Saturday, 08 June 2013 08:13

“ከካፖርት ስር ግልገል ሱሪ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

አንድ ሰሞን ‘እምብርትዬዋ’ ታየች ብለን “እሪ!” እንዳላልን… ይኸው “ኽረ እምብርት ምን አላት፡ ሺህ ጊዜ ትታይ!” የምንልበት ጊዜ መጣ! እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ሰኔ ግም አለ አይደል! ‘በሰኔ ካልዘሩ በጥቅምት ካለቀሙ እህል አይገኝ ከድንበር ቢቆሙ፣’ ይላሉ የጥንት ሰዎች፡፡ ልጄ…እንደ ምንም ‘መሥራት እስከተቻለ’ ድረስ በሰኔ ለመዝራት መሞከር ነው፡፡ እንቅስቃሴው ሁሉ የሆነ የአርክቲክ በረዶ መጥቶ የተዘረገፈበት ይመስል ቀዝቅዟል ይላሉ፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የአፍሪካ ህብረትን ‘ጎልደን ጁብሊ’ን አከበርን አይደል! እሰይ…እንኳን በሰላም መጥተው በሰላም ሄዱማ! በእንግዳ ተቀባይነታችን ‘ወዛም ወዛሞቹ’ በሚያልፉባቸው መንገዶች ‘ዝር ማለት’ ትተን፣ አብዛኞቻችን በቺቺኒያና በቦሌ መድሀኔዓለም አካባቢ ካሉ መዝናኛዎች ባንታመምም እንደታመመ ‘ሲክ ሊቭ’ ወስደን፣ በሆቴሎች በር ላይ ተብጠርጥረን እየተፈተሽን… አስተናግደናል፡፡

እናላችሁ…ያው በእንግዳ ተቀባይነታችን የእኛን ጠማማ ጭልፋና ቀዳዳ ትሪ ደብቀን ለእንግዳ የምናስቀምጠውን አብለጭላጭ ጭልፋና ሊነኩት የሚያሳሳ አውጥተን በዛ ሰሞን ‘እንግዶቻችንን ስናስተናግድ’ የአዲስ አበባ እንትናዬዎች የስንት ዓመታቸውን ዘጉ አሉ! (ወላ ‘ዶላር’፣ ወላ ‘ዩሮ’፣ ወላ ‘ፓውንድ’ ፈሰሰ አሉ!) እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል …ልጄ ስንት አይነት ‘ኢንቪዚብል’ ቱሪዝም አለ መሰላችሁ! እናንተ የቲማቲም ዋጋ እንዲህ እንደ ወዳጃችሁ ‘ብለድ ፐሬዠር’ በአንዴ ሽቅብ ስለተወረወረበት ምክንያት ስትመራመሩ…በዚቹ በእኛዋ ሸገር ስንት ነገር ይካሄድባታል መሰላችሁ! (እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…ሰሞኑን የ‘ብለድ ፕሬዠር’ ነገርዬው ተባብሷል ያልከኝ ወዳጄ…ምኞትህን ነው የነገርከኝ ወይስ… መረጃው ከየት ተገኘ!) እናላችሁ…በፊት እንትን ሰፈር እንትን ቀበሌ ብለን የምናወራላቸው እንትናዬዎቹ ሔዋን ‘እጸ በለሱን ከመብላቷ በፊት’ እንደነበረችው ሆነው የሚደንሱባቸው ቤቶች…አሁን በየሰፈሩ ፈልተዋል ነው የሚባለው፡፡ ደግሞላችሁ…የእንትን ሰፈር የሦስት ብር ከሀምሳ ብር ሻይ ከስኒዋ በስተቀር ምኗም ሳይቀየር አሥራ ምናምን ብር የሚሸጥባት ሰፈር ብቻ ሳይሆን…ገና ‘ስቶን ኤጅ’ ውስጥ ናቸው የሚባሉት ሰፈሮች ሁሉ ‘መለመላችንን’ ሆነን የምንደንስባቸው ቤቶች ብዛት…አለ አይደል… ልክ እንደ ‘ምናምን ኤክስቴንሽን’ የተበተኑ ሊመስሉ ምንም ያህል አልቀረም፡፡ ምን ችግር አለ መሰላችሁ…አሁን አሁንማ ነገሮች በጣም የተለዩ እየሆኑብን ለመገረምም፣ ለመደነቅም ‘መተንፈሻ’ እያጣን ነው፡፡

