Print this page
Wednesday, 12 June 2013 14:16

ልክ እንደ እናት

Written by  ነ.መ
Rate this item
(5 votes)

አገሬን አገሬ እምላት
“በባዶ እግርህ አትሂድ
ሲሚንቶው ይቀዘቅዝሃል” ያለችኝ’ለት
…ልክ እንደእናት፡፡

አገሬን አገሬ እምላት
“ባዶ ሆድህን ነህኮ
እህል ባፍህ ይዙር እንጂ!”
ያለችኝ’ለት
…ልክ እንደእናት፡፡

አገሬን አገሬ እምላት
“የውሃውን ደረሰኝ
ደህና ቦታ አስቀምጥ ኋላ
ከጠፋ ጣጣው ብዙ ነው!”
ያለችኝ ለት
…ልክ እንደ እናት

አገሬን አገሬ እምላት
“የመብራቱን ደረሰኝ ያዝ”
ከጠፋ ጣጣ ነው ኋላ”
ያለችኝ’ለት
…ልክ እንደእናት

አገሬን አገር የምላት
በሩን መለስ አድርገው
አባትህ አልገባም አደል?
ውሃው አልተዘጋም እየው፤
“ወንድምክን አንዳፍታ እቀፈው”
ያለችኝ’ለት
ልክ እንደእናት!
አገሬን አገር የምላት
“ጐረቤትህን ጥራ እንጂ
ቤት ያፈራውን ብሉ
ያላችሁን ተካፈሉ
ለብቻ መብላት መጥፎ ነው
ኋላ “ከልጅ ልጅ ቢለዩ
አንድ አመትም አይቆዩ!”
ያለችኝ’ለት
ልክ እንደእናት

አገሬን አገር የምላት…
ለእኔ ስትል ከጐረቤት
ስትጣላ ያየኋት’ለት
…ልክ እንደእናት፡፡
ልጄ መጋኛ እንዳይመታህ
በጣይ አትሂድ እየበላህ
…ካንተ በላይ ቆንጆ የለም
ለእገሌ ልጅ ነው ‘ምድርህ
በል ፀጉርህን አበጥር
በል ዩኑፎርምህን ልበስ…

አገሬን አገር የምላት
“እህትህን እያየሃት
ጐረምሶች እንዳይጠይቋት
ደሞ ዳርዳሩን ሂዱ
ብቻዋና እንዳትተዋት”
ያለችኝ’ለት…ልክ እንደእናት፡፡
አገሬን አገር የምላት
ኪስህን ሰብስብ እንጂ
እሰው ኪስጋ ድርሽ አትበል
የሰው ሀቅ ያንቃል ይባላል
እጅህ ይፁም ያለችኝ’ለት
ልክ እንደእናት፡፡
አገሬን አገር የምላት
ከምድጃዋ ዳር ስታፍሰኝ
ከፈላ ውሃ ስታርቀኝ
በፍቅር አክናፍ ስትከልለኝ
በወሊድ ምጥ ማጣሯ አንሶ፣ ከኑሮ ምጥ ልታወጣኝ፤
ሽል ደሜን ማማጧ ሳያንስ፤
በቁም -ስቅል ልታሳድግ
ቁም - አካሌን ስታምጠኝ፡፡
የእናት ምጥ ያገር ነውና
ያገር ምጥ የእናት ነውና፤

ኃያል ሳይሸልል ሳይፎክር
ደካማው ሳያቀረቅር
በግፍ የማትደፈር እት
በሳግ የማይደፋ ግት
ልጅ ማሳደግ የማይሰቃት
በባል እማታለቅስ ሚስት
በአባት የማትናቅ እናት
የኖረኝ እለት፡፡
ያኔ ነው እኔ በወጉ፣ እናቴን አገሬ’ምላት፡፡
ያን ግዜ ነው እኔ በውል፣ አገሬን እናቴ ‘ምላት!!
ከእናቴ ጡት ወደ አገር ጡት፤ መሸጋገሬን እማቀው
እሷም ልጄ የምትለኝ፣ እኔም እናትዬ ‘ምላት
ያኔ ነው የእናት ቀን በውነት’!!
ቆይቼ ግን ሳስበው
አገሬን አገሬ እምላት
እናቴን አባቴ ብዬ በሷ የተጠራ ሁኝ ‘ለት!!
ለእናቶች ቀን እና ለእናቴ
2005 ግንቦት 21

Read 4095 times