Saturday, 08 June 2013 09:12

በስህተት ያፈተለከው የግብፅ ፖለቲከኞች ሙግት

Written by  ኤልሳቤት እቁባይ
Rate this item
(27 votes)

ሰሞኑን የአባይ ወንዝ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን የግብፅ የፖለቲካ አቅጣጫም እንደተቀየረ የተለያዩ ሚዲያዎች ዘገባ ይጠቁማል፡፡ በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ አካል የሆነው የወንዙን አቅጣጫ የማስቀየር ስራ መጀመር እና በግብፅ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን የተቋቋመው ግድቡ ላይ ጥናት ሲያደርግ የከረመው የአለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ቡድን ሪፖርት ይፋ መደረጉን ተከትሎ የግብፅ ፖለቲከኞች የተለያዩ አስተያየቶችን እየሠጡ ይገኛሉ፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ ባለፈው ሰኞ ከተለያዩ ፖለቲከኞች ጋር በግድቡ ዙሪያ ያደረጉት ንግግር በሁለቱ አገሮች መካከል ባለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይ ውጥረት ማስፈኑ አልቀረም፡፡

በግብፅ ፓርላማ ሀያ አምስት በመቶ መቀመጫ ያለው ፓርቲ መሪ የሆኑት ዩኑስ ማክኖን በሰጡት አስተያየት፤ ግብፅ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያመፁ ወገኖችን በመደገፍ ግድቡን ማፍረስ አለባት ያሉ ሲሆን መጀመሪያም ግድቡ እንዳይሠራ ግብፅ አለመቃወሟ ስትራቴጂካዊ ስህተት ነው ሲሉ ተችተዋል። “ኢትዮጵያ በመንግስት ላይ ባመፁ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ የተዳከመች በመሆኗ ከታጣቂዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠርና ድጋፍ በመስጠት ግድቡን እንዳትሠራ በመደራደርያ ልንጠቀምበት እንችላለን” የሚል አስተያየት የሰነዘሩት ዩኑስ፤ ሙከራው ካልተሳካ ግብፅ ያላት ብቸኛ አማራጭ የሰለላና ደህንነት መረጃን በመጠቀም ግድቡን ማውደም ነው በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል - ቀጥታ በተላለፈ የቴሌቪዥን ስርጭት፡፡ የውይይቱ ተሳታፊ ሌላው ፖለቲከኛ አይመን ኑር፤ ግብፅ ግድቡን ለማውደም የሚያስችላት አውሮፕላኖችን እንዳዘጋጀች የፈጠራ ወሬ በማሰራጨት ኢትዮጵያ ግድቡን ከመስራት እንድትቆጠብ ማድረግ ይቻላል ቢሉም የዋስ ፓርቲ መሪ አቡ አል ኢላማዲ ሃሳባቸውን አጣጥለውታል።

አቡ አል “ኢትዮጵያን የሚያስፈራራ የውሸት ወሬ ማሰራጨት ኢትዮጵያውያን በግብፅ ላይ እንዲተባበሩ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም” ብለዋል - የፓርቲው መሪ፡፡ ማግዲ ሁሴን የተባሉ ፖለቲከኛ ግን የሁለቱንም ሃሳብ አልተቀበሉትም። በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሠድ በሚለው ሃሳብ ላይ መነጋገር እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው ያሉት ፖለቲከኛው፤ ውጤቱ ኢትዮጵያውያን ጠላት ማድረግ ስለሆነ ጉዳዩ በዲፕሎማሲ ቢያዝ የተሻለ ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በፕሬዚዳንቱ የተመራው ስብሰባ በቀጥታ እንደሚሰራጭ መረጃው ያልነበራቸው የግብፅ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የህዳሴ ግድብ ለማሰናከል የሰነዘረችው ሃሳቦች ከተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡበት ይገኛል። የ“ፍሪ ኢጂፕት” ፓርቲ መሪ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት አሞር ሃምዛዊ ከፕሬዚዳንቱ ጋር የተደረገው ውይይት ለግብፅ ኪሳራ ነው ብለዋል፡፡

