Saturday, 01 June 2013 15:50

በሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራና ማስረጃ ማሰባሰቡ ቀጥሏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞብናል አሉ 21 ኩባንያዎች ኦዲት እንዲደረጉ ታዟል የተጠርጣሪዎች ቁጥር 58 ደርሷል በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶች፣ ትራንዚተርና ደላላዎች ላይ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የመርማሪ ቡድን አስቀድሞ በጠየቀው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ የተከናወኑትን ስራዎች ለፍ/ቤቱ ካቀረበ በኋላ ቀሪ የምርመራ ስራዎች እንዳሉት በመግለጽ በድጋሚ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ካለፈው ሠኞ ግንቦት 19 ጀምሮ እስከ ትናንት ግንቦት 23 ቀን ከሠአት በኋላ ሲሠየም የሠነበተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎቱ፤ በአራት መዝገቦች የቀረቡ የተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ሲመለከት ቆይቷል፡፡

ሠኞ እለት በተሠየመው ችሎት ጉዳያቸው የታየው በሁለተኛው መዝገብ የተጠረጠሩት የባለስልጣኑ ም/ዳይሬክተር የነበሩት የአቶ ገብረዋህድ እና የ 11 ግለሠቦች ጉዳይ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በዚህ መዝገብ ላይ የምርመራ ቡድኑ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት እንዲያስረዳ ጠይቆ፤ መሠረት የምርመራ ቡድን አባላቱና አቃቤ ህግ በዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ላይ የተገኙ የሠነድ ማስረጃዎችን መመርመራቸውን፣ ከመኒ ላውንደሪንግ ጋር በተያያዘ ምርመራ መከናወኑን፣ ተጠርጣሪዎቹ አቋርጧቸዋል ከተባሉት 60 መዝገቦች ውስጥ 28ቱ መሠባባቸውን፣ የገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ጋር ያላቸውን የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች መሠብሠቡን፣ ከተለያዩ ባንኮች የአራጣ ብድር የተጠረጠሩበትን ማስረጃዎች፣ ከአራጣ ብድር ጋር ተያይዞ የተቋረጡ የክርክር መዝገቦችን፣ በአንድ ንግድ ድርጅት ላይ ተወስኖ የነበረን 9 ሚሊዮን ብር ግብር ወደ 3 ሚሊዮን የተቀነሠበት የሠነድ ማስረጃ፣ 87 ሚሊዮን ብር ግብር እንዲከፍል ተወስኖበት የነበረን ድርጅት በህገወጥ መንገድ ወደ ስምንት ሚሊዮን ብር ዝቅ እንዲል የተደረገበት የሠነድ ማስረጃ አሠባስበው ማጠናቀቃቸውን አመልክተዋል፡፡

በመርማሪ ቡድኑ ያልተከናወኑ ቀሪ ስራዎች ተብለው ከተዘረዘሩት መካከልም 40 ተጨማሪ መዝገቦችን ማሠባሠብ፣ ለምርመራው አጋዥ የሆኑ ሠነዶችን ከፋይናንስ ተቋማት ማሠባሠብ፣ 8 ኩባንያዎችን ኦዲት ማድረግ፣ የኦዲተሮችን ቃል መቀበል እንዲሁም የተያዙ የሠነድ ማስረጃዎችን የመተንተን ተግባራት የሚሉት የሚገኙበት ሲሆን እነዚህን ተግባራት ለማከናወንም ፍርድ ቤቱ የ14 ቀነ ቀጠሮ እንዲሠጣቸዉ ጠይቀዋል፡፡ የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው፤ ወንጀሉ በጥቅል የተነገረ በመሆኑ ምላሽ ለመስጠት አዳጋች ነው፣ ከዚህ በፊት ያልቀረቡ አዳዲስ ወንጀሎች ተጨምረዋል (እንደሙኒ ላውንደሪንግና የመሣሠሉ)፣ ቀሩ የተባሉት የምርመራ ስራዎች የተጠርጣሪዎቹ በእስር መቆየትን የግድ የማይሉ ናቸው የሚሉትን የመከራከሪያ ነጥብ አቅርበዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹም አስተያየት እንዲሠጡ በተሠጣቸው እድል፤ ጠቅለል ብሎ ሲቀርብ የቤተሠብ፣ የጤና ጉዳይን ጨምሮ ሠብአዊ መብቴ በምርመራ ወቅት ተጥሷል፣ ቃል እስካሁን አልሠጠንም እና የተጠረጠርንበት ወንጀል አልተነገረንም የሚሉ ነጥቦችን አንስተው ተከራክረዋል፡፡

