Monday, 27 May 2013 14:50

ሙስናም የኢኮኖሚ ዕድገቱ ውጤት ነው እንዳንባል ሰግቻለሁ!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ያልተዘመረላቸው ጃንሆይ እየተዘመረላቸዉ ነው! (ዕድሜ ለአፍሪካ 50ኛ ዓመት!)
የፓርላማ አባላት የመንግስት ባለሥልጣናትን እያፋጠጡልን ነው (እሰይ!)
ወደፊት ለምትመሰረተው “አንድ አፍሪካ” የሂሩት በቀለን ዘፈን መረጥኩላት!

  ሰሞኑን በኢቴቪ እየቀረበ ያለውን የሙስና “ድራማ-መሳይ” ማስታወቂያ አይታችሁልኛል? መቼም ይሄንን የፀረ-ሙስና ዘመቻው አካል ነው ማለት በጣም ያስቸግራል፡፡ (ሙስናን ለማባባስ ያሰበ ወገን አለ እንዴ?) የአንድ መ/ቤት ሃላፊ (ካድሬ ይመስላል) ሠራተኞቹን ሰብስቦ ሙስናን በጋራ መታገል እንደሚገባቸው ሲደሰኩር ነው ሞባይሉ የሚጮኸው፡፡ ይቅርታ ጠይቆ ስብሰባውን አቋርጦ ይወጣና ቢሮው ውስጥ ከባለሃብት ጋር ይወያያል (የሙስና ውይይት እኮ ነው!) በመጨረሻም ከባለሃብቱ በፖስታ የታሸገ መጠኑ የማይታወቅ ገንዘብ (ሙስና) ተቀብሎ ወደ ሙስና ስብሰባው ይመለሳል፡፡ ከዚያም ምንም እንዳልተፈፀመ “ሙስናን በቁርጠኝነት መታገል አለብን” የሚል የካድሬ ሰበካውን ይቀጥላል፡፡ በዚሁ ነው የሙስና ማስታወቂያው የሚቋጨው፡፡

(ሳይጀመር እኮ ነው ያለቀው!) ቆይ ዓላማው ግን ምንድነው? መቼም አስመሳይ ሞሳኞችን ማስተዋወቅ አይመስለኝም (ምን ሊሰራልን?) ወይስ ለማዝናናት ዓላማ የተሰራ ነው? (እንደኔ ግራ ከመጋባት ይሰውራችሁ!) እኔ ከማስታወቂያው የተረዳሁትን ልንገራችሁ? “ሙስናም ሰርቶ በሰላም ስብሰባን መቀጠል ይቻላል!” የሚል ነው፡፡ እውነቴን እኮ ነው---ከሙስና በኋላ ኑሮ ያለችግር ይቀጥላል የሚል መልዕክት ነው ያለው። (ሞሳኝ እንዳይቀጣ የሚደነግግ ህግ ወጣ እንዴ?) አያችሁ … የሙስናን ነገር አላምነውም፡፡ ወረርሽኝ ነገር እኮ ነው! እናም ሞሳኙ ሳይቀጣ የሚጠናቀቅበት የሰሞኑ ማስታወቂያ ሙስናን እንደሚፀየፍ አንድ ዜጋ አልተመቸኝም ለማለት ያህል ነው፡፡

(እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም እንዲያ ነሽ አሉ!) በነገራችሁ ላይ ያንን የኢህአዴግ ካድሬ ወዳጄን ከስንት ጊዜ በኋላ አግኝቼው በሙስና ዙርያ ብዙ አወጋን፡፡ (እሱ እኮ የፖለቲካ ትኩሳት ሲፈጠር ብቻ ነው ብቅ የሚለው!) እናላችሁ ---- የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ያልተጠበቀ እርምጃ፣ ያልተገመቱትን ተጠርጣሪ ባለሥልጣናት (በህልሜ ነው በእውኔ አሉ!) እርምጃውን በተመለከተ አስተያየት ስለሰጡት ተቃዋሚዎች፣ በንዴት የታጀበ አስተያየት በኢቴቪ ስለሰነዘሩት ነጋዴዎች ወዘተ--- ብዙ ቁም ነገሮችን፣ ወሬዎችን፣ ሃሜቶችን -- እንደ ጉድ አልነው - በጃምቦ ድራፍታችን እያወራረድን፡፡ ደህና ቆይተን ቆይተን ችግር የተፈጠረው መቼ መሰላችሁ? ካድሬው ወዳጄ አራተኛ ጃምቦውን ሲያገባድድ ነው፡፡ ድንገት ተነሳና “ሙስና ለምን እንደበዛ ታውቃለህ?” ሲል ጠየቀኝ፡፡

