Print this page
Saturday, 12 November 2011 08:13

ለቆርንጦስ ሰዎች

Written by  መሐመድ አድሪስ
Rate this item
(1 Vote)

እውነተኛ ታሪክ - እንደ አጭር ልቦለድ 
ዛሬ ስለቆርንጦስ ሰዎች እንዳወራላችሁ ሁኔታዎች አስገደዱኝ፡፡ ከብዙ ሺህ ዘመን በፊት ስለነበረችው እውነተኛዋ የመጽሐፍ ቅዱስዋ ሳይሆን፤ እዚሁ የአዲስ አበባ እንብርት ላይ ስለምትገኘው እኛ ነዋሪዎችዋ ቆርንጦስ ስላልናት ለገሐር፡፡ በቅርቡ የተገነባው ትልቁ ሰማይ ጠቀስ የአዋሽ ባንክና ኢንሹራንስ ህንፃ ልክ ግዳዩን እንዳገኘ ዳይናሶርስ እላይዋ ላይ አንዣቧል፡፡ የመድን ህንፃ ቁልቁል ያያታል፡፡ የፀረ ሙስና ህንፃም ያዝኩሽ ደረስኩብሽ እያላት ነው፡፡ አዲስ የሚሰራውም የባህርና ትራንዚት ህንፃም በላሁሽ ሰለቀትኩሽ እያላት ነው፡፡

ግዙፍ ህዝባዊና መንግስታዊ ተቋማት ይከብቧታል፡፡ በሰሜን ብሄራዊ ትያትር፣ በደቡብ ለገሐር ባቡር ጣቢያ፣ በምዕራብ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት፣ በምስራቅ ታላቁ የአዲስ አበባ ስታዲየም፡፡ የመድሐኔአለም ቤተክርስትያን፤ ለጠፉት ልጆቹ ያለቅሳል፡፡ ነገር ግን በለገሃር ጸሐይ ወጥታ ትጠልቃለች፡፡ በውስጥዋ የሌለ ነገር የለም፡፡  
ከታዳሚዎችዋ አንዱ እኔው እራሴ ነኝ፡ በኮሜርስ በኩል ስትመጡ ኤን ፒን (ናዝሬት ፔንሲዮንን) አልፋችሁ፣ በስተግራ የማርታ ቤትን ካለፋችሁ በኋላ ፎዝያ ቤት ከመድረሳችሁ በፊት፣ “ከፍ” ቤት ወይም መዓዛ ቤትን ታገኛላችሁ፡፡ እኔና ጓደኞቼም ያለነው እዚያ ውስጥ ነው፡፡
መዓዛ የደስ ደስ ያላት ወጣት ባለትዳር ሴት ናት፡፡ ለኛ ጫት ትሸጣለች፡፡ ሂሳብ አትሳሳትም፡፡ ቀልድ የማታውቅ ኮስታራ ሴት ብትሆንም ቀልድ ላስለምዳት ሞክሬያለሁ፡፡ እንደኔ ቀልድ ሊያስለምዳት ከሞከረው ጓደኛችን አንዱ ብስራት ወይም በቅጽል ስሙ ቡጢ በመባል የሚታወቀው ጓደኛችን ነው፡፡
ቡጢ ለምን ቡጢ እንደተባለ አላውቅም፡፡ ግን ቡጢ ነው፡፡ ውሃ ጠብሶ የበላ የካዛንቺስ አራዳ! ወደ ውሃው ያዘነብላል፡፡ ትንሽ ጫት ብዙ ድራፍት፡፡ ለምሳሌ እስከ አስር ሰአት ድረስ ጫት ከቃመ በኋላ አንድ ሰአት ላይ ወልዴ ቤት የሚሰየም ማነው ብትሉ? ቡጢ ነው እላችኋለሁ፡፡ ሌላው ቃሚ ከጫት በኋላ ስታዲየም ሊገባ ሊሞክር ቀርቶ ሊያስብ አይችልም፡፡
