Print this page
Saturday, 01 June 2013 14:19

..ሴት መሆንና በእድሜ መግፋት ለጡት ካንሰር.....

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ስለተለያዩ በሽታዎች ንቃተህሊና ተፈጥሮ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲኖር ወይንም ስለበሽታዎቹ ትኩረት ተሰጥቶ ተገቢው ሕክምና እንዲደረግ ለማሳሰብ የተለያየ ቀለም ያላቸው ሪቫኖች አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ፒንክ ሪቫን ነው፡፡ ፒንክ ሪቫን ኣለም አቀፍ እውቅና ያለው በጡት ካንሰር ላይ ንቃተህሊናን እንዲፈጥር ታልሞ የተሰራ ልዩ ምልክት ነው፡፡ ይህ ሪቫን ለእይታ ሲቀርብ ወይንም ስለሪቫኑ ሲነገር በጡት ካንሰር ለተጠቁ ሰዎች የሞራል ድጋፍ ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡ ፒንክ ሪቫን በስፋት የሚነገርለትና ወደ እይታም ሆነ ወደ ጆሮ በስፋት የሚቀርበውና የሚሰማው የብሔራዊ የጡት ካንሰር ወር በሚከበርበት ወቅት ነው፡፡ ፒንክ ቀለም የተመረጠለት ሪቫን ከጡት ካንሰር ጋር ተቆራኝቶ መልእክት እንዲያስተላልፍ ሲደረግ 22/ ዓመት ሆኖታል፡፡ በዚያን ጊዜ መቀመጫውን በኒውዮርክ ከተማ ያደረገው ሱዛን ጂ ኮሜን komen ፋውንዴሽን እ.አ.አ በ1991/የጡት ካንሰር በሽታን ተቋቁመው ከበሽታው ነፃ መሆን ስለቻሉ ሰዎች የተዘጋጀ ውድድር ላይ ለተሳታፊዎች ሪቫኑ ከተበተነ በ ት ቀን ወዲህ ሪቫኑን መጠቀም ልማድ ሆኖ ቀርቷል፡፡

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ፒንክ ሪቫን እ.ኤ.አ በ1992 ወይንም ከ21 ዓመታት በፊት ሰፊ እውቅና ተሰጥቶት የብሔራዊ የጡት ካንሰር ንቃተ ህሊና መፍጠሪያ ልዩ መለያ መሆን ችሎአል፡፡ የኤችአይቪ ኤይድስ ምልክት ከሆነው ቀይ ሪቫን ሐሳብ ተወስዶ ለጡት ካንሰር የተሰራው ፒንክ ሪቫን አሌክሳንድራ ፔኒ እና ከጡት ካንሰር በሽታ አገግማ ለመዳን በበቃችው ኤቭለን ላውደር ምክንያት ተፈጥሮ በመላው ኒውዮርክ እንዲሰራጭ ትላልቅ ለሆኑ የኮስሞቲክስ ኩባንያዎች ተሰጥተዋል፡፡ አሌክሳንድራ የሴቶች ጤናን አስመልክቶ በሚዘጋጀው የ..ሰልፍ.. መጽሔት ዋና አዘጋጅ ስትሆን ኤቭለን ደግሞ የ..ኤስ ላውደር.. ኮስሞቲክስ ኩባንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ናት፡፡

ፒንክ ሪቫን ከሰማያዊ ሪቫን ጋር አብሮ ሲደረግ አጋጣሚው በጣም ጥቂት ቢሆንም በወንዶች ላይ ስለሚከሰተው የጡት ካንሰር አመላካች ይሆናል፡፡ ከ17/ ዓመታት በፊት የጆን ደብሊው ፋውንዴሽን መስራችና ፕሬዚዳንት የሆኑት ናንሲኒክ ሪቫኑን በሁለት ቀለም አቀናጅተው ሲፈጥሩ ..ወንዶችም የጡት ካንሰር ይይዛቸዋል.. የሚለውን ነጥብ ለማሳሰብና ግንዛቤውንም ለመፍጠር ሲሉ ነው፡፡ የፒንክ ሪቫን ቀለም ፒንክ የሆነበት ምክንያት ምእራባውያን አገሮች በሰነጾታ የሴቶች ተሳትፎን የሚገልጹበት በመሆኑ እና ቀለሙ ሴቶችን ስለመንከባከብ እንዲሁም ቆንጆ መሆንን ስለሚያመላክት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፒንክ ቀለም ጥሩ መሆንንና ተባባሪ መሆንን ይገልጻል ተብሎም ይታመናል፡፡ ፒንክ ሪቫን ሲወሳ ፡- በጡት ካንሰር ላለመያዝ መጠንቀቅ፣ በበሽታው የተያዙ ለወደፊቱ ተስፋ እንዲያደርጉና የጡት ካንሰር በሽታን ለማጥፋት ንቅናቄ እንዲደረግ ያሳስባል፡፡

