Saturday, 15 June 2013 10:28

ዓለም ኢትዮጵያን እንዴት አያውቃትም!?

Written by  ገ/ሚካኤል ገ/መድህን (በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የዶክመንተሪ ፕሮግራሞች ከፍተኛ ኤዲተር)
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ የት እንዳለች የማያውቁ የአፍሪካ ጋዜጠኞች ገጥመውኛል... የሰው ዘር መገኛ ኢትዮጵያ ናት ኬንያ?

በቅርቡ ለጋዜጠኞች በተዘጋጀ ስልጠና ለመካፈል ወደ ናይሮቢ ኬንያ ተጉዤ ነበር፡፡ በእርግጥ የመጀመሪያዬ አልነበረም፡፡ ግን ይህኛው ለየት ያለ ነገር ነበረው፡፡ አጋጣሚው ከአርባ አምስት የአፍሪካ ሃገራት የመጡ በርካታ ጋዜጠኞችን አሰባስቧል፡፡ ሁሉም ስለ ሃገሩ ይናገራል፣ ስለሌላውም ይጠይቃል፡፡ እኔም እንዲሁ ከሚጠይቁትና ሃገራቸውን ከሚያስተዋውቁት መካከል አንዱ ሆንኩኝ፡፡ ምናልባት ወደ ሃምሳ ጋዜጠኞች ይሆናሉ የተጋበዙት፡፡ ከኢትዮጵያ እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ሞቅ ያለ ውይይትና ትውውቅ እናደርጋለን፣ ሃሳብ እንለዋወጣለን፡፡ አብዛኞቹ ስለ ኢትዮጵያ ለማወቅ የነበራቸው ጉጉት ገርሞኛል፡፡

እኔ ኢትዮጵያን በሚገባ ያውቋታል ብዬ ሳስብ በተቃራኒው ምንም ዓይነት መረጃ የሌላቸው ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡ በዚህ ቆይታዬ ጋዜጠኞቹ ስለ ኢትዮጵያ ያላቸው ግንዛቤ ምን እንደሚመስል መረዳት ችያለሁ፡፡ በዚህች አጭር ፅሁፌ ከጋዜጠኞቹ የታዘብኩትን ላጋራችሁ እወዳለሁ፡፡ በናይሮቢ ያሰባሰበን ድርጅት ፓን-አፍሪክ በሚባል ጉደኛ ሆቴል የእራት ግብዣ አደረገልን። የመዝናኛ ፕሮግራምም ነበረው፡፡ የመድረክ መሪው ኬንያን ለማስተዋወቅ ይጠቀምበት የነበረው መንገድ በጣም ይገርማል፡፡ አፍሪካ ያለ ኬንያ ምንም አይደለችም የሚያስብል ነበር፡፡ ‹‹የሰው ዘር መገኛ ወደ ሆነችው ኬንያ እንኳን በሰላም መጣችሁ›› ብሎ ጀመረ፡፡

‹‹ዓለም በዚህ ብቻ አይደለም የሚያውቀን። ውብ የሆነው የእንግዳ ተቀባይነት አፍሪካዊ ባህልም መፈጠሪያው እዚህ ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ወደየሃገራችሁ ስትመለሱ ለዓለም ህዝብ ስለዚህ ውብ ኬንያዊ ባህል እንደምትመሰክሩ…….››እያለ ቀጠለ፡፡ ወይ ጉድ አልኩኝ በውስጤ፡፡ በተለይ የሰው ዘር መገኛ የሚለው አባባሉ በጣም ከነከነኝ፡፡ ይህ የታሪክ ሽሚያ ነው ወይስ የሳይንሳዊ መረጃ መፋለስ። ይህን አባባል እኛ በሰፊው እንጠቀምበታለን፣ ኬንያውያንም እንዲሁ፡፡ ዓለም ማንኛችንን ይመን? በዚህ ሆቴል እራት እየበላን ነው፡፡ ከፊት ለፊቴ ማላዊትዋ ሰሊና ተቀምጣለች፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የምታውቀውን ትናገራለች፡፡ እኔን ጨምሮ ብዙ ጋዜጠኞች እንሰማታለን፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በራስታዎች ትታወቃለች፡፡ በጃማይካና በሌላውም ዓለም የሚገኙ ራስታዎች የህይወት ዘመን ምኞታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ሄደው መኖር ነው፡፡ በራስ ተፈሪ ያመልካሉ፣ ነብያችን ናቸው ይሉዋቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ አፄ ሃይለስላሴ በማላዊ በጣም ይታወቃሉ፡፡