ቡጢ አጠር ብሎ ደልደል ያለ ነው፡፡ ጉንጩ ሞላ ያለ፡፡ ሌላ ባህርዩ መለኪያ ሲጨብጥ፣ የሚወደው ሙዚቃ ሲመጣ ሰው ኖረም አልኖረም እስኪያልበው ድረስ መወዛወዙ ነው፡፡
ቡጢን ሰላም ብዬ ወደ ውስጥ ገባሁኝ፡፡ ኤልያስና አብርሃም የተቀመጡበት ጠረጴዛ አጠገብ ያለውን አንድ ወንበር ስቤ ተቀመጥኩኝ፡፡
ኤልያስ ደልደል ያለ የስፖርተኛ ቅርጽ ያለው፣ የተጠቀለለ ጸጉሩን መቋጨት የሚወድ ሲሆን አብርሃም ደግሞ ቀጠን ያለ፣ ቀለል ያለ ካናቴራ መልበስ የሚያዘውትር ወጣት ነው፡፡ ሁለቱ ሁልጊዜ አንድ ላይ ናቸው፡፡ በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ጭምር፡፡
የኤልያስ ስራ ጠረጴዛው ሙሉ መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ሁለቱ ካሉ ጫት በገፍ ይኖራል፡፡ ሻይና ቡና በላይ በላይ ነው፡፡ አንድ ፓኮ ሲጋራ ጠረጴዛው ላይ ይኖራል፡፡ የፈለገ ከዚያ እየመዘዘ ማጨስ ብቻ ነው፡፡ ስለሂሳቡ መጨነቅ አያስፈልግም፡፡ ኤልያስ አለ፡፡ እሱ ከሌለ አብርሃም፡፡
በስተግራ በኩል ካለው ጠረጴዛ ላይ ዳዊት አለ፡ እንደተለመደው ብቻውን ነው፡፡ ከፊት ለፊቱ የታሸገ ውሃና አንድ ጠርሙስ ኮካኮላ አይጠፋም፡፡ ሁሌ ሽቅርቅር፤ ሁሌ ንፁሕ፡፡ የሱሪው እጥፋት በተኩስ አብዶ እንደ ጐራዴ አንገት የሚቆርጥ ይመስላል፡፡
ገና ጃኬቴን አውልቄ ወንበሩ ላይ ከማንጠልጠሌ፣ ፊት ለፊቴ የተቀመጠው ደረጄ ሰላም አለኝ፡፡ ሁልጊዜ ጀርባውን ለግድግዳው ሰጥቶ ነው የሚቀመጠው፡፡ በበቂ ርቀት ሆኖ ነው የሚጫወተው፡፡ ጫወታው ታድያ ገብስ ገብሱን ነው እንጂ ጠለቅ ያለ አይደለም፡፡ ጥቂት ቃላትን ጣል አድርጐ ከራሱ ጋር ማውራት ይጀምራል፡፡
ግማሽ ጫት አዘዝኩና መቃም ጀመርኩ፡፡ አጠገቤ ካለው ወንበር ሃይሌ ተቀምጦ እንደተለመደው ውዳሴ አርሴናሉን እያነበነበ ነው፡፡ ሃይሌ ስለኳስ አላወራም ማለት ስለፖለቲካ እያወራ ነው ማለት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ሁለቱም ርዕሶች አይመቹኝም፡፡ አለምና ፖለቲካ እንደሆነ የአሸናፊዎች ነው፡፡ እግር ኳስም እንደዚያው፡፡ ከደገፍኩ ደግሞ ሊቨርፑልን ነው የምደግፈው፡፡
“አርሴናልን የሚደግፉ እኮ ድሮ እቤታቸው ቲቪ ያልነበራቸው ናቸው፡፡ ጐረቤት ሄደው የሚያዩ” አልኩኝ አንድ ሲጋራ እየለኮስኩኝ፡፡
