨምሮ 17 የፓርቲው አመራሮች ከፓርቲው የታገዱት የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ነው፡፡ ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት በመውሰድ ሲከራከሩ የነበሩት እነ ማሙሸት አማረ እና እነ ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ሲሆኑ ፍ/ቤቱም ተከሳሽ የነበሩ እነ ማሙሸት “ምንም አይነት ሁከት አልፈጠሩም” በማለት ወደ ፓርቲው እንዲመለሱ መስጠቱ ይታወሳል። ሆናም ትዕዛዙ ተግባራዊ ሳይሆን አንድ ዓመት አልፎታል፡፡ “ፓርቲው ውስጣዊ ችግሮች አሉበት” በማለት የሚናገሩት እነ አቶ ማሙሸት፤ ዛሬ የፓርቲውን ችግር በውይይት ለመፍታትና “ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራ” በማለት ከምርጫ ቦርድና ከኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ጋር እየተነጋገሩ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ አቶ ማሙሸት አማረን አነጋግራለች፡፡

ከመኢአድ ከታገድክ ስንት ጊዜ ሆነህ?

በ2003 ዓ.ም በተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው የዚህ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ በመሆን የተመረጥኩት። ከዚያ በኋላ ነው የታገድኩት፡፡ በአቶ ሃይሉና በአቶ ያዕቆብ ከፓርቲው ውጪ በሄደ ደንብ የውስጥ አለመግባባት ተፈጥሮ አቶ ኃይሉ ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ወስዶ ክርክር ከተደረገበት በኋላ ፍ/ቤቱ የተከሰስንበት ጉዳይ ስህተት መሆኑን አውቆ ወደ ፓርቲያችን እንድንመለስና ጠቅላላ ጉባኤው ተሰብስቦ የመጨረሻ እልባት እንዲሰጥ ተወሰነ፡፡ ከሳሾች ፍ/ቤቱ ትክክል አልፈረደም ብለው ለከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ጠይቀው ነበር፡፡ ሆኖም ፍ/ቤቱ የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ አጸና፡፡ አቶ ሀይሉና ሌሎቹ ግን የችሎቱን ትዕዛዝ ማክበር ባለመቻላቸው፣ ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ሰጠልኝ፡፡ ቦርዱም ይህንን መነሻ በማድረግ ለአቶ ሃይሉ በ2004 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠሩ ትዕዛዝ ቢሰጥም ጉባኤው ሳይጠራ ቀረ፡፡ እኛም ትግላችንን በህጋዊ መንገድ በመቀጠል ያላሰለሰ ጥረት አደረግን፡፡ ይኼም ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ እንግዲህ እንደምንሰማው አቶ ሃይሉ “አባረናል አጥርተናል” ይላሉ፡፡ ሆኖም እሳቸው የማባረርም የማጽዳትም ስልጣን የላቸውም፡፡

የመኢአድ አባል ስትሆን ምኑን መርጠህ ነው?

ከ1984 ሚያዚያ 15 ጀምሮ መ.አ.ህ.ድ ነበርኩ። ኢህአዴግ ከገባ በኋላ በአማራው ተወላጅ ላይ በየክልሉ ከፍተኛ በደል ሲያደርግ ይሄ በደል ይቁም በማለት በዚህ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ነው አባል የሆንኩት፡፡ ከዚህ በኋላ የታገልንለት ህዝብ ለምን ለአማራው ብቻ ትታገላለችሁ ሁሉም ብሔሮች ችግር እየደረሰባቸው ነው ያሉት፤ ለምን ለሁሉም ብሔር አትታገሉም የሚል ከፍተኛ አስተያየት በመኖሩ አባላቱ በሰጡት ውሳኔ መሠረት በ1995 ዓ.ም መአህድ ወደ መኢአድ ተቀየረ፡፡ መአህድ ወደ መኢአድ ከተቀየረ 10 አመት ሆኖታል፡፡ በዚህ ጊዜ የፕሬዚዳንቱን ችግር አታውቁም ነበር? በዚህ ፓርቲ ውስጥ በርካታ ችግሮች ይታዩ ነበር፡፡ ነገር ግን የሚፈቱት በውይይት ነበር፡፡ አንድ ሰው ችግር አለበት ተብሎ ከታሰበ ውይይት ላይ ይቀርባል፡፡ ያ ውይይት የቀረበበት አጀንዳ፣ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ በጊዜያዊነት ያግድና ለላዕላይ ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ ም/ቤቱም ያይና የመጨረሻ ውሳኔ በመስጠት በጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያሳውቃል፡፡ የእኛ መታገድ ግን ከዚህ የተለየ ነበር፤ በፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ ብቻ ነው “ሁከት ፈጥራችኋል” ተብለን ወደ ፍ/ቤት የሄድነው መጀመሪያም ወደ ፍ/ቤት የሄድነው ያለ አግባብና ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጪ ነው፡፡ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ሄደው ሳይሳካ ሲቀር ነው ፍ/ቤት የሚኬደው፡፡ ሌሎች በህገደንቡ መሠረት ከፓርቲው ከታገዱና ከተሰናበቱ ለምን እናንተ በህገወጥ መንገድ ሆነ ትላላችሁ?