በጡት ካንሰር ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ተቋማት ስራቸውን ከጡት ካንሰር ጋር ይበልጥ ለማቆራኘት ፒንክ ሪቫንን ይጠቀሙበታል፡፡ ፒንክ ሪቫንን ፡- መግዛት፣ ማድረግ ወይንም ለእይታ ማብቃት ...ሪቫኑን የያዘው ሰው ወይንም ተቋም ስለሴቶች ያላቸወን ጥንቃቄና እንክብካቤ ያሳያል፡፡ በየአመቱ ጥቅምት ወር ላይ በሺዎች ወይንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ምርቶች በፒንክ ሪቫን ይወከላሉ ወይንም ደግሞ ፒንክ ቀለም እንዲኖራቸው ይደረጋሉ፡፡ በተጨማሪም ከምርቶቹ ሽያጭ ከሚገኘው ገቢ የተወሰነውን ስለጡት ካንሰር ስለሚደረግ ምርምርና ስለበሽታው ስለሚኖረው የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ እንዲውል ይደረጋል፡፡ የዛሬ ሰባት አመት 15/ሺህ ከብር የተሰሩ ሳንቲሞች ሮያል ካኔዲያን ሚንት የተሰኘው የካናዳ ሳንቲም አምራች ተቋም ሰርቷል፡፡ የሳንቲሞቹ አንደኛው ጎን የንግስት ኤልሳቤጥ ምስል የተቀረጸበት ሲሆን በሌላኛው ጎኑ ደግሞ ሪቫን ተቀርጾበታ፡፡

በዚህ ብቻ ያልተገታው የፒንክ ሪቫን ሳንቲሞች ስሪት የ25/ሳንቲም ዋጋ ያላቸው 30/ሚሊዮን ሳንቲሞች በአንዱ ጎናቸው ፒንክ ሪቫን ተቀርጾባቸው ለተለመደው የግብይት ስርአት እንዲውሉ ተሰራጭተዋል፡፡ በአንድ ጎኑ ቀለም ያለው ሳንቲም ሲቀርብ ፒንክ ሪቫን በታሪክ ሁለተኛው እንደሆነ ይነገራል፡፡ የጡት ካንሰርን በሚመለከት ስላለው አለም አቀፍ እውቅና ይህንን ህል ካልን የጡት ካንሰርን አመጣጥና ሕክምናውን ለአንባቢዎች ባልንበት ባለፈው እትም ዶ/ር አበበ በቀለ እንደገለጹት ሕመሙ በኢትዮጵያ ውስጥ መታከም የሚችል ሲሆን ነገር ግን ሕክምናው ውስን በሆነ ሆስፒታል መሰጠቱ አንዱ ጎጂ ነገር ነው፡፡ የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ጎጂ ወይንም ገዳይ ነው የሚለውን ለመገመትም አስቸጋሪ የሚሆኑ ነገሮች እንደሚኖሩና ለዚህም እንደማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ብዙ ሰዎች ሕክምናውን በአቅራቢያቸው ስለማያገኙ እና ሕመሙም ወደተቀረው የሰውነት ክፍላቸው ከመሰራጨቱ አስቀድሞ እርምጃ የማይወስዱ ብዙዎች መሆናቸው ነው ብዋል፡፡

