Saturday, 18 May 2013 11:23

የሁለቱ ወጣት ሴቶች አሳዛኝ ወግ-በመተሃራ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(16 votes)

ከአዲስ አበባ 135 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የመተሀራ ከተማ የነዋሪዎች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ ሆኖም ከተማዋ ጅቡቲን ጨምሮ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ መንገደኞችና ሹፌሮች መናኸሪያ ናት፡፡ ከምሽቱ 12፡30 ጀምሮ ከተማዋ ትሟሟቃለች፡፡ ቡና ቤቶችና ጭፈራ ቤቶች ይደምቃሉ፡፡ መተሃራ ህንፃ የበዛባት ከተማ አይደለችም፡፡ በፍራፍሬዎቿ ግን ትታወቃለች፡፡ ሌላው መታወቂያዋ 11ሺ ሠራተኞች ያሉት የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ነው፡፡ ፋብሪካው ለሠራተኞቹ የራሱ የመኖርያ ካምፕ አለው - እንደ ጤና ጣቢያ ያሉ ማህበራዊ አገልግሎቶች የተሟሉለት፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ይሄ ካምፕ ትልቅ አደጋና ስጋት ተጋርጦበታል፡፡ ኤችአይቪ በስፋት ተሰራጭቷል፡፡ እማዋይሽ (ሃና) የዛሬ ሰባት ዓመት ናዝሬት ከምትሠራበት የምሽት ክበብ ወደመተሃራ ካምፕ የመጣችው የትዳር ጓደኛ አግኝታ ነው - በጓደኛዋ በሊንዳ አማካኝነት፡፡ ሊንዳ በናዝሬት የምሽት ክበብ ከእማዋይሽ ጋር ትሰራ የነበረች የልብ ወዳጅዋ ስትሆን ከእሷ ሦስት ዓመት ቀድማ ነው መተሃራ የገባችው - ባል አግብታ፡፡ እሷ ከቡና ቤት ህይወት እንደተላቀቀችው ሁሉ ጓደኛዋንም ለማላቀቅ አስባ፣ እማዋይሽን ከባለቤቷ ጓደኛ ጋር አስተዋወቀቻት፡፡ እናም ትዳር ይዛ መተሃራ ከተመች - እማዋይሽ፡፡

ከባሏ ጋር የተስማማችው እሱ በሚሰጣት ገንዘብ ቤታቸውን በማስተዳደር የቤት እመቤት እንድትሆን ነበር፡፡ በጉዳዩ ተስማምታ ወደ ትዳሩ ብትገባም ቅሉ መዝለቅ ግን አልቻለችም፡፡ የጫትና የሲጋራ ሱስ አለባት፡፡ እነዚህን ሱሶቿን የምታረካበት በቂ ገንዘብ ግን በእጇ ላይ ልታገኝ አልቻለችም፡፡ ባለቤቷ ከሚሰጣት የአስቤዛ ወጪ ለሱሷ የሚሆን ገንዘብ ለማትረፍ ብትሞክርም አልሆነላትም፡፡ ገንዘቧ ትንሽ ናት፡፡ ስለዚህም ነው ትታው ወደመጣችው ህይወት ተመልሳ የገባችበት፡፡ ከባለቤቷ ተደብቃ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር መማገጥ ጀመረች፡፡ እንዲያም እያለች ለሲጋራና ጫት መግዢያ በቀን ሀያና ሃያ አምስት ብር ድረስ ታገኝ ነበር፡፡

አሳዛኙ ነገር ባለቤቷን ማጭበርበሯ ብቻ አልነበረም፡፡ ጥንቃቄ የጐደለው ወሲብ መፈፀሟም ጭምር እንጂ፡፡ እማዋይሽ ሠባት አመታት በትዳር ስትኖር አጥብቃ የምትመኘው ልጅ የመውለድ ነገር አልተሳካላትም፡፡ ያልሔደችበት ሀኪም ቤት የለም፡፡ ያላማከረችው ሰው የለም፡፡ የማታ ማታ ግን ለምታምነው ታቦት ተስላ ማርገዝ መቻሏን ትናገራለች፡፡ እርግዝናዋ እየገፋ ሲመጣ በህክምና ባለሙያዎች ግፊት የጤና ምርመራ ለማድረግ ተገደደች፡፡ ውጤቱ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ቫይረሱ በደሟ ውስጥ እንዳለ ተነገራት፡፡ እውነታውን ለመቀበል ተቸገረች። ሌላ ክሊኒክ ሄዳ ብትመረመርም ውጤቱ ያው ሆነ። የምርመራ ውጤቷን ለማንም እንዳይነግሩባት ለካምፑ የጤና ባለሙያዎች ብትነግርም፣ እማዋይሽ እቤቷ ሳትደርስ ነበር ጐረቤቶቿ ሲያሟት የሠማችው። ለባለቤቷ ውጤቱን ማርዳት አስፈርቷት ሳትነግረው ወንድ ልጅ በሰላም ተገላገለች፡፡ ልጁ ግን ጤነኛ አልነበረም፡፡

