Saturday, 18 May 2013 11:08

ከጐዳና ተዳዳሪነት ወደ ጐዳና መጽሐፍ ነጋዴነት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(3 votes)

“የሚገጥመኝ እንግልት ብዙ ነው”

በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያውን የመፃሕፍት መሸጫ መደብር በመክፈት የሄዶን ዜግነት የነበራቸው ሚስተር ዴቪድ ቀዳሚ ሲሆኑ፤ መፃሕፍት አዙሮ በመሸጥ ደግሞ ተስፋ ገብረሥላሴ መሆናቸውን “ዘመን ተሻጋሪ ባለውለታ” የተባለው መጽሐፍ ይጠቁማል። ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ባስቆጠረው የመፃሕፍት ዝግጅት፣ ህትመትና ስርጭት ዙሪያ ካሉ ያሉ ችግሮች ዛሬም ድረስ አልተፈቱም፡፡ በጐዳና የመፃሕፍት ንግድ ሥራ ላይ የሚገኘው ወጣት ድንቁ ግርማ የሚደርስበት እንግልት ለዚህ ምሳሌ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል። የአምስት ዓመታት የመጽሐፍ ንግድ ሥራ ሂደቱና የሕይወት ውጣ ውረዱን አውግቶኛል፡፡

የእግር ጉዳትህ የተፈጥሮ ነው?

አይደለም፡፡ ጤናማ ሆኜ ነው የተወለድኩት። ወላጆቼ እንደነገሩኝ ከሆነ የ3 ዓመት ልጅ እያለሁ ወድቄ፤ በወቅቱ ወደ ሐኪም ቤት ስላልተወሰድኩ ለእግር ጉዳተኛነት ተዳረግሁ፡፡ ትውልድህና ዕድገትህ የት ነው? በ1980 ዓ.ም በሱሉልታ መንደር ነው የተወለድኩት፡፡ ሦስት እህትና ሁለት ወንድሞች አሉኝ፡፡ እኔ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ በሱሉልታ ብዙ አልቆየሁም፡፡ ደብረብርሃን (ደነባ) ሄጄ ከዘመድ ጋር ስድስት ዓመታት ኖሬያለሁ፡፡ ከዚያ ጠፍቼ በመምጣት በአዲስ አበባ በጐዳና ተዳዳሪነት ሁለት ዓመታት ያህል ቆይቻለሁ፡፡ ከጐዳና ተዳዳሪነት መውጣት እንዴት ቻልክ? መርካቶ ሃብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ ነበር የማድረው፡፡ አድራሻው እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ የሆነ “ሲዳርታ” የሚባል የበጐ አድራጐት ድርጅት ከጐዳና አንስቶ ወደ ማዕከሉ አስገባን፡፡

ከትምህርት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘሁት እዚያ ነው፡፡ በማዕከሉ አራት ዓመት ስቆይ ደብል እየመታሁ 6ኛ ክፍል ደርሻለሁ፡፡ ሰርከስ ሊያሰለጥኑን ሞክረዋል፡፡ የእንጨትና የብረታ ብረት ሥራም አስተምረውናል። ከዚያ በኋላ ራሳችሁን ቻሉ ተብለን ተሰናበትን፡፡

ቀጣይ የሕይወት አቅጣጫህ ምን ሆነ?

በእንጨትና በብረታ ብረት ሥራ ተቀጥሬ ለመሥራት የተለያዩ ቦታዎች ሄጄ ብጠይቅም የሚቀበለኝ አጣሁ፡፡ ከሲዳርታ ማዕከል ስሰናበት ዊልቸር (ብስክሌት) እና 600 ብር ተሰጥቶኝ ስለነበር በዚያ ካፒታል ሶፍት፣ ማስቲካና ከረሜላ እያዞርኩ መሸጥ ጀመርኩ፡፡ መጽሐፍ አዙሮ የሚሸጥ ጓደኛዬ ከዚህ ሥራ ጋር አገናኘኝ፡፡ ፒያሳ ጐዳና ላይ መጽሐፍ በመሸጥ አምስት ዓመታት አስቆጥሬያለሁ፡፡ የመፃሕፍት ንግድ እንዴት ነው? ሥራው ጥሩ ነው፡፡ የመፃሕፍት ሕትመት ቁጥር ብቻ ሳይሆን አንባቢም እየጨመረ ነው፡፡ የመፃሕፍት ዋጋ እየተወደደ ቢመጣም ሕዝቡ የማንበብ ፍላጐት እንዳለው ይታያል፡፡

የአንባቢያን የመፃሕፍት ምርጫ ምን ይመስላል?

