Print this page
Saturday, 15 June 2013 10:14

ይቺ እንዴት ትጨፍራለች? ቢባል፤ ልብስ አጥታ እቤት የቀረችውን ባየህ አለ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

አንዲት የቆቅ ልጅ የስንዴ እሸት ትርክክ ብሎ በስሎ በሚገኝበት እርሻ አጠገብ ወጥመድ ተጠምዶ አይታ እናቷን “እናቴ ሆይ እሸት አምሮኝ ነበር፤ ከዚህ ማሣ ገብቼ እንዳልበላ ወጥመድ እንዳይዘኝ ሰጋሁ ምን ይሻለኛል?” ስትል ጠየቀቻት፡፡ እናቷም፤ “ተይ ልጄ ይቅርብሽ ትያዣለሽ አይሆንም” ብላ መከረቻት፡፡ ልጅቷ ግን “ግድየለሽም አይዙኝም ትንሽ ተክ ተክ አድርጌ ልውጣ” አለቻትና ገብታ ስትበላ ያ ወጥመድ እናቷ እንደፈራችው እግሯን ጥርቅም አድርጐ ያዛት፡፡ መቼም መከራ በመጣ ጊዜ በመጀመሪያ የሚታሰቡት ወላጆች ስለሆኑ፤ ያቺ የእናቷን ምክር አልሰማ ያለች ልጅ፤ “እናቴ ኧረ ተያዝኩልሽ” አለቻት፡፡ እናትየዋም፤ “ምነው ልጄ አስቀድሜ ነግሬሽ አልነበረም? አሁን ምን ላደርግልሽ እችላለሁ?” አለቻት፡፡

እማምዬ እባክሽ እርጂኝ? ፍቺልኝ ገመዱን?” “በምን እጄ?” “ታዲያ እንዴት ልሁን? ምን ይበጀኝ የኔ እናት?” “በዚህ ጊዜ እናት ለልጁዋ ምን ጊዜም ምክር አዋቂ ናትና፤ “ዝም ብለሽ የሞትሽ መስለሽ ተኝ” “ባለወጥመዱ ሲመጣ ሞታለች ብሎ ፈትቶ ይለቅሻል፡፡ ያኔ ታመልጫለሽ” አለቻት፡፡ ልጅ እንደተባለችው አደረገች፡፡

ባለወጥመዱ ሰው ሰብሉን ጐብኝቶ መጣና ቢመለከት ዝልፍልፍ ብላ ተኝታ ዐይኗን ጨፍና አገኛት፡፡ አጅሬ የሞተች መሰለውና “አዬ ጉድ ወጥመዴ ቆቅ ይዞልኝ ነበረ፡፡ ነገር ግን ሞተች” አለና አዘነ፡፡ ጓደኛው ከበላዩ ሰብል ይጠብቅ ነበርና “ወንድም” ብሎ ተጣራ “ወጥመዴ ቆቅ ይዞልኝ ነበረ፡፡ ነገር ግን በክታ አገኘኋት” ባልንጀራውም፤ እስቲ ወደላይ አጉናት” አለው ባለወጥመዱ ወደ ሰማይ ወርወር አደረጋት፡፡ ቆቋ ቱር ብላ ከጫካው ጥልቅ አለች፡፡

                                             * * *

ምክር መቀበልና ማክበር ይገባል፡፡ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችልን ነገር አስቀድሞ ማሰብ፣ ማውጠንጠንና መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ብዙ አደጋዎችን፣ ብዙ ችግሮችን፣ ብዙ ውጣ - ውረዶችን ያየችው አገራችን መከራዋን ትወጣው እንጂ አብዛኛዎቹ የተከሰቱት ምክር በማይሰሙ መሪዎች፣ ኃላፊዎችና ሥራ አስኪያጆች ሳቢያ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የታለፉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አጋጣሚዎች ደግመን ማጣት ከእንግዲህ ብርቱ ዋጋ ያስከፍለናልና ጥንቅቅ ብለን ማሰብ ይገባናል፡፡ የድህነት ነገር ሆኖብን ሁሌ ሥራችንን በዘመቻ እንድንሠራ እንገደዳለን፡፡ አንድን ሥራ በነጥብ መብራት አተኩረን መሥራት ትልቅ ጉልበት በማከማቸት ግብ እንድንመታ ይረዳናል፡፡ ሆኖም ዘላቂና የኔነት ስሜት ያለው ሥራ እንድንሠራ በሙያዊ ብቃት፣ በሥራ ክፍፍልና በሙሉ ስሜት እንድንራመድ ካልሆነ ለብዙ ችግር እንጋለጣለን፡፡ ጦርነትም ቢሆን እንኳ በኃይል በኃይሉ፣ በክህሎት በክህሎቱ ሲሰደር ነው ለግብ ይበቃል የሚባለው፡፡ የጋራ ጥቅም ላይ ያነጣጠሩ መስሎ የግል ጥቅምን በጐን ማሳደድ ሊነቃበት የሚገባ ጨዋታ ነው፡፡ “ሌላ ጊዜ አንቺ ይላል፤ ጠላ ስትጠምቅ እሜቴ ይላል” የሚለውን የወላይታ ተረት ከልብ ማስተዋል ዋና ነገር፡፡

መቼም የሀገራችን ነገር አንዱ ሲወርድ አንዱ ሲወጣ ያለበት ነው፡፡ ከሥራውም ይልቅ ሰውዬውን ለሚያይ ዘላቂነት ያለውና ያለፈውን ስህተት ለማረም የቻለ ጉዞ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ የሠራተኛው፤ የፓርቲ አባሉ፣ የበታች ኃላፊው ሁሉ፣ ሁልጊዜ “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው” የሚልበት ዘመን ያከተመ ይመስላል፡፡ “ተሰናባች አይርገምህ፤ ተተኪው አይጥላህ” የሚለውን በጥንቃቄ ካዩት ትርጉም ያለው ቁምነገር ያስጨብጠናል። ተሰናባች በግፍ፣ በምቀኝነት ወይም በአድልዎ ተባሮ ከሆነ እርግማኑ ይደርስብኛል ብሎ ማሰብ የአባት ነው፡፡ ተተኪው በተንጋደደ ዐይን የሚያይ ከሆነና “ለዚያኛው ያልተኛ እኔን አይምረኝም” ብሎ ያሰበ ከሆነም ሲሰጉ መኖር ነው፡፡ ከዚህም ይሰውረን፡፡

የሚመጣውን ሁሉ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያለ ነው፡፡ ጣር መጣ ጦር መጣ እያሉ በጣም ያስፈራሩት ጀግና፤ በዝግታ እየተዘጋጀ፤ “ይምጣ ከመጣ ሞቼ ልጠብቀው እንዴ ልዘጋጅ እንጂ!!” አለ የሚባለውንም አንዘንጋ፡፡ ጉዳዩን የሚያቅ፤ የበሰለ፣ ባለገድልና ባለታሪክ ሰዋችንን አንናቅ፡፡ ከየቦታው ሰብስበን ሥራ ላይ እንዲቀመጥ እናድርግ፡፡ ልታይ ልታይ የሚለውንና የአደባባይ ጌጥ የሆነውን ትተን፤ ከልቡ ለሀገር የሚያስበውን እናስተውል፡፡ “ይቺ እንዴ ትጨፍራለች?” ቢባል፤ “ልብስ አጥታ እቤት የቀረችውን ባየህ!” አለ፤ የሚባለው የወላይታ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡

Read 3899 times
Administrator

Latest from Administrator