እኛ ያቀረብነው መከራከሪያ ሃሳብ ትክክለኛ መረጃ ይዘን ነው፡፡ ለምሳሌ ከታህሳስ 15-17 2003 ዓ.ም በተካሄደ ጠቅላላ ጉባኤ፣ አቶ ሃይሉ አቶ ያዕቆብን ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጭ ተቀዳሚ ሊቀመንበር አድርጌ ሾሜዎአለሁ አሉ፤ እሳቸው ይህንን ማድረግ አይችሉም፡፡ እሳቸው የሚችሉት ከሌላ ስራ አስፈፃሚዎች ጋር ሆነው ሌላ ስራ አስፈፃሚ የሚሆኑትን በመምረጥ ለላይዕላይ ም/ቤት ያቀርባሉ፤ ላዕላይ ም/ቤቱ ነው የሚያፀድቀው፡፡ ይኸ ሹመት ነው፡፡ በሊበራል ስርዓት በአንድ ግለሰብ የሚመረጥ ሹመት የሚባል ነገር የለም፡፡ በምርጫ ነው የሚደረገው፤ ባላቸው የስራ ልምድና የትምህርት ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ ከተመረጠ ያልፋል፡፡ ካልተመረጠ ይወድቃል፡፡ እሳቸው ግን ቀጥታ አምጥተው አቶ ያዕቆብን ተቀዳሚ ሊቀመንበር አድርገው ሾሙ፡፡ ይሄ ነው ችግሩ፡፡ አንደኛ አቶ ያዕቆብ የድርጅቱ አባል አልነበሩም፡፡ የዕለቱ ዕለት ነው ለላዕላይ ም/ቤት ቀርቦ አባል ነው የተባለው፤ ዛሬ አባልነቱ ቀርቦ ወዲያውኑ ፕሬዚዳንት የሚሆንበትን ስርዓት ደንባችን አይፈቅድም፡፡ ይሄ ታዲያ በአቶ ሃይሉ ዘንድ እንደቂም ተወሰደ፡፡ እንዴት እኔ የምለውን አያከብሩም ብለው ተቆጡ፡፡ እኛ ደግሞ ማንም ከመተዳደሪያ ደንባችን ውጭ ከሆነ ስለምንታገል፤ ዋና አላማችንም ይሄ ስለሆነ እስከ መጨረሻው ፀንተናል፡፡ አቶ ሃይሉ አንድ አባልን ማገድ እንኳን የሚችሉት ለሁለት ወር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እኛ ደግሞ አመራሮች ነን፤ በእሳቸው ልንታገድ አንችልም፡፡ ወሳኙ ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡ ከ105 የላዕላይ ም/ቤት ውስጥ በተለያዩ ችግሮች 82 ሲቀሩ፣ ከነዚህ ውስጥ 57 የሚሆኑት አባላት ከእኛ ጋር ናቸው፡፡ ስለዚህ ይሄንን ሃሳባቸውን ለም/ቤቱ አቅርበው የሚያፀድቅላቸው ስለሌለ ነው አኩርፈው የተቀመጡት፡፡ አሁንም ለመነጋገር የማይፈልጉትም ለዚህ ነው፡፡ አሁንም “በውይይት እንፍታ ሲባሉ አልፈልግም” ያሉት ለዚህ ነው፡፡ የተቃወምነውን ትክክል ነው ብለን ሲቃወሙን ከቆዩ በኋላ አቶ ያዕቆብን በደብዳቤ አባረዋል፡፡ እናንተ በፓርቲው ውስጥ አመራር በነበራችሁ ጊዜ የኢንጂነር ኃይሉ ተቀናቃኞች ኢንጂነሩ ስልጣናቸውን ይልቀቁ ይሉዋችሁ ነበር፡፡

እናንተ ይሄን ችግር በወቅቱ አታውቁም ነበር?

