Saturday, 01 June 2013 14:12

ጊዮርጊስ በካይሮ ኢኤንፒፒአይን ይገጥማል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ካፕ የምድብ ድልድል ለመግባት ነገ በካይሮ የግብፁን ኢኤንፒፒአይ ሊፋለም ነው፡፡ ጊዮርጊስ ከሜዳ ውጭ በሚያደርገው በዚህ ወሳኝ ጨዋታ አቻ መለያየት እና በማናቸውም ውጤት ማሸነፍ የሚበቃው ሲሆን በኢኤንፒፒአይ 1ለ0 ቢሸነፍ እና በ1 የግብ ልዩነት ቢረታ እንኳን ጥሎ የማለፍ እድልን ይዟል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ የምድብ ድልድል ለመግባት በያዘው እቅድ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ሳይካለት ቢቀርም በኮንፌደሬሽን ካፑ እንደሚያካክስ ተስፋ ተደርጓል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በኮንፌደሬሽን ካፕ ጥሎ ማለፉ የመጀመርያ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ጊዮርጊስ 2ለ0 ኢኤንፒፒአይን እንዳሸነፈ ይታወሳል፡፡ ለጊዮርጊስ ወሳኝ እና ምርጥ ሁለት ጎሎችን ከመረብ ያዋሃዱት ደግሞ በ4ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ እና በ27ኛው ደቂቃ አበባው ቡጣቆ ናቸው፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ማይክል ክሩገር ለካፍ ኦንላይን በሰጡት አስተያየት ‹‹በሜዳችን የገጠምነው ኢኤንፒፒአይ ጥሩ ፉክክር እና ጥንካሬ አሳይቷል፡፡ እኛም ባስመዘገብነው ውጤት ወደፊት ለመጓዝ የምንችልበትን በራስ መተማመን ጨምረናል፡፡ በመልሱ ጨዋታ ከተጨዋቾቼ ታሪካዊ ውጤት እጠብቃለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም በግብፁ ክለብ ዛማሌክ ላይ በሻምፒዮንስ ሊግ እንዲሁም በኮንፌደሬሽን ካፑ ጥሎ ማለፍ በሌላው የግብፅ ክለብ ኢኤንፒፒአይ ላይ ሁለት ምርጥ ጎሎችን ያገባው ሽመልስ በቀለ በበኩሉ‹‹ ወደየምድብ ድልድል የምንገባበት ጥሩ ደረጃ ይዘናል፡፡

በዛማሌክ ከደረሰብን ሽንፈት ተምረናል፡፡ ውጤታችንን ለማስጠበቅ እንፈልጋለን›› በማለት ለካፍ ድረገፅ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ የኢኤንፒፒአይ ወሳኝ አጥቂ አህመድ ራውፍ በበኩሉ አልሃራም ለተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት‹‹ በጊዮርጊስ የተሸነፍንበትን 2ለ0 ውጤት ቀልብሰን ወደ የምድብ ድልድል እንገባለን፡፡ ማንኛውን ከኢትዮጵያ የመጣን ቡድን በካይሮ ማሸነፍ የማይቻል ነገር አይደለም›› ብሏል፡፡

Read 2103 times