Saturday, 01 June 2013 12:51

ነጋዴዎች የዓመቱን ግብር በሁለት ወራት እንዲያጠናቅቁ ማሳሰቢያ ተሰጠ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

“ሙስናን የሚያስተምረው ራሱ ገቢዎችና ጉምሩክ ነው” - ነጋዴዎች አብዛኛው ነጋዴ በፍርሃት ከአገር እየወጣ ነው ለነጋዴው ግዴታው እንጂ መብቱ አይነገረውም ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ትላንት ረፋዱ ላይ ባደረገው ውይይት ሙስናን ለነጋዴው የሚያስተምረው ገቢዎችና ጉምሩክ እንደሆነ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ተናገሩ፡፡ በአዲስ አበባ የስብሰባ ማዕከል በተደረገው እና በገቢዎችና ጉምሩክ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ሥራ አስኪያጅ በአቶ አሰፋ ወሰን አለነ፣ በባለስልጣኑ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በአቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ እና በባለስልጣኑ የለውጥና ሞደርናይዜሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በአቶ አብርሃም ንጉሴ አወያይነት በተካሄደው ውይይት ነጋዴዎች በሰጡት አስተያየት፤ “የጉምሩክ ሠራተኞች በራስ መተማመን የላቸውም፣ በየደረጃው ውሳኔ የመስጠት አቅም አጥተዋል፣ መረጃ ፈጥነው ለመስጠት ይቸገራሉ” በማለት ይህም ለነጋዴውም ሆነ ለአገሪቱ ከፍተኛ ጉዳት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአገሪቱ እጅግ በርካታ መልካም ፖሊሲዎች ቢኖሩም አፈፃፀም ላይ በጣም ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው የገለፁት ነጋዴዎቹ፤ እነዚህ የአፈፃፀም ችግሮች ለሙስና በር ከፋች በመሆናቸው መጀመሪያ መጥራትና መጠረግ ያለበት እዛው ገቢዎችና ጉምሩክ ውስጥ ያለው አቧራ ነው ብለዋል፡፡ “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዕቃ ግዢ ፈጽመን ደረሰኝ ብንጠይቅ ሊሠጠን ባለመቻሉ ስንከራከር ገቢዎችና ጉምሩክ ሄደህ ክሰሳ እንባላለን፤ እነዚህ ሰዎች ገቢዎችና ጉምሩክ የሚሠራ ተባባሪ እንዳላቸው ግልጽ ነው” ያሉት አንድ ከፍተኛ ግብር ከፋይ፤ ይህን ሁሉ እየተመለከትን ነጋዴ መሆናችንን እየጠላ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር ግብር በአጭር ጊዜ መሰብሰቡንና ለዚህም ውጤት አሁን ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የባለስልጣኑ ዳይሬክተሮች ትጋት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያወሱት ሌላ ከፍተኛ ግብር ከፋይ በበኩላቸው፤ እኒህ ግለሰቦች በጥፋት ተጠርጥረው በታሰሩበት ወህኒ ቤት ድብደባና እንግልት መፈፀሙ በጣም እንደሚሰቀጥጣቸው ተናግረዋል፡፡ ነጋዴው አክለውም “ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለም፣ ሙስና በጣም ያሳስታል፣ አጥፍተውም ይሆናል፤ ነገር ግን ውለታቸው መዘንጋት ስለሌለበት በእስር ላይ እያሉ መብታቸው ሊከበር ይገባል” ካሉ በኋላ በጥፋታቸው አይቀጡ ማለቴ አይደም ብለዋል፡፡

“እግር ኳስን እንመልከት፤ ይሄ ሁሉ ብር እየወጣባቸው አንዴ እንኳ አሸንፈው አያውቁም፤ የመብራት ነገርም እንደዛው ነው” ያሉት ግብር ከፋዩ፤ ትንሽ ጥፋት ሲያጠፉ ከፍተኛ ልምድ እና እውቀት ያላቸውን ከጥፋታቸው አርሞ እንደመመለስ፣ ከስራ እያስወገዱ በአዳዲስ መተካት ለዚህች አገር ከፍተኛ ጉዳት እንደሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ እቃዎች ላይ፣ በዲቪደንት ፈንድ እና በሲሚንቶ ሥራ ላይ ስለተከሰተው ችግር ሰፊ ሃሳብ ያቀረቡት ሌላው ከፍተኛ ግብር ከፋይ፤ በታክስ ስርዓት ላይ ህጐች ሲወጡ ወደፊት ሊያመጣ የሚችለው ተጽእኖ ተገምቶ መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ የወጡት ህጐችም ቢሆኑ ጥሩዎቹ ቀጥለው የማያሰሩት መወገድ አሊያም መከለስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ “ህገ-ወጦች ወደ ሙስና ሲሮጡ እናንተ የምትከታተሉት ግን ህጋዊ ነጋዴዎቹን ነው” ያሉት ሌላው ነጋዴ፤ ህጋዊው ምን እንደሚሸጥ፣ እንዴት እንደሚሸጥ፣ ገቢና ወጪው ምን እንደሆነ ስለምታውቁ ከዚያ ዝንፍ እንዳይል ትከታተላላችሁ” ብለዋል፡፡ ህገ -ወጦች ግን አካሄዳቸው የጨለማ ስለሆነ እነሱን አትከታተሉም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