ሌሎች ከፓርቲው ወጥተው ነገሩን ይተውታል አሊያም ሌላ ፓርቲ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ቅልውጥና ነው፤ ሌላ ነገር አይደለም፤ ማንም የፖለቲካ ሰው ላሰበበት ዓላማ መሳካት እስከመጨረሻው መታገል አለበት፡፡ አንድም አባል ግን እኛን ይሄንን ችግር አደረሳችሁብኝ ብሎ አጀንዳ ያስያዘ የለም፡፡ የመጀመሪያው እኔ ነኝ፡፡ እኛን ብዙ ጊዜ ሲሰድቡን አውቃለሁ፡፡ እኔ ግን ለግለሰብ አጐብድጄአለሁ፡፡ በፍፁም ሌሎቹ በጭቆና አይደለም የሚወጡት፡፡ እኛ ብቻ ነን በጭቆና የታገድነው፤ ስለዚህ እስከዚያ ድረስ በፓርቲው ውስጥ ትልቅ ችግር የሚባል አልነበረም፡፡ የእናንተ ቅሬታ ኢንጂነር ኃይሉ አቶ ያዕቆብን በመሾማቸው ነው፡፡

ኢንጂነር ሃይሉ እንዲመረጡ ደግሞ አንተ በአባላቱ ላይ ግፊት አድርገሃል፡፡ ታዲያ አሁን ለምን ችግር አለ ትላለህ?

በመጀመሪያ አቶ ያዕቆብ በምርጫ ባለመመረጣቸው ነው ቅሬታ ያቀረብነው፡፡ አቶ ያዕቆብን ያመጡዋቸውም አቶ ሃይሉ ናቸው፡፡ ይሄ ስንቃወም ስልጣን ፈልጋችሁ ነው ተብለናል፡፡ ከ400 በላይ ለሆኑ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት አቶ ሃይሉን ምረጡ ብዬ የቀሰቀስኩት እኔ ነኝ፡፡ በዛን ሰአት እኔን ምረጡኝ ማለት እችል ነበር፡፡

ለምን ኢንጂነር ሃይሉ እንዲመረጡ አደረግህ?

ፓርቲው ላይ ትንሽ ችግር ነበር፡፡ አቶ ሃይሉ ለስምንት ወራት ከ2002 ምርጫ በኋላ ወደ ፓርቲው አልመጡም፡፡ ለዶ/ር ታዲዮስ ውክልና ሰጥተው ነበር የሚፈረመው፡፡ ጠቅላላው ጉባኤው ይጠራ ብለን ወጥረን ስንይዝ፣ አቶ ያዕቆብ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ አልፈለጉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤው አቶ ያዕቆብን አያውቃቸውም፡፡ በዚህ መሃል አቶ ኃይሉ ወደ ቢሮ እንዲመለሱ አቶ ያዕቆብ ግፊት እያደረጉ ነበር፡፡ አንተ ለአባላቱ ከነገርክልኝ ልመረጥ እችላለሁ ማለታቸውን ያወቅነው ከጠ/ጉባኤ አባላቱ ሲወጡ “እንዲህ እየተባልን ነው፤ አቶ ሃይሉ ደውለው አቶ ያዕቆብን ምረጡ እያሉን ነው” የሚል ነገር ነገሩን፡፡ የላዕላይ ም/ቤቱ የሚያቀርብላችሁን ሰው እጃችሁን አውጥታችሁ ስትመርጡ ነው እንጂ በጐን እየተደወለ ምረጡ ስለተባላችሁ ብትመርጡ አይሆንም አልን፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አይነት ችግር ከመጣ ሠላማዊ ሽግግር ስለሚያስፈልግ ተብሎ አቶ ሃይሉ ይሄንን ፓርቲ ለስድስት ወር መምራት አለባቸው በሚል የጠቅላላ ጉባኤውን አባላት ምርጫችሁ ኢንጂነር ሃይሉ መሆን አለበት ብያቸው ነበር፡፡ ሁሉም በደስታ ተቀብለው የተባሉትን አደረጉ፡፡ እሳቸውም መድረክ ላይ ወጡና ደከመኝ ስል አልሰማም ብላችሁ እኔን መርጣችኋል፤ ስለዚህ እኔን እንዲያግዙኝ አቶ ያዕቆብ ልኬን ወክያለሁ ሲሉ ችግር ተፈጠረ፡፡

ችግር የፈጠሩት ኢንጂነር ሃይሉ ናቸው እያላችሁ ነው፤ ቀድማችሁ አቶ ያዕቆብን ምረጡ ማለታቸውንም ታውቃላችሁ፡፡ ይሄንን እያወቃችሁ ለምን እንዲመረጡ ፈለጋችሁ?