ዋናው መንገዳችን በሳቸው ነው የተሰየመው፡፡ ኮረብታ ላይ የተገነባ አንድ በጣም ጥንታዊና የሚያምር ሆቴልም በሳቸው ስም ይጠራል›› አለችን፡፡ ይህኛው ታሪክ በጣም ተመቸኝ፣ ከዛም አልፎ ሲበዛ አስደነቀኝ። በሃገራቸው አንድም ማስታወሻ የሌላቸው ንጉስ በሰው ሃገር ብዙ ይባልላቸዋል፡፡ እኔም በተራዬ አንድ ጥያቄ ሰነዘርኩላት ‹‹ባለፈው ዓመት የተሾመችው ፕሬዚዳንታችሁ እንዴት እየሰራች ነው፣ እስቲ ስለሷ ንገሪኝ? በሐምሌ 2004 ዓ.ም ማላዊ መካሄድ የነበረበት የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በሃገሬ አይካሄድም በማለቷ በአዲስ አበባ ተደረገ፡፡ ይህ የሆነው የሱዳኑን ፕሬዚደንት አልበሽርን ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አሳልፌ ነው የምሰጠው በማለቷ ነበር፡፡

እሷ ግን ለአፍሪካ ህብረት ህገ ደንብ አትገዛም ማለት ነው?›› አልኳት። ሰሊና ስትመልስም ‹‹ምን መሰለህ አንደኛ ነገር ባለቤቷ የፍትህ ሚኒስትር ነው፡፡ ስለዓለምዓቀፍ ህግ ጠንቅቆ ያውቃል፣ በዚህ ላይ ዋና አማካሪዋ ነው፡፡ ማላዊ ለዓለም አቀፉ ፍርድቤት ፈርማለች፣ ስለዚህ አልበሽር እዛ ቢገኝ አሳልፋ ነው የምትሰጠው፡፡ እዚህ አበሳ ውስጥ ከመግባት ግን ስብሰባው ማላዊ ውስጥ እንዳይካሄድ ማድረግ ተመራጭ ነበር፡፡ ሁለተኛ ለአፍሪካ ህብረት ህገ-ደንብ ተገዢ አትሆንም ወይ ላልከው ተገዢ መሆን የለባትም። የአፍሪካ ህብረት እኮ የአምባገነኖች ስብስብ ነው። አስበው እስቲ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ያረደው መንግስቱ ሃይለማርያም እኮ ዚምባብዌ ውስጥ ነው የመሸገው፡፡

የአፍሪካ ህብረት ለአፍሪካ ህዝቦች ፍትህና ብልፅግና የቆመ ተቋም ቢሆን ኖሮ ሮበርት ሙጋቤን አሳምኖ መንግስቱን ለፍርድ ያቀርበው ነበር፡፡ ግን አላደረገውም፡፡ ስለዚህ አፍሪካ ህብረት ማለት ህዝባዊ ሃላፊነት የማይሰማቸው ሰዎች ተሰባስበው የገነቡት ተቋም ነው›› አለችኝ፡፡ እውነቷን ነው፣ በዚህ አባባሏ በከፊል እስማማለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ አህጉራዊው ተቋም ብዙ የቤት ስራ እንደሚቀረው አምናለሁ፡፡ ታንዛኒያዊው ኪዜቶ የዛምቢያው አሮንን ስለ ኢትዮጵያ ያጫውተዋል፡፡

በመሃል ተቀላቀልኩዋቸው፡፡ አንድ ጥያቄ ጠየቀኝ ‹‹አሁን አንድ መፅሃፍ እያነበብኩ ነው፣ አርዕስቱ ‘ዘ አፍሪካን ስቴትስ’ ይላል፡፡ እዛ መፅሃፍ ላይ መንግስቱ ሃይለማርያም የ1977ቱን ድርቅ ለዓለም ህዝብ ለመንገር ፈቃደኛ እንዳልነበር አንብቤያለሁ። በጣም አዘንኩ፣ ለምን ግን መደበቅ ፈለገ?››፡፡ ጉዳዩ የፖለቲካ ጨዋታ እንደነበር መለስኩለት፡፡ ‹‹ለመንግስቱ ሃይለማርያም ፖለቲካው እንጂ የህዝቡ መራብ ጉዳዩ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ተርባለች ብሎ ማወጅ ለእሱ ውርደት ነበር፣ እናም አይኑ እያየ ብዙ ህዝብ አለቀ፡፡ የአምባገነን መሪዎች አንዱ መገለጫ ይህ ነው፣ የሚኖሩት ለህዝቡ ሳይሆን ለራሳቸው ዝናና ክብር ነው›› አልኩት፡፡ የደቡብ አፍሪካዋ ካትሪን ቀጠለች ‹‹ያኔ እነ ቦብ ጌልዶፍ ባይደርሱላችሁ ኖሮ እርግጠኛ ነኝ ታልቁ ነበር፡፡

