Saturday, 08 June 2013 07:54

“ፓርላማው ጥርስ አውጥቷል?”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፓርላማ ውስጥ የመነቃቃት ስሜት መፈጠሩን የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች፤ የምክር ቤቱ አባላት በተለየ ሁኔታ መንቀሳቀስ እንደ ጀመሩ ይገልፃሉ፡፡ በፊት አንድ የሚኒስቴር መ/ቤት ያቀረበውን ሪፖርት አዳምጠው “የሚበረታታ ነው”፣ “መልካም ጅምር ነው” የመሳሰሉ አስተያየቶች ሰጥተው ይሸኙ ነበር ይላሉ - ታዛቢዎች፡፡ አሁን ግን በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመስርተው መሞገት፣ የሰላ ሂስ መሰንዘርና ድክመቶችን መንቀስ ጀምረዋል፡፡

“ፓርላማው ጥርስ እያወጣ ነው” ይላሉ፡፡ በዚህ የሚስማሙም የማይስማሙም የም/ቤት አባላት አሉ፡፡

“ፓርላማው ድሮም አሁንም ጥርስ የለውም” - አቶ ግርማ ሠይፉ -

በፓርላማ የመድረክ ተወካይ “ፓርላማው በቅርቡ ጥርስ ማውጣት ጀምሯል በሚለው አልስማማም” -ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ - “የፓርላማውን እንቅስቃሴ የማወዳድረው ከልጅ እንዳልካቸው ዘመን ጋር ነው” - ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ - በአ.አ.ዩ የፍልስፍና መምህር “የፓርላማ አባላት አሁን እየሠሩ ያሉት ቀደም ሲል የሚሰሩትን ነው” - አቶ ታደሠ መሠሉ - የፓርላማ አባል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመድረክ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሠይፉ፤ ፓርላማው ጥርስ አውጥቷል በሚባለው ነገር እንደማይስማሙ ይናገራሉ፡፡

“ባይሆን ነቃ ነቃ ብሏል” ቢባል ይሻላል የሚሉት አቶ ግርማ፤ ፓርላማው ድሮም አሁንም ጥርስ እንደሌለውና ለማብቀልም ብዙ እንደሚቀረው ገልፀዋል፡፡ የፓርላማው መነቃቃት ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ህልፈት ጋር የተያያዙ ሊሆን እንደሚችል የገለፁት አቶ ግርማ፤ በፊት ጠ/ሚኒስትሩ ሁሉ ነገር ስለነበሩ የፓርላማው ሚና አነስተኛ ነበር ይላሉ፡፡ “አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃ/ማሪያም ደሣለኝ ግን አውቀውም ይሁን ሳይውቁ ፓርላማውን በእጅ አዙር የመቆጣጠር አዝማሚያ የላቸውም” የሚሉት አቶ ግርማ፤ የምክር ቤት አባላትም ይህን ዕድል በመጠቀም የሚፈልጓቸውን አካላት ለመቆጣጠር እየሞከሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን የፖሊሲ ለውጥ ባይኖርም ሹፌሩ ሲለወጥ በተወሠነ መልኩ ለውጥ እንደሚመጣ ጠቅሠው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ የፓርላማውን መነቃቃት እንዲፈጠር ያምናሉ፡፡