ዶ/ር አበበ በቀለ አክለው እንደገለጹትም ጡት ላይ ያበጠ ነገር ሁሉ ካንሰር አለመሆኑን ነው፡፡ ሰዎች በዚህ መደናገጥ አይገባቸውም፡፡ ሆኖም ግን ያበጠ ነገር ባእድ መሆኑን ካለመዘንጋት በፍጥነት ወደሐኪም ዘንድ መቅረብ ይጠቅማል፡፡ ጉዳዩ ከሐኪም ዘንድ ከደረሰ በሁዋላ ካንሰር ነው አይደለም ለማለት በመጠኑ ከእባጩ ሴል ላይ በመርፌ ለምርመራ ይወሰዳል፡፡ ነገር ግን ብዙ ሰዎች ሰውነን መርፌ ከነካው በሽታው ወደሌላ አንሌ ይሰራጨል ከሚል የተሳሳተ ግምት ሕክምናውን እስከነጭርሱም ትተውት ይሄዳሉ፡፡ ይሄ ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ ውሳኔ መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡ ይህ ምርመራ መደረጉ የግድ መሆኑን እና ሰዎች እንደሚሉት አይነት ጉዳት የማያመጣ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ህክምናውን በተገቢው ማድረግ ይገባል፡፡ ምርመራውን ለማድረግ የሚፈጀው ጊዜ ከሁለት ደቂቃ ያልበለጠ ሲሆን ምላሹም በ24 ሰአት ውስጥ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ታማሚዎች ሳይረበሹ ምርመራውን ሐኪም በሚያዘው መሰረት ካካሄዱ መዳን ወይንም እድገቱን በመግታት መቆየት ይቻላል፡፡

ጡት ካንሰር ሁሉንም ሴቶች ወይንም ሰው አይይዝም፡፡ ነገር ግን ሁለት መንገዶች አሉት፡፡ 1/እድሜ፡- ማንኛዋም ሴት ከሰላሳ እና ሳላሳ አምስት አመት በፊት ሲሆናት የጡት ካንሰር እንዲያውም አይታይባትም ማለት ይቻላል፡፡ ከሰላሳ አምስት እስከ 50/ አመት አካባቢ ከሰላሳ ወይንም ከሰላሳ አምስት ሴቶች አንዱዋ ላይ ጡት ካንሰር ይታያል፡፡እድሜ ወደ ሰባ ሰማንያ ሲደርስ ከስምንት ሴቶች አንዷ ላይ የጡት ካንሰር ይከሰታል፡፡ ስለዚህ ሴት መሆንና በእድሜ መግፋት ለጡት ካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ 2/ሆርሞን፡- ሴቶች ላይ ኢስትሮጂንና ፕሮጀስትሮን የተባሉ ሆርሞኖች ይገኛሉ፡፡ የሰውነት ክፍል በብዛት ለኢስትሮጂን እየተጋለጠ ከሄደ ለጡት ካንሰር የመጋለጥ እድሉም የሰፋ ይሆናል፡፡ ኢስትሮጂን በብዛት ያላቸው ሴቶች የወር አበባ ከ13/አመት በፊት የሚያዩ ወይንም የወር አበባቸው ሳይቋረጥ እስከ ሀምሳ እና ሀምሳ አምስት አመት ድረስ የሚቆይባቸው ናቸው፡፡ ልጅ ሳይወልዱ የሚኖሩ ወይንም መጀመሪያ ልጃቸውን ከሰላሳ አመት በሁዋላ የሚወልዱ እንዲሁም ወልደው ጡት ያላጠቡ ሴቶች እና ለተለያየ ምክንያት ኢስተትሮጂንን ለሕክምና ወይንም እንደምግብ የወሰዱ ሴቶች ብዙውን ጊዜ ለጡት ካንሰር ሕመም ይጋለጣሉ ብለዋል ዶ/ር አበበ በቀለ፡፡ ....ባለፈው ሳምንት እትም ዶ/ር አበበ ፈለቀ ተብሎ የተጻፈው ዶ/ር አበበ በቀለ በሚል እርምት እንዲነበብ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡..

Read 4200 times
Administrator

Latest from Administrator