“ችግሩ የተፈጠረው ስብሰባው በቀጥታ በመተላለፉ ሳይሆን አንዳንድ ተሳታፊዎች ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ የጀምስ ቦንድን ሚና ለመጫወት ባደረጉት ጥረት ነው” ያሉት ሃምዛዊ፤ “ግብፅ እስከ ስብሰባው እለት ድረስ የምትታወቀው ከፍተኛ በሆነ የውሀ ችግር የምትጨነቅ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚደርሳት የውሀ መጠን በላይኛው የተፋሰስ አገር ችግር እንደተጋረጠባት አገር ነበር፤ አንዳንድ የፖለቲካ ሀይሎች በሰነዘሯቸው አስተያየቶች ግን በጎረቤት አገሮች ላይ ወታደራዊ ጥቃት ለመፈፀም እንደተዘጋጀች አገር መስላ ቀርባለች፤ ይህ ደግሞ የህግ እና የፖለቲካ መዘዝ ያመጣል” ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺንም “የግብፅ ፖለቲከኞች የህዳሴ ግድቡን ለማውደም በይፋ ተናገሩ” በሚል ርዕስ በፅሁፍ ባሰፈሩት አስተያየት፤ “ፖለቲከኞቹ ንግግር ሲያደርጉ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት መታየቱ፤ የዓመቱ ዋነኛ ህዝብ ግንኙነት ኪሳራ ነው” ብለውታል፡፡ ፕሮግራሙ በቀጥታ መተላለፉን በተመለከተ የፕሬዚዳንት ሙርሲ አማካሪ በሰጡት መግለጫ፤ ስብሰባው እንዲካሄድ የተወሰነው በአስቸኳይ ባለቀ ሠአት በመሆኑ በቀጥታ ስርጭቱ እንዲተላለፍ የተወሰነውም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ነው” በማለት ለተሳታፊዎቹ ቀጥታ እንደሚተላለፍ ባለመናገራቸው ለተፈጠረው ሁሉ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ይቅርታውን “የዓመቱ ግድየለሽ አነጋገር” ሲሉ ነቅፈውታል፡፡ በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ከአዲስ አድማስ ተጠይቀው፤ ላልተወሰነ ጊዜ መግለጫ እንደማይሰጡ ያስታወቁ ሲሆን በስብሰባው ላይ በተሠነዘሩ አስተያየቶች መደንገጣቸውን አንዳንድ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ “እንዲህ አይነት ንግግሮችን በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ማስተላለፉ ለምን አላማ ነው ብዬ ካይሮ ደወልኩ” ያሉት አምባሳደሩ፤ ስብሰባውን በቴሌቪዥን እየተከታተልኩ በሆነው ነገር ራሴን ማመን አልቻልኩም ነበር፡፡