ጠቅላላ ጉባኤ የምንጠራበት ጊዜ ሊያልፍብን በመሆኑ ሳያልፍ ነበር ለማካሄድ ያስፈለገው። በወቅቱ ደግሞ ለፕሬዚዳንትነት የተሾመ ሰው አልነበረም፡፡ ስለዚህ አቶ ሃይሉን ስንመርጥ በህመምና በመሰልቸት ምክንያት ቤታቸው ቀሩ ብለን አስበን እንጂ እንዲህ አይነት ተንኮል ለማድረግ አስበዋል ብለን አልገመትንም። ይሄንንም የሰማነው አባላቱ ተጠቃለው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ነው፡፡ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን የሰማኸው ጠቅላላ ጉባኤው ሊካሄድ ሁለት ቀን ሲቀረው ነው ብለሃል። ነገር ግን ችግሩን ከመፍታት ይልቅ መልሳችሁ እሳቸውን መርጣችኋል፡፡ አሁን ደግሞ ችግር ፈጠሩ እያላችሁ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ማሙሸት እራሱን በአቶ ያዕቆብ ቦታ ለመተካት አስቦ ስለነበር ነው ይላሉ… ይሄ ከእውነት የራቀ የሞኞች ሃሳብ ነው። እኔ የስልጣን ጥም የለብኝም፡፡ ብፈልግ ደግሞ እኔ እራሴን አስመርጥ ነበር እንጂ አቶ ሃይሉን አላስመርጥም ነበር። ይሄንን ለማድረግ ለእኔ ቀላል ነው፡፡

አቶ ያዕቆብ ለጠቅላላ ጉባኤ ምርጫ በዕጩነት ባለመቅረባቸው ነው ችግራችሁ ወይስ ሙሉ በሙሉ ለዕጩነት መቅረብ አይችሉም ነው ተቃውሟችሁ?

አቶ ያዕቆብ አይደለም ለአመራርነት ለፓርቲ አባልነትም አይበቁም፡፡ በጣም ችኩል ናቸው። የቆዩትም በብዙ ችግር ነው፡፡ አቶ ያዕቆብ የፓርቲ አባል ሆነው አያውቁም፡፡ ዛሬ ጠዋት የመኢአድ የላይላይ ም/ቤት አባል ሆነው፣ ነገ ደግሞ ስራ አስፈፃሚ ሆነው መሾም አይችሉም፡፡ ደንቡም አይፈቅድም፡፡ ሌላው ደግሞ አቶ ሃይሉ መሾም አይችሉም፤ ይሄ የአልጋ ወራሽነት አሠራር አይደለም። እሳቸው ትልቅ ጂም ሠርተዋል፤ ከፈለጉ የዚያ ሃላፊ ሊያደርጓቸው ይችላሉ።

አቶ ያዕቆብ እንዲመረጡ ካልፈለጋችሁ ኢ/ር ሃይሉ ደከመኝ እያሉ ከምትመርጡ ለምን ፓርቲው በም/ፕሬዚዳንቱ እንዲመራ አላደረጋችሁም?

እኛም ያንን ነበር የጠበቅነው፤ ከደከማቸው ለሌላኛው ም/ፕሬዚዳንት መስጠት ይችላሉ፤ ያንን ባለማድረጋቸው እና አባል ላልሆነ ሰው ስልጣን በመስጠታቸው ነው ትልቁ ችግራችን፡፡ ካላወቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል ነው የሚለው ቃሉ፡፡ ከፓርቲው ከተለያችሁ ሁለት አመት ሆኗችኋል።

በዚህ ጊዜ ምን ሠራችሁ? የጠ/ጉባኤ ጥሪያችሁ ምን ይመስላል?

ፓርቲን የማደራጀት ስራ ነው እየሰራን የቆየነው፡፡ ፓርቲያችንን ለማንቃት እየሰራን ነው፡፡ 320 የሚሆኑ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ፈርመው ለምርጫ ቦርድም አስገብተዋል ግን እስካሁን የተወሰነ ነገር የለም፡፡ እናንተ የምትጠይቁትን ነገር ኢንጂነር አልቀበልም ቢሉስ? የፓርቲው አባላት ይሰበሰባሉ፤ ውይይት ያደርጋሉ። ከዚያም ሁለት አመት ሙሉ የሔደበትን ለዚህ አጣሪ ጉባኤ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ስራ የሰራም ከሆነ የሰራውን፣ ያልሠራም ከሆነ ያልሠራበትን፤ ችግሮች ካሉ ችግሮቹን በሙሉ ያቀርብና ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ከዚያ ከአምስት እጩዎች ውስጥ አንድ ለፕሬዚዳንትነት፣ ሌሎቹ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ይቀርባሉ፡፡ አቶ ሃይሉ በዚያ ጠቅላላ ጉባኤ ካልተመረጡ ውድቅ ይሆናሉ፡፡ ቦርዱም እውቅና እሚሰጠው በዚያን ጊዜ ለተመረጡት ፕሬዚዳንት እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡ እለቃለሁ ስላሉ አይለቁም፤ አልለቅም ስላሉም አይቆዩም፡፡

Read 4927 times