አላውቅም አልኩት (አንተ ንገረኝ በሚል ስሜት!) ምን ገዶት እሱን! እንዲህ አለኝ፤ “ሙስናውን ያመጣው እኮ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ነው!” ቃል ሳልተነፍስ ከአጠገቡ ተነስቼ ወጣሁ - የስምንት ጃምቦ ዕዳ አሸክሜው፡፡ (እንደ ጥፋቱማ የስምንት በርሜል መክፈል ነበረበት!) አይገርማችሁም … ሙስና የዕድገት ውጤት ሲሆን! “ኑሮ ተወደደ” ሲባል “የኢኮኖሚ ዕድገቱ ያመጣው ነው”፤ “ኔትዎርክ የለም” ስንል “የዕድገት ውጤት ነው” እንዴ --- ዕድገት ይሄ ሁሉ መዘዝ ካለበት ለምን ጦሳችንን ይዞት አይሄድም፡፡ ይሄውላችሁ … የትራፊክ አደጋ በዛ ስንልም እኮ የዕድገት ውጤት ነው ልንባል ነው፡፡ የእናቶች ሞት ጨመረ ስንልም እንዲሁ ማለት ነው፡፡ እኔ የምለው---ሁሉም አገራት ያደጉት በዚህ የመከራ ሂደት ውስጥ አልፈው ነው እንዴ? (ልማታዊ መንገድ እኮ ጉድ አፈላ!) እናንተ … በገዢው ፓርቲ አባላት የተሞላው ፓርላማ ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ ደፋር የሆነው? (ሰርጐ ገብ ቡድን ገባ እንዴ?) የፓርላማ አባላቱ ስንቱን ቱባ ቱባ የመንግስት ባለስልጣን መሰላችሁ ሲያፋጥጡ የሰነበቱት! አንድ የፓርላማ አባል ስለ ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስተያየት ሲሰጡ “ኮሚሽኑ ጥርስ እንዳለው አሳይቷል” ብለው ነበር፡፡ እኔ ደግሞ “ፓርላማው ጥርስ እንዳለው አስመስከረ!” ብያለሁ - ለራሴ፡፡ ከምሬ ነው … እንደ ድሮ አጨብጭቦና እጅ አውጥቶ መለያየት ቀረ እኮ! (እንኳን ፈጣሪ ገላገለን!) ባለፈው ጊዜ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ለፓርላማ ሪፖርታቸዉን ካቀረቡ በኋላ ከግራና ከቀኝ እንዴት በጥያቄ እንዳፋጠጧቸው አልነግራችሁም፡፡ አንዱ አባል፤ በተወከለበት አካባቢ የኔትዎርክ መቆራረጥ መኖሩን ሲገልፅ፤ ሌላኛው እሱ በተወከለበት አካባቢ ግን ከእነአካቴው ሞባይል እንደማይሰራ ተናገረ፡፡

(ምን ያድርግ ሃቅ ነዋ!) ሃላፊው ታዲያ ምናቸው ሞኝ ነው፡፡ ጥያቄው እንኳንስ በእሳቸው የስልጣን ዘመን በተተኪው ትውልድም መልስ የሚያገኝ ስላልመሰላቸው ስለ ቴሌኮም ማውራቱን ትተው ስለ አገሪቱ ዕድገት መስበክ ጀመሩ፡፡ (ክሊሼ እኮ ነው!) “ምስቅልቅሎች ይኖራሉ፤ ግን የዕድገት ምስቅልቅሎች ናቸው!” አሉን ሚኒስትሩ፡፡ (አዲስ ነገር ግን አልነገሩንም!) እኔ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ከሁለቱ “ጉልቤ” የመንግስት ድርጅቶች የሚገላግለን እናገኝ ይሆን? እንግዲህ ለኤልፓና ለቴሌኮም ስንል ጫካ አንገባ? እውነቴን ነው … ኤልፓ የዕለት ተዕለት ኑሮአችንን አመሰቃቀለው እኮ! እሱም እንደባልደረባው “ምስቅልቅሉ የዕድገት ምስቅልቅል ነው!” እንዳይለን እሰጋለሁ፡፡ (ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉ ይባል የለ!) ይታያችሁ … በአንድ ከሰዓት በኋላ ብቻ ሦስቴ መብራት እየጠፋብን ነው፡፡ ቴሌኮምም ቢሆን እኮ ብሶበታል፡፡ ቅዳሜ ማታ እዚሁ አዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ ለሚኖር ጓደኛዬ የላክሁት ማሴጅ መቼ ቢደርስ ጥሩ ነው? ማክሰኞ ማታ - በአራተኛው ቀን ማለት ነው፡፡

