Saturday, 01 June 2013 15:47

ከሥልጣን የተነሱት የፍትህ ሚኒስትር፣ ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው

Written by 
Rate this item
(20 votes)

ከ10 በላይ አቃቤ ህጐችም ይከሰሳሉ ተባለ

በቅርቡ ከስልጣን የተነሱት የፍትህ ሚኒስትር አቶ ብርሃነ ኃይሉና ከአስር በላይ አቃቤ ህጐች በሙስና፣ በሽብርተኝነትና በግድያ ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የተመሰረተን ክስ ያለአግባብ አቋርጠዋል በሚል በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ምንጮች ገለፁ፡፡ ፖሊስ በሚኒስትሩና በአቃቤ ህጐቹ ቢሮ ባካሄደው ከፍተኛ ብርበራ በርካታ መዝገቦችን ማግኘቱንና ለምርመራ መውሰዱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በፖሊስ ብርበራ የተገኙት መዝገቦች ያለአግባብ ተቋርጠው እንዲዘጉ የተደረጉ ክሶች ናቸው ተብሏል፡፡

ተከሳሾች ላይ በቂ ማስረጃ ማቅረብ ካልተቻለ ክሶቹን አቋርጦ መዝገቡን መዝጋት የፍትህ ሚኒስትርና የአቃቤ ህጐች ስልጣን መሆኑ ቢታወቅም ከሙስና፣ ከሽብርተኝነትና ከግድያ ጋር የተያያዙት እነዚህ በፖሊስ ብርበራ የተገኙ ከደርዘን በላይ የሆኑ መዝገቦች ግን፣ በቂ ማስረጃ እያለ፣ ያለ አግባብ የተቋረጡ ናቸው ተብሏል፡፡ ምርመራው ተጠናቆ እንዳበቃ በሚኒስትሩና በአቃቤ ህጐቹ ላይ ክስ እንደሚመሰረትም ምንጮች ጠቁመዋል። ለሰራተኞች አቤቱታ ምላሽ ባለመስጠትና በሥራ ድልድል በደል ፈጽመዋል በሚል ቅሬታ ይቀርብባቸው የነበሩት የፍትህ ሚኒስትሩ፤ በተለይ የጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ይታያሉ የተባሉ ችግሮችን እንዲፈቱ አራት የማሳሰቢያ ደብዳቤዎች ተጽፎላቸው እንደነበር ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በሚኒስትሩ ላይ ከባለጉዳዮችም የተለያዩ ቅሬታዎች ይሰነዘሩ ነበር ያሉት ምንጮች፤ የታራሚዎች የይቅርታ ጥያቄን ማዘግየትና ተገቢ ምላሸ አለመስጠት በዋናነት እንደሚጠቀስ ገልፀዋል፡፡

በቅርቡ በተካሄደው የኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባኤ ላይ ከፓርቲው መሪዎችና አባላት ለሚኒስትሩ የቃል ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው እንደነበር ምንጮች ገልፀው፣ ፓርላማም የመ/ቤቱ በርካታ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ በኢህአዴግ ዘጠነኛ ጉባኤ ላይ የአገሪቱ ዋና ችግር በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የሚታይ እንደሆነ መገለፁ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ሶስት ሚኒስትሮች በወንጀል ተጠርጥረው ከስልጣን የወረዱ ሲሆን፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ከአገር መኮብለላቸው ይታወሳል፡፡

Read 8997 times