ፓርላማው ጥርስ አወጣ የሚባለው መቼ ነው በሚል ተጠይቀው ሲመልሱም፤ “ጥርስ ማውጣት ማለት በስራ አፈፃፀሞች፣ የሚታዩ ጥፋቶችን ሞግቶ አስተማማኝ ድምፅ በመስጠት ሚኒስትሮችን ማስቀየር ሲችል ነው” ብለዋል አቶ ግርማ፡፡ ፓርላማው ይሄ ስልጣን ቢኖረውም ለበርካታ ጊዜያት እንዳልተጠቀመበት በመግለጽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንከር ያሉ ውይይቶችን ማድረግ እንደጀመረ ተናግረዋል፡፡ “ሁሉም ሚኒስትሮች ሲመጡ ከፓርላማ ተወካዮች የሚቀርቡት ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከሩ መጥተዋል” ያሉት አቶ ግርማ፤ ቀደም ሲል “አበረታች ነው”፣ “ገንቢ ነው” በማለት የሚታወቁ የፓርላማ ተወካዮች፤ “ልክ አይደላችሁም”፣ “በደንብ አልሰራችሁም” ማለት መጀመራቸው ትልቅ ለውጥ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ ሆኖም “ጥርስ አውጥቷል” እስከሚለው አያደርስም ብለዋል፡፡ አቶ ግርማ አንድ ስጋት አላቸው፡፡ “የፓርላማ አባላቱ ዘንድ መነቃቃቱ የተፈጠረው ከጠ/ሚኒስትር ለውጥ ጋር ተያይዞ ነው የሚል አዝማሚያ ከታየባቸው ጠርናፊዎች ወደ ቀድሞ ዝምታቸው ሊመልሷቸው ይችላሉ” ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ በበኩላቸው፤ “የአሁኑን የፓርላማ እንቅስቃሴ የማወዳድረው ከልጅ እንዳልካቸው ዘመን ጋር ነው” ይላሉ፡፡ “ከተሞክሮዎች እንደሚታወቀው አንድ ጠንካራ ሠው ከቦታው በሚነሳ ጊዜ የፖለቲካ ክፍተት ይፈጠራል” ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ በዚህ ጊዜ የተለያዩ አካላት እንደሚበረቱ ገልፀው፤ የሀገራችን ፓርላማም እዛ ሠዓትና ወቅት ላይ እንዳለና ይህ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ እንደመጣ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ የፓርላማ እንቅስቃሴው ቀጣይነት ቢኖረው ጠቀሜታው የጐላ እንደሆነ የገለፁት ምሁሩ፤ “የእኔ ስጋት የተወሠነ ቡድን ወይም ሀይል ጫና አሣድሮ ይሄ ጭላንጭል እንዳይጠፋ ነው” ብለዋል፡፡ “የፓርላማው ስራ ሁለት ነው፤ አንዱ ህግ ማውጣት ሲሆን ሌላው የተለያዩ መስሪያ ቤቶችን እየተከታተሉ የስራ አፈፃፀማቸውን መገምገም ነው” የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ አሁን እየታየ ያለው የፓርላማ አባላት እንቅስቃሴና ጠንካራ ሙግቶች በጣም አስገራሚ በመሆኑ ጅምሩን ልናበረታታ ይገባል ብለዋል፡፡

“እኔ በሁኔታው በጣም እየተረገምኩ ነው፤ ይህን ሁሉ ጉልበት ከየት አመጡት? እስከዛሬ የት አስቀምጠውት ነበር?” ሲሉ የጠየቁት ምሁሩ፤ ይህንን ጠንካራ እንቅስቅሴ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ጋር የሚያያይዙት “አቶ መለስ አትናገሩ ብለዋቸዋል” ለማለት ሳይሆን ብዙ የሚያውቅ ሠው ባለበት ቦታ የሌሎች አንገት መድፋት በፖለቲካ ውስጥ የሚከሠትና የተለመደ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ “የፓርላማ አባላት ሁሉንም ነገር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ያውቃሉ” ብለው ሥለሚያምኑ ለመናገር ድፍረት ያንሳቸው እንደነበር እገምታለሁ” ሲሉም አስረድተዋል፡፡ በተለይ አሁን ከፍተኛ ሙግትና ትችት እያነሱና በድፍረት እየታገሉ ላሉት ሴት የፓርላማ ተወካዮች ትልቅ አክብሮት እንዳላቸው የገለፁት ዶ/ሩ፤ በተለይም “ይህን ጉዳይ ሌላ ስም አጥቼለት ነው፤ ግን ሌብነት ነው” ሲሉ በሙስና በተጠረጠሩ ሙሠኞች ላይ ትችት ለሠነዘሩት ሴት የፓርላማ ተወካይ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡ ስለፓርላማው እንቅስቃሴ ከወዲሁ ድምዳሜ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል፡፡ የፓርላማውን እንቅስቃሴና ቀጣይነት ወደፊት የምናየው ይሆናል በማለት፡፡

