Monday, 27 May 2013 13:35

ከረሃብ ለመዳን ጥንዚዛና ምስጥ፣ አንበጣና ጉንዳን ብሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ዩኤን) ባለፈው ሳምንት ከሮም ከተማ ለአለማችን ረሃብተኞች አንድ ምክርና የምስራች ወሬ አሰራጭቷል። የምስራች ወሬው፣ “እነ ጥንዚዛን በመመገብ ከረሃብ መገላገል ይቻላል” የሚል ነው። በደግነት የለገሰን ምክር ደግሞ፣ ከረሃብ ለመዳን “ነፍሳትን ብሉ” ይላል። ዩኤን ይህን “ምክርና የምስራች” በይፋ ለመላው አለም ያበሰረው፣ የአለም ምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ባዘጋጀው ባለ 200 ገፅ ሰነድ አማካኝነት ነው። የሰነዱ ርዕስ እንዲህ ይላል፣ Edible insects፡ Future prospects for food and feed security። እነ ጉንዳን፣ የመጪው ዘመን የምግብ ዋስት ተስፋዎቻችን እንደሆኑ የሚሰብክ ሰነድ ነው። “ረሃብተኛ ሆኖ ለብዙ አመታት በተመፅዋችነት መቆየት፣ መጨረሻው ውርደት ሆነ? ‘ጥንዚዛ ብላ!’ የሚል የስላቅ ምላሽ የምንሰማበት ደረጃ ላይ ደረስን?” የሚል ጥያቄ የሚፈጠርባቸው የድሃ አገር ሰዎች መኖራቸው የማይቀር ነው። በእርግጥም፣ በርካታ አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት፣ ዜናውን የዘገቡት በስላቅ መንፈስ ነው።

“ዩኤን ለአለማችን ረሃብተኞች አንድ ምክር አለው - በራሪ ነፍሳትን መብላት…” በማለት ነው ያሁ-ኒውስ ዘገባውን የሚጀምረው። የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባም ተመሳሳይ ነው። “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ረሃብን፣ የአለም ሙቀትንና ብክለትን ለመዋጋት አዳዲስ መሳሪያዎችን ታጥቋል” በማለት የሚጀምረው የአሶሼትድ ፕሬስ ዜና፣ የዩኤን መሳሪያዎችን ለማየት ከፈለግን ሩቅ መሄድ እንደማይኖርብን ይገልፃል። አካበቢያችንን ብንቃኝ በቂ ነው። የዩኤን “ዘመናዊ” መሳሪያዎች፣ በሄድንበት ቦታ ሁሉ በዙሪያችን የሚያንዣብቡና አፍንጫችን ስር ሳይቀር “በረራ” የሚያዘወትሩ ናቸው። ይህንን የስላቅ አገላለፅ በማስቀደም አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባውን ሲቀጥል… በዩኤን እምነት፣ የአለም ረሃብተኞች የወደፊት ተስፋ በራሪ ነፍሳትን መመገብ እንደሆነ ይገልጻል።

በዩኤን ስር፣ ለረሃብተኞች የእርዳታ እህል በማጓጓዝ የሚታወቀው ፋኦ፣ በራሪ ነፍሳት ለመብል የሚስማሙ መሆናቸውን ሲያስረዳ “በራሪ ነፍሳት በፕሮቲን የበለፀጉ ናቸው” ብሏል። እናም፣ ዩኤን እና ፋኦ፣ ረሃብን ለመከላከል ተስፋቸውን የጣሉት በበራሪ ነፍሳት ላይ ነው። ግን የነፍሳት ጥቅም፣ ከምግብነትም የላቀ እንደሆነ የገለፁት ዩኤንና ፋኦ፣ ለአካባቢ ጥበቃ ግሩም መፍትሄ ይሆንልናል ብለዋል። በሬና ላም፣ በግና ፍየል ብዙ ሳር እየበሉ አካባቢን ያራቁታሉ፤ የተለያዩ የጋዝ አይነቶችን እያመነጩ አካባቢን ይበክላሉ ይላል ዩኤን። ስለዚህ፣ አካባቢን የማያራቁቱና የማይበክሉ በራሪ ነፍሳት፣ ቀለባችሁ ይሁኑ በማለት ምክሩን ለግሷል። 1900 ያህል የነፍሳት ዝርያዎች ለምግብነት ተስማሚ መሆናቸውን ዩኤን ጠቅሶ፣ ጉንዳን፣ ጥንዚዛ፣ አንበጣ፣ ዝንብ፣ ምስጥ፣ አባጨጓሬ እንዲሁም ሌሎች በራሪና ተስፈንጣሪ ነፍሳትን በምሳሌነት ዘርዝሯል። የዩኤን እና የፋኦ መግለጫ፣ በረሃብተኞች ላይ የተሰነዘረ ስላቅ ይመስላል ብለው የሚቆጡ መኖራቸው አይቀርም።

ነገር ግን ብዙም አይገርምም። እድሜ ልክ እርዳታ እየጠበቀ የሚኖር ረሃብተኛ፣ ውሎ አድሮ “ከራበህ ጥንዚዛ ብላ!” የሚል ምላሽ ማግኘቱ የማይቀር ነው። ውርደት ሊመስል ይችላል። ከሁሉም የከፋ ውርደት ግን፣ ራስን ለመቻል አለመጣርና አለመቻል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ጥንዚዛና ዝንብ ተመገቡ” የሚለው ዘመቻ፣ በየጊዜው የሚያገረሽ የዩኤን እብደት ይመስላል። እናም፣ ለጊዜው ከተወራለት በኋላ፣ ወረቱ ሲያልቅ ተረስቶ ይቀራል ብለን እንገምት ይሆናል። ግን በዋዛ አይረሳም። ባለፉት 10 አመታት ለዘመቻው በጀት ሲመደብለት ቆይቷል። አሁንም ይመደብለታል። ለምን ቢባል… ዩኤንና ፋኦ ምላሽ አላቸው -ነፍሳትን የመመገብ ልምድ እንዲስፋፋና የህዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግ (awareness raising) በጀት ይመድባሉ።

ሰነዶችን ለማዘጋጀትና ለማሰራጨት፣ በአባል አገራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ፣ አዳዲስ ህጎችንም ለማዘጋጀት ገንዘብ ያወጣሉ። አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት፣ በራሪ ነፍሳትን የማርባት ሥራ እንዲጀምሩም ይደጉማሉ። ዩኤንና ፋኦ፣ ይሄን ሁሉ የሚያደርጉት፣ “ረሃብተኞችን ለመደገፍ” ነው። በሌላ አነጋገር፣ ዩኤንና ፋኦ፣ ብዙ ገንዘብና ሃብት ሳያባክኑበት በፊት፣ “የበራሪ ነፍሳት ፕሮጀክታቸውን” በአጭር ጊዜ እንደዘበት ይረሱታል ተብሎ አይጠበቅም።

Read 3618 times