Monday, 27 May 2013 13:42

የታሪክ ሊቁ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት አረፉ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የታሪክ ሊቅ የነበሩት ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ከትላንትና በስቲያ አረፉ፡፡ ፕሮፌሰር ታደሰ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በተመራማሪነትና በተለያዩ የአመራር ኃላፊነቶች የሠሩ ምሁር ነበሩ፡፡ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክ ለአገርና ለዓለም ያበረከቱ ሲሆን፤ በተለይም ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት በኢትዮጵያ (Church and State in Ethiopia, 1270-1527) የተሰኘው መጽሐፋቸው ዓለም አቀፍ እውቅና አስገኝቶላቸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ታደሰ የረቀቀ የምርምር ችሎታቸውን በድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ለተማሪዎቻቸው ለማስተላለፍ የበቁ ምሁር ሲሆኑ የምርምር ሥራዎቻቸው ዓለም አቀፍ እውቅናን አትርፈው፣ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ፣ በኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ፣ በበክኔል ዩኒቨርሲቲና በኢሊኖይ ዩኒቨርሲቲ በጎብኚ ፕሮፌሰርነት ለማገልገል በቅተዋል፡፡

በተጨማሪም ፕሮፌሰር ታደሰ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የኮሌጅ ደ ፍራንስ የክብር ሜዳይና የድኅረ ምረቃ ትምህርት ያካሄዱበት ከነበረው “ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን” የአፍሪካና እስያ ጥናት ማዕከል የክብር ፌሎውነት ሽልማት አስገኝቶላቸዋል፡፡ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፤ ከምርምር መስኩ ባሻገር ለአያሌ ዓመታት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በተለያዩ የአመራር ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ1977-84 በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር፤ ከ1986-92 የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን፤ ከ1995-99 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ዳይሬክተር ዋና ኤዲተር ፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር በመሆን ብቁ አመራር ከመስጠታቸውም በላይ 8ኛውን ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ በማዘጋጀት የኢትዮጵያ ጥናት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ምንጊዜም የማይዘነጋ ውለታ ውለው ያለፉ ምሁር ናቸው፡፡

Read 2991 times