“እንዴት”? አለ፤ ሃይሌ ደሙ ፈልቷል፡፡
“ቲቪማ ቢኖራቸው ኖሮ የሊቨርፑልን ታሪክ ያውቁ ነበር፡፡ የአያን ረሽና የጆን ባርነስን አጨዋወት ያየ እንዴት ሌላ ቡድን ይደግፋል” አልኩኝ ፍርጥም ብዬ፡፡
አብዛኛው የአርሴናል ደጋፊ ስለሆነ እቤቱ ተንጫጫ፡፡ የሽሜና የጥሩ ሰውም ድምፅ ሳይቀር ተሰማኝ፡፡ ሁለቱን የሚያመሳስል ብዙ ነገር አላቸው፡፡ ሽሜና ጥሩ ሰው፡፡
ሁለቱም ሜካኒኮች ናቸው፡፡ ሁለቱም ውጭ በረንዳው ላይ ነው የሚቅሙት፡፡ ጥሩ ሰው ሲጋራውን የሚያጨስበት የራሱ ፒፓ አለችው፡፡ ሽሜ ደግሞ አንድ ሌላ ከኔው ከራሴ ጋር የሚመሳሰልበት ነገር አለው፡ ትልቅ ዳሌ ያላት ሴት መውደዱ፡፡ እሱ ክንፍ ነው የሚለው፡፡ አሪፍ ሴት አይቶ የመጣ ቀን “ዛሬ ያየሁት ባለ ክንፍ” ሲል ወሬ ይጀምራል፡፡ “መልአክ አደረካት እኮ! ቅዱስ እገሊትን አየሁ እንዳትል” ብሎ የመለሰለት ሰው ማን እንደሆነ ረስቼዋለሁ፡፡
ያን ቀን ኤልያስ ማታ እንደሚፈልገኝ በጆሮዬ ሹክ አለኝ፡፡ ማታ ይፈልገኛል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ እዚያው ቆርንጦስ ክልል ውስጥ ያለው ወልዴ ቤት ነው የተቀጣጠርነው፡፡ ሀገረ ዳንኪራ!
የቀረ ሰው አልነበረም፡፡ ከይሳቅ በስተቀር ውቤ፣ አሌክስና ብሩክም ነበሩ፡፡ ስደርስ
በቆርንጦስ አነጋገር ሁሉም ገብቶላቸው ነበር፡፡ ሰክረዋል ማለቴ ነው፡፡ ቡጢ እንደተለመደው በቦብ ማርሌይ ዘፈን እየደነሰ ነበር፡፡ ሁለት ልጆችም አብረውት ይደንሳሉ፡፡ ኤልያስ እንደተለመደው ጸጉሩን እየጠቀለለ ጠረጴዛው ሙሉ መሆኑን ይቆጣጠራል፡፡ ሃይሌ ስለ ኑሮ ውድነት እያወራ ነበር፡፡
አፌን በዱለት አሟሸሁና አንድ ጃምቦ ይዤ ተቀላቀልኩኝ፡፡ እውነት ለመናገር ግን በልቤ “አርብ እሮብ የማትጾሚ ሁላ ጉድሽን ትልቁ ጋዜጣ ላይ ባላወጣው” እያልኩ እዝት ነበር፡፡
ከወልዴ ቤት ቀጥሎ ወደ በለጡ ቤት ነበር ያመራነው፡፡ አምስት ነበር የቀረነው፡፡ ሌላው እየተንጠባጠበ ወደ ሚሄድበት አምርቷል፡፡ በለጡ ቤት አራት አራት ቢራ ከተጠጣ በኋላ ወደ ኤን ፒ (ናዝሬት ፔንስዮን) ተኬደ፡፡ በሴቶቹ ብዛትና አይነት ናላችን ዞሮ ነው የመጣነው፡፡ በመጨረሻ የሁላችንም ምርጫ የሆነው የኖህ መርከብ ነው፡ እዛው ቆርንጦስ ክፍል የሚገኘው ኢስት አፍሪካ ሆቴል፡፡ ሁሌ ጥንድ ጥንድ ሆነው ስለሚመገቡበት ነው የኖህ መርከብ የተባለው፡፡ ክፍልም ሆነ ሌላው በርካሽ ስለሚገኝበት የሁላችንም ምርጫ ነበር፡፡
