Print this page
Saturday, 01 June 2013 14:05

አርቲስት ፈቃዱን በባንኮክ ለማሳከም ርብርቦሹ ቀጥሏል *ለህክምናው 450 ሺ ብር ያስፈልጋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በነርቭ ሕመም እየተሰቃየ ለሚገኘው አርቲስት ፍቃዱ አያሌው የሕክምና ገንዘብ ለማሰባሰብ ታስቦ ባለፈው ግንቦት 16 የተከፈተው የስዕል አውደርእይ እስከ ፊታችን ረቡዕ እንደሚቀጥል አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ አርቲስቱን በባንኮክ ለማሳከም 450ሺ ብር እንደሚያስፈልግ ታውቋል፡፡ አርባ አርቲስቶች ሥራቸውን በአውደርእዩ አሳይተው ሽያጩን በቀጥታ ለሰዓሊው መታከሚያ ለማዋል አቅደው የነበረ ሲሆን አሁን የአርቲስቶቹ ቁጥር 68 መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአውደርዕዩ ላይ ከሚሳተፉ አንጋፋና ወጣት ሰዓሊያን መካከል ዘርይሁን የትም ጌታ፣ ታደሰ መስፍን፣ መዝገቡ ተሰማ፣ ወርቁ ጐሹ፣ ብርትኳን ደጀኔ፣ ሮቤል ተመስገን፣ ሃይሉ ክፍሌ ይገኙበታል፡፡ በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡ ስእሎች ከአንድ ሺህ እስከ አስራ አምስት ሺህ ብር በመሸጥ ላይ እንደሆኑ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ ሥነጥበባትና ዲዛይን ትምህርት ቤት የ2001 ዓ.ም የከፍተኛ ማእረግ ተመራቂ የሆነውን አርቲስት ፍቃዱ አያሌውን ባንኮክ፣ ታይላንድ ለማሳከም ከ450ሺህ ብር በላይ የተጠየቀ ሲሆን ይህንኑ ከግምት በማስገባት አውደርእዩ የተዘጋጀበት የአዲስ አበባው ጣይቱ ሆቴል ባለቤቶች በቀን ሁለት ሺህ ብር ይከራይ የነበረውን አዳራሽ ለ12 ቀናት በነፃ ፈቅደዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከጀርመን የልማት ተቋም (GIZ) ድጋፍ ተጠይቆ ምላሽ እየተጠበቀ ሲሆን ሰዓሊው ከእለት ወደ እለት ህመሙ እየጠናበት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ሠዓሊ ፍቃዱን መርዳት የሚፈልጉ በስልክ ቁጥር +2510919193132 እና +251911635840 ደውለው መርዳት እንደሚችሉ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡

Read 3380 times
Administrator

Latest from Administrator