መስከረም ላይ ራሳችንን ይዘን “ጉድ! ጉድ!” ያልንበት ነገር…ህዳር ላይ ብዙ ዓመት አብሮን የኖረ ይመስል ትከሻችን ሸከሙን ይለምደዋል፡፡ (‘ሌሎች ሸክሞችን እንደቻለው’ የሚለውን ማስከተል ይቻላል፡፡) ስሙኝማ…ካነሳነው አይቀር እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሚዲያው ላይ አልፎ፣ አልፎ እነዚህ አይነት ችግሮች ‘እግረ መንገድ’ ጠቀስ ተደርገው ቢያልፉም…ብዙ ጊዜ.. አለ አይደል…የሩኒን ቁርጭምጭሚት ያህል እንኳን… የአየር ሰዓት ሲሄዱ አይታዩም፡፡ ታዲያላችሁ…የዘንድሮ የእንትናዬዎቻችን አለባባስ ለየት ብሎ ነበር አሉ፡፡ (ልክ ነዋ… “ለሀምሳኛ ዓመት ያልሆነ….ዳዋ ይምታው!” የተባለ ይመስል ነበር!) አለ አይደል…እንዴት ነበር አሉ መሰላችሁ…ካፖርት ይለበሳል፣ ከዛ ስር የ‘ብሬስት’ መያዣና ‘ግለገል’ ሱሪ ብቻ! አራት ነጥብ! (እናማ…ይህ ሁሉ በማታ ሳይሆን በጠራራው ጸሀይ እንደሆነ ልብ በሉልኝማ! አሁንማ…ዋናው ቦሌ በያዝ ለቀቅም ተከፈተ አይደል…ለሌሎች ‘ጉዶች’ መዘጋጀት ነው!) እናላችሁ…ይሄ የሆነው እዚቹ እኛዋ ስልጣኔዋ ‘አናቷ ላይ የወጣባት’ ከተማችን ውስጥ ነው! (ወይም…ስልጣኔ አዲስና አገር በቀል ‘ዴፊኒሽን’ ያገኘባት የምትመስል ከተማ ውስጥ!) ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ለከርሞ ደግሞ (‘ለከርሞ’ የሚለው ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት መሆኑ ይመዝገብልን!) ከቀሩት ሁለቱ ነገርዬዎች አንደኛዋ ትጣልና…ካፖርትየውም ርዝመቱ በግማሽ ሊያጥር ይችላል፡፡

አንድ ሰሞን ‘እምብርትዬዋ’ ታየች ብለን “እሪ!” እንዳላልን…ይኸው “ኽረ እምብርት ምን አላት፡ ሺህ ጊዜ ትታይ!” የምንልበት ጊዜ መጣ! እናላችሁ…የዛ ሰሞኑ “ከካፖርት ስር ግልገል ሱሪ…” ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፡፡ የእኛዋ ከተማ የስልጣኔ ‘ዝግመተ ለውጥ’ ያመጣው ነው፡፡ ቂ…ቂ… ሀሳብ አለን…“ወዴት እየሄድን ነው?” የሚለው ጥያቄ (“ምን አይነት አገር እየሆንን ነው?” እንዳልል የኮፒራይት ጥያቄ ያስነሳብኛል ብዬ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…) የጠቃሚነቱ ዘመን ያበቃለት መሆኑን የሚገልጽ የሆነ መመሪያ ምናምን ነገር ይውጣልንማ።

