Saturday, 15 June 2013 09:00

የ2ሚ. ብር መጋዘን ያለአግባብ ፈርሶብኛል ሲሉ አንድ ባለሀብት አማረሩ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ግንባታው ህገ-ወጥ በመሆኑ ሊፈርስ ችሏል” የወረዳ 11 ፍ/ፅ/ቤት

                    በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 11 ውስጥ ጥቁር ድንጋይ ለማምረት የ7 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው በስራ ላይ የሚገኙት የደረጀ በለጠ የጥቁር ድንጋይና ገረጋንቲ ማምረቻ ድርጅት ባለቤት አቶ ደረጀ በለጠ ለድርጅታቸው እቃ ማከማቻ ፈቃድ ወስደው የገነቡት የሁለት ሚሊዮን ብር መጋዘን ያለአግባብ ፈርሶብኛል ሲሉ አማረሩ፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ፍትህ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ግንባታው ህገወጥ በመሆኑ ሊፈርስ ችሏል በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን ብር ግብር ከፋይ እንደሆኑ የተናገሩት የድርጅቱ ባለቤት፤ በ70ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታቸው ላይ ለሚያካሂዱት የጥቁር ድንጋይ ማምረት ሥራ ከስራው ጋር ተያያዥነት ያለውና እስከ ድርጅቱ የስራ ዘመን ማብቂያ የሚቆይ ጊዜያዊ ግንባታ አካሂደው እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በ29/06/2004 ዓ.ም የሰጣቸውን የፈቃድ ደብዳቤ አቶ ደረጀ በዋቢነት አቅርበዋል፡፡

ድርጅታቸው ከ80 በላይ ሠራተኞችን ቀጥሮ እንደሚያስተዳድር የተናገሩት ባለሀብቱ፤ አንድም ከህግ ውጭ እንዳልተንቀሳቀሱ ገልፀው፣ አፍርስ ሲባሉ ወደ ህግ በማምራት ከፍ/ቤት የእግድ ትዕዛዝ ማውጣታቸውን ተናግረው፣ ከእግዱ በኋላ በፍ/ቤት ከወረዳው ጋር ክርክር መያዛቸውን ገልፀዋል፡፡ “በክርክሩ ወቅት ሚያዚያ 10 ቀን 2005 ፍ/ቤት ቀርበን ለውሳኔ ግንቦት 21 ተቀጠርን” ያሉት አቶ ደረጀ፤ የፍ/ቤቱ ቀጠሮ ከመድረሱ አንድ ወር በፊት (ሚያዚያ 21 ቀን) ከሳሽና ተከሳሽ በሌሉበት ፍ/ቤቱ እግዱን አንስቷል፣ እንዲፈርስም አዟል በሚል ለውሳኔ በተቀጠረበት ግንቦት 21 ቀን መጥተው መጋዘኑን እና በውስጡ ያለውን ንብረት ያለማስጠንቀቂያ በግሬደር እንዳፈረሱባቸው በምሬት ገልፀዋል፡፡ በቦታው ተገኝተን ለመታዘብ እንደቻልነው መጋዘኑ ከነተሰራበት አይጋ ቆርቆሮ፣ ብሎኬትና ብረታ ብረት ፈርሷል፡፡ “ይግባኝ እንኳን እንዳልጠይቅ እኔ በማላውቀው መንገድ ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሰጥቶ አንድ ወር ሙሉ የውሳኔ ቀጠሮውን እየጠበቅሁ እንድቆይ አድርጐኛል፡፡ በዚህም ሞራሌ ተነክቶና በዜግነቴ ላይ ጥርጣሬ አድሮብኛል” ብለዋል አቶ ደረጀ፡፡

የአቶ ደረጀ ጠበቃ አቶ ደሶ ጨመደ በበኩላቸው፤ ፍ/ቤቱ ግንቦት 21 ቀን ለውሳኔ ቀጠሮ ተሰጥቶ አጀንዳቸው ላይ መመዝገባቸውን ገልፀው፣ ፋይሉን ከቀጠሮው ወር በፊት ማን እንዳንቀሳቀሰው ሳናውቅ ሚያዚያ 21 ቀን ውሳኔ መስጠቱ ግራ አጋብቶናል” ብለዋል፡፡ በቦሌ ክ/ከተማ የወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳቤት መንግስቱ፤ ባለሀብቱ በስራ ላይ እንዳሉ፣ በገነቡት መጋዘን ክርክር ላይ እንደነበሩ እና በፍ/ቤት እግድ ማውጣታቸውን እንደሚያውቁ ተናግረው፣ የፍርድ ሂደቱ በወረዳው ፍ/ጽ/ቤት የሚካሄድ በመሆኑ መረጃ እንደሌላቸው ገልፀውልናል፡፡ “መጋዘኑን አውቀዋለሁ የፈረሰው ህገ-ወጥ ነው ተብሎ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፤ በ2004 ዓ.ም ወረዳው ህገወጥ የሆኑ ግንባታዎችን ማፍረሱንና የአቶ ደረጀ መጋዘንም ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንዲፈርስ ታዞ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በወረዳው የፍትህ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ወይዘሪት አንቀፀ ዮሐንስ በበኩላቸው፤ አቶ ደረጀ ከአካባቢ ጥበቃ ባስልጣን የጥቁር ድንጋይ ማምረት ፈቃድ አውጥተው እንደሚንቀሳቀሱ ገልፀው፤ ወረዳ 11 ውስጥ ያለው ቦታ ሙሉ በሙሉ ሰነድ አልባ መሆኑንና ማንኛውም ግለሰብ ግንባታ ሲያካሂድ ወረዳው የግንባታ ፈቃድ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ አቶ ደረጀ ከወረዳው ፈቃድ ሳይወስዱ በመገንባታቸው መጋዘኑ ሊፈርስ እንደቻለም ሃላፊዋ ገልፀዋል፡፡

ከአካባቢ ጥበቃ ቀጥታ ለወረዳ 11 የተፃፈውን የፈቃድ ደብዳቤ አስመልክተን ላነሳነው ጥያቄ ሃላፊዋ ሲመልሱ፤ አካባቢ ጥበቃ ፈቃድ ሲሰጥ መነሻው ወረዳው ሊሆን እንደሚገባ የገለፁት ወ/ሪት አንቀፀ፤ አካባቢ ጥበቃ የፈቃድ ደብዳቤ ቢጽፍላቸውም የገነቡት ግን የወረዳውን ይሁንታ ሳያገኙ በመሆኑ፣ በፍ/ቤት ክርክሩም ሚያዚያ 21 ቀን ፍ/ቤቱ እግዱ እንዲነሳና መጋዘኑ እንዲፈርስ በመወሰኑ ሊፈርስ እንደቻለ አስረድተዋል፡፡ ለግንቦት 21 የውሳኔ ቀጠሮ ተይዞ እንዴት በአንድ ወር ቀድሞ ውሳኔ እንዳገኘ ተጠይቀው፤ ይሄ የቦሌ ክ/ከተማ ፍትህ ቢሮ ነገረፈጆችን እንጂ እኔን አይመለከትም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የቦሌ ክ/ከተማ ፍትህ ቢሮ የፍ/ቤቱን ነገረ ፈጅ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ግን አልተሳካም፡፡

Read 7621 times