በመዝገቡ አንደኛ ተጠርጣሪ የሆኑት አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ ለችሎቱ ሁለት ህፃናት ልጆቻቸዉ እስካሁን የት እንዳሉ እንደማያውቁ፣ በእሣቸው ምክንያት ቤተሠባቸው መታሠር እንደሌለበት፣ 14 የቦታ ካርታ ተይዟል ተብሎ የተነገረው የመንግስት ሠራተኞችን ሃብት ለማስመዝገብ ተብሎ በኮሚሽኑ እጅ ተመዝግቦ ያለ የተለያየ ሌኬሽኖችን የሚያመለክት አንድ ካርታ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ቀሩ የተባሉ የምርመራ ስራዎች የ14 ቀን ቀጠሮ የማያሠጡ በመሆኑ ቀጠሮው እንዲያጥርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሶስተኛ ተጠርጣሪ የሆኑት አቶ ጥሩነህ በርታ በበኩላቸው፤ የጤና ችግር እንዳለባቸው፣ በምርመራ ወቅት አይናቸውን በጃኬት እየታሠሩና ውሃ እየተደፋባቸው፣ በጥፊ በእርግጫ እየተመቱ መመርመራቸውን እንዲሁም ተለይቶ የተነገራቸው የፈፀሙት ወንጀል እንደሌለ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት በዋስ ይለቀቁ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡ ሌላው በምርመራ ወቅት የሠብአዊ መብት ጥሠት ተፈፅሞብኛል ያሉት የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር ሲሆኑ የልብ በሽተኛ መሆናቸውን በዚህም ሁለት ጊዜ ራሣቸውን ስተው መውደቃቸውን፣ በምርመራ ወቅትም ሠብአዊ ክብራቸውን የሚነካ ተግባራት እንደሚፈፀሙ በመግለፅ “አሁን ሃገሬ ምን እንደምትመስል አውቄያለሁኝ” በማለት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት ምርጥ ታክስ ከፋይ ከተባሉትና እውቅና ካላቸው ነጋዴዎች አንዱ እንደነበሩና 33 ሚሊዮን ብር አውጥተው ፖሊ ቴክኒክ ት/ቤት በማስገንባት፣ ለመንግስት በማስረከብ ሠናይ ተግባራትን ማከናወናቸውን አቶ ነጋ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ሌሎች ተጠርጣሪዎችም አስቀድሞ ከተዘረዘሩት ነጥቦች አንፃር መከራከሪያቸውን አቅርበው የዋስ መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ በተነሡት የመከራከሪያ ነጥቦች ዙርያ ምላሽ እንዲሠጥ በፍ/ቤቱ የታዘዘው የምርመራ ቡድኑ በበኩሉ፤ የወንጀሉ ዝርዝር በተናጥል ይቅረብልን የሚለውን በተመለከተ ወንጀሉ በመተባበርና እርስ በእርስ በመተሣሠር በመመሣጠር የተከናወነ እንጂ በተናጠል የተሠራ ባለመሆኑ በጅምላ ሊቀርብ መቻሉን፣ አዳዲስ ወንጀሎች ተጨምረዋል መባሉም ስህተት እንደሆነና ከዚህ ቀደም በቀረበው ማመልከቻ ህገወጥ ጥቅም ለማግኘት በሚለው ስር የሚጠቃለሉ መሆናቸውን የሚገልፅ ምላሽ የሠጠ ሲሆን ጤናን በተመለከተም በማረፊያ ቤቱ ክሊኒክ አገልግሎቱ እየተሠጠ መሆኑን፣ ሠብአዊ መብት ጥሠት ተፈፅሟል የሚለውም በማስረጃ የተረጋገጠ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም ከወንጀሉ ክብደትና ውስብስብነት አንፃር የ14 ቀን ቀጠሮውን መፍቀዱን፣ ሠብአዊ መብትን በተመለከተ የምርመራ ቡድኑ ክትትል እንዲያደርግ እንዲሁም በቀጣይ ክሡን በግልፅ እና ጠቅላይ ባልሆነ መልኩ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡን ለሠኔ 3/2005 ከሠአት በኋላ ቀጥሯል፡፡ በአዳሪ ተቀጥሮ ረቡዕ ከሠአት በታየው አቶ መላኩ ፋንታን ጨምር 7 ተጠርጣሪዎች የተካተቱበት መዝገብም በተመሣሣይ የመርማሪ ቡድኑ በተሠጠው የ14 ቀን ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት ፍርድ ቤቱ ሠኞ እለት ባዘዘው መሠረት በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ በተናጠል ያቀረበ ሲሆን በአንደኛ ተጠርጣሪ አቶ እሸቱ ወ/ሠማያት፣ 3ኛ ተጠርጣሪ አቶ መርክነህ አለማየሁ እና 4 ኛ ተጠርጣሪ አቶ አስመላሽ ወ/ማርያም መሳተፋቸውን ከዚህ ጋር የተያያዙ ቀሪ ማስረጃዎችም እየሰባሰቡ መሆኑን በፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