እኛ የምንሄድበት ቦታ በቃ…ሌላው የሰው ልጅ ያልደረሰበት ቦታ ነዋ! ልክ ነዋ…ምን መሰላችሁ… እኛ ስልጣኔያችን ከምንም ተነስቶ አራትና ከዛ በላይ ዲጂት ዕድገት ማስመዝገቡን ለማየት…አለ አይደል…መንገዶቻቸው በሰፉ፣ ህንጻዎቻቻው በረዘሙ፣ አብዛኞቹ የሚዝናኑባቸው ደንበኛዎቻቸው የሚይዙት የሚጨብጡትን ባሳጣቸው፣ የአንድ ምግብ ዋጋቸው ለፒያሳና ለጉለሌ የወር በጀት በሆነባቸው አካባቢዎች ብቅ ማለት ይበቃል፡፡ እናማ…“ከካፖርት ስር ግለገል ሱሪ…” ዝም ብሎ የመጣ ነገር ሳይሆን የደረስንበት የስልጣኔ ደረጃ ማስመስከሪያ ነው! ነገርዬው…‘ውሀ ለሚወስደው ሰው በትርህን እንጂ እጅህን አትስጠው’ ነው፡፡ እናማ…አንዳንድ ነገሮችን ስታዩ ‘ውሀ እየወሰደን’ ያለን መአት ሰዎች ነን፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ…ውሀ ውስጥም ሆነን፣ የውሀውም ከፈታም እየጨመረ…ደረቅ መሬት ላይ ያለን የሚመስለን እየበዛን ነው፡፡ የፉክክር አገር ሆኖላችኋል…አለ አይደል…እንትና ያደረገውን እንትና በማግስቱ ካላደረገ ‘የምጽአት ቀን መጣች’ አይነት ነገር ሆኗል፡፡ አያችሁልኝ ወይ ይህን አይነት ግፍ ተጉዘን ተጉዘን ስንደርስ አፋፍ እኔ ሴቷ ቆሜ ወንዱ ደክሞት ሲያርፍ፣ አሉ የድሮ እናቶቻችንና እህቶቻችን፡፡

እናላችሁ ዘንድሮ ደግሞ እንትናዬዎቹ ነገርዬአቸውን “ከካፖርት ስር ግለገል ሱሪ…” ሆኖ በ‘ስልጣኔ መርሸው’ ፕሬሚየር ሊግ ሲደርሱ…አለ አይደል… ወንድዬው ገና ሦስተኛ ዲቪዥን ሆኖ ‘ሱሪ ዝቅ’ ላይ ነው! ስሙኝማ…‘ሱሪ ዝቅ’ ነገር በጣም፣ በጣም…አለ አይደል…“ምን ይሻለን ይሆን?” የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የታክሲ ረዳቱም መካኒኩም…‘ሱሪ ዝቅ’ እየሆነ ስታዩ ዛሬን ሳይሆን ነገን ትፈሩታላችሁ፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ የግብጽ ነገርዬው እንዴት ነው? ታሪክ ራሱን አይደግምም…ምናምን ያለው ማነው? አሀ…መጠየቅ አለብና! ሲዶልቱብን በስውር ቪዲዮ ተቀረጹ ነው ምናምን የተባሉት…የፈርኦን አገር ባለስልጣኖች የምር ከአንጀታቸው ነው እንዴ! እናማ…ሰኔም ግም አለ…የወጣም ወጣ፣ የወጣም ‘እንዳልወጣ ሆነ’…የወጣም ‘ገባ’…ብቻ የወጣ እንደወጣ የሚቀረው ‘አማሪካን’ ምናምን ብቻ ሆኗል፡፡

ልጄ…የተወጣበት መሰላል ነቅነቅ ያለ እንደሆን አንደኛውን ስቦ ለመጣል ያለው ግፊያ ከቡናና ጊዮርጊስ ‘ደርቢ’ ካለው ግፊያ የባሰ እየሆነ ነው፡፡ አለ አይደለም…“መቼ በወደቀና እንደ ረግቢ ስፖርት ተጫዋቾች ላዩ ላይ በተከመርንበት…” ምናምን እያልን የምንጸልይ ነው የሚመስለው፡፡ እናላችሁ….ዘንድሮ ስንት ነገር እየሆነ፣…ለታሪክ አስቀምጦን እየታዘብን ነው፡፡ እንዴት ያለው ሩቅ ጭንቅ ያለው መንገድ አሻቅቦ ወጥቶ ወደ ታች መውረድ አሉ አባቶች…ወይ ሲወጡ መሰላሉ እንዳይነቃነቅ ጠለቅ አድርጎ ‘መቅበር’…ወይም ‘መውደቅ’ የማይቀር ከሆነ ህመሙ እንዳይሰማ ጂም መግባት! ቂ…ቂ…ቂ… (እነ እንትና ‘ጂም’ የተባለው ‘ወተር ማትረስ’ የሚሉት ‘የጭድ ፍራሽ ጠላት’ ላይ የሚደረገውን የ‘ሆሊዉድ ስተንት’ የሚመለከት እንዳልሆነ ልብ ይባልማ!) እናላችሁ…“ከካፖርት ስር ግልገል ሱሪ…” ጦስ ውጤቱ አሁን ሳይሆን እየቆየ ትውልድ ላይ እንደ ጥላ ተተክሎ አልለቅ እንዳይል አንድዬ ተአምሩን ያምጣልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3401 times