እንደገባን የሁሉም ሰው አይን እኛ ላይ ተተከለ፡ ድራፍት ስላልነበረ አልኮል ነበር የተጠጣው፡፡ ሁሉም ገልመጥ ገልመጥ እያለ ሴቶቹን ማማተር ጀምሯል፡፡ እኔ በበኩሌ ዳሌዋ “አሰላም አለይኩም” ከሚል አንዲት ኮረዳ ጋር በአይን ተግባብቼ ጨርሻለሁ፡፡ ሁሉም የሚፈልጋትን እየጠራና እየደባበሰ መንሾካሾክ ጀመረ፡፡ ጋባዣችን ኤልያስና አብርሃም “ክፍል ተይዟል፡፡ እንደፈለጋችሁ ሁኑ” ብለው አብስረዋል፡፡ ኤልያስ ስልክ ደውሎ “ያ ነገር እንደተጠበቀ ነው? ይጠበቅ መጣሁ” ብሎ የራሱን እንጀራ አበሰለ፡፡ እኔም ኩሩ ዳሌ ያላትን ያቺን ሽንጠ ሎጋ ኮረዳ አጠገቤ ሻጥ አደረግሁኝ፡፡
አንዱ ጓደኛችን ብቻ ቀርቷል፡፡ እስካሁን አላስተዋወቅኳችሁም፡፡ ለነገሩ አዳራችን ከሱ ጋር ስለሆነ በደንብ ታውቁታላችሁ፡፡ ቁመቱ ስድስት ጫማ ይሆናል፡፡ በጥንቃቄ የለበሰ ነው፤ ሚልዮን ይባላል፡፡
ሚልዮን “ከፍ” ቤት ውስጥ ሶስት ሙሉ ጫት ነበር የቃመው፡፡ በምርቃና ብዛት አይኑ ፈጦ እየተንሳፈፈ ወልዴ ቤት ገባ፡፡ አካሄዱ ከረጅም ቁመቱ ጋር ሲታይ ልክ ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃ ላይ ሲሄድ የሚታየውን ይመስል ነበር፡፡ ከሁሉም ሰው በላይ ደጋግሞ ብዙ ድራፍቶችን የጠጣው እሱ ነበር፡፡ በለጡ ቤትም ወደ አራት ደብል ጂን ጠጣ፡ሰከረ፡፡
የኖህ መርከብ ከገባ በኋላ ግን ስካሩ በጣም ከልክ አለፈና፣ በጣም ጮሆ ጠረጴዛ ላይ የነበረውን ብርጭቆ ሁሉ ደርምሶ መሬት ላይ አፈረጠው፡፡ ሰው ሁሉ እሱን ማየት ጀመረ፡፡ ሴቶቹን በሃይለኛ ትዕዛዝ አንድ በአንድ ቢጠራም ወደሱ ድርሽ የምትል የሄዋን ዘር ጠፋች፡፡ ከዚያ በኋላ ነው በአንድ ድምፅ ገብቶ እንዲተኛ የተወሰነበት፡፡
ይሄን የስራ ድርሻ የወሰደው ኤልያስ ነበር፡ እንደምንም አግባብቶ ፎቅ ወዳለው ክፍሉ ይዞት ሄደ፡፡ ሆቴሉ ረጅም የሳንቃ ኮሪደር አለው፡፡ ለሱ የተያዘለት ክፍል አምስተኛው ተርታ ላይ ያለው ነበር፡፡
ኤልያስ በጀርባው አልጋው ላይ ሲያጋድመው እንዲህ አለ፡፡ “አሁኑኑ አንዲት ሴት ላክልኝ፤ ብቻዬን አላድርም”