ጌልዶፍና ቦኖ ባዘጋጁት ኮንሰርት ብዙ እርዳታ አሰባስበዋል፣ ሚሊዮኖችን እንደታደጉም እገምታለሁ›› አለችኝ፡፡ እሷ ባለችው ተስማማሁ፡፡ያ የዕርዳታ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ያስከተለውንም መዘዝ እያሰብኩኝ፡፡ እውነቷን ነው፣ የጌልዶፍ የዕርዳታ ጥሪ 150 ሚሊዮን ፓወንድ በማሰባሰብ በርካቶችን ከሞት ታድጓል፡፡ ግን ደግሞ የታላቋን ሃገር ስምና ዝና ለዘላለም እንዳጎደፈው ማን በነገራት አልኩኝ በውስጤ፡፡ ዓለም ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያን የሚያውቃት ይኸው ሰውዬ ባዘጋጀው ኮንሰርት ላይ በመላው ዓለም በቴሌቪዥን መስኮት በአራት መቶ ሚሊዮን ህዝብ ዘንድ በደረሱ የተራቡ ህፃናት ምስል ነው፡፡ ከያኔው ጀምሮ ኢትዮጵያና ረሃብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆነው ይጠራሉ፡፡ ከ1958-1961 ዓ.ም ባጋጠመው በታላቁ የቻይና ረሃብ ወደ 43 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ቢያልቁም የቻይና ስም ግን የኢትዮጵያን ያህል አልጎደፈም፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ምነው በቀረብን እላለሁ፡፡

ውይይታችን ቀጠለ፣ ጨዋታውም ደርቷል። ሁሉም በየተራ ይናገራሉ፡፡ ሂልማ የናሚቢያ ጋዜጠኛ ነች፡፡ ሃገሯን ለማስተዋወቅ የነበራት ጉጉት የሚገርም ነበር፡፡ በደንብ ተዘጋጅታ መጥታለች። በሃገሯ የሚታተሙ ጋዜጦች፣ የተለያዩ ፅሁፎችና የናሚቢያ የቱሪስት መስህብ የሆኑ አካባቢዎችን የሚያስተዋውቁ ብሮሸሮች ሰጠችን፡፡ በፎቶና ቪድዮ የተደገፈ የማስተዋወቅ ስራ በማከናወን ሁላችንም ስለ ናሚቢያ የተወሰነ ግንዛቤ እንዲኖረን አድርጋለች፡፡ ሂልማን ስለ ኢትዮጵያ የምታውቀው ነገር ይኖር እንደሁ ጠየቅኳት፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ነው የምትገኘው?›› በማለት ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰችልኝ፡፡ የአፍሪካ መዲና የሆነችውን ሃገር እንዴት አታውቃትም ብዬ ራሴን ጠየቅሁ። ከዚህ በኋላ ማድረግ የነበረብኝ ነገር የቻልኩትን ያህል ስለ ኢትዮጵያ መንገር ነው፡፡

በዚህ ቆይታችን ጥሩ ግንዛቤ እንዳገኘች ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከጎኔ የተቀመጠው ኡጋንዳዊ ጋዜጠኛ ፒተር በአዲስ አበባ ከጓደኞቹ ጋር ሲዝናኑ ስላጋጠማቸው ሁኔታ ሊነግረኝ ጓጉቷል፡፡ እስቲ ልስማው ብዬ ጆሮ ሰጠሁት፡፡ አብረውን የተቀመጡ ሰባት ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ ፒተር ቀጠለ ‹‹በአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ሄደን ነበር፡፡ አልጋ የተያዘልን ሒልተን ሆቴል ነው፡፡ መሸትሸት ሲል ከሂልተን ሆቴል አራት ሆነን ለመዝናናት ወጣን፡፡ በሩ ጋ ስንደርስ የጎዳና ተዳዳሪዎች የሆኑ ህፃናት አገኘን፡፡ ከሌላ ሃገር እንደመጣን ወድያውኑ ለዩን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ችግር ይሄ ነው፣ መመሳሰል አይቻልም፣ ማንም ሰው አይቶ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆንክ በቀላሉ ይለይሃል፡፡ እነዚህ ህፃናት በዝቅተኛ ዋጋ የምንዝናናበት ቦታ ሊያሳዩን እንደሚፈልጉ ነገሩን፣ ተስማምተን ሄድን፡፡

