Saturday, 11 May 2013 13:47

ከ10 ዓመት እገታ በኋላ ነፃነታቸውን ያወጁ ሶስቱ ሴቶች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዛሬ አስር ዓመት የአስራ ሰባተኛ ዓመት የልደት በአሏን ለማክበር አንድ ቀን ሲቀራት ለስራ እንደወጣች አልተመለሰችም- አሜሪካዊቷ አማንዳ ቤሪ፡፡ ደብዛዋ ከመጥፋቱ በፊት ግን እህቷ ጋ ደውላ ከምትሰራበት ቦታ ወደ ቤት የሚመልሳት መኪና እንዳገኘች ተናግራ ነበር፡፡ የ14 ዓመቷ ጂና ደግሞ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ትምህርትቤት እንደሄደች አልተመለሰችም፡፡ ናይት ከሁለቱ ቀደም ብላ በ2002 ዓ.ም ደብዛዋ የጠፋ የ20 አመት ወጣት ነበረች፡፡ ሶስቱ ሴቶች በተለያዩ ጊዜዎች የጠፉ ቢሆንም ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው፡፡ ሶስቱም ፔድሮ ካስትሮ በተባለ ግለሰብ ታግተው በመኖሪያቤቱ ምድርቤት ውስጥ የተለያዩ ስቃዮችን አሳልፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰቡ ሴቶችን በመኪና ልሸኛችሁ (ሊፍት ልስጣችሁ) እያለ ነበር ወጥመድ ውስጥ ያስገባቸው፡፡

ሶስቱ ሴቶች እንደታገቱ በተለያዩ ክፍሎች ተነጣጥለው እንዲቀመጡ ያደረገ ቢሆንም በኋላ ላይ አንድ ላይ እንዳደረጋቸው ባለታሪኮቹ ይናገራሉ፡፡ በዓመታት የእገታ ቆይታቸው ተገደው ተደፍረዋል ፤ ለሳምንታት ምግብ ተከልክለዋል፤ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል ፤ በሰንሰለትም ታስረዋል፡፡ በፖሊስ መረጃ መሰረት ፤ ከሴቶቹ አንዷ አምስት ጊዜ ተገዳ ተደፍራ አምስት ጊዜ የፅንስ መጨናገፍ ደርሶባታል - በተፈፀመባት ድብደባ እና የምግብ ክልከላ የተነሳ፡፡ የሴቶቹ የመሰወር ምስጢር በቅርቡ እስኪታወቅ ታዲያ የተለያዩ ግለሰቦች ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ እንስቶቹ ሞተዋል በሚል ግምትም ፖሊስ አስከሬናቸውን ለማግኘት ያልፈነቀለው ድንጋይ አልበረም፡፡ በቅርቡ ግን ሁሉም በህይወት ተገኝተዋል፡፡

ታጋቾቹ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ከክፍላቸው ወጥተው ውጭውን ያዩት አንድ ጊዜ ብቻ ነው - ያውም እዚያው ቤት ግቢ ውስጥ፡፡ ሰዎች ማንነታቸውን እንዳይለዩዋቸው መነጽር፤ ኮፊያ እና ዊግ እንዲጠቀሙ ተገደው እንደነበርም አስታውሰዋል - ለፖሊስ በሰጡት ቃል፡፡ በአሜሪካን ኦሃዮ ግዛት፤ ክሌቭላንድ ውስጥ ለ10 አመት ገደማ ታግተው የቆዩት ሴቶች ባለፈው ሰኞ ነው ነፃ የወጡት- ያገታቸው ግለሰብ ከቤት ሲወጣ አማንዳ ቤሪ ባሰማቸው የድረሱልን ጥሪ፡፡ ከዚያ በፊት ግን እንዲህ ያለ ሙከራ አድርገው እንደማያውቁ አማንዳ ለፖሊስ ገልፃለች፡፡ በመጀመርያ ሙከራዋ ውጤታማ መሆናም ጀግና አሰኝቷታል፡፡ ወደ ማገቻው መኖርያ ቤት የገቡት ሶስቱ ሴቶች ብቻ ቢሆኑም ሰሞኑን ነፃ ሲወጡ ግን የውጭውን ዓለም የማታውቅ የስድስት አመት ህፃንም አብራ ነበረች፡፡ ልጅቷ የቤሪ እንደሆነች የታወቀ ሲሆን አባቷ ማን እንደሆነ ለማወቅ ግን ምርመራ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