ምርጫው እንደየሰው ፍላጐት የሚለያይ ነው። የፍቅር፣ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የሳይኮሎጂ…መፃሕፍትን ሰው እንደየፍላጐቱ ነው የሚገዛው፡፡ አንተስ ታነባለህ?

የመጽሐፍ ምርጫህስ ምንድነው?

የማንበቡ ፍላጐት አለኝ፡፡ ግን የሥራዬ ባህሪና ያለብኝ የሥራ ችግሮች እንደምመኘው ለማንበብ አላስቻለኝም፡፡ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ ነው የምሰራው፡፡ የጐዳና ላይ ነጋዴ ስለሆንኩ በየዕለቱ ከፖሊስ፣ ከሕግና ደንብ አስከባሪዎች ጋር ጭቅጭቅ ነው፡፡ ብዙ መንገላታትና በተለያዩ ጊዜያት የንብረት መወረስም ገጥሞኛል፡፡ በአንድ ወቅት 7ሺህ ብር የሚገመት መፃሕፍት ወስደውብኝ እንዲመለስልኝ በተደጋጋሚ ባመለክትም የሚሰማኝ አላገኘሁም፡፡ የሚገጥመኝ እንግልት ብዙ ነው፡፡ በቅርቡ በእኔ እርዳታ ስር ያሉ እህቶቼን ከተረጂነት ወጥተው ራሳቸው እንዲችሉ 10ሺህ ብር የሚያወጣ የተለያዩ ቁሳቁስ ገዝቼላቸው ከእኔ ጋር ቁጭ ብለው እንዲሰሩ አድርጌ ነበር፡፡ እሱም በሕግና ደንብ ሰዎች ተወሰደባቸው፡፡ እህቶቼ ተመልሰው ወደ ቤት በመግባት የእኔን እርዳታ ጠባቂዎች ሆነዋል፡፡ ቀበሌ በአነስተኛና ጥቃቅን እንዲያደራጅህ እና የመሥሪያ ቦታ እንዲሰጥህ አልጠየቅህም?

እናደራጃችኋለን ይላሉ፡፡ ሄደን ስንጠይቅ የሚያስተናግደን የለም፡፡ ዛሬ ቃል ገብቶልን ተስፋ ሰጥቶን ያነጋገረን ኃላፊ፣ በማግስቱ ስንሄድ በሌላ ሰው ተተክቶ ይገጥመናል፡፡ ዋና የሚባሉትን ኃላፊዎች ለማነጋገር ደግሞ እንከለከላለን፡፡ ስለዚህ ወደ ቀበሌ ለመሄድ ማሰቡ ራሱ ያስጠላል፡፡ የድካሜ ውጤት የሆነውና በሕግና ደንብ ሰዎች የተወረሰብኝን መፃሕፍት እንዲመለስልኝ ስጠይቅ “የሌላ ሰው ሥራ ነው የያዛችሁት” የሚልና አካል ጉዳተኞች መሥራት አይችሉም ብለው እንዲያምኑ ለመረዳት ችያለሁ፡፡

በአካል ጉዳተኝነትህ ልዩ ማበረታቻ አግኝተህ አታውቅም?

መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ማበረታቻ ያደርጋል ሲባል ከምሰማው ውጭ እኔ እስካሁን ያየሁትም ሆነ ያገኘሁት ነገር የለም፡፡ የአካል ጉዳተኝነት ልዩ ተጠቃሚነቱ ቀርቶ እንደ ዜጋ ለጠየቅነው የመደራጀትና የመሥሪያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ ባገኝ እንዴት ጥሩ በሆነ ነበር፡፡ ጥያቄያችንን ለቀበሌው ብቻ ሳይሆን ለክፍለ ከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ብናስገባም ሰሚ የለም፡፡ የአካል ጉዳተኞች ማህበር አባል ነህ? የብሔራዊ አካል ጉዳተኞች ማህበር አባል ነኝ፡፡ ዓመታዊ ክፍያ አስከፍለው መታወቂያም ሰጥተውኛል፡፡ ለአንድ ሺህ አካል ጉዳተኞች ኮንዶሚኒየም ቤት በቅድሚያ ይሰጣል ብለውን ገንዘብ ከፍለን ነበር፡፡ እስካሁን ምንም ያገኘነው ነገር የለም፡፡ ከሌላው ጊዜ በተለየ የጎዳና ላይ የመፃሕፍት ንግድ ምን ችግሮች አሉበት? ክረምት ተማሪዎች ከትምህርት የሚያርፉበት ወቅት ስለሆነ የመጽሐፍ አንባቢያን ቁጥር ይጨምራል፡፡ ክረምት ለመፃሕፍት ሽያጭ ጥሩ ጊዜ ቢሆንም በየዕለቱ ጎዳና ላይ የዘረጋናቸውን መፃሕፍት ከዝናብ ለመከላከል የምናደርገው ትግል ከባድ ነው። መፃሕፍቱን ከታች በጎርፍ፣ ከላይ ከዶፍ መከላከሉ አስቸጋሪ ነው፡፡ መፃሕፍት ማሳደሪያ ቦታ የለኝም፡፡ እዚሁ አካባቢ ያሉ ዘበኞች እንዲጠብቁልኝ አደራ ሰጥቼ ነው ወደ ቤት የምሄደው፡፡ ሌሊት ዶፍ ሲወርድባቸው ከተሸፈኑበት ላስቲክ ውጭ መከላከያ የላቸውም፡፡

አሁን ከማን ጋር ነው የምትኖረው?

ብቻዬን የግለሰቦች ቤት ተከራይቼ ነው ያለሁት። በዚህ ሥራ ራሴን ብቻ ሳይሆን እናቴንና እህት ወንድሞቼን እረዳለሁ፡፡ የቤቱ ታላቅ ልጅ በመሆኔም ታናናሾቼን የማገዝ ኃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ በየዕለቱ በሥራው ላይ የሚገጥሙኝ ችግሮች ሕይወቴ በሥጋት እንዲወጠር ያደርገዋል።

ይህን ሥራ ባጣ እንዴት መኖር እችላለሁ?

የቤት ኪራይስ ምን እከፍላለሁ? እያልኩ እጨነቃለሁ፡፡ ተረጋግቼ ውዬ የማድርበት ቀን የለም፡፡

ቀጣይ የሕይወት ዓላማህ ምንድነው?

ተረጋግቼ ሥራዬ የምሰራበት ቦታ፣ የራሴ ቤትና ትዳር እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ መንግሥት ለዜጎች፣ ለወጣቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች … ያስቀመጣቸውን መብቶች ተግባራዊ ሲያደርግ የእኔም ምኞት በፍጥነት ይሳካል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ነገር በየሚዲያው ብቻ ማውራት ጥቅም አይኖረውም። ልመና ይቁም፤ ሥራን እናበረታታ እየተባለ ብዙ ይነገራል፡፡ ሲሆን የሚታየው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ እኔ በግሌ በልመና መተዳደርን አልፈልግም፤ ሠርቶ የመኖር ብቻ ሳይሆን የማደግ ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ፡ የፈለገ ችግር ቢገጥመኝ ሠርቼ ለመኖር መታገሌን አላቋርጥም፡፡ በመጨረሻ የምታነሳው ሀሳብ ካለ … ጤናማ ሆነውም ይሁን በአካል ጉዳተኝነት፤ በጎዳና ተዳዳሪነትና በልመና የሚኖሩ፤ ሥራ ፈጥረው ለመኖር ቢሞክሩ ከራሳቸው ባለፈ ሌላውን ሊረዱ ይችላሉ፡፡ ሠርቶ ለመኖርም ቢሆን ችግሮች እንዳሉ እኔ በራሴ ልምድ አይቻለሁ፡፡ ፖሊስ ወይም የቀበሌ ሕግና ደንብ ሰዎች መፃሕፍቶቼን በማንገላታትና በመውረስ ሲያንገላቱኝ በተቃራኒው ሕብረተሰቡ “ሠርቶ ይኑርበት” ብሎ ሲሟገትልኝ አይቻለሁ፡፡ ስለዚህ ለምኖ ከመኖር ሠርቶ ማደር እንደሚያስከብር አረጋግጫለሁ፡፡ ሌሎችም እንዲሰሩ አበረታታለሁ፡፡

Read 2229 times