የሆነ ጊቢ ውስጥ አስገቡን፣ መብራቱን አጠፉት፣ ከሁሉም አቅጣጫ ወሮበሎች ተሰባሰቡና የያዝነውን በሙሉ ዘርፈው አስወጡን፣ ይህን አጋጣሚ መቼም አልረሳዉም›› አለ፡፡በመሃል እኔ ቀጠልኩ ‹‹ኢትዮጵያ የነፃነት ሃገር ነች ስላችሁ ገነት ነች ማለት አይደለም፡፡ አልፎ አልፎ ችግር ያጋጥማል፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ እናንተ ዓይነት እንዝላልነት ሲታከልበት ነገሩ የከፋ ይሆናል፡፡ሁሌም እንግዳ የሆነ ሰው የተወሰነ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት እገምታለሁ፡፡ እንዴት የማላውቀውን ሰው ተከትዬ ናይሮቢ ወዳሉት መዝናኛ ቤቶች እሄዳለሁ›› አልኩት፡፡ ሁሉም ተስማሙ፡፡ ፊሊፕ ኬንያዊ ነው፣ ከዚምባብያዊ ጓደኛው ማርኮ ጋር ይጫወታል፡፡ ስለ ኢትዮጵያውያን ቆነጃጅት አውርቶ የሚጠግብ አይመስለኝም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የቆነጃጅት ምድር ነች፣ እዚህ የምታያቸው ጋዜጠኞች ሁሉ አዲስ አበባን ቢያዩዋት ኖሮ ቤታቸውን እዛ ይገነቡ ነበር፡፡ ልንገራችሁ የዓለም ቆንጆ ያለው አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ Addis is a home of love. አዲስ አበባ የፍቅር ሃገር ነች፡፡ የአፍሪካ መዲና መሆኗ ይገባታል፡፡

ብዙ የሚያዝናኑ ነገሮች አሏት……›› እያለ ስለ ኢትዮጵያ በጎ ነገሮች መናገሩን ቀጠለ፡፡ እኔም ተቀብየው ቀጠልኩ፡፡‹‹ፊሊፕ እንዳለው ኢትዮጵያ የውበት መንደር ነች፣ የዓለም ቆነጃጅት መኖሪያም ጭምር፡፡ የዋህና እንግዳ አክባሪ፣ በታሪኩና በማንነቱ የሚኮራ፣ ለአፍሪካውያን ነፃነት፣ ደህንነትና ብልፅግና የሚተጋ ህዝብ አላት፡፡ አዲስ አበባ የፍቅር፣ የህይወትና የነፃነት ከተማ ነች። Welcome to Addis Ababa: a City of Love, Life and Freedom ብዬ የጉብኝት ግብዣ አቀረብኩላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነፃነት በእጅጉ የሚያኮራ እንደሆነ አፌን ሞልቼ መናገር ችያለሁ፡፡ ሃገራችን ወንጀል እምብዛም ያልተበራከተባት ስለሆነች ከየትኛውም የዓለም ክፍል የመጡ እንግዶች በነፃነት ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ኬንያዊቷ ጋዜጠኛ በአንድ ወቅት ስትነግረኝ ‹‹ናይሮቢ ውስጥ እየሄድክ ስልክ ቢደወልልህ በነፃነት ማውራት አትችልም፡፡ የሆነ ቦታ ተደብቀህ ነው የምታናግረው፡፡