የቤሪን ጩኸት ሰምቶ ሴቶቹን ነፃ እንዲወጡ የረዳቸው ቻርለስ ራምሴ የተባለ የካስትሮ ጎረቤት ነው፡፡ በዚህ መልካም ሥራውም ከመላው አሜሪካ ከፍተኛ አድናቆት እየጎረፈለት መሆኑ ታውቋል፡፡ ራምሴ የሚሰራበት ሬስቶራንት የፌስቡክ ገፅ ላይ የሰፈረው ፅሁፍ እንዲህ ይላል “በባልደረባችን መልካም ተግባር እጅግ ኩራት ተሰምቶናል፡፡ እሱ የክሌቭላንድ ጀግና ነው፡፡” ራምሴ ስለሁኔታው ሲገልፅም፤ “ድምፅ ሰምቼ ከቤቴ ስወጣ አንዲት ሴት ከጎረቤት ካለው ቤት ለመውጣት ስትታገል አገኘሁ፡፡ በሩን እየደበደበች ያለማቋረጥ የምትጮኸውን ሴት ከዚህ በፊት አይቻት አላውቅም፡፡ “እኔ ታግቼ ነው፡፡ እዚህ ቤት ለአመታት ተዘግቶብኝ ኖሬያለሁ፡፡ አሁን ነፃ መውጣት እፈልጋለሁ” አለችኝ ፡፡ ለምን 911 አትደውይም ስላት መውጣት እንደምትፈልግ አጥብቃ ነገረችኝ ፡፡ እኔና ሌላ ሰው በሩን በመክፈት ተባበርናት፡፡ እናም 911 በመደወል እኔና ቤሪ ሁኔታውን አስረዳን፡፡ ፖሊስ ሲመጣ ሌሎች ሁለት ሴቶች ውስጥ እንዳሉ ገልፃ ሁሉም ነፃ ወጡ” ብሏል፡፡ ራምሴ በአጋችነት የተጠረጠረውን ጎረቤቱን እንዲህ ያለ ተግባር ይፈፅማል ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡

“ስለጎረቤቴ ምንም የተለየ ነገር አላውቅም ነበር፡፡ ብዙ ምሽቶችን ስጋ እየጠበስንና ሳልሳ ሙዚቃ እየሰማን አሳልፈናል፡፡ ግቢው ውስጥም ሁልጊዜ ከውሾቹ ጋር ሲጫወት ነው የማየው፡፡ ዛሬ ካየሁት ውጪ የሚያስገርም ነገር ሲያደርግ አይቼ አላውቅም” በማለት መገረሙን ገልጿል፡፡ የአውቶቡስ ሾፌሩ ካስትሮ፤ የፖርቶሪኮ ተወላጅ ሲሆን የላቲን ባንድ የሙዚቃ ተጫዋች ነበር፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ በአሁኑ ወቅት አብራው በማትኖር ሚስቱ የድብደባ እና የግድያ ዛቻ ክስ ቢቀርብበትም ክሱ ውድቅ ተደርጓል፡፡ የፖሊስ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በ2000 እና በ2004 ዓ.ም ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ በካስትሮ ቤት ላይ ፍተሻ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ፍንጭ ሳያገኝ ተመልሷል፡፡ አሁን የሶስቱ ሴቶች ህይወት ተቀይሯል፡፡ አማንዳ ቤሪ የ27 አመት ሴት እና የስድስት አመት ልጅ እናት ሆናለች፡፡ እናቷን በህይወት ለማግኘት አልታደለችም፡፡

በልጃቸው ድንገተኛ መሰወር ልባቸው ክፉኛ የተሰወረው እናቷ ከጠፋችበት እለት አንስቶ ህይወታቸው እስክታልፍ ድረስ ያለመታከት ልጃቸውን ሲያፈላልጉ ቆይተዋል ሆኖም የልጃቸውን ዓይን ሳያዩ በደረሰባቸው የጤና እክል ህይወታቸው አልፏል፡፡ ሚሸል ናይት የ30 አመት ሴት ሆናለች፡፡ እሷ ከታገተች በኋላ የተወለደች አዲስ እህት አግኝታለች፡፡ እናቷ በሰጠችው አስተያየት፤ “ልጄን በህይወት ማግኘቴ ታላቅ ስጦታ ነው፡፡ ቶሎ እንድታገግም አግዛታለሁ” ብላለች፡፡ ከትምህርት ቤት ወደቤት ለመመለስ ዘጠኝ አመታት የፈጀባት ጂና፤ ቤተሰቦቿን የተቀላቀለችው የ23 አመት ወጣት ሆና ነው፡፡ በእነዚያ ዓመታት ብዙ ስቃዮችን ብታሳልፍም ፊቷን በሹራቧ ሸፍና የአውራ ጣቷን ወደ ላይ በመቀሰር ዳግም ከቤተሰቧ ጋር መቀላቀሏ የፈጠረባትን ደስታ ገልፃለች፡፡

ሦስቱም ሴቶች ከደረሰባቸው የአካልና የሥነልቦና ጉዳት ለማገገም ሆስፒታል ገብተው የነበረ ሲሆን ሁለቱ ህክምናቸውን አጠናቀው ሲወጡ እናቷን በሞት ያጣችው ናይት ግን አሁንም እዚያው ትገኛለች፡፡ መርማሪዎች ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ማስረጃዎችን ከካስትሮ ቤት ሰብስበዋል፡፡ የክሌቭላንድ ከንቲባ ፍራንክ ጃክሰን፤ ሶስቱ ሴቶች በህይወት መገኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀው ሆኖም ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ ብለዋል፡፡ ለምን ተወሰዱ? እንዴት ተወሰዱ? ይህን ያህል ጊዜስ ያሉበት እንዴት ሳይታወቅ ቀረ የሚሉና ሌሎችም፡፡ ከንቲባው እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ምርመራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡ ምንም እንኳን ቤሪ እናቷን ለማየት ባትታደልም እናት ለመሆን በቅታለች፡፡ ጂና እና ናይት ደግሞ ከእናቶቻቸው ጋር ለመገናኘት ችለዋል፡፡ እናም ሦስቱ ሴቶች ከአስር ዓመት እገታ በኋላ ነፃ መውጣታቸው ነገ ለሚከበረው “የእናቶች ቀን” መልካም ስጦታ ሆኖላቸዋል፡፡

Read 5382 times