የኢህአዴግን ፖሊሲ እደገፋለሁ የሚሉት በፓርላማ የግል ተመራጭ የሆኑት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፤ የፓርላማውን እንቅስቃሴ በተመለከተ የተለየ አስተያየት አላቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፓርላማው ጥርስ ማውጣት ጀምሯል በሚለው ጉዳይ አልስማማም ባይ ናቸው። ፓርላማው በፊትም መስራት ያለበትን ሥራ እየሰራ መሆኑንና አዲስ የተፈጠረ ነገር እንደሌለም ይናገራሉ። “እኔ ገና በግሌ ተወዳድሬ ፓርላማ ስገባ. አብዛኛው ወንበር የኢህአዴግ በመሆኑ ስጋት ገብቶኝ ነበር” ያሉት ዶ/ር አሸብር፤ የመጀመሪያው ስጋታቸው በአንድ ፓርቲ አብላጫ መቀመጫ የተያዘ በመሆኑ ከፍተኛ ሙግቶችና የሀሳብ መንሸራሸሮች አይኖሩም የሚል እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ስጋታቸው ደግሞ በግላቸው ተወዳድረው እንደመግባታቸው በፓርላማው ብቸኛና ባይተዋር እሆናለሁ የሚል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ “ወደ ፓርላማ ስገባ የጠበቅሁትና ከገባሁ በኋላ ያገኘሁት ሁኔታ ግን በጣም ይለያያል” ያሉት ዶ/ር አሸብር፤ ፓርላማው ሥራ ከጀመረ በኋላ አዋጆች ከመፅደቃቸው በፊት ብዙ ክርክሮች ይደረጉ እንደነበር ተናግረዋል። በብዙዎቹ ሪፖርቶች ላይም ከፍተኛ ክርክሮች፤ ውይይቶችና አስተያየቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን በመግለጽ፤ ሰሞኑን የተለየ እንቅስቃሴ እንዳለ አድርጐ መናገሩ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡

በፓርላማው ወደ 16 ያህል ቋሚ ኮሚቴዎች እንዳሉ የጠቆሙት ዶክተሩ፤ እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ በተመደበባቸው መስሪያ ቤቶች ቁጥጥር፣ ግምገማና የመስክ ጉብኝት ሳይቀር በማድረግ ሃላፊቱን ሲወጣ መቆየቱንና አሁንም እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል። “በመሆኑም ፓርላማው በሙሉ ቁመናው እየሰራ ነው” ባይ ናቸው፡፡ሰዎች ጉዳዩን እንደ አዲስ የቆጠሩት ለምን እንደሆነ ሲያስረዱም፤ በፓርላማውና በሚዲያው በኩል ያለው ክፍተት እየጠበበ በመምጣቱና ሚዲያዎች የፓርላማውን እንቅስቃሴ በትክክል እየዘገቡ በመሆናቸው ነው ያሉት የፓርላማ ተወካዩ፤ ከበፊትም ጀምሮ እያንዳንዱ መስሪያ ቤት ወደ ፓርላማ ሲመጣ ተጨብጭቦለት ሳይሆን የሚሄደው በደንብ ተጠይቆ፤ ተገምግሞና ተፈትሾ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፓርላማ አባላት የመገዳደር አቅማቸው የጠነከረው የስራ ልምድ እየጨመረ ሲሄድ ከሚዳብር እውቀት እንጂ ምንም አዲስ ነገር አልተፈጠረም” ያሉት ዶ/ር አሸብር፤ “እኔ እንደሚገባኝ በፊት ፓርላማውና ሚዲያው የተገናኙ አልነበሩም፤ አሁን ሚዲያው የፓርላማውን ሙግትና ፍጭት አጉልቶታል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አለመኖር የተነሳ የፓርላማ ተወካዮች ከፍርሀት ተላቀው መናገር ጀምረዋል በሚለው ጉዳይ ፈፅሞ እንደማይስማሙ የገለፁት ዶ/ሩ፤ “እውነት ለመናገር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጠንቅቄ አውቃቸዋለሁ፤ ሠዎች ሲናገሩ ሲከራከሩና ሀሣባቸውን ሲገልፁ የሚወዱ እንጂ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ አልነበሩም” ብለዋል፡፡ ምናልባት እንዲህ አይነት ፍርሀት የሚፈጠረው ከአቅምና ከእውቀት ችግር ይሆናል፤ በእውቀቱና በአቅሙ ሙሉ የሆነ ሠው ፍርሃት አያድርበትም ሲሉ አብራርተዋል። “እሳቸው እያሉ እንዴት እናገራለሁ -በጭንቅላትም፣ በልምድም በትምህርትም ይበልጡኛል ብሎ ቅድሚያ ተሸንፎ የገባ አባል ካለ፤ እሱን አላውቅም፤ ነገር ግን በሀሣብና በእውቀት ሙሉ ሆኖ ለቀረበና ለሚገዳደራቸው ሠው ተደስተው ተገቢውን ምላሽ ይሠጣሉ” ብለዋል ዶ/ር አሸብር፡፡ ፓርላማው በአሁኑ ሠዓት አገርን ማዕከል ያደረገ፣ የህዝብን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ክርክር እንጂ የተቃዋሚና የደጋፊ ፓርቲ የሚል አጀንዳ እንደሌለው የገለፁት ዶ/ሩ፤ አላማው ይህቺን አገርና ህዝቧን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ በመሆኑ ድሮ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው፤ አሁን ጥርስ እያወጣ ነው የሚለውን ትተን፣ በአገሪቱ እና በህዝቧ ጥቅም ላይ ፓርላማው አትኩሮ መስራቱን እንዲቀጥል ትኩረት ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በፓርላማ የኢህአዴግ ተወካይ አቶ ታደሠ መሠሉም፤ ከዶ/ር አሸብር ሃሳብ ጋር ይስማማሉ፡፡