አዲስ አበባ ግን በነፃነት የፈለከውን ያህል ታወራለህ፣ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ምንም ያህል ብትዞር ወንጀል እስካልሰራህ ድረስ ሃይ ባይ የለህም፡፡ ለእኔ ነፃነት ማለት ይህ ነው››ብላኛለች፡፡ እውነቷን ነው፣ ናይሮቢ ውስጥ የውጭ ሃገር ዜጎች ያለ ፓስፖርት መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ ፖሊስ ያስቆማቸውና ይጠይቃቸዋል። ከሌላቸው የሆነ ጉራንጉር ውስጥ ወስዶ ያላቸውን ዘርፎ እስር ቤት ያስገባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በዚያች ሃገር የመንቀሳቀስ ነፃነት ያለ ህግ የተገደበ ነው፡፡ ኡጋንዳዊው ጌራልድ ስለ ኢትዮጵያ የተወሰነ እውቀት አለው፡፡ ‹‹የህዳሴው ግድብ ግንባታ እንዴት እየሄደ ነው?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ ግንባታውን እያፋጠነው እንደሆነ ነገርኩት፡፡ ቀጠለ ጌራልድ ‹‹ግብፆቹ ደግሞ በጣም እየተንጫጩ ነው፡፡ ውሃውን ለብቻቸው እንዲጠቀሙበት ነው የሚፈልጉት›› አለኝ። ትክክል ብለሃል፣ ወንዙን ላለፉት በርካታ ዓመታት እንዳደረጉት ሁሉ ለብቻቸው ለመጠቀም ይፈልጋሉ፡፡ ለዛ ነው ነጋ ጠባ የሚንጫጩት። ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው እነሱንም ለመጥቀም ነው፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚመነጨው ሃይል ለነሱም ይደርሳል፡፡ ይህን ውሃ ለሃይል ማመንጫነት ነው የምንጠቀምበት፡፡ ውሃው ሃይል አመንጭቶ እንደተለመደው ወደ ግብፅ ይሄዳል። ስለዚህ ተቃውሟቸው ብልሃት ይጎድለዋል ብዬ ውስጤ የነበረውን ንዴት ጭምር ተነፈስኩለት፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በመለስ ዜናዊ አመራር በጣም ተራምዳለች፣ ሁሌም ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገርመኝ አንድ ነገር አለ፡፡ እንሰራለን ካሉ በአንድ ልብ ተነሳስተው ይሰራሉ፣ ለለውጥ ይነሳሉ። በእኛ ሃገር የሌለው ይህ ነው፡፡ ህዝቡ በጣም የተከፋፈለ ነው፣ አንድ ሆኖ አያውቅም፣ በዚህ መልኩ ኡጋንዳን ማሳደግ የምንችል አይመስለኝም›› አለ፡፡ ለጌራልድ ያለኝን አድናቆት ገልጬ ወደ ኬንያዊው ጋዜጠኛ ሄድኩኝ፡፡ ኬምቦይ ይባላል፡፡ በዚህ ጉዞዬ የታዘብኩት አንድ ነገር አለ፡፡ ኬንያውያኑ ችግር አለባቸው፡፡ አፍሪካ የምትባለዋን አህጉር እነሱ የሰሩዋት ነው የሚመስላቸው፡፡ ኬንያ የአፍሪካ እስትንፋስ ነች፣ ህዝቦቿ ደግሞ የአፍሪካዊ ማንነት መገለጫዎች ናቸው ይላሉ፡፡ ከነሱ በላይ አፍሪካዊ ላሳር ነው፡፡ ኬምቦይ በዚህ መንፈስ ነበር የተዋወቀኝ። ‹‹ወደ እውነተኛው የአፍሪካ ምድር እንኳን በደህና መጣህ›› አለኝ፡፡ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ከሆነች ሃገር ለሄደ ሰው ይህ አባባል ትንሽ ይጎረብጣል፡፡ ለማንኛውም መልስ መስጠት ነበረብኝ።