ኤልያስ ክፍሉ ድረስ እንደሚልክለት ቃል ገባ፡ አልጋው ላይ ካጋደመው በሁዋላ በሩን ከውጭ ሸጉጦበት ወደ እኛ ተመለሰ፡፡ በሩን ከውጭ የሸጐጠበት በጣም በመስከሩ እንደገና ወጥቶ እንዳይረብሽ ነበር፡ ኤልያስ ወደ ቸበርቻቻው ተመልሶ ድብልቅልቁ ወደወጣው ጸብ ሲገባ፣ ለሚልዮን ቃል የገባውን ቀርቶ እራሱን ሚልዮንን ረሳው፡፡
ሚልዮን ግን አልረሳም፡፡ የፈለገ ቢሰክር ሁለት የማይተዋቸው ባህርያት አሉት፡፡ ልብሶቹን ሳያጣጥፍ አለመተኛትና ኮንዶም ሳያደርግ ከሴት ጋር አለመተኛት፡፡
በሽታ ከምንም ነገር በላይ ይፈራል፡፡ በተለይ ኤች አይቪን፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ ከኪሱ ኮንዶም አይለይም፡ አሁንም አንድ ፓኬት ኮንዶም ይዟል፡፡ ተነስቶ ልብሱን አጣጥፎ ኮንዶሙን አውጥቶ ኮሞዲኖው ላይ አስቀመጠ፡፡ ኪሱ ውስጥ ምንም ነገር የለም፡ አራት ሲጋራዎች ግን ኪሱ ውስጥ አግኝቷል፡ በጀርባው ተንጋሎ ሲያስብ ስካሩ እንደመተው አለው፡፡
አንዱን ሲጋራ ለኮሰ፡፡ የሲጋራውን ጭስ ሲምግ ስሜቱ እንደገና አገረሸበት፡፡ ትመጣለች የተባለችው ሴት የውሃ ሽታ ሆና ቀርታለች፡፡ ሚልዮን ተበሳጨ፡
ከራሱ ጋር ሙግት ጀምሯል፡፡ ምን እየሆንኩኝ ነው? ሲል ጠየቀ፡፡ ገደብ የሌለው የሴት አምሮት፡፡ የሴት ሽታ .. ሴት፡፡ በአሁኑ ሰአት የሚታየው ይሄ ብቻ ነው፡፡ ቋ.ቋ.ቀጭ የሚል የታኮ ጫማ ድምፅ በረጅሙ የሳንቃ ኮሪደር ላይ ተሰማ፡፡ የሚልዮን ጆሮዎች እንደአንቴና ቆሙ፡፡ ምናቡ ወደኋላ ተመለሰ፡ ልቡ እንደታንቡር መምታት ጀምሯል፡፡ አሁን እየመጣች ያለችው የሄዋን ዘር ቅድም ያያት ጨበሬ ፀጉር ያላት ሽንቅጥ ለመሆንዋ አልተጠራጠረም፡፡ ኤልያስ አሪፍዋን መርጦ ልኮላታል፡፡
ፊትዋ ስልክክ ያለ፣ ሽንጧና ቀጭን እግሮችዋ የሚያምሩ ቀይ ቀሚስ የለበሰች ነበረች፡፡ እስዋ እንደሆነች ምንም አልተጠራጠረም፡፡ ኮንዶሙን ከጠረጴዛው ላይ አነሳና ከፍቶ አጠለቀው፡፡
አሁንም ቋ… ቀጭ የሚለው ድምፅ እየቀረበ መጣ፡፡ የሚልዮን ልብ መምታቱን ቀጠለ፡፡ ግን ብዙም አልቆየም፡፡ ድምፁ የሱን በር አልፎ እየራቀ እየራቀ መጣ፡፡ ሚልዮን የሚሆነውን ማመን አልቻለም፡ ልጅቱ የሱን በር አልፋ ሄዳለች፡፡ ከዚያ አንድ ሌላ በር ተከፍቶ ስትገባ ድምፁን አዳመጠ፡፡
ምን እየሆንኩ ነው ሲል አሰበ፡፡
ቄሳርም ለክሊዮፓትራ ተንበርክከዋል፡፡ ናፖሊዮን ቦናፓርቴም ለጀሴፊን፡፡ ሁለቱም አለምን ካልገዛን ያሉ ጀግኖች ነበሩ፡፡ ግን ለሄዋን ዘር ተንበርክከዋል፡፡
እና እሱ ማነው?
