Saturday, 18 May 2013 10:11

በቤት ፕሮግራሙ እስከ 1.3ሚሊዮን ህዝብ ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

የአዲስ አበባ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኤጀንሲ በቀጣዩ ወር በሚጀመረው የቤቶች ልማት ፕሮግራም ምዝገባ ላይ እስከ 1.3 ሚሊዮን የሚደርስ ቤት ፈላጊ ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአንድ የምዝገባ ጣቢያ ስር እንዲካተት ከተደረገው የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ በስተቀር በሌሎች ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 113 ወረዳዎች በሶስት የቤት ፕሮግራሞች ዘርፍ እንደሚከናወን ታውቋል፡፡ ኤጀንሲው ከመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር 11 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጐ ዘመናዊ የምዝገባ አሠራርን የዘረጋ ሲሆን ይህን እንዲያስፈፅሙ ከ4ሺህ በላይ ሙያተኞች ስልጠና እንደተሰጣቸውም ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን መንግስቱ ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ፤ አዲስ የሚጀመረው የቤቶች ልማት በ1996 ዓ.ም የተጀመረው ቀጣይ ፕሮግራም መሆኑን አስታውሠው፣ በአሁኑ ፕሮግራም ዝቅተኛ ገቢ ላለው ህብረተሠብ ታሣቢ ያደረገ የ10/90፣ መካከለኛ ገቢ ላላቸው የ20/80 እንዲሁም የህብረት ስራ ማህበራት በጋራ ለሚያከናውኑት የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም እንደተቀረፀ አስታውቀዋል፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ታሣቢ ያደረገው የ10/90 ፕሮግራም፤ ተመዝጋቢዎች በወር 187 ብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሣብ እያስቀመጡ ከ2-3 ዓመት ባለው ጊዜ እስከ 4ሺህ ብር እንዲቆጥቡ ይጠይቃል፡፡ የአገልግሎቱ ፈላጊ የወር ገቢው ከ1200 ብር በታች የሆነ ይህንንም ለማረጋገጥ ተቀጣሪ ሠራተኛ ከሆነ ከመስሪያ ቤቱ ማስረጃ ማቅረብ የሚችል በግል የሚሠራ ከሆነም ከሚኖርበት ወረዳ ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኝ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

አሁን ባለው የግንባታ ወጪ ስሌት፤ የአንዱ ቤት ዋጋ 38ሺህ ብር እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡ የ20/80 የቤት ፕሮግራም፤ 20 በመቶ ወጪውን ቤት ፈላጊው 80 በመቶውን ደግሞ መንግስት የሚሸፍን ሲሆን በ1997 ዓ.ም ለኮንዶሚኒየም የተመዘገቡና እስከ ዛሬ እጣ ያልወጣላቸውም በዚሁ መርሃ ግብር ይታቀፋሉ ተብሏል፡፡ ምዝገባው ለነባር እና አዲስ ተመዝጋቢ በሚል የተለየ ሲሆን፤ ነባር ተብለው የተለዩት በ1997 የተመዘገቡት ናቸው፡፡ እኒህ ቤት ፈላጊዎች ለአምስት አመት በየወሩ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለነባር ተመዝጋቢዎች አራት አይነት ቤቶች የተዘጋጁ ሲሆን 61ሺህ ብር የተገመተውን ስቱዲዮ ቤት ፈላጊ በወር 151 ብር መቆጠብ ሲገባው፤ 176ሺ721 ብር የተገመተውን ባለ አንድ መኝታ ቤት ፈላጊ ደግሞ በወር 274 ብር መቆጠብ ይጠበቅበታል፡፡

224,000 ብር ይፈጃል ለተባለው ባለ ሁለት መኝታ ቤት በወር 561 ብር እንዲሁም 304,215 ብር ይፈጃል ለተባለው ባለሦስት መኝታ ቤት በወር 685 ብር መቆጠብ እንደሚያስፈልግ ታውቋል፡፡ ነባር ተመዝጋቢዎችም በመረጃ ቋት ውስጥ ስማቸው መኖሩን ለማረጋገጥ እንዲችሉ ኤጀንሲው ከግንቦት 25-30 በተለያዩ ሚዲያዎች ዝርዝራቸውን ይፋ እንደሚያደርግ አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡ የ20/80 የቤት ፕሮግራም አዲስ ተመዝጋቢዎች በየወሩ በሚፈልጉት የቤት አይነት ዋጋ ለሰባት አመታት መቆጠብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች በሶስት አይነት ቤቶች ብቻ ተመዝጋቢ ይሆናሉ - ባለ1 መኝታ ቤት፣ ባለ2 እና ባለ3 መኝታ ቤቶች፡፡ ዋጋቸው ከነባሮቹ ጋር ተመሣሣይ ሲሆን፤ ስቱዲዮ ቤት ለአዲስ ተመዝጋቢዎች አይፈቀድም ተብሏል፡፡ የ10/90 እና የ20/80 የቤት ፕሮግራሞች ምዝገባ ከሠኔ 3-21/2005 ዓ.ም የሚከናወን ሲሆን ለምዝገባው የሚያስፈልጉ መስፈርቶችም፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቁጠባ መጀመሩን የሚገልፅ ማስረጃ፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ በአዲስ አበባ ከሁለት አመት በላይ የኖረ መሆኑን የሚገልፅ ማስረጃ ሲሆኑ በምዝገባው ወቅትም ስለተመዝጋቢው ዋና ዋና መረጃዎች እና የጣት አሻራ ይወሠዳል፡፡