I am from the heart of Africa, Ethiopia, nice to meet you. የአፍሪካ ማዕከል ከሆነችው ኢትዮጵያ ነው የመጣሁት፣ ስለተዋወቅን ደስተኛ ነኝ ብዬ መለስኩለት፡፡ ኬምቦይ ቀጠለ ‹‹ኢትዮጵያን አይቻት አላውቅም፣ ማየት አለብኝ። ከእንግዲህ ከምጎበኛቸው ሃገሮች ቀዳሚ የምትሆነው አዲስ አበባ ነች፡፡ ወዳጆች ነን፡፡ ጥሩ ግንኙነት አለን፣ ብዙ የምንጋራቸው ነገሮች አሉ፡፡ ግን አሁን አሁን ኢትዮጵያ ኬንያን ለመጉዳት እየሰራች ነው፣ ለምን እንደዛ ታደርጋላችሁ? የጊቤ ሶስት የሃይል ማመንጫ ግድብን በመስራታችሁ ልትኮሩ አይገባም፡፡ በታችኛው ተፋሰስ ያሉ ኬንያውያንን ይጎዳል፣ የቱርካና ሃይቅም ጨዋማ ይሆናል፣ የውሃ መጠኑ ይቀንሳል፡፡ ሌላው ደግሞ በኬንያ ድንበር የሚገኙ ጎሳዎቻችሁ የእኛን ዜጎች እያሰቃዩዋቸው ነው፡፡ ድንበር ጥሰው በመግባት ከብቶቻቸውን ይዘርፉባቸዋል›› አለኝ፡፡ የዚህን ጋዜጠኛ የተዛባ አመለካከት በተገቢው መንገድ ማስተካከል ነበረብኝ።

‹‹ግድቡ የታችኛው ተፋሰስ ህዝቦችን የሚጎዳ ከሆነ የሚጎዱት የእናንተ ዜጎች ብቻ አይደሉም፣ የእኛም ናቸው፡፡ ምክንያቱም ይህን ወንዝ ተከትለው የሚኖሩ የደቡብ ኦሞ ህዝቦች አሉን፡፡ እኛ ደግሞ ህዝባችንን ለመጥቀም እንጂ ለመጉዳት የምንሰራው ነገር የለም፡፡ እኛ በምንሰራው ስራ ዜጎቻችንን ጠቅመን ጎረቤቶቻችንም እንዲጠቀሙ ነው የምንፈልገው፡፡ አሁን ለጂቡቲና ለሱዳን የኤሌክትሪክ ሃይል መላክ ጀምረናል፣ ቀጥለን ለእናንተም እንልካለን፡፡ ስለዚህ እኛ በምንሰራው ስራ እናንተም ተጠቃሚዎች ናችሁ፡፡ አሁን አንተ የምትለኝ ቀደም ሲል “ፍሬንድስ ኦፍ ሌክ ቱርካና” የሚባል ድርጅት ያናፈሰው መሰረት የሌለው ወሬ ነው፡፡ የወንዙ ፍሰት በምንም መልኩ የሚቀንስ ወይም የሚቋረጥ አይደለም። የጎሳዎቹን ግጭት ለማርገብ ደግሞ ሁለቱም መንግስታት በጋራ እየሰሩ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ የሁለቱም ሃገራት ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል እምነት አለኝ›› በማለት ላስረዳው ሞከርኩ፡፡ ሆኖም ግን የተዋጠለት አይመስለኝም፡፡ በስልጠናው መሃል የውይይት ጊዜ ነበር። የምንወያየው በቡድን ተከፋፍለን ነው፡፡ እናም በሁለተኛው ቀን ሁላችንም በአምስቱም የአፍሪካ ቀጣና ተከፋፍለን እንድንወያይ ተፈለገ፡፡ የትኛው ሃገር በየትኛው ቀጠና እንደሚመደብ መነጋገር ተጀመረ፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ዝርዝር መጥራት ሲጀመር ኢትዮጵያ የለችበትም፡፡ አንዱ እጁን አወጣና ‹‹ኢትዮጵያ ሰሜን አፍሪካ ውስጥ ነው የምትመደበው?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ አስተባባሪው መልስ ሰጠ ‹‹ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ የሶማሊያ ጎረቤት ነች፡፡

ለዛ እኮ ነው ከአልሸባብ ጋር የምትዋጋው›› አለ፡፡ ከዚህ በኋላ እኔና ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ውስጥ ተካተትን፡፡ ከዚህ ምደባ በኋላ ለእያንዳንዱ ቡድን አስተባባሪ እንዲመደብ ተፈለገ፡፡ አስተባባሪዎች በምን መንገድ ይመረጡ ሲባል ምርጫ ይካሄድ ተባለ፡፡ በዚህ ውሳኔ መሰረት ለምስራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች አስተባባሪ ለመምረጥ ዕጩዎችን የመጥራት ሂደት ተጀመረ፡፡ ከተለያዩ ሃገራት ሶስት እጩዎች ተጠሩ፡፡ ከኢትዮጵያ ግን ዕጩ የሚጠራ ሰው ጠፋ፡፡ በዚህ ጊዜ እጄን አውጥቼ ራሴን በእጩነት አቀረብኩ፡፡ አዳራሹ በሳቅ ታወከ፡፡ ሆኖም ተቀባይነት አግኝቼ እጩ ተወዳዳሪ ሆንኩኝ፡፡ ከእኔ ጋር አራት ዕጩዎች ቀረብን፡፡ ምርጫው ተጀመረ፣ የታንዛኒያው ኪዜቶ አብላጫውን ድምፅ ሲያገኝ ለእኔ ግን ድምፅ የሰጠሁት እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ በስልጠናው አዳራሽ ከሩዋንዳውጋዜጠኛ ፍሬድሪክ ጎን ነበር የተቀመጥኩት፡፡ ስለ ኢትዮጵያ መናገር ፈልጓል፡፡ ሩዋንዳውያን ስለ ኢትዮጵያ ጥሩ አመለካከት አላቸው፡፡