በጣም መጥፎ አጋጣሚ ነው፤ የተሳሳተ ስሌት ውስጥ ከምንገባ ጉዳዩን በሠከነ መንገድ በብልሀት ማየት ነበረብን” ብለዋል፡፡ በስብሰባው ላይ ያልተገኙት የናሽናል ሳልቪሽን አስተባባሪ መሀመድ አል ባራዲ፤ ፕሬዚዳንት ሙርሲ በመሩት ስብሰባ ላይ የተነገሩ ሀላፊነት የጎደላቸው ንግግሮችን በተመለከተ ኢትዮጵያዊያና ሱዳንን፣ በግብፃውያን ስም ይቅርታ እንዲጠይቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሙርሲ በስብሰባው ላይ በተንፀባረቁሱ አስተያየቶች ዙሪያ አቋማቸውን ባይገልፁም በማጠቃለያ ንግግራቸው፤ የኢትዮጵያ ግድብ የሚያመጣቸዉ ተፅዕኖዎች በቅጡ እንዲታዩ እንደሚፈልጉ፣ ግብፅ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደምታከብርና ወደ ጦርነትም እንደማትገባ ገልፀዋል፡፡ በፅህፈት ቤታቸው በኩል የተሠጠ መግለጫ ደግሞ የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሮች፤ ግድቡ በግብፅ የውሀ ኮታ ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖ ከኢትዮጵያ መንግስት መረጃዎችን እንዲያመጡ መወሠኑንና ግብፅ ታሪካዊውን የውሀ ድርሻዋን ለማስጠበቅ ሁሉንም አማራጭ እንደምትጠቀም ተጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ባወጣው መግለጫ፤ በግብፅ ፖለቲከኞች ያልተጠበቀ ቂም አዘል ንግግር መንግስትና ህዝብ እጅግ አዝነዋል ብሏል። በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር የመንግስታቸውን አቋም እንዲያብራሩ ተጠይቀው ምላሻቸው እየተጠበቀ ነው፡፡ኢትዮጵያ አሁንም በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዋን ታራምዳለች ብሏል” የአለም አቀፍ የኤስፐርት ቡድኑ ውጤት ምንም የሚቀይረው ነገር አይኖርም፡፡

የሚስተካከል ነገር ካለ ኢትዮጵያ በቀናነት ታየዋለች፡፡ ዋናው ግብፆች የሠጥቶ መቀበል መርህን ማክበራቸው ላይ ነው በማለት የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሰሞኑን በተካሄደው የአረብ ሊግ የውሀ እና የመስኖ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ዋና ትኩረት የተሰጠው ሲሆን በግብፅ በኩል በተንፀባረቀው አስተያየት፤ “ከናይል ውሀ አንዲት ጠብቃ መቀነስ የለበትም፡፡ ይህን ታሪካዊ መብት የሚለውጥ ነገር ከመጣ ማንኛውም አማራጭ ግምት ውስጥ ይገባል” ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ግድብ በናይል ወንዝ ላይ መንገድ የቀረየ ታሪካዊ ለውጥ ነው ያሉት የግብፅ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አሚር ሙሳ፤ “ኢትዮጵያ የግብፅን፣ ግብፅም የኢትዮጵያን ጥቅም በማስጠበቅ መንፈስ መስራት አለባቸው፡፡ ግብፅ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ስምምንት ውስጥ መግባት አለበት” በማለት አሳስበዋል፡፡

በግብፅ የሱዳን አምባሳደር ከማል ሀሰን አሊ “ሱዳን የግድቡን ግንባታ ትቃወማለች” በሚል ሰጥተዋል የተባለውን አስተያየት የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚ/ር አስተባብሏል፡፡ የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቡ-በከር አል ሲዲግ፤ “ሱዳን ይህን አይነት አቋም የላትም፤ የሱዳን የውሀ ሀብት እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የውሀው አቅጣጫ መቀየር በሱዳን ላይ የሚያመጣው አደጋ እንደ ሌለው አረጋግጧል፡፡ ከኢትዮጵያ እና ከግብፅ ጋር በመተባበር ውሀውን ለጋራ ጥቅማችን እናውላለን” ብለዋል፡፡ በግብፅ የሱዳን አምባሳደር ኦናዱሉ ኤጀንሲ በበኩላቸው፤ ጋዜጠኛ ያላልኩትን በመጥቀስ ነው ዜናውን ያሰራጨው በማለት አስተባብለዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ግብፅ ከዚህ ቀደምም ያልተሳኩ ሙከራዎች ማድረጓን በማስታወስ በግብፅ ፖለቲከኞች የተሠጠውን አስተያየት “የቀን ህልም” በማለት አጣጥለውታል፡፡ በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚ/ር በኩል በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር የመንግስታቸውን አቋም እንዲያሳውቁ ተጠይቀው ምላሽ እየተጠበቀ ነው፡፡ የዲፕሎማሲው አቅጣጫ ይቀየር ይሆን?

Read 4934 times