በተመሳሳይ 5ኛ ተጠርጣሪ አቶ ከተማ ከበደ፡ 6ኛ ተጠርጣሪ አቶ ስማቸው ከበደ እንደሁም 7ኛ ተጠርጣሪ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ በአራጣ ብድር ምክንያት፣ በቀረጥ ማጭበርበር ተከሰው ጽ/ቤት እንዳይቀርቡ ክሱ እንዲጨናገፍ ምርመራውም እንዳይጣራ አድርገዋል በሚል የተረጠሩ መሆናቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ በእነዚህ ላይ መረጃ የሰባሰበ ሲሆን ሌሎች ያልተሰሩ ስራዎች ብሎ የመርማ ቡድኑ ከጠቀሳቸው መካከልም የግብር እና የታክስ ስወራን ለማጣራት ኩባንያዎችን ኦዲት ማድረግ፣ የበርካታ ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ኦዲት የሚያደርጉትን ባለሙያዎች ቃል መቀበል እንዲሁም የሙስና ምንጮች ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩ የሃብት ምንጮችን የማጥናት ስራ መጀመሩ ይገኝበታል፡፡ “ሁሉም ተጠርጣሪዎች ተባብረው በትስስር የተፈፀመ ወንጀል ስለሆነ በጋራ ማጥራት እንዲሁም እውነቱን አጥርቶ ለማውጣት ጊዜ ወስዶ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት የመርማሪ ቡድን አባላቱ፤ ተጠርጣሪዎቹ እነዚህ ሳይጣሩ በዋስ ቢለቀቁ ባላቸው ሃብት እና ከፍተኛ ስልጣን ተጠቅመው በትስስር ማስረጃዎቹን ሊያጠፉ ይችላሉ በሚል የ14 ቀን ተጨማሪ ቀጠሮ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ በእለቱ ኮማንደር ብርሃኑ አበበ አስተዳደራዊና ሰብአዊ መብትን በተመለከተ በፍ/ቤቱ ሊያብራሩ የቀረቡ ቢሆንም ጽ/ቤቱ ቀደም ባሉት ችሎቶች የተሰጠውን ትዕዛዝ ፖሊስ ወስዶ ይሰራል ብሎ ስለማያምን ማብራራቱ አያስፈልግም ብሏል፡፡

የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን አባላት እና አቃቤ ህግ ካቀረባቸው ነጥቦች አንፃር የመከራከሪያ ነጥባቸውን እንዲያቀርቡ የተጠየቁት አንደኛ ተጠሪጣሪ አቶ መላኩ ፋንታ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት መከራከሪያ፣ የምርመራ ቡድኑ ስርአቱን ተከትሎ ተግባሩን እያከናወነ አለመሆኑን በማውሳት፤ አስቀድሞ ኩባንያዎች ኦዲት ሣይደረጉና ጉዳዩ ሣይጣራ ደንበኛቸው መታሠራቸው አግባብ አለመሆኑን፣ ይሠበሠባሉ የተባሉ መዝገቦች መስሪያ ቤት የሚገኙ መሆኑንና ተጠርጣሪው ሊያጠፏቸው የማይቻላቸው እንደሆነ ከገለፁ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋሉት ለአመታት በተሠራ ጥናት ነው ከተባለ “እንዴት በህገወጥነት የተጠረጠሩ ሃብቶችን ማጥናት ጀምረናል ይባላል” ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ ምስክሮችን ሊያባብሉና ሊያጠፉ ይችላሉ የተባለውን በተመለከተም የምስክሮች ማንነት ባለመገለፁ ይህን ማድረግ አይቻላቸውም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም ጠበቆቹ አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ሰው ሊያዝ የሚገባው በቂ ምክንያት ሲገኝ መሆኑን በመግለጽ የሁለት አመት ምርመራ ተደርጓል ከተባለ ያ በቂ ስለሆነና በቂ ምክንያት አግኝቼ ይዣቸዋለሁ እስከተባለ ድረስ እስካሁን ክስ መመስረት ይገባ እንደነበር በማለት ደንበኛቸው ቢቻል እንደዚሁ፣ ካልተቻለም በዋስ እንዲለቀቁ ጠየቀዋል፡፡