ያኔ እርስ በርሳቸው ሲጨፋጨፉ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል ደርሶላቸዋል፡፡ ይህን ታላቅ ተግባር ሁሌም ያስቡታል፡፡ የሃገሪቱ መሪ ፖል ካጋሜ በአቶ መለስ የቀብር ስነ ስርዓት ተገኝተው የተናገሩትን አስታውሳለሁ፡፡ ‹‹መለስና የኢትዮጵያ ህዝቦች በሃገራችን ከተፈፀመው አሰቃቂ እልቂት ማግስት ሰላም ለማስፈን ያደረጉትን ድጋፍ የሩዋንዳ ህዝቦች መቼም ቢሆን የሚዘነጉት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ድጋፍ ያደረገችው ራሷ ገና በሽግግር ሂደት ላይ በነበረችበት ወቅት ነበር›› ብለዋል፡፡ ከፍሬድሪክ ጋር ወጋችንን ቀጠልን፡፡ “እስቲ ስሜን በአማርኛ ፊደል ፃፍልኝ” አለኝ፣ ፃፍኩለት። እሱም ደጋግሞ ሞከረው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን እጅግ ልትኮሩ ይገባችኋል፣ ከአፍሪካ ሃገራት ውስጥ የራሳችሁ የቀን አቆጣጠርና ፊደል ያላችሁ ብቸኛ ሃገር ናችሁ፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የራሳችሁን አዲስ ሚሌንየም ማክበራችሁን ሰምቻለሁ፡፡ የሰዓት አቆጣጠራችሁም እንዲሁ የተለየ ነው፡፡ በርግጥ ግራ እንደሚያጋባ አንድ ጓደኛዬ ነግሮኛል፡፡ አሁን በናንተ አቆጣጠር ስንት ሰዓት ነው?›› ብሎ ጠየቀኝ። ጥቂት ማብራሪያ ሰጥቼ ፍሬድሪክን ተለየሁት። ከኋላዬ የተቀመጠው ከቡሩንዲ የመጣው ሉሙምባ እንድተዋወቀው ይጎተጉተኛል፡፡ ወደሱ ዞርኩኝ፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የነገረኝን ላጋራችሁ፡፡

‹‹አየር መንገዳችሁ በዓለም አሉ ከሚባሉት ውስጥ ይመደባል፣ ምቾቱ፣ መስተንግዶው፣ ደህንነቱ፣ ዘመናዊነቱ ልዩ ነው፣ አስተናጋጆቹም በጣም ያምራሉ፡፡ ግን አንድ ችግር አለው፣ በዓለም አቀፍ በረራ ሰዓት አያከብርም፣ የመንገደኞች ሻንጣም በተደጋጋሚ ይጠፋል›› በማለት ጥሩውንም መጥፎውንም ነገረኝ፡፡ ይህን ቅሬታ እንዳለ ዋጥኩት፣ ምክንያቱም አየር መንገዳችን በዚህ ነገር በተደጋጋሚ እንደሚወቀስ ከእሱ በላይ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ከናይጄሪያዊው ጋዜጠኛ ጋር ለመተዋወቅ ወንበር ቀየርኩኝ፡፡ ‹‹አታዪ እባላለሁ ናይጄሪያዊ ነኝ›› ብሎ ተዋወቀኝ፡፡ ገ/ሚካኤል እባላለሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬ ራሴን አስተዋወቅኩ፡፡ ‹‹ሚካኤል የክርስቲያኖች መልዓክ ነው፣ ክርስቲያን ነህ እንዴ?” አለኝ፤ አዎ አልኩት፡፡ “ይገርማል! ኢትዮጵያ ውስጥ ክርስቲያኖች አሉ ማለት ነው?›› ብሎ ቀጠለ፡፡ በዚህ ጥያቄው እኔን ሳይገርመኝ በእኔ መልስ እሱ መገረሙ ገረመኝ፡፡ እንዴት ስለ ኢትዮጵያ መረጃ የለውም፣ በውስጤ የሚመላለስ ጥያቄ ነበር፡፡ ያውም ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የክርስቲያኖች ሃገር እየተባለች የምትጠራዋን ኢትዮጵያ፡፡ ክርስትና ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ አፍሪካ ምድር የገባው በኢትዮጵያ በኩል ነው፡፡ እስልምናውም ቢሆን መንገዱ ይኸው ነበር፡፡