ነጋዴውን ወደ ታክስ ሥርዓቱ ማስገባቱ አስፈላጊ ቢሆንም ወደ ታክስ እንዲገባ የተደረገበት መንገድ በጣም የተሳሳተ መሆኑን የተናገሩት ሌላ ተሳታፊ ነጋዴ፤ ገቢዎችና ጉምሩክ የመንግስት ሠራተኛን የአገር ተቆርቋሪ፣ ነጋዴውን ደንታ ቢስ አድርጐ እየፈረጀ በመቆየቱ በባለስልጣኑና በነጋዴው መካከል ከፍተኛ ክፍተት ተፈጥሮ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ባለስልጣኑ ግብርን በጉልበት ለማስገበር ነጋዴውን ሲያስር እና ሲያንገላታ የነበረበት መንገድ በባለስልጣኑ ላይ ጥላቻን ዘርቶ እንደነበር የገለፁት እኚህ ነጋዴ፤ ኦዲተሮቹም የባለስልጣኑም ሠራተኞች ጉልበተኞች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ “ነጋዴው ለኦዲት የሚያቀርበው ትክክለኛ ሂሳብ እንኳን ቢሆን እኔ ካላመንኩበት አልቀበልም እስከማለት መብት አላቸው” ያሉት ነጋዴው፤ ይህ የሚያሳዝንና ነጋዴው ከዘርፉ እንዲወጣ የሚገፋፋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ነጋዴው አክለውም ምን ያህሉ ኦዲተሮች ንፁህ እንደሆኑም አላውቅም ብለዋል፡፡

ነጋዴው ለፍቶና ጥሮ ባመጣው ሀብት አጭበርብረሃል እየተባለ በመሆኑ አብዛኛው ነጋዴ ለድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ እየቀጠረ በፍርሃት ከአገር እየወጣ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡ በግብር ከፋዩና ሰብሳቢው መካከል እንዲሁም በግብር ሰብሳቢው ሥራ አስፈፃሚዎችና በበላይ ባለስልጣናት መካከል የመረጃ ክፍተት መኖሩን፣ መረጃ በጽሑፍ ከሚሰጥበት በቃል የሚሰጥበት ጊዜ መብዛቱን፣ ለነጋዴው በአብዛኛው የሚነገረው ግዴታው እንጂ መብቱ አለመሆኑን የጠቆሙት ሌላው ከፍተኛ ግብር ከፋይ፤ መረጃ ከጽሑፍ ይልቅ በቃል መሰጠቱ ለሙስና ከፍተኛ በር እንደሚከፍት ገልፀው፤ ባለስልጣኑ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የኢ-ታክስ ሲስተም መዘርጋቱ መልካም መሆኑን፣ ነገር ግን መረጃ የመቀበል አቅሙ አነስተኛ በመሆኑ መላ ሊፈለግለት እንደሚገባም በውይይት መድረኩ ተነስቷል፡፡