የኤችአይቪ ቫይረስ በደሙ ውስጥ ነበረበት፡፡ የልጁ ጤንነት ማጣት ያሳሰበው ባሏ ነው ህፃኑን ወደ ጤና ጣቢያ ወስዶ ያስመረመረው፡፡ ከጤና ጣቢያው ሲመለስ “አንቺ ሸርሙጣ፤ ልጄን ገደልሽው” ብሎ አምባረቀባት፡፡ ልብሶቿን አውጥቶ በመወርወር ድምፅ ሳታሠማ ከቤቱ እንድትወጣለት አዘዛት፡፡ ትኩስ አራስ የነበረችው እማዋይሽ፤ የባሏ እግር ላይ ወድቃ እንዳያባርራት የሙጥኝ አለችው፡፡ ይቅርታ እንዲያደርግላት ተማጠነችው፡፡ ሁለቱም የመጣባቸውን መከራ በጋራ ተቀብለው አብረው እንዲኖሩ ለመነችው፡፡ ይሄኔ ነው ቱግ ብሎ ሃቁን የነገራት “አንቺ ነሽ መከራ ያለብሽ እኔ ነፃ ነኝ፣ ባንቺ ቤት እኔን የጐዳሽ መስሎሻል፤ ልጄን ግን በላሽው” በማለት የተመረመረበትን ወረቀት አሳያት፡፡ ለካስ እሱ ከቫይረሱ ነፃ ነው፡፡

ይሄኔ ምንም ሳታመነታ ልብሷን ሰብስባ ከቤት ወጣች፡፡ ግን ወዴት እንደምትሔድ አታውቅም ነበር፡፡ አንድ ሳምንት ልጇን ይዛ ጓደኛዋ ጋር ተቀመጠች፡፡ ልጇም በወር ከ15 ቀን ዕድሜው ህይወቱ አለፈ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው እማዋይሽ መተሃራ መናኸሪያ ጐን ካለ አንድ የማንጐ ዛፍ ስር ላስቲክ በመወጠር የጐዳና ኑሮዋን አንድ ብላ የጀመረችው፡፡ በዚህ ቦታ መኖሯን የምታውቀው ብቸኛ ጓደኛዋ ሊንዳ ነበረች፡፡ እየመጣችም ትጠይቃታለች፡፡ አንድ ቀን ግን ሊንዳ ፀጉሯን አንጨባራ ባዶ እግሯን እንደ እብድ እየሮጠች እማዋይሽ ጋ ትመጣለች፡፡ “ምን ሆነሽ ነው?” ትላታለች፡፡ “ጐሹ” “ጐሹ” ብቻ ነበር የምትለው - ሊንዳ፡፡ ጐሹ ባለቤቷ ነው፡፡ በአንድ ድርጅት ውስጥ ሥራ ለመቀጠር የጤና ምርመራ አድርጐ፣ የኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ በደሙ ውስጥ መኖሩ ሲነገረው፣ በሽታውን ያመጣችበት ሚስቱ እንደሆነች ቅንጣት አልተጠራጠረም፡፡

ለዚህም ነው ቤት እንደገባ ዱላ የጀመረው፡፡ ይሄኔ አምልጣ ወደ ብቸኛ ጓደኛዋ እማዋይሽ መጣች፡፡ ነገሩ ለእማዋይሽ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ለአንድ ቀንም ቢሆን ከሊንዳ ባል ጋር መተኛቷን ታውቃለች። ክፉኛ አዝና ብታቀረቅርም ከባሏ ጋር መማገጧን አልተናዘዘችላትም፡፡ ሊንዳ በነጋታው ወደ ጤና ጣቢያ ትሄድና ምርመራ ታደርጋለች፡፡ ያልተጠበቀ ነበር ውጤቱ፡፡ ከቫይረሱ ነፃ ነሽ ተባለች፡፡ ከዚህ በኋላ ሊንዳ ጓደኛዋን ራቀቻት፡፡ ሁለቱ የነፍስ ጓደኛሞች ዳግም ላይገናኙ ተለያዩ፡፡ እማዋይሽ ምክንያቱን ባታውቀውም፡፡ ዛሬ እማዋይሽን ከህመሟ በላይ የሚያሠቃያት ልጇን ከቫይረሱ ነፃ ማድረግ እየቻለች ለህልፈት መዳረጓ ነው፡፡ የእግር እሳት የሆነብኝ የልጄ ነገር ነው ትላለች፡፡ ልጄ ቢኖር ኖሮ መፅናኛዬ ይሆነኝ ነበር በማለት ሀዘኗን በእንባ ትገልፃለች፡፡

ሌላው ውስጧን እያመሰ የበጠበጣት ደግሞ በጓደኛዋ ላይ የፈፀመችው ክህደት ነው፡፡ ከገዛ ጓደኛዋ ባል ጋር ተኝታ በሽታውን በማስያዝ ትዳር ማፍረሷ በፀፀት ያንገበግባታል፡፡ የራሷ ሳያንስ የጓደኛዋን ህይወት መበጥበጧ መልሶ ይበጠብጣታል፡፡ “መሞት ስለምፈልግ የፀረ- ኤችአይቪ መድሃኒቱን አልጠቀምም” ትላለች ተስፋ በቆረጠ ስሜት፡፡ አሁን እማዋይሽ ደካክማለች፡፡ ፊቷ እና እጆቿ ቆሳስለዋል። የእነዚህ ጓደኛሞች አሳዛኝ ታሪክ ማለቂያ ያለው አይመስልም፡፡ ሊንዳ የእማዋይሽን የቀድሞ ባል አግብታ እየኖረች ነው - ራሷ እማዋይሽ እንደነገረችኝ፡፡ እሷ ግን ሞቷን ትጠባበቃለች፡፡ አሳዛኝ የህይወት ክስተት ይሏል ይሄ ነው!!

Read 20060 times