እኛ ድፍን ዓለም እንደሚያውቀን ነው የምናስበው፣ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ዓለም ስለኛ የሚያውቀው በጣም ውስን ነገር ነው፣ እንደ አታዪ ያሉ ሰዎች ደግሞ ምንም አያውቁም፣ አለያም ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚያውቁት ነገር በጣም የተዛባ ነው፡፡ በዚህ ቆይታዬ ስለራሳችን ያለን ግምት፣ ግንዛቤና አመለካከት ፍፁም የተጋነነ፣ በመረጃ ያልተደገፈና ጠቃሚ ያልሆነ እንደሆነ ተገነዘብኩ፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለዋ ሃገር በየትኛው የአፍሪካ አቅጣጫ እንደምትገኝ፣ ምን ደረጃ ላይ እንዳለች፣ የህዝቦቿ ታሪክና እምነት ምን እንደሚመስል፣ ከነጭራሹ ስለዚህች ታላቅ ሃገር ሰምተው የማያውቁ ጋዜጠኞች አጋጥመውኛል፡፡ እነዚህ የመረጃ ሰዎች ለኢትዮጵያ ያላቸው ግንዛቤ ይህን ያህል አናሳና የተዛባ ከሆነ ሌላው ህዝብ ምን ያህል ያውቀናል የሚለው ጥያቄ ውስጤ ተመላለሰ። ለምንድን ነው ዓለም በሚገባ ያላወቀን፣ እኛ ስለምንርቃቸው ነው ወይስ እነሱ ስለማይቀርቡን? ይሄኔ በአንድ መጣጥፍ ላይ ያነበብኩት አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ‹‹ለሶስት ሺህ ዓመታት የዘነጋቸውን ዓለም ዘንግተው ለብቻቸው የኖሩት ኢትዮጵያውያን አሁን ከዘመናት እንቅልፋቸው የነቁ ይመስላሉ›› ይላል፡፡ ፀሃፊው ይህን አባባል የተጠቀመው አሁን እየታየ ያለውን የኢኮኖሚ መነቃቃት ሲገልፅ ነው፡፡ በዛ ስልጠና ላይ የተገኙ ጋዜጠኞችን አመለካከት ለማስተካከል ብዙ ጥሬያለሁ፡፡ ግንዛቤያቸው እንደተሻሻለም እርግጠኛ ነኝ፡፡

ምናለበት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሄደበት ስለሃገሩ ተናግሮ የገፅታ ግንባታ ስራ ቢያከናውን አልኩኝ፡፡ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሀምሳ ሰው ጌጡ ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች ስራቸው ምን እንደሆነ ይገርመኛል፡፡ ዋና ተግባራቸው መሆን ያለበት ኢትዮጵያን ለውጩ ዓለም ማስተዋወቅ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት መሳብ፣ ለዜጎች ጥብቅና መቆም እንዲሁም ለሃገርና ህዝብ የሚጠቅም መረጃ መሰብሰብ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በየሃገራቱ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃንን መጠቀም ይገባቸዋል። ሃላፊነታቸውን ጠንቅቀው የተገነዘቡ ግን በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ይመስሉኛል፡፡ ይህን ባህል መቀየር አለብን፡፡ ሃገራችንን ማስተዋወቅ ይጠበቅብናል፡፡ በሄድንበት ሁሉ ሁለመናችን ስለ እናት ሃገር፣ ስለ ህዝባችንና ስለ መልካም ባህላችን ይናገር፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ጊዜ ነው፡፡

Read 4026 times