አንድ ሲጋራ ለኮሰ፡፡ ምን አይነት ጫት ነው የቃምኩት ሲል አሰበ፡፡ እንደዛሬው በስሜት ተቅበጥብጦ አያውቅም፡፡ ሲጋራውን አጭሶ እንደጨረሰ ከፍተኛ የሴት ማስካካት ድምፅ ተሰማ፡ ከዚያ የተለመደው ሳንቃው ላይ የሚራመድ የታኮ ጫማ ድምፅ፡፡ አሁን ለሱ የተላከችዋ ሴት ለመሆንዋ ጥርጥር የለውም፡፡
እቺ ደግሞ ወፍራም ወንዲላዋ ለመሆንዋ ጥርጥር የለውም፡፡ ቅድም አስሬ ስታየው ነበር፡ አንዱን ኮንዶም ላጠና አዘጋጀ፡፡ “ማን ፉል አለ” አለ በልቡ፡፡ ለአምስት ደቂቃ ስሜት ብሎ ህይወቱን ማጣት የለበትም፡፡ አሁንም ግን በለስ አልቀናውም፡ እርምጃው የሱን በር አልፎ እየራቀ እየራቀ ሄደ፡ የሰማውን ማመን አልቻለም፡፡ ብድግ ብሎ ተነሳና በሩን ለመክፈት ሞከረ፡፡ ከውጭ ተቀርቅሯል፡ በቁልፉ ቀዳዳ በኩል አጮልቆ ለማየት ሞከረ፡ ምንም አይታይም፡፡ ኤልያስ ነፍሱን አይማረው! ዛሬ ተጫውቶብኛል፡፡ ኮንዶሙን ጣለና በጀርባው ተንጋሎ አሁንም ሲጋራ ለኮሰ፡፡
ወሲብ ለመፈጸም መፈለጌ ምን ሐጢያት አለበት? ሲል አሰበ፡፡ ሰዎችም ውሾችም ንቦችም ዝንቦችም ሌላው ቀርቶ አበቦችም ይፈጽማሉ፤ ከአሜባ በስተቀር፡፡ እሱ ብቻ ነው ራሱን እየከፋፈለ የሚራባው፡፡ ወንድ ነው አሜባ፡፡
ሚልዮን በአሜባ እየቀና ሌላ የታኮ ድምፅ እንደገና ተሰማ፡፡ አሁን የምትመጣዋ ሴት የሱ ለመሆንዋ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ድምፁ እየቀረበ መጣ፡፡ ከዚያ የሱ በር ተነቀነቀ፡፡ ሚልዮን ኮንዶሙን እያዘጋጀ ማነው? አለ
“ኦው ይቅርታ ሰባት ቁጥር ነው የፈለግሁት” አለ አንድ ደስ የሚል ድምፅ፡፡ ድምፁ እየራቀ ሄደ፤ አንድ በር ሲከፈት በዚያው ጠፋ፡፡
አሁን ሚልዮን ተስፋ ቆረጠ፡፡ በጀርባው እንደተንጋለለ የቆጥ የባጡን ሲያብሰለስል እንቅልፍ ይዞት ሄደ፡፡ ጠዋት የክፍሉ በር ተከፈተ፡፡ ኤልያስ በስካር የቀሉ አይኖቹ እንዳይታዩ መነጽሩን አድርጐ ፊት ለፊቱ ቆሟል፡፡
“አንተ የውሻ ልጀ” አለ ሚልዮን ከእንቅልፉ ነቅቶ እያዛጋ
“የሆንኩትን ብታውቅ እንደዚህ አትልም” ኤልያስ ሰበብ ለመፍጠር እየሞከረ፡፡ ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ሁለቱም ተያይዘው ወጡ፡፡ አንዱን ክፍት ቱቦ ሲያይ ሚልዮን ሽንቱ እንደመጣ አስተዋለ፡፡ “ሽንቴን ልሽና” ብሎ ወደ ቱቦው ሲጠጋ ኤልያስም አጠገቡ ቆሞ መሽናት ጀመረ፡፡ ያየውን ግን ማመን አልቻለም፡፡ ሚልዮን የሚሸናው ብልቱ ላይ የተጠለቀው ኮንዶም ላይ ነበር፡፡ ሚልዮን እራሱ በድንጋጤ ኮንዶሙን አየና አውልቆ ጣለው፡፡ ኤልያስ በሳቅ ፈነዳ፡፡ በቆርንጦስ ከተማ የማይታይ ነገር የለም፡፡ አሁን ጸሐይ ወጥታለች፡፡ ስትጠልቅ ደግሞ የሚሆነው አይታወቅም፡፡

Read 5486 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 08:18