Saturday, 18 May 2013 10:20

አስጐብኚዎች 300 መኪኖች በጉምሩክ ተይዘውብናል ሲሉ አማረሩ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(3 votes)

ከሦስት መቶ በላይ መኪኖች በጉምሩክ ተይዘው ያለ ስራ ለሁለት አመታት እንደተቀመጡ የገለፁ አስጐብኚ ድርጅቶች፣ የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን ሃላፊዎች አቤቱታችንን ለመስማትም ሆነ እኛን ለማነጋገር ፍቃደኛ ባለመሆናቸው እንግልት ደርሶብናል ሲሉ ባካሄዱት ስብሰባ ገለፁ። በመቶ የሚቆጠሩ ድርጅቶች በአባልነት የያዘው የአስጐብኚዎች ማህበር ትናንት በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንቅስቃሴን እንደሚደግፍ በመግለፅ፣ የኛ አቤቱታና መረጃ ለኮሚሽኑ ጠቃሚ ግብአት ይሆናል ብሏል፡፡ የማህበሩ አባላት የሆኑ አስጐብኚ ድርጅቶች ከባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ሃላፊዎች ከባድ ተጽእኖና እንግልት እንደደረሰባቸው ማህበሩ ገልፆ፤ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የነሱን መረጃ የሚቀበል ዴስክ እንዲያቋቁም ጠይቀዋል፡፡

ለቱሪዝም እድገት የትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ እንዲቋቋም ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ መወሰናቸውን እንደሚደግፉ የገለፁ የማህበሩ አባላት፣ ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ግን የቱሪዝም ዘርፉን በሚያቀጭጩ እንግልቶች ሳቢያ በርካታ አስጐብኚ ድርጅቶች እየተዳከሙና እየከሰሩ ከስራው ወጥተዋል ብለዋል፡፡ አስጐብኚ ድርጅቶች የቱሪዝም ስራቸውን ለማሳደግ ከውጭ ያስመጧቸው ከ300 በላይ መኪኖች ለሁለት አመታት ያለምንም ምክንያት ያለስራ በጉምሩክ ግቢ ውስጥ መቆማቸውን የማህበሩ አባላት ገልፀው፤ ሃላፊዎች ዘንድ ብንሄድም መፍትሔ አላገኘንም። የሚያንገላቱና የሚያንጓጥጡ ሃላፊዎች በርካታ በደሎችን ፈጽመውብናል ያሉት የማህበሩ አባላት፣ ይህንን በግልጽ የሚያሳዩ ማስረጃዎቻችን የፀረሙስና ኮሚሽን እንደሚቀበለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

Read 2134 times