አሁን በፓርላማው እየተሰራ ያለው ድሮም የነበረ እንጂ አዲስ ነገር የለም ይላሉ፡፡ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች አስፈፃሚ አካላትን የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የመደገፍ ሀላፊነት ተሰጥቶታል ያሉት አቶ ታደሰ፤ እየሰራ ያለውም ይሄንኑ ነው ብለዋል፡፡ ምክር ቤቱ የጐደሉ የስራ አስፈፃሚ በጀቶችንና በአግባቡ ያልተከናወኑ ስራዎችን በተመለከተ መሞገቱ ከዚህ ቀደምም የሚያደርገው እንጂ አዲስ አይደለም ሲሉም አክለዋል፡፡ የፓርላማ አባላት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሚፈሩ አይናገሩም ነበር፤ አሁን በድፍረት መናገር ጀመሩ በሚባለው ጉዳይ ፈጽሞ እንደማይስማሙ የገለፁት አቶ ታደሠ፤ “ለሰው የተለየ ነገር የመሠለው ይህቺን አገር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሲታትሩ ያለፉትን የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር ራዕይ ለማሳካት የፓርላማው አባላት በእልህና በቁጭት መነሳሳታችን ነው” በማለት ብለዋል፡፡ ም/ቤቱ፤ ስራ አስፈፃሚውን ብቻ ሳይሆን የአስፈፃሚውን መሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጭምር ጠርቶ የማነጋገር ስልጣን አለው ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ ጠ/ሚኒስትሩ ምክር ቤቱ እየጠራቸው ሪፖርትም ማብራሪያም ይሠጡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አቶ ታደሰ እንደሚሉት፤ የም/ቤት አባላቱ በየጊዜው በሚያገኙት ሥልጠና ልምዳቸውን እያካበቱ መምጣታቸው፣ ከባለራዕዩ መሪ ሞት ጋር ተዳምሮ በእልህና በወኔ እንዲንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል፡፡ ይሄ ማለት ግን ድሮ አይንቀሣቀሱም፤ አይሠሩም ማለት እንዳልሆነ በመጥቀስ የፓርላማው እንቅስቃሴ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም ብለዋል፡፡

Read 5623 times