ለዚህ ለዚህማ እኔው ራሴ እቤቱ ሄጄ መልዕክቱን አደርስለት ነበር (ከመንገድ ትራፊክ የቴሌ ትራፊክ ባሰ እኮ!) የፖለቲካ ወጋችን ችግርና መከራ ብቻ ሆነ አይደለ! ምን ይደረግ? ወደን እኮ አይደለም! እንደውም የችግራችንን ያህል አላመረርንም (ቻይ አድርጐ ፈጥሮናላ!!) በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ግን ፓርላማ ያሳየው ያልተለመደ ድፍረትና ቁርጠኝነት አስደምሞኛል (የምስቅልቅል ዘመን ጀግናችን ብየዋለሁ!) ይሄውላችሁ … የም/ቤት አባላትን ማበረታታት አሁን ነው (የፓርላማው ህዳሴ ሳይጀመር አልቀረም!) እናም ውዳሴ ብቻ ሳይሆን ማበረታቻም ያስፈልጋቸዋል ባይ ነኝ - ኪስ የሚገባ፡፡

ባለ ሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገቱ ለነሱ ደሞዝ ጭማሪ ካልሆነ ምን ፋይዳ አለው? (ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንዲሉ) ግዴለም እነሱ ሚኒስትሮቹን ያፋጡልን እንጂ እኛ በሰላማዊ ሰልፍም ቢሆን ደሞዛቸውን እናስጨምርላቸዋለን። (“እከክልኝ ልከክልህ” ሆነ እንዴ?) በኢህአዴግ ቋንቋ ግን “ሰጥቶ መቀበል” ይባላል፡፡ እናላችሁ ... ፓርላማችን “የዓመቱ ደፋር ተቋም” የሚል ስያሜ እንዲያገኝ ፊርማ ማሰባሰብ ጀምሬአለሁ (ቸኮልኩ እንዴ?) በዚህ ተነሳሽነቴ “ኮምፕሌክስ” ያቃጠላቸው ፀረ ህዝቦች ምን እያሉ እንደሚጠሩኝ ታውቃላችሁ? “ፈጠነች!” (እውነት ፈጥኜ ይሆን እንዴ?) እናንተ በቀደም ጠ/ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 90 ሚሊዮን መሆኑን ሲናገሩ በኢቴቪ ሰምቼ ክው ነው ያልኩት፡፡ እንዴ --- መቼ ተቆጥረን ነው አምስት ሚሊዮን የጨመርነው? የህዝብ ቁጥር “በአስማት!” ይጨምራል ልበል? ግን እኮ ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው ይባላል (ስለ ህዝቡ ከመሪው በላይ የሚያውቅ አለ እንዴ?) ያ ካድሬ ወዳጄ 90 ሚሊዮን መድረሳችንን ቢሰማ ኖሮ ምን እንደሚል ታውቃላችሁ? “የዕድገታችን ውጤት ነው!” (የዕድገት አባዜ ሳይዘው አይቀርም!) እኔ የምላችሁ … የአፍሪካ ህብረትን 50ኛ ዓመት በዓል እንዴት አያችሁት? ኢቴቪ ሰሞኑን የሚያነጋግራቸውን ሰዎች (ነዋሪዎች) ታዝባችሁልኛል፡፡ አንድ ነዋሪ “ህዝቡ በዓሉ መቼ ነው እያለ ነው” ብለዋል - ጉጉቱን ለመግለፅ፡፡