አንድ ነጋዴ ኦዲት ለማስደረግ ወደ ኦዲተር ሲቀርብ በዶክመንቶቹ ላይ ክፍተቶች ካሉ “ይሄ ይሄ በዚህ ይስተካከል” ብሎ ኦዲተሩ በመግለጽ ነጋዴው አስተካክሎ እዛው መክፈል ሲገባው “ይሄ ትክክል አይደለም” ተብሎ እንዲመለስ እየተደረገ የዘጠኝና የአስር አመት ውዝፍ ግብር ክፈል እያሉ ነጋዴውን ማስጨነቅ አግባብ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡ ገቢዎችና ጉምሩክ አንድን ድርጅት ደውሎ በ10 ቀን ውስጥ ኦዲት ስለምትደረግ ተዘጋጅ ማለቱ አግባብ እንዳልሆነ በመጠቆምም በስልክ የሚተላለፍ ትዕዛዝ ለሙስና ድርድር በር እንደሚከፍትና ባለስልጣኑ በደብዳቤ ማሳወቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ “አንዳንዴ ችግሮች ሲፈጠሩ ግብር ይግባኝ ለመሄድ የግብሩን 50% ማስያዝ ይጠበቅብናል” ያሉት ሌላው ግብር ከፋይ፤ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የሚከፍሉት ከፍተኛ ስለሆነ የዛን ግማሽ ማስያዝ ይከብዳቸዋል፡፡ ለዚህም ወደ ¼ኛ ዝቅ ቢል የተሻለ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሌላው ግብር ከፋይ በባለስልጣኑ ፕሮፌሽናል ሰዎች እንደሌሉ ጠቁመው “እኔ ካሽ ሬጅስተር ማሽን ይዤ ስሄድ የምን ብረት ነው ያለኝ ሰው አጋጥሞኛል” ካሉ በኋላ፤ ባለስልጣኑና ግብር ከፋዩ እንዲናበብ በየቦታው የተሰጣቸው ሃላፊነት የሚመጥኑ ፕሮፌሽናል ሰዎች ሊመደቡ ይገባል ብለዋል፡፡ የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት የስራ ሃላፊዎች ከተወያዮቹ ለተነሱት አስተያየቶችና አንዳንድ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን እስካሁን የዚህን አመት ግብር ያልከፈሉ የከፍተኛ ግብር ከፋይ ነጋዴዎችም በቀሪዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ አጠናቀው እንዲፍሉ አሳስበዋል፡፡ በተወያዮቹ ከህግ እና ከአመራር አኳያ የተነሱትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ የባለስልጣኑ የሥራ ሃላፊዎች ክፍተቶቹ መኖራቸውን አምነው በዘላቂነት ችግሮቹን ለመቅረፍ የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከነዚህ የማሻሻያ ስራዎች መካከልም የህግ ዝግጅቶችም በዋናነት እንደሚካተቱ የጠቆሙት ሃላፊዎቹ፤ በቅርቡ የጉምሩክ ህግን ባለስልጣኑ አዘጋጅቶ በመጨረስ ወደ አጽዳቂው አካል ለመምራት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይም በገቢ ዘርፍ የሚታዩ የአሠራር ጉድለቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ገቢን የተመለከቱ አንቀፆች ብቻ የተካተቱበት ህግ ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑንና በዝግጅቱ ወቅት ነጋዴዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉበት ተመልክቷል፡፡ ዲቪደንት ታክስን በተመለከተ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የስራ ሃላፊዎቹ፤ ከዚህ በፊት ግማሹ ነጋዴ እየከፈለ ቀሪው ሳይከፍል መቆየቱን ታሳቢ በማድረግ ሁሉንም ዜጋ በእኩል ለማገልገል ከሚል እሣቤ ሳይከፍሉ የቆዩት እንዲከፍሉ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አመልክተው፤ የክፍያ አፈፃፀሙንና ሂደቱን በተመለከተ ከደንበኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎች በአስተዳደራዊ እርምጃ የሚፈቱበት መፍትሔ አማራጭ መቀመጡን አስታውቀዋል፡፡ ከነዚህ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መካከልም የተከማቸ ግብር ከሆነ ደንበኛው በረጅም ጊዜ እንዲከፈል እንዲሁም ቀደም ሲል ቅጣትና ወለድ መጨመር አለበት ተብሎ የነበረው ቀርቶ ያለባቸው እዳ ብቻ ተሰልቶ ከወለድና ቅጣት ነፃ በሆነ መልኩ እንዲከፍሉ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ከዚህ ባለፈ አንከፍልም ለሚሉት በህጉ አግባብ ባስልጣኑ እርምጃዎች ይወስዳል ብለዋል - ሃላፊዎቹ፡፡ የስራ ሃላፊዎቹ በሙስና ተጠርጥረው ስለተያዙት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ባለሀብቶች እንዲሁም የተለያዩ ስራ ሃላፊዎች ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ መሆኑን በመጥቀስ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ በባለስልጣኑ የአመራር ቦታ አዳዲስ ሰዎች ሲሾሙ ለስራ ሂደቱ እንግዳ ስለሚሆኑ በአሰራሩ ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ለቀረበው አስተያየትም፣ በፀረ ሙስና ኮሚሽን እርምጃው ከተወሰደ በኋላ ወደ መስሪያ ቤቱ የመጣ አዲስ የስራ ሃላፊ አለመኖሩን ያመለከቱት የስራ ሃላፊዎቹ፤ መንግስትም በቀድሞ ሃላፊዎች ምትክ ለመሾም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በነጋዴዎች የተሰጡት አስተያየቶችም በቀጣይ ለሚሠሩት ስራዎች ግብአት ይሆናሉ ተብሏል፡፡ የስራ ሃላፊዎቹ በውይይቱ ሁለተኛ አጀንዳም በባለስልጣኑ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ 865 ከፍተኛ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ገልፀው፤ በ2005 ዓመት ከነዚህ ግብር ከፋዮች ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው 35 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን 28 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንና በቀጣይም እያንዳንዱ ግብር ከፋይ የሚጠበቅበትን ግብር በግንቦትና በሰኔ ወር ከፍሎ እንዲጨርስ አሳስበዋል፡፡

Read 3129 times