Saturday, 11 May 2013 13:20

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሠራተኞቹ ትኩረት ይስጥ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

መጋቢት 29 ቀን 2005 ዓ.ም ማለዳ እንግዶች ለመቀበል ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ነበርኩ፡፡ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት እንግዶችን የሚቀበሉም ሆነ የሚሸኙ ሰዎች የሚገቡበት በር አልተከፈተም ነበርና ውጭ ለመቆም ተገደድኩ፡፡ ብዙ አውሮፕላኖች ስለአረፉ ተጓዦች፣ ሆስተሶችና ፓይለቶች ወደ ውጭ ይጎርፋሉ፡፡ ሆስተሶቹና አንዳንድ ፓይለቶች ቆመው ወደቤታቸው የሚወስዳቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መኪና ይጠባበቃሉ፡፡ የሚጠብቁት መኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ ሆነው ነው፡፡ ምንም መቀመጫ ስላልነበረም አንዳንዶቹ ሆስተሶች ሻንጣቸው ላይ ተቀምጠው አየሁ፡፡ ነገሩን ለመቀበል ስላዳገተኝ በሞባይሌ ጥቂት ፎቶዎች አነሳሁ፡፡

እነዚህ ሆስተሶች እዚህ የደረሱት ቢያንስ ከአራት ሰአት በረራ በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊትም ዝግጅት ማድረግ ስለሚኖርባቸው ሌሊቱን ሳይተኙ ነው የመጡት ማለት ነው፡፡ በበረራው ጊዜም አንድ አውሮፕላን ህዝብ ሲንከባከቡ እንዳደሩ ግልጽ ነው፡፡ እንደኔ ግምት እነዚህ ሰዎች በዚያ ጠዋት የሚመኙት ዋና ነገር ቢኖር ወደቤታቸው ቶሎ ሄደው መተኛት ነው፡፡ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢቻል እንደመጡ የሚወስዳቸው መኪና፣ባይቻል ደግሞ ከነክብራቸው የሚቆዩበት ማረፊያ ቦታ ማዘጋጀት ለምን ተሳነው? ነገሩን መቀበል ያቃተኝ እኔ ብቻ አልነበርኩም፡፡ አንድ ከፊቴ የቆመ ሰው “እስቲ አሁን ዝናብ ቢኖር እንዴት ነው እዚህ ሆነው የሚጠበቁት?” አለ፡፡

ሌላው ያስገረመኝ ነገር ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሆስተሶቹንና ፓይለቶቹን ለማጓጓዝ የሚጠቀምበት ብዙ ዓመታት ያገለገሉ መኪኖችን ነው፡፡ እቃ መጫኛ ስለሌለው ሻንጣም ሰውም አብሮ ነው የሚጫነው፡፡ አንድ ከሻንጣ ጋር የተጫነ ፓይለት እያየሁ እንዲህ ስል አሰብኩ “በመቶዎች የሚቆጠር ሰዎችን በጥንቃቄ ሲያበር ያደረን ሰው እንዲህ መጫን ምን ይባላል?” ስንት ከባድ ነገሮችን አቅዶ ለሚያሳካው አየር መንገድ ምክር ካስፈለገው ከኋላቸው የሚከፈቱ ሚኒባሶች ቢኖሩት ሰዎቹ ከፊት ከነክብራቸው ሲቀመጡ፣ ሻንጣዎች ከኋላ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻል ይሆናል፡፡ አየር መንገዱን የላቀ አየር መንገድ ለማድረግ፣ለሠራተኞቹ አያያዝ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ባስታውሰው ከአጉል ድፍረት እንደማይቆጠርብኝ በመተማመን ነው፡፡

Read 4138 times