እኔ ግን ለምን ይዋሻል? ብያለሁ፡፡ ሌላ ነዋሪ ደግሞ “አሁን የአፍሪካ ቀንድ እንደሆንን የዓለምም ቀንድ መሆን አለብን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አንዲት ወጣት እንዲሁ “ወጣቱ መቼ ነው በዓሉ እያለ ነው!” ስትል ትንሽ ማጋነን የታከለበት በፕሮፖጋንዳ የታሸ አስተያየት ሰጥታለች፡፡ ከሁሉም ምን እንዳስደነቀኝ ታውቃላችሁ? ኢቴቪ ከበዓሉ ጋር በተገናኘ ባዘጋጀው ፕሮግራም፤ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ያከናወኗቸው ድንቅ ድንቅ ሥራዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲነገርላቸው መስማቴ ነው፡፡ (አምላክ ወረደ ብያለሁ) ቢያንስ ቢያንስ የአፍሪካ አንድነት መስራችነታቸው፣ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው፣ ለአገራቸው ዘመናዊ አስተዳደርን እንዳስተዋወቁ፣ በአገሪቱ የመጀመሪያውን ዩኒቨርስቲ እንደከፈቱ ወዘተ-- ተገልፆላቸዋል (ኧረ ይበቃቸዋል!) እኔማ…እንኳንም የአፍሪካ 50ኛ ዓመት በዓል መጣ ብያለሁ (ያልተዘመረላቸው ንጉስ ተዘመረላቸዋ!) ኢቴቪም ያለፈውን መንግስት ሁሉ ከመጣው ጋር ሆኖ ከማውገዝ አባዜው መላቀቁ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ (የአንድ ሺ ኪ.ሜትር ጉዞ የሚጀመረው በአንድ እርምጃ ነው እንዲሉ!) እኔ የምላችሁ ግን የተባበረች የአፍሪካ መንግስት (The United States of Africa) ይመሰረታል የሚባለው ከምር ነው እንዴ? ነፍሳቸውን ይማረውና አምባገነኑ የሊቢያ መሪ የጋዳፊ ቅዠት መስሎኝ ነበር እኮ! መተባበሩና አንድ አፍሪካ መመስረቱ ባልከፋ ነበር … መጀመሪያ ግን እርስበርስ መግባባት አይቀድምም ትላላችሁ? እንደ አገር ሳንስማማ 53 አገራት ደባልቀን ጉድ እንዳይፈላ! አንዳንድ ህልሞች ከምድጃ ውስጥ ሳይበስሉ ይወጡና “ሊጥ” መብላት ይመጣል፡፡

እናም ለትንሽ ጊዜ እዚያው ኦቭን ውስጥ ቢቆይና ቅንብር እስኪል ቢበስል ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ ለምን መሰላችሁ? አፍሪካ እኮ ገና ናት! (እንደሚወራው አይምሰላችሁ!) ፕሮፌሰር ተስፋፅዮን መንግስቱ የተባሉ ምሁር ስለ አፍሪካ ለኢቴቪ በሰጡት አስተያየት ምን አሉ መሰላችሁ? “አፍሪካ ድሃ የሆነችው በአስተዳደር ችግር ነው - በመሪዎቿ!” (የነገሩን ስስ ብልት አግኝተውታል!) ፕሮፌሰሩ ሌላም አንጀት የሚያርስ ነገር ተናግረዋል፡፡ “አፍሪካ ምን ሰርተን እንሙት የሚሉ መሪዎች ያስፈልጓታል” (“ምን በልተን እንሙት” ባዮቹ በዙኣ!) አያችሁ…የአፍሪካ መስራች አባቶች (Founding Fathers) ህልም እውን ከመሆኑ በፊት የመሰረት ሥራው ተጠናክሮ መሰራት አለበት - በጥሩ ግንበኛ፡፡ ያለዚያ ግን “መክሸፍ እንደ አፍሪካ ታሪክ” ልንል ነው፡፡ እኔ የምለው ግን የተባበረችው አፍሪካ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ማነው የሚሆነው? እርግጠኛ ነኝ ኩዴታ የሚባል ነገር አይኖርም (ማነው ያለው እንዳትሉኝ!) ለማንኛውም ግን Happy Anniversary ብያለሁ - ለአፍሪካ 50ኛ ዓመት!! ወደፊት ትመሰረታለች ለተባለችው The united States of Africa የአንጋፋዋ ድምፃዊት የሂሩት በቀለን ዘፈን መርጬላታለሁ፡፡ (ግጥሙ በእንስት ፆታ ነው የቀረበው - ለአፍሪካ እንዲመች!) “ዝናቡም ዘነበ ደጁም ረጠበ ትመጫለሽ እያልኩ ልቤ እያሰበ እስኪ መጥተሽ ልይሽ እንዳሉሽም ሆነሽ ቆንጆ ነሽ ይላሉ ማን አየሽ ማን አየሽ!!”

Read 3788 times