አንድ ሠው ከሶስቱ ፕሮግራሞች በአንዱ ብቻ መሣተፍ እንደሚችል ያስገነዘቡት የስራ ሃላፊዎቹ፤ ባልና ሚስቶችም እንደ አንድ አንድ ሠው እንጂ በተናጥል መመዝገብ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ አንድ ሠው ወይም ባለ ትዳሮች ከተፈቀደላቸው በላይ ተመዝግበው ቢገኙ ከፕሮግራሙ ሙሉ ለሙሉ ከመሠረዛቸውም በላይ ወንጀሉ ከ5-15 አመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል ተብሏል፡፡ ሌሎች ከምዝገባ ሊያሠርዙ የሚችሉ ጉዳዮችም በመግለጫው ተጠቅሰዋል፡፡ ማንኛውም ተመዝጋቢ በራሱ ጊዜ አቋርጦ ገንዘቡ እንዲመለስለት ሲጠይቅ፣ ለ6 ተከታታይ ወራት የሚጠበቅበትን ቁጠባ ሳይቆጥብ ሲቀር እንደሆነ እንዲሁም በራስም ሆነ በትዳር አጋሩ የመኖሪያ ቤት አሊያም የመስሪያ ቦታ ያለው ሆኖ ከተገኘ ከፕሮግራሙ ይሠረዛል የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ተመዝጋቢው በምዝገባው ወቅት ፎርሞቹን ማግኘት የለበት ከሚመዘገብበት ማዕከል ብቻ ሲሆን በፎቶኮፒ የተባዛ ፎርም ተቀባይነት አይኖረውም ተብሏል፡፡

ከተመዘገበ በኋላም መለያ ቁጥር በመውሰድ በየጊዜው በኢንተርኔት አማካይነት በመረጃ ቋት ውስጥ ስሙ መኖሩንና አለመኖሩን መከታተል ይችላል፡፡ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገው የ40/60 የቤቶች ልማት ፕሮግራም ግንባታው አስቀድሞ የተጀመረ መሆኑን ያመለከቱት የስራ ሃላፊው፤ የዚህ እድል ተጠቃሚ ለመሆን የፈለገ ሰው ቅድሚያ 40 በመቶ በባንክ መቆጠብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ዝርዝር መረጃዎች በቅርቡ እንደሚወጡም አቶ መስፍን ገልፀዋል፡፡ ከሰኔ 15 በኋላ ምዝገባው በይፋ በሚጀመረው የህብረት ስራ ማህበራት የቤት ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ አካላት፣ 24 ሆነው መደራጀት የሚጠበቅባቸው ሲሆን የግንባታውን ውጪም ሙሉ ለሙሉ መሸፈን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ማህበራቱ ለምዝገባ ሲቀርቡም የግንባታውን ወጪ 50 በመቶ የገንዘብ መጠን በዝግ ሂሳብ ይዘው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡

በዚህ የቤት ፕሮግራም ልዩ ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉ ሲሆን ሴቶች ከዚህ ቀደም እንደነበረው በእጣው ወቅት የ30 በመቶ ቅድሚያ የማግኘት እድል ይሰጣቸዋል፡፡ የመንግስት ሠራተኛውም የ20 በመቶ ቅድምያ እድል ይኖረዋል፡፡ ለመንግስት ሠራተኞች በ33 መስሪያ ቤቶች ውስጥ የምዝገባ ሂደቱ የተመቻቻላቸው ሲሆን የመንግስት ሠራተኛውን በልዩ ሁኔታ ለማስተናገድ የተፈለገውም መረጃው በየመስሪያ ቤቱ በቀላሉ ስለሚታወቅ መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ የ20 በመቶ ቅድሚያ እድል የተሰጠውም በኑሮ አቅሙ ተጐጂ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ ለሁሉም የቤት ፕሮግራሞች በየወሩ እንዲቆጠብ የሚፈለገውን የገንዘብ መጠን ቀድሞ በባንክ አስቀምጦ መጨረስ የሚቻል ሲሆን በየጊዜው እየናረ ያለውን የግንባታ ወጪ መነሻ በማድረግም የመዋጮው መጠን ሊጨምር እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

Read 4245 times