2ኛ ተጠርጣሪ የሆኑት አቶ እሸቱ ወ/ሠማያትም በጠበቃቸው አማካይነት መከራከሪያቸውን ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን ጠበቃው ባቀረቡት መከራከሪያ፤ የደንበኛቸው ቤት እና ቢሮ ተበርብሮ አስፈላጊ የተባሉ ሰነዶች መወሰዳቸውን፣ ቀሩ የተባሉ ሠነዶችን ተጠርጣሪው እንደሚያጠፉ ተጨባጭ የሆነ ማረጋገጫ አለመቅረቡን፣ ተጠርጣሪው የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውንና ቤተሰባቸውም በሳቸው ደሞዝ እንደሚተዳደር በማመልከት በዋስ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ የ3ኛ ተጠርጣሪ አቶ መርክነህ አለማየሁ ጠበቃ በበኩላቸው፤ ይሰበሰባሉ የተባሉት መዝገቦች በአንድ ቦታ እንደሚገኙና ይህን አሰባስቦ አለማጠናቀቅ የመርማሪ ቡድኑ ስህተት መሆኑን እንዲሁም ግብርን በተመለከተ ከደንበኛቸው የስራ ባህሪ ጋር የማይያያዝ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት በዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ በእለቱ ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች መካከል ሃሳባቸውን ለመግለጽ የጠየቁት አቶ መርክነህ በዋስ ሆነው ጉዳያቸው ለመከታተል በቂ ምክንያት እንዳላቸው በመጠቆም፣ ያለመከሰስ መብት ሳይሆን አለማቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቬንሽኖችና ስምምነቶቹ ከእሣቸው የአካል ጉዳት ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ተደርገው ህጐቹ በሚፈቅዱት መሠረት ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ አመልክተዋል፡፡

ለመፀዳጃ ቤት፣ ለምግብና ለመሳሰሉት የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በሌሎች እስረኞች መልካም ፍቃደኛነት ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑን ያብራሩት አቶ መርክነህ በዚህ ሁኔታ በእስር ላይ አቆይቶ ምርመራ ማድረግ የእኔን ሰብዓዊ መብት ከመጋፋት የዘለለ አይሆንም” ብለዋል፡፡ ስልጣንን በጠቀም መረጃ ያጠፋሉ ለተባሉትም “እኔ እስር ቤት ከገባሁ ጀምሮ ስልጣን የለኝም” በማለት መረጃውን የማጥፋት አቅም እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ የ4ኛ ተጠርጣሪ አስመላሽ ወ/ማርያም ጠበቃ በበኩላቸው፤ በደንበኛቸው ላይ አንድ የወንጀል ጥርጣሬ ብቻ መቅረቡንና በሌሎቹ እንደማይመለከታቸው ከመርማሪ በይፋ በመገለፁ፣ ከሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጋር ሳይሆን ጉዳያቸው ለብቻው መታየት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ይዘው መገኘት በሚለው በቤታቸው የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ መገኘቱ በግለጽ የሚታወቅ በመሆኑ ሌላ ማስረጃ አያስፈልገውም፡፡ ምስክርም ማሰማት አያስፈልገውም፤ በዚህ ወንጀልም ሊቀጡ የሚችሉበት ከ3-5 አመት እስራት በመሆኑ የዋስ መብት አያስነፍጋቸውም ስለዚህ በዋስ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን ያሉ ሲሆን፤ ከዳኞች በቀረበ አስተያየትም እሣቸው የጠቀሱት አዋጅ 657/2002 በአዋጅ 780/2005 መሻሩን በማመልከት የቀረቡት የቅጣት እርከን መከራከሪያ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ በድጋሚ የመርማሪ ቡድኑን ባቀረበው አስተያየት ላይም የመዝገቦች ማቋረጥ የሚለውም እሣቸውን እንደማያካትት ገልጿል፡፡ የ5ኛ ተጠርጣሪ አቶ ከተማ ከበደ ጠበቃ፤ በ1ኛ ተጠርጣሪ ጠበቃ የተጠቀሰው በሙሉ እንዲመዘገብላቸው ጠይቀው በተጨማሪም ስልጣን የሌላቸው ሰው ስለሆኑ ማስረጃ ያጠፋሉ ተብለው ሊገመቱ አይገባም፤ የምስክሮች ስም ባለመጠቀሱም ሊያባብሉ አይችሉም በማለት በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

ይህ ካልሆነም ማለቂያ በሌለው እስራት መቀጣት ስለሌለባቸው ለመጨረሻ ጊዜ ከማስጠንቀቂያ ጋር ቀሪ ማስረጃዎችን መርማሪ ቡድኑ አሰባስቦ ክስ እንዲመሠረት ፍርድ ቤቱ ያሳስብልኝ ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የ8ኛ ተጠርጣሪ አቶ ስማቸው ከበደ ጠበቆችም፤ በ2ኛ ተጠርጣሪ ጠበቆች የተነገረው እንዲመዘገብላቸው ጠይቀው፣ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን እያጓተተ የሚገኘው በራሱ ችግር ስለሆነና ደንበኛቸው የንግድና የተለያዩ የግንባታ ስራዎችን ስለሚሰሩ በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ እሣቸው በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴልም አለማቀፍ ባህሪ ያለው ሆኖ ሳለ ከሣቸው መያዝ ጋር ግንኙነት ሳይኖረው የድርጅቱ መዛግብቶችና ሰነዶች መያዛቸው አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ከክስ ማቋረጥ ጋር የተያያዙ ክሶች እንዲሁም ይሰበሰባሉ የተባሉ መዛግብቶች እሣቸውን የሚመለከቱ ባለመሆናቸው በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ የ7ኛ ተጠርጣሪ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ጠበቃ በበኩላቸው፤ ዶ/ር ፍቅሩ የተጠረጠሩበት ጉዳይ የዛሬ ሁለት አመት እሣቸው ባላወቁት ምክንያት ከተቋረጠው ክሣቸው ጋር በተያያዘ ብቻ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በማመልከት እንዲሁም የእሣቸው መዝገብ በፍርድ ቤት የሚገኝና የሚጠፋ ባለመሆኑና ዶ/ሩ ከሚሰጡት ሰብአዊ አገልግሎት አንፃር ከኢትዮጵያ እንዳይወጡ ታግደው፣ ወገናቸውን በሙያቸው ይረዱ ዘንድ በዋስ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡

በቀረቡት መከራከሪያዎች ላይ አስተያየትን እንዲሰጡ የተጠየቁት የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን አባላትና አቃቤ ህግ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎችን ሲይዝ ለሁለት ዓመት ክትትል ማድረጉን ገልፆ ለመመርመር በቂ ማስረጃ አለኝ ነው ያለው እንጂ ለክሱ ማስረጃ ሰብስቤ ጨርሻለሁ አላለም፤ የሰው ማስረጃዎችንም ሊያጠፉ ይችላሉ ያልነው ግለሰቦቹ ከማን ጋር ምን ሲሰሩ እንደነበር ስለሚያውቁ ያውቋቸዋል ወይም ይጠረጥሯቸዋል፣ ባለስልጣንና ከፍተኛ ባለሃብቶች በመሆናቸው ሰነድ የማስጠፋት አቅም አላቸው በማለት በጥቅሉ ሰጥተዋል፡፡ ምላሽ ያቀረቡ ሲሆን ኮማንደር ብርሃኑ አበበ በበኩላቸው፤ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ለቀረቡት አስተያየቶች በሰጡት በምላሽ፤ አቶ ስማቸው ከበደን በተመለከተ ለሆቴል ብለው ያመጡትን ከቀረጥ ነፃ እቃ ለተባለው አላማ ስለአለመዋሉ በዚህም መንግስት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲያጣ ማድረጋቸውና ሌሎች ከቀረጥ ነፃ የገቡ እቃዎች ይኖራሉ ተብሎ ስለሚጠረጠር ማስረጃዎች እየተሰባሰቡ መሆኑን ገልፀው፣ አቶ ከተማ ከበደን በተመለከተ ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በአራጣ ብድር ተጠርጥረው በቂ ማስረጃ ቀርቦባቸው ሳለ ከ1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪ ጋር ባላቸው ትስስር ክሳቸው ወደ ህግ እንዳይቀርብ መደረጉን፣ አቶ መርክነህም ከአካል ጉዳተኝነት ጋር አያይዘው ያነሱትን በተመለከተም አለማቀፍ ህጐችን ባከበረ መልኩ ምርመራው እየተከናወነ መሆኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ችሎቱም የሚከተለውን ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አንደኛ ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ችሎቱ በመረዳቱ ከምርመራው ውስብስብነትና እየተሰባሰቡ ካሉ ማስረጃዎች ስፋት አንፃር የዋስትና ጥያቄውን ባለመቀበል የ14 ቀን ቀጠሮ ተፈቅዷል፡፡

ሁለተኛ በችሎቱ ክርክር ሲካሄድ ስርአቱን ጠብቆ የመከራከር ሁኔታ እንዲከበር የሚሉት ትዕዛዞች ከተላለፉ በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ ለሰኔ 4 ቀን ተሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሐሙስ እለት ቀጥሎ በዋለው ችሎት፣ በእነ መሐመድ ኢሣ መዝገብ የሚገኙ የሰባት ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ሲመለከት ውሏል፡፡ የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን በተፈቀደለት 14 ቀን ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባሮች ከመግለፁ በፊት እያንዳንዱ ተጠርጣሪ የተጠረጠሩበትን ምክንያት ለፍ/ቤቱ አብራርቷል፡፡ በዚህ መሠረት አንደኛ ተጠርጣሪ አቶ መሃሙድ ኢሣ፣ የናዝሬት ጉምሩክ ቅርንጫፍ እና የሞጆ ደረቅ ወደብ እቃዎች በገንዘብ በመደራደር ሳይፈትሹ እንዲገቡ በማድረግ መንግስት ሊያገኝ የሚችለውን የቀረጥ ገቢ አሳጥተዋል፣ በመንግስት ላይም ጉዳት አድርሰዋል የሚል ነው፡፡ በተለይም ከ4ኛ 3ኛ እና 5ኛ ተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር የተገለፀውን ድርጊት ፈጽመዋል ይላል- የመርማሪ ቡድኑ ሪፖርት፡፡ ሁለተኛ ተጠርጣሪ ሰሙ ንጉሴ በሞጆ ወደብ የመጋዘን ሠራተኛ ሲሆኑ ከ5ኛ ተጠርጣሪ ሙሉቀን ተስፋዬ ጋር በመመሳጠር እቃዎች ሳይፈተሹ እንዲያልፉ በማድረግ የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም ለመንግስት ይገባ የነበረውን የቀረጥ ገቢ አሳጥተዋል የሚል ነው፡፡ በ3ኛ ተጠርጣሪ ዘሪሁን ዘውዴ እና 4ኛ ተጠርጣሪ ማርሸት ተስፋዬ (የትራንዚት ሠራተኛና ባለቤት ናቸው) ላይ የቀረበው ደግሞ የግል ጥቅማቸውን በማስቀደምና ህገወጥ ብልጽግናን በመሻት ከሠራተኞች ጋር ተመሳጥረው ተሽከርካሪዎች ሳይፈተሹ እንዲያልፉ በማድረግ ከቀረጥ ይገኝ የነበረን የመንግስት ገቢ አሳጥተዋል ተብሏል፡፡

እንዲሁም 5ኛ ተጠርጣሪ ሙሉቀን ተስፋዬ ከ2ኛ ተጠርጣሪ ጋር ባላቸው የቅርብ ግንኙነት እቃዎች እንዳይቀረጡ በጉቦ ያስፈፀሙና የፈፀሙ ናቸው ተብሏል፡፡ 6ኛ ተጠርጣሪ ዳኜ ስንሻው መርማሪ ሆነው ሲሰሩ የምርመራ መዝገብ በሌላ መዝገብ ከተጠረጠሩት ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር እንዲቋረጥ ያደረጉና በዚህም ለመንግስት የሚገባን ቀረጥ ያሳጡ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ 7ኛ ተጠርጣሪ የሆኑት ወ/ሮ ፍሬ ህይወት ጌታቸው የህይወት ትራንዚት ባለቤት መሆናቸው ተገልፆ ጉቦ የሚያቀባብሉ እና ቀረጥ ለመንግስት እንዳይገባ የሚያደርጉ ተጠርጣሪ ናቸው ተብሏል፡፡ የመርማሪ ቡድኑ በተጠርጣሪዎች ላይ በ14 ቀን ውስጥ ያሠባሰበውን ማስረጃም በጥቅሉ እንደሚከተለው አቅርቧል፡፡ በተጠርጣሪዎች ቤት እና ቢሮ የተገኙ ሰነዶችና በፍተሻ የተያዙ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ተለይተዋል፣ 21 ኩባንያዎችን ኦዲት ለማድረግ ለዋናው ኦዲተር ደብዳቤ ተጽፏል እንዲሁም የምስክሮችን ቃል የመቀበል ስራ ተሰርቷል፡፡ በምርመራ ቡድኑ ያልተከናወኑ ተግባራት ተብለው በድጋሚ ለ14 ቀን ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ቀሪ ስራዎችን ሲገልፁም ፤ኩባንያዎችን ኦዲት ማስረግና የኦዲተሮችን የምርመራ ውጤት መቀበል፣ ህገወጥ ሆነው ህጋዊ ተደርገው ተይዘዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሃብቶችን የማጣራት ስራ እንዲሁም የበርካታ ምስክሮችን ቃል መቀበል ይቀራል ተብሏል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆችም የቀረበው የምርመራ ቡድኑ ሪፖርት ከባለፈው ሪፖርት ጋር ያልተጣጣመ ነው፤ በተጠረጠሩበት መዝገብ ባለሃብት የለም ስለዚህ ከኩባንያ ጋር “የተያያዘ ስራ ስለሌለ ኦዲት ማድረግ እነሱን አይመለከትም፡፡ ደሞዝተኞች ስለሆኑ ምስክር የማባበል አቅም የላቸውም፣ ቤታቸውም መስሪያ ቤታቸውም ተፈትሾ ሰነዶች ተወስደዋል የሚሉ ሲሆን 7ኛ ተጠርጣሪ ወ/ሮ ፍሬህይወት ጌታቸው ራሳቸው ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት መከላከያ ፤ “እኔ ከጉዳዩ ጋር ምን ግንኙነት የለኝም፤ በስመ ሞክሼ ጭንቅላቴ ተበላሽቷል” በማለት አመልክተዋል፡፡ የሁሉም ተጠርጣሪዎች ጠበቆች እነዚህን ምክንያቶች መነሻ በማድረግ የዋስ መብት ተከብሮ ደንበኞቻቸው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ በተነሱት የመከራከሪያ ነጥቦች ላይ የምርመራ ቡድኑ በሰጠው ምላሽም፤ ለተጠርጣሪነት በቂ ማስረጃ ያዝን እንጂ በቂ ማስረጃ ሰብስበን ጨርሰናል አላልንም፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ባላቸው ተሰሚነት ሰነዶችን ያጠፋሉ እንዲሁም ለወደፊት የሚመሰረተው ክስ ከባድ የሙስና ወንጀል በመሆኑ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲሆን ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡ ችሎቱም የምርመራ ሂደቱ ውስብስብና ብዙ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ በመገንዘብ፣ የምርመራ ቡድኑ የቀሩትን ስራዎች በትጋትና በፍጥነት እንዲያከናውን አሳስቦ፣ ተጠርጣሪዎች የተጠየቁትን የዋስ መብት ውድቅ በማድረግ የ14 ቀን ቀጠሮውን ፈቅዷል፡፡

በዚህ መሠረት ለሰኔ 5 ቀን 2005ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የምርመራ ቡድኑ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ ስር የሚካተቱ ሁለት አዳዲስ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ የ14 ቀን የምርመራ ቀን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ እነዚህ ተጠርጣሪዎች የአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ የቀረጥ ትመና እንዲሁም ፈታሽ ኦፊሰር ሆነው ሲሰሩ የነበሩት አቶ ጫላ ንጉሴ እና የናትራንና ብስራት የንግድ ባለቤት እንዲሁም የእልፍኝ ባህሩ ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ባህሩ አብርሃም ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ምክንያትም እቃዎች ሳይቀረጥባቸው እንዲያልፉ በማድረግ እንዲሁም የቫት ክስ እንዲቋረጥ በመመሳጠር ቀረጥና ታክስ ዝቅ እንዲል አስደርገዋል በሚል መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር ሰኔ 4ቀን 2005ዓ.ም እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ በአጠቃላይ የተጠርጣሪዎቹ ብዛት 58 